አንተነህ ቸሬ
ድምፃዊ፣ ተወዛዋዥ፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ አስተማሪ፣ ደራሲና የኪነ-ጥበብ ስራዎች ኃላፊ ሆኖ አገልግሏል ። በእርግጥ እርሱ ስፖርተኛም ነበር ።የልጃቸው ‹‹አዝማሪ›› መባል ያስጨነቃቸውን የወላጆቹን ጫና ተቋቁሞ በኪነ ጥበብ ባሕር ውስጥ በብቃት መዋኘት ችሏል ።
ብቃቱና ተሰጥኦው ደግሞ ብዙዎች የዋናው ታዳሚዎችና አፍቃሪያን እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ። አንጋፋውና ዝነኛው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ ‹‹የሙያ አባቴ ነው›› ብሎ ያሞካሸዋል ።ይህ ባለሙያ በኢትዮጵያ የትያትርና የሙዚቃ ዘርፍ ላይ ደማቅ አሻራውን ማሳረፍ የቻለው የጥበብ መሃንዲሱ ኢዩኤል ዮሐንስ ነው ።
ኢዩኤል የተወለደው በ1927 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው ።አባቱ አቶ ዮሐንስ ትርፌ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ስለነበሩ ልጃቸው ገና በሕፃንነቱ መንፈሳዊ ትምህርት ላይ እንዲያተኩር አደረጉ ።ንባብና ፀዋትዎ ዜማን ከሊቀ ጠበብት ኃይለጊዮርጊስ ዘንድ ተምሮ ተጨማሪ ትምህርቶችን በሌሎች አካባቢዎች ተዘዋውሮ ተምሯል ።
ከትምህርቱ በኋላም በአዲስ አበባ ጊቢ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በዲቁና አገልግሏል።ኢዩኤል በዲቁና በሚያገለግልበት ወቅት ድምፁን የሰሙ ሁሉ ያደንቁትና በዚያም እንዲገፋበት ይመክሩት ነበር።ከመንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ ዘመናዊ (የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ) ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ካቴድራልና በሌሎች ትምህርት ቤቶች ተከታትሏል።
ኢዩኤል በልጅነቱ እግር ኳስ መጫወትና ሙዚቃ ማዳመጥ ይወድ ነበር ።በሬዲዮ የሚተላለፉ ዘፈኖችን ሲያዳምጥ አባቱ ደግሞ ሬዲዮውን ይደብቁበት ነበር።የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማኅበር መስራች የነበሩት አቶ መኮንን ሀብተወልድ ሕዝቡ ለአገር ፍቅርና፣ ለነፃነትና ለአንድነት እንዲታገል በዘፈን፣ በቀረርቶና በሽለላ የሚያነሳሱ ሰዎችን ሲያሰባስቡ ታዳጊው ኢዩኤልም በድምፀ መረዋነቱ ተመርጦ በ1936 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ተቀጠረ ።
ኢዩኤል ወደ ሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ለመግባት ያየው ፈተና ቀላል አልነበረም ።ኢዩኤል ገና በጠዋቱ በጠራቸው የኪነት መድረክ እና አባቱ አቶ ዮሀንስ ትርፌ ልጃቸው ‹‹አዝማሪ›› እንዳይባልባቸውና በመንፈሳዊው ትምህርት በርትቶ እንዲቀጥል ባላቸው ፍላጎት መካከል ተወጥሮ ቆመ ።የሆነው ሆኖ ኢዩኤል አንዱን መምረጥ ግዴታው ነበርና ወደ ተፈጥሯዊ ዝንባሌው፣ ወደ ኪነት፣ አደላና የሀገር ፍቅር ማኅበር አባል ሆነ ።
ከፋሺስት ኢጣሊያ መባረር በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማኅበር በአዲስ መልክ ተደራጅቶ የጠላት መባረርን፣ ነፃነትንና ጀግንነትን የሚያወድሱ ሙዚቃዎችንና የተውኔት ስራዎችን ለሕዝቡ ሲያቀርብ ታዳጊው ኢዩኤል ለኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ የመክፈቻና የመዝጊያ መዝሙር ይዘምር ነበር ።
ግጥምና ዜማ እየደረሰ ያቀርብም ነበር ።ፍፁም ወልደብረማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ ‹‹ … በወቅቱ ሕዝቡ ለዝግጅቱ የነበረውን ፍቅርና አድናቆት ሲገልፅ ‹ያ ትንሹ ልጅ አለ ከተባለ ሕዝቡ የሙዚቃ ዝግጅቱን ለማየት ይጓጓ ነበር› …›› በማለት ‹‹የኢትዮጵያ ድምጽ›› ጋዜጣን ዋቢ አድርጎ ገልጿል ።
በ1936 ዓ.ም የተቀፀል ጽጌ በዓል (በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን የሚከበረው የአጼ መስቀል በዓል) በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሲከበር ኢዩኤል ሲያዜም የሰሙት ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ለታዳጊው የገንዘብና የካባ ሽልማት አበርክተውለት እንደነበር የሚገልጽ ጽሑፍ በጋዜጣው ላይ ታትሞ እንደነበርም በዚሁ መጽሐፍ ላይ ተመልክቷል ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ኢዩኤልም ቢሆን የሀገሩን መንፈሳዊ ትምህርት በጥልቀት ሳይማር ወደ ስራ ዓለም በመግባቱ ቅር ተሰኝቶ ስለነበር በእርሱ ፍላጎትና በወላጆቹ ግፊት ከሀገር ፍቅር ማኅበር ወጥቶ ወደ ሰላሌ በመሄድ አለቃ ጥበቡ ገሜ ከተባሉ ስመ ጥር የቅኔ መምህር ዘንድ ቅኔን ከነአገባቡ ተማረ ።
ከቅኔ ትምህርቱ በኋላ በድጋሚ ወደ ሀገር ፍቅር ማኅበር አባልነቱ ሲመለስ ከኪነ ጥበብ ጋር ዳግም ተገናኘ። አባቱ ግን አሁንም በልጃቸው ምርጫ ደስተኛ አልነበሩም።አቶ መኮንን ሀብተወልድ የኢዩኤልን ተሰጥኦ ስላወቁ በእርሳቸው ድጋፍ ወደ ኪነ-ጥበቡ ዓለም ይበልጥ እየተሳበ መጣ ።
ወጣቱ ኢዩኤል የሙዚቃ ስራዎቹን ከማቅረብ በተጨማሪ የተለያዩ ቴያትሮችን እያዘጋጀ ወደ ተመልካቹ ብቅ አለ ።‹‹ … ኢዩኤል ዮሀንስ የመጀመሪያው የሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ተውኔት ደራሲ መሆኑን በተመለከተ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሠሠ ‹‹አጭር የኢትዮጵያ ቴአትር ጥናት ።ከመጀመሪያው እስከ ከበደ ሚካኤል›› በሚለው ጥናታቸው ውስጥ፡- ‹ … ከዚህ ጋር የሚሄድ የሙዚቃ ስልት በበገና ወይም በመሰንቆ ይመታ ነበር ። ከዚያም ጽሑፍ የነበራቸው ቴያትሮች በኢዩኤል ዮሐንስ መቅረብ ጀመሩ …› በማለት ይገልፃሉ … ›› ሲል ፍፁም በመጽሐፉ ጠቅሷል ።
ኢዩኤል በድምፃዊነት፣ በተወዛዋዥነትና በተዋናይነት ሲሰራ የሚያቀርባቸው ሙዚቃዎችም ሆኑ ትርዒቶች በወቅቱ አዲስ ስለነበሩ ሕዝቡ ወደ ትያትር ቤት እንዲመጣ ስበውት ነበር ።
የሀገር ፍቅር ማኅበር የቴያትር ክፍል ሲመሰረት ከመጀመሪያው ጀምሮ በንቃት ሲሳተፍ የነበረው ኢዩኤል፤ አርቲስቶችን እያሰለጠነ፣ ዜማዎችን እየደረሰና ለቴያትር ክፍሉ አስፈላጊውን ግብዓት ሁሉ እያዘጋጀና እያደራጀ ያቀርብ ነበር ።በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ቴያትር ክፍሉ ሴት ተዋንያን ስላልነበሩት ኢዩኤል በኋላ ደግሞ እነፍሬው ኃይሉ የሴት ገጸ ባህርያትን ወክለው ይጫወቱ ነበር ።
ኢዩኤል በለጋ እድሜው ካቀረባቸውና ተደናቂነትን ካተረፈባቸው ሙዚቃዎቹ መካከል ‹‹አዲስ አበባ ለምለም እንዳንቺ የለም››፣ ‹‹የሀገር ፍቅር ትዝታው አይረሳም ለሚያውቀው››፣ ‹‹አበባ፤ እልል ብዬ ልግባ መስከረም ከጠባ›› እና ‹‹እንዲያው ለነገሩ አለሽ ወይ በአገሩ›› የሚሉት ስራዎች ይጠቀሳሉ ።በጽሑፍ ያቀርባቸው የነበሩት አብዛኞቹ ተውኔቶች አጫጭር ሙዚቃዊ ተውኔቶች ሲሆኑ ፊልም ሲመለከት ያስተዋለው የመድረክ ዝግጅትና አቀራረብ እነዚህን ስራዎቹን ለማቅረብ አግዞታል፡፡
በ ‹‹መነን›› መጽሔት የታኅሳሥ ወር 1951 ዓ.ም ዕትም ላይ ስለኢዩኤል የሰፈረው ጽሑፍ እንዲህ ይነበባል …
‹‹ … ይህ ወጣት በኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማኅበር የመጀመሪያ የተመልካቾች መግቢያ በር ነው ። ለዚህ የተቀደሰው ጥሩ ተግባር መሳሪያ ሆነው ከሚገኙት ሁሉ የመጀመሪያ መሳሪያ ነው … ›› (ፍፁም፣ 2006 ዓ.ም)
ከ1935 እስከ 1942 ዓ.ም ኢዩኤል በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት በሬዲዮና በመድረክ ዘማሪነት፣ በተወዛዋዥነት እንዲሁም በተዋናይነትና በተዋናዮች ኃላፊነት አገልግሏል። ኢዩኤል ለመጀመሪያ ጊዜ በተዋናይት ብቅ ያለበት ተውኔት በ1942 ዓ.ም በአቶ ዓለሙ ተሰማ የተደረሰው ‹‹ደባ እራሱን ስለት ድጉሱን›› የተሰኘው ስራ ነው ።
በ1944 ዓ.ም ደግሞ ‹‹እድሜ መስታወት›› በተባለው ተውኔት ላይ በመሪ ተዋናይነት ተጫውቷል ።በ1947 ዓ.ም የበኩር ስራው የሆነውን ‹‹አቻ ጋብቻ›› ተውኔትን ለመድረክ አበቃ ።ይህ ተውኔት በ1948 ዓ.ም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ታይቶ ከፍተኛ አድናቆትን አትርፎለታል ።
ኢዩኤል በስራዎቹ አማካኝነት የሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች ስለሀገር እድገት፣ አንድነትና አብሮ መስራት ጠቃሚነት እንዲሁም በዘርና በሃይማኖት ስለመከፋፈል ጎጂነት የሚያጠነጥኑ ነበሩ ።ሕዝቡ የሥራን ክቡርነት እንዲገነዘብና መብትና ግዴታውን እንዲያውቅ ቀስቅሷል ። እነዚህም ሃሳቦቹንም ‹‹ከእጅ አይሻል ዶማ››፣ ‹‹ከአባ መስተጋድል››፣ ‹‹ሀገር መውደድ››፣ ‹‹ወፎቹ ተንጫጩ›› እና ‹‹ይመሻል ይነጋል›› በተሰኙት ተውኔቶቹና ትርኢቶቹ ገልጿል።
ኢዩኤል በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት የኪነ-ጥበብ ኃላፊና የተውኔት ደራሲ ሆኖ ባገለገለባቸው ዓመታት ድምፃውያንን እየመለመለና እያሰለጠነ ለመድረክ ያበቃ ነበር ።ከእነዚህ መካከል ጥላሁን ገሠሠ፣ ፍሬው ኃይሉ ግርማ ብስራት፣ ሙናዬ መንበሩ፣ ዘነበች ታደሰ፣ የሺ ተክለወልድ፣ በላይነሽ አመዴ፣ ሳራ ተክሌና ሌሎች ባለሙያዎች ይጠቀሳሉ ።
ኢዩኤል ከ1954 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ረዳት ስራ አስኪያጅ፤ ከ1964 ዓ.ም እስከ 1967 ዓ.ም ደግሞ የቴያትር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ሰርቷል። የቴያትር ቤቱ የሙዚቃና የቴያትር መሪ እና የመድረክ ውዝዋዜ አቀናባሪ (ኮሪዮግራፈር) ሆኖም አገልግሏል ።
በ1964 ዓ.ም ወደ እንግሊዝ ሄዶ የቴያትርና የሙዚቃ ትምህርት አጥንቶ ልዩ ዲፕሎማ ተቀብሏል ።ከትምህርቱ ጎን ለጎንም በዚያው በባህር ማዶ ‹‹ኤዲፐስ››፣ ‹‹12ኛው ሌሊት›› እና ሌሎች ትያትሮችን ሰርቷል ።በዚያው ዓመት ሞስኮ ላይ በተካሄደው ሰባተኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ጠበብት ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳትፏል ። በጉባዔው ላይም ኢዩኤል ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ አጠር ያለ ማብራሪያ ለታዳሚዎቹ አቅርቦ ነበር ።
ከአብዮቱ በኋላ በ1968 ዓ.ም ወደ ባህል ሚኒስቴር ተዛውሮ ከ1968 ዓ.ም እስከ 1970 ዓ.ም በቴያትር ጥበብ ኤክስፐርትነት፤ ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በሕዝባዊ ኪነ ጥበባት ዋና ክፍል ተመድቦ በየክፍላተ አገራትና አውራጃዎች በመዘዋወር የኪነ ጥበብ ማዕከላት የሚስፋፉበትን፣ ሕዝቡ በኪነ-ጥበባት ትምህርት አማካ ኝነት ንቃትና መዝናኛ የሚያገኝበትን መንገድ በመጠቆም፤ አማተር የኪነ ጥበባት ቡድኖችን በማቋቋም፤ ጥናት በማድረግና ማስረጃ በማቅረብ ሕዝባዊ ኪነ-ጥበብ እንዲዳብርና ሕዝባውያን ኪነቶች ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ።
ኢዩኤል ከ70 በላይ ረጃጅም፣ አጫጭርና ሙዚቃዊ ተውኔቶችን ደርሶ ለመድረክ ያበቃ ስመጥር ባለሙያ ነው ። ከስራዎቹ መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-
- አቻ ጋብቻ
- የሕይወት ፋና የወጣት ዜና
- ዘጠኝ ፈተና ያለፈ ጀግና
- የእግዚአብሔር ቸርነት የአርበኞች ጀግንነት
- ልደት
- ምን ትችል ምድር
- ቃልኪዳን አፍራሹ
- መንገደ ሰማ
- ስራ ለሰሪው እሾህ ላጣሪው
- ከእጅ አይሻል ዶማ
- ከአባ መስተጋድል
- ሀገር መውደድ
- ወፎቹ ተንጫጩ
- ይመሻል ይነጋል
- ብቸኛ የሃሳብ ጓደኛ
- የቆጡን አወርድ ብላ፥ የብብቷን ጣለች
- ዘመን ሲለወጥ
- አያልነሽ
- የቸነፈር ዘመን
- የልጃገረድ ሳሎን
- ሳይቸግር ጤፍ ብድር
- ማን ጠግቦሽ
ኢዩኤል በሀገር ፍቅር ትያትር ቤት እንደሴት ቀሚስ እየለበሰ በመተወን ቴያትር ቤቱን ያሳደገ፣ የኪነ ጥበብ ዘርፉ በርካታ አፍቃሪዎች እንዲኖሩት ያደረገና የኪነት ሰዎችንና ስራዎቻቸውን ሞገስ ያጎናፀፈ ታላቅ ባለሙያ ነው ።‹‹እንተዋወቅ›› የሚል በሀገርኛ ሙዚቃ ላይ ያተኮረ መጽሐፍም ጽፏል ።የኢዩኤል የሙዚቃ ዝግጅቶች ከኢትዮጵያ አልፈው በሱዳን፣ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በናይጀሪያ፣ በቻይና፣ በአውሮፓ፣ በሶቭየት ኅብረት፣ በካናዳና በሜክሲኮ ለታዳሚዎች ቀርበዋል ።
ስለኢዩኤል ዮሀንስ በሌሎች ባለሙያዎች ከተሰጡ ምስክርነቶች መካከል፡-
‹‹ … እንደሕዝባውያን ጸሐፍተ ተውኔት ሊቆጠሩ የሚበቁት እንደኢዩኤል ዮሀንስ፣ ማቴዎስ በቀለና መላኩ አሻግሬ ያሉ ባለሙያዎች በየክፍላተ አገሩ እየተዘዋወሩ የቴያትር ሙያ በማሳወቅ ያበረከቱት አገልግሎት በቀላሉ የሚገመት አይደለም …›› ደራሲና ባለቅኔ ደበበ ሰይፉ
***
‹‹ … ኢዩኤል ከፍተኛ ሰብዓዊነት ያለው፣ ለሰው የሚያስብ፤ ሰው የሚወድ፣ በአገርና በወገን ፍቅር በአርዓያነት ሊጠቀስ የሚችል፣ የኃላፊነት ስሜቱ ላቅ ያለ፣ የተሟላና የተዋጣለት የኪነ-ጥበብ ሰው፣ ባለቅኔ፣ ግዕዝና አማርኛን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ የውጩን ከሀገሩ ጥበብ ጋር አጓድኖ የጨበጠ፤ በገና፣ ክራርና መሰንቆ ተጫዋች፣ ጸሐፌ ተውኔትና ጥልቀት ያለው ኮሜዲያንና ቁም ነገረኛ አክተር ነበር ።ምናልባት እንደዚህ ዓይነት የተሟላ የኪነ-ጥበብ ሕይወት የተላበሱ ሰዎች ብቅ የሚሉት እጅግ በተራራቀ ዘመን ውስጥ ነው … ›› ደራሲና ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ
***
‹‹ … ኢዩኤል ደራሲ፣ ተዋናይ፣ ድምፃዊ፣ ስፖርኛ፣ አካሉ በስፖርት የተገነባ፣ ብስክሌት መንዳትና በእግሩ መሄድ የሚወድ … ምን የማይሆነው ነገር አለ የኪነ-ጥበብ ፍላጎቱ ክብርና ርቀት አለው …›› ጋዜጠኛ መርስዔ ኃዘን አበበ
ኢዩኤል ለስራዎቹ በተለያዩ ጊዜያት ልዩ ልዩ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝቷል ።ከሽልማቶቹ መካከል ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የተሸለማቸው የወርቅ ብዕርና የእጅ ሰዓት ተጠቃሽ ናቸው ።በወታደራዊው መንግሥት ዘመንም ብዙ ሽልማቶችንና እውቅናዎችን አግኝቷል ።
በኢትዮጵያ የቴያትርና የሙዚቃ ዘርፍ ላይ ደማቅ አሻራውን ማሳረፍ የቻለው የጥበብ መሃንዲሱ ኢዩኤል ዮሐንስ ኅዳር 11 ቀን 1981 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 19/2013