ፋንታነሽ ክንዴ
ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግብርና ሥራ እንደሚተዳደር መረጃዎች ያመለክታሉ:: ከፊሉ ሰብል በማምረት ኑሮውን ይገፋል:: ሌላው ደግሞ እንስሳት በማርባትና ንብ በማነብ ላይ ኑሮውን ሲመሰርት፣ቀሪዎቹ ደግሞ ሁሉንም የግብርና ዘርፎች በቅንጅት በመከወን ሕይወታቸውን ይመራሉ::
የሀገሪቱ አብዛኛው ሕዝብ በግብርና ሥራ የተሰማራ መሆኑ፣የሀገሪቱ መልከዓምድር፣ የሚታረስ ሰፊ መሬት መኖር ፣የአየር ንብረት እና ሌላውም ታክሎበት የአገሪቱ ኢኮኖሚም ግብርና መር እንዲሆን አስገድዷል:: ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለሚደረገው ጉዞም መልካም መደላድል ሆኖ የሚያገለግለው ይሄው ዘርፍ ነው።
ግብርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ እንዳልዘመነና በሚታሰበው ልክ ውጤታማ እንዳልሆነ ይታወቃል:: ይህም በመሆኑ ዛሬም ድረስ የምግብ ዋስትናውን ያላረጋገጠው የኅብረተሰብ ክፍል ሰፊ ቁጥር አለው። በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ አገሪቱን የኋላ ቀርነትና የተረጂ ተምሳሌት ተደርጋ እንድትቆጠር ሆናለች።
በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ከፍተኛ የውሃ ሀብት የአፍሪካ የውሃ ማማ ተብላ እንደምትጠራ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ:: ይህ መሆኑ ግን የዝናብ እጥረት በሚኖርበት ወቅት ሁሉ በድርቅ ምክንያት በሚከሰት ረሀብ ዜጎቿን ከመነጠቅ ሳይታደጋት ቆይቷል::
አብዛኛው አርሶ አደር ምርቱን የሚያመርተው ዝናብ ጠብቆ በዓመት አንዴ በመሆኑ በአጋጣሚ የዝናብ መጠኑ ከቀነሰ ወይም ስርጭቱ ከተዛባ ብዙ ሰው ለከፋ ድርቅና ችግር ይዳረጋል:: ላለፉት አያሌ ዓመታት አብዛኛው አርሶ አደር ትኩረቱ ለዝናብ እንጂ ዓመቱን ሙሉ በአቅራቢያው ያለጥቅም ለሚፈሱ ወንዞች ግድ አልነበረውም::
በመስኖ ማልማትና በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት እንደሚችል አድርጎም አይቆጥርም። በመሆኑም አብዛኛው ጊዜውን የሚያሳልፈው ያመረተውን በድግስ እና በመሳሰለው በማባከን ነው። ያለው ላይ በመጨመር ሳይሆን ያለውን በማባከን። ይህም በመሆኑ የአብዛኛው አርሶ አደር ኑሮ ከእጅ ወደአፍ ከመሆን የዘለለ አልነበረም።
አሁን አሁን ግን በመንግሥትና ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል ይህንን ልምድ ለመቀየር ሰፋፊ ጥረት ሲደረግ ይስተዋላል:: በሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ባይባልም ዛሬ ላይ ግን ነገሮች እየተቀየሩ መጥተዋል::
ከዝናብ በተጨማሪ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው የሚገኙ ወንዞችን በመጥለፍ አንዳንዴም ዝናብን በማጠራቀም ጭምር ትርፍ ምርት እያመረቱ እና ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ:: በዛሬው እትማችንም በመስኖ ሥራ ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል የአንዱን የሕይወት ተሞክሮ ልናጋራችሁ ወደናል::
እንግዳችን ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ዞን በአሶሳ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው አፋሲዝም ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ ናቸው:: አቶ አልሂሴን ደፋአላህ ይባላሉ:: ባለትዳር እና የስምንት ወንዶችና የሰባት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ ሕይወታቸውን የሚመሩት በእርሻ ሥራ ነው::
አርሶ አደር አልሂሴን ለዘመናት ዝናብን በመጠቀም የእርሻ ስራቸውን ሲከውኑ ነበር:: ቤተሰቦቻቸውን አስተባብረው ህይወታቸውን ለመለወጥ ሲታትሩ ቢቆዩም ውጤቱ ግን ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ይህም በመሆኑ ልጆቻቸውን ለማስተማር እና ኑሯቸውንም በአግባቡ ለመምራት አዳጋች ሆኖባቸው ነበር::
ሰፊ ቁጥር ያለው ቤተሰባቸውን እሳቸው እንዲሆንላቸው በሚፈልጉት መንገድ መምራትም ተቸግረዋል። እናም የሁልጊዜ ምኞታቸው እንዴት አድርጌ ነው ከዚህ ኑሮ ቤተሰቤን የምለውጠው የሚል ነው። በመገናኛ ብዙኃን የሚመለከቷቸው በመስኖ ሥራ ስኬታማ የሆኑ አርሶ አደሮች ልምድ ግን ለእሳቸውም መነሳሳት ምክንያት ሆናቸው ።
እሳቸውም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በአካባቢያቸው የሚገኘውን ወንዝ በመጥለፍ በመስኖ ማልማቱን አንድ ብለው ጀመሩ ። የጀመሩት የመስኖ ሥራም ጥሩ ውጤት አስገኘላቸው ።ሽንኩርት፣ ጎመንና የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ምርታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ይገልጻሉ::
በተለይ የሽንኩርት ምርት ከፍተኛ ውጤት አስገኝቶልናል የሚሉት አቶ አልሂሴን፣ ባለፈው የምርት ዘመን ብቻ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት ሽንኩርት መቶ ኩንታል ምርት መስጠቱን ለአብነት ይጠቅሳሉ:: ይህንን ምርት ለገበያ አቅርበው ወደ 100 ሺህ ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘታቸውንም ያስታውሳሉ::
በመስኖ ማምረት ከጀመሩ በኋላ በራሳቸውና በቤተሰባቸው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ መኖሩን የሚናገሩት በደስታ ስሜት ተውጠው ነው:: በተጨባጭ ያገኙትን ለውጥ ስያብራሩም ‹‹ከዚህ በፊት እኔና ቤተሰቦቼ በትንሿ ደሳሳ ጎጆ ቤት ውስጥ ተጨናንቀን እንኖር ነበር፤ ዛሬ ግን ታሪክ ተቀይሮ የተንጣለለ ቆርቆሮ ቤት ሰርተን ተንፈላሰን እየኖርን ነው›› ይላሉ::
‹‹በአሁንና በቀደመው ኑሯችን መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን የእኛ ሕይወት አካባቢው ራሱ ይመሰክራል:: አካባቢያችን ሁሌም ለምለም፣ አረንጓዴና ማራኪ ሆኖ ይታያል›› በማለት ልዩነቱን ይገልፃሉ ::ያሳለፉትን ረጅም የችግር ዘመንም ሲያስታወሱ ይቆጫሉ። ያኔ ውሀውም መሬቱም ጉልበቱም ነበር ያጣነው ልቡንም ነው ሲሉ ይናገራሉ። ቢሆንም ግን ዛሬ ክረምት ከበጋ አምራች መሆናቸው ያስደስታቸዋል። ከዚህ በኋላም ኑራቸው ለሌሎችም አስተማሪና አርዓያ እነደሚሆኑም ያምናሉ።
የግብርና ሥራ ብዙ ጉልበት የሚጠይቅ መሆኑን የሚያነሱት አርሶ አደሩ፤ ስራቸውን ሲያከናውኑ የቤተሰቦቻቸው እርዳታ ከፍተኛ መሆኑ ውጤታማነታቸውን እንዳፈጠነው ይጠቅሳሉ:: ‹ሁሉንም ሥራ የምንሰራው በመተባበርና በመረዳዳት ነው:: ልጆቼም ሆኑ ባለቤቴ ሁሌም ከእኔ ጋር ስራ ላይ ናቸው፤ ይህም በመሆኑ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ውጤት አስገኝቶልናል›› ይላሉ::
እርሳቸው በግብርና ሥራ ይሰማሩ እንጂ ልጆቻቸው ትምህርት ተምረው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ጥረት እንደሚያደርጉ ይናገራሉ:: በመሆኑም ልጆች እሳቸውን ለማገዝ በሥራ ሲጠመዱ ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ:: ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን በሥራ ያግዛሉ::
ይህንም ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ አሥረኛ፣ ዘጠነኛ፣ ስምንተኛና ስድስተኛ ክፍል የደረሱ ልጆች እንዳሏቸው ጠቅሰዋል:: ወደፊትም ትምህርታቸውን አጠናቀው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ያብራራሉ ::
እስካሁን ያገኙት ውጤት የበለጠ በርትተው እንዲሰሩ እንዳነሳሳቸው የሚናገሩት አርሶ አደር አልሂሴን፤ ባለፈው ዓመት በግማሽ ሄክታር መሬት ተወስኖ የነበረውን የሽንኩርት ልማት በዘንድሮው ዓመት ወደ ሦስት ሄክታር ማሳደጋቸውን በማሳያነት ይጠቅሳሉ:: በዚህ ዓመት ወደ 600 ኩንታል የሚጠጋ ምርት ሊያገኙ እንደሚችሉ ተስፋ አድርገዋል::
ምርቱ ለገበያ ሲቀርብም ከ500 እስከ 600ሺህ ብር ገቢ ሊያገኙ እንደሚችሉ ይገምታሉ::ይህም ከባለፈው ዓመት ምርት ጋር በእጅጉ ከፍ ያለ ውጤት እንደሚያስገኝላቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል:: ወደፊትም ከዚህ በላይ ጠንክረው እንደሚሰሩና ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት::
እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ መንገዶች አልጋ በአልጋ እንዳልነበሩ እና ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ ነገሮች መስመር እየያዙ መምጣታቸውን ይናገራሉ:: ከዚህ በላይ የመስራትና የመለወጥ ተስፋ እንዳላቸውና ከሚመለከታቸው አካላት የምርጥ ዘር እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል::
ለመስኖ የተጠቀሙት የውሀ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ሽንኩርትና ጎመን ከማምረት ያለፈ ሥራ እንዳይሰሩ አግዷቸዋል። ሆኖም ግን አሁን ተጨማሪ ሌሎች ሰብሎችንም ለማምረት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ይሄንን ፍላጎታቸውን ለማሳካትም ከግብርና አካባቢ ተገቢውን ድጋፍ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን ተያይዘውታል። የሚፈልጉትን ድጋፍ እንዲሁም ዘርና ቴክኖሎጂዎችን ማሟላት ከቻሉ ገና ብዙ ነገር ለመስራት እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል::
ምን ያህል ካፒታል እንዳላቸው ላነሳንላቸው ጥያቄ እስካሁን ያገኘሁትን ገንዘብ በሙሉ ወደ ሥራ ስላስገቡት በአሁኑ ሰዓት እዚህ ግባ የሚባል ጥሬ ገንዘብ እንደሌላቸውና ጠቅላላ ሀብታቸውን ለመግለጽ እንደሚቸግራቸው ነው የተናገሩት። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን ጥሩ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ በልበ ሙሉነት ይገልጻሉ ::
ከዚህ ቀደም ዝናብ ብቻ ጠብቀው ማሽላ፣ በቆሎና ሌሎችንም ሰብሎች ያመርቱ ነበር:: የሚያገኙት ገቢ ግን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም:: ይህን የተረዱት ታታሪው አርሶ አደር ሌሎች አርሶ አደሮችም የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል መስኖን በመጠቀም ትርፍ አምራች እንዲሆኑና ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ይመክራሉ::
ይህን ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ምክንያት ደስተኛ እንዳልነበሩ አስታውሰው ዛሬ ግን በሕይወታቸው ብዙ ለውጥ አይተዋል:: ዋነኛ መዝናኛቸውና የደስታቸው ምንጭ ሥራ መሆኑን ይናገራሉ።
ከስራ የተረፈቻቸውን ጥቂት ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቡና ተፈልቶ፣ ቤት ያፈራው ተዘጋጅቶና ቀርቦ በደስታ ያሳልፋሉ::‹‹ ዛሬ ምን እንበላ ይሆን፣ ልጆቼን ምን አለብሳቸው ይሆን ብዬ ሳልጨነቅ ለቤቴ የሚስፈልገኝን ሁሉ አደርጋለሁ›› ይላሉ::
ሰው በስራው ውጤታማ ሲሆን ደስተኛና ሰላማዊ ሕይወት ይኖረዋል። ከራሱም ቤተሰብ አልፎ ለሌሎችም ያስባል። መስራት ማደግና መለወጥ እንዳለባቸውም ይመክራል የሚሉት አርሶ አደር አልሂሴን፤ ሁሉም ሰው በተሰማራበት ሙያ በርትቶ እንዲሰራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
የወላጆች ጥንካሬ ደግሞ ልጆችም የስራ ሰው እንዲሆኑ ያደርጋል። ከወላጆቻችን የበለጠ ወይም የተሻለ ኑሮ መኖር አለብን ብለው ይበልጥ እንዲሰሩ ያበረታታል።ስለዚህ ወላጆች ለቤተሰባቸው ዓርአያ መሆን እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013