“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ” የሚል ብሂል ባለበት እና የብዙውን ልብ በገዛበት ማህበረሰብ ውስጥ ሙስናን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርንና ከዚህ የሚመነጩ ማህበራዊ ችግሮችን አሸንፎ መውጣት በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም። ይህንን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃና ከፍ ያለ ቁርጠኝነት ይጠይቃልና።
ሰው በፍጥረቱ የአካባቢው ተጽኖ ውጤት ነው። በየትኛውም መልኩ ማህበረሰብ እንደ ማህበረሰብ የገነባነባቸው በጎም ሆኑ መጥፎ እሴቶች ያንን ማህበረሰብ ሊያሻግሩት ወይም ዋጋ ሊያስከፍሉት የመቻላቸው እውነታ ለጥያቄ የሚቀርብም አይደለም። እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የተዘራ ዘር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መታጨዱ አይቀርም።
ለማጨድ የሚከፈለው ዋጋ እንደ ማህበረሰቡ የእድገት ደረጃ የሚሰላ ቢሆንም አንድ ትውልድ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ማህበረሰብ የሚፈጥራቸው ማህበራዊ እጸጾች ይዋል ይደር እንጂ በቀጣይ ትውልዶች ላይ የሚያሳርፉት ተጽእኖ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም። ችግሩ እየከፋ የሚሄደው ደግሞ እጸጾቹ እንደ አንድ በጎ የማህበረሰብ እሴት በትውልዶች ልብ ውስጥ ቦታ ሲያገኝ እና ፍሬ የሚያፈራበት ማህበራዊ መሰረት ሲኖረው ነው።
ነገሩ ከዚህም በላይ አሳሳቢ የሚሆነው ደግሞ ለነዚህ ማህበራዊ እጸጾች መፋፋት የሚያግዙ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሁንታዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ኖረው የመገኘታቸው ነገር ነው። በዚህ ወቅት እነዚህ ማህበራዊ ህጸጾች ህጋዊ መሰረት ያላቸው እስኪመስሉ ህጋዊ ሆነው የሚታዩበት አውድ መፈጠሩ ነው።
የሀገራችን የትናንትም ሆነ የዛሬ ተጨባጭ እውነታዎች ብዙም ከዚህ የራቁ አይደሉም። አብዛኞቹ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ከግለኝነት የራቁ አለመሆናቸው፤ ከዛም በላይ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ እሳቤ እና የቀደሙ ተሞክሮዎች ለስልጣን የሠጡት ተሞክሯዊ ትርጓሜ በብዙ መልኩ የተበላሸ መሆኑ፣ በቀደሙት ዘመናት ትውልዶችን ዋጋ ያስከፈሉ አስተሳሰቦች ዛሬም ያለውን ትውልድ ዋጋ አስከፋይ ሆነው ዘልቀዋል።
የፖለቲካው መሰረቱ ስልጣንን አልፋና ኦሜጋ አድርጎ ከማየት ፊውዳላዊ አስተሳሰብ የመነጨና በ21ኛው ክፍለዘመን የሚገራው መንፈሳዊ ሆነ ሞራላዊ አስተሳሰብ ገዝፎ አለመውጣቱ፣ ከዛ ይልቅ በየዘመኑ የሚፈጠሩ የፖለቲካ ልሂቃን ባልታደሰ ማንነት፣ በቋንቋ በተገነዘ ህይወት አልባ ዲስኩር መታመን፤ ይህንንም ወደ ስልጣን መወጣጫ ስትራቴጂ አድርጎ መውሰድ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ ቆይቷል።
በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ የቅርቡን እንኳን ብናይ የፍትህ፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር እና የነጻነት ጥያቄ አንስተው ወደ ትግል የገቡ ለዚሁ ትግል ስኬት በሺዎች የሚቆጠሩ የዋሃንን አሰልፈው ከብዙ መስዋእትነት በኋላ ወደ ስልጣን በመጡት የህወሀት ጁንታዎች የሆነውን ተጨባጭ እውነታ መጥቀስ ይቻላል።
ቡድኑ ስልጣን ከያዘ ማግስት ጀምሮ የሄደባቸው መንገዶች ለትግሉ መስዋእት ከሆኑ ሰማእታት ተስፋንና እራይ ጋር ሲነጻጸር ምን ሊመስል እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም። ትግሉ ትርጉም አልባ፤ የሰማእቱም ደም ከንቱ ስለ መሆኑ ማሰብ ለሚችል ጤነኛ አዕምሮ የሚሰወር አይደለም።
እንዲያውም ነገሩ ከመጀመሪያው ስህተት የኋለኛው እንደሚባለው ይህ ቡድን አውግዞ በተነሳበት ህገወጥነት፣ ኢፍትሀዊነት እና አምባገነናዊነት በከፋ መልኩ ተገልጦ ሀገርና ህዝብን የቱን ያህል የከፋ ዋጋ እንዳስከፈለ እና እያስከፈለም እንዳለ ለመናገር ወቅቱ ሩቅ አይደለም።
ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት በብዙዎች የመስዋእትነት ደም በተገነባ የስልጣን መደላደል ቤተመንግስት ከገባ ማግስት ጀምሮ ስልጣንን አልፋና ኦሜጋ አድርጎ በመውሰድ፤ ስልጣንን የእብሪትና የሀብት ምንጭ፣ የዘረፋ ፈቃድ፣ ከዛም በላይ የእውቀት ምንጭ እስከማድረግ የሄደበት መንገድ ሀገርና ህዝብን ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍሏል።
በመጨረሻም ቡድኑ የአስተሳሰብ መስረት ካደረገው ከዚህ አስተሳሰብ የተነሳ እርሱንም ለከፋ አደጋ አሳልፎ የሰጠበት ሁኔታ መከሰቱ ይታወሳል። በመሰረታዊነት ይህ ቡድን ያሳተና ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍልና ህዝብና ሀገር በተመሳሳይ መልኩ ዋጋ እንዲከፍሉ ያደረገው ችግሩ አዲስ ማህበራዊ ተግዳሮት ሆኖ ስለመጣ አይደለም። ወይም የችግሩ ፈጣሪ እራሱ ስለሆነም አይደለም። ከዛ ይልቅ ከትናንት ካለመማርና በትናንት አስተሳሰቦች ከመታመንናከመሳት የመነጨ ነው ስህተት ነበር።
ይህን እውነታ በአግባቡ መረዳት ካልተቻለ ነገሩ ማነው ባለተራ መሆኑ የማይቀር ነው። የባለተራነቱ ጉዳይ ደግሞ ከቀደመው በከፋ መልኩ ዋጋ የሚያስከፍል ስለመሆኑ ከቀደሙት ታሪኮች ለመማር የሚከብድ አይደለም። ከዚህ አንጻር የለውጡ ሀይል ይህንን እውነታ ሊለውጥ የሚችል አስተሳሰብ መሰረት መፍጠር ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ተጠያቂነትንና አሰራሮችን በቁርጠኝነት ማስፈን ይኖርበታል።
ችግሩ ከመጣበት ረጅም መንገድ አንጻር እና በዚህ ረጅም መንገድ ሀገርንና ህዝብን ካስከፈለው ከፍ ያለ ዋጋ አንጻር ማሰብን ይጠይቃል። ከሁሉም በላይ ጠንካራ የተጠያቂነት የአሰራር ስርአት መፍጠርና ለአሰራሩ ታማኝ መሆን ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ጊዜ አይኖርም።
የአዲስ አበባ መስተዳድር በመሬት ወረራ በህገወጥ መንገድ በተያዙ የጋራ መኖሪያና የቀበሌ ቤቶች የነበረውን ችግር በተጨባጭ ለማየት የሄደበት መንገድ፤ ችግሩን በጥናት ከማወቅ ባለፈ የጥናቱን ውጤት ለህዝብ ይፋ ማድረጉ የሚበረታታና የፍጻሜው ጅማሪ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። መስተዳድሩ አሁን የመጣበት መንገድና ቁርጠኝነት ወደ ኋላ እንዳይመለስ ግን ለችግሩ ባለቤት መስጠትና ተጠያቂ ማድረጉ ደግሞ ወሳኝ ነው።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ የለውጡ ሀይል ወደ አደባባይ እንዲመጣና የተለያዩ ተግዳሮቶችን እያሸነፈ እንዲሄድ ያደረገው የህዝብ ምሬት ከሚፈለገው በላይ አቅምና የቁርጠኝነት መሰረት ሊሆነው እንደሚችል ይታመናል። ስለሆነም ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው ብሄል የፈጠረው አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ያስከፈለን ከፍ ያለ ዋጋ በለውጡ ሀይል በአግባቡ ሊገራ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥር 20/1013