አንጋፋው የስፖርት ሰው – ፍቅሩ ኪዳኔ

አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ እ.ኤ.አ ታህሳስ 26 ቀን 1935 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። ገዳም ሰፈር አደጉ። ትምህርታቸውንም በሊሴ ገ/ማርያም የተከታተሉት እኚህ ዓለም ዓቀፍ የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ የስፖርት ጋዜጠኝነት ፍላጎት ገና በወጣትነት ዕድሜያቸው ስላደረባቸው በቀድሞ ማስታወቂያና መርሐ ብሔር ሚ/ር በኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ ሥር በየሳምንቱ ቅዳሜ እየታተመች የምትወጣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የስፖርት ዓምድ አዘጋጅ ሆነው ተቀጠሩ። በኢትዮጵያ ሬዲዮም የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን የኳስ ሜዳ ውድድሮችን በቀጥታ በሬዲዮ በማስተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የ1968 እና 1976 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን አዘጋጅ ኮሚቴ እና ዋና ፀሐፊ በመሆን ሥራቸውን በተሳካ መልኩ ተወጥተዋል። እንዲሁም በጋዜጠኝነት በስፖርት መምህርነትና በአሠልጣኝነት ሀገራቸውን ኢትዮጵያን በከፍተኛ ሁኔታ አገልግለዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድን ለመዋጋት በግልና በኮሚቴ ሰብሳቢነት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በሕይወት ዘመናቸው በተለያዩ የሥራ መስኮች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ከባድ ፈተናዎችን አልፈዋል። ከ1956 –1958 የአካል ማሰልጠኛ መምህር፣ ከ1958 –1960 በጋዜጠና በሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኛ ከ1960-1961 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኮንጎ ጦርነት ወቅት ሠራተኛና በኋላም በዚሁ ድርጅት እስከ 1974 ዓ.ም ተቀጣሪ ሠራተኛ በመሆን በከባድ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡

የበርካታ ሙያ ባለቤቶች ሆነው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ከ1974 – 1976 ዓ.ም ለቢቢሲ፣ ለሬድዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል፣ ለአሜሪካና ለጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ጣቢያዎች በጊዚያዊ (ፍሪላንሰርነት) ሠርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ‹‹L. Equip›› ለተባለው ሳምንታዊ የፈረንሳይ እግር ኳስ ጋዜጣና ለሌሎችም ታዋቂ የስፖርት ጋዜጦች በመሥራት ችሎታዎቻቸውን አስመስክረዋል። ከሊሴ ገ/ማርያም የቀሰሙትን የፈረንሳይኛ ቋንቋ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠቀሙበት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ከ1977–1982 መቀመጫቸውን ፈረንሳይ ሀገር በማድረግ ‹‹Jeuxd Af­ricque›› በአፍሪካ የተባለ ስፖርት ላይ ብቻ ያተኮረ መጽሔት ዋና አዘጋጅ በመሆን ከመሥራታቸው በተጨማሪ ከ1982–1989 ዓ.ም በፈረንሳይኛና በእንግሊዘኛ የሚታተም አፍሪካዊ (አህጉራዊ) የስፖርት መጽሔት መሥራችና ዳይሬክተር በመሆን ለአፍሪካ፣ ብሎም ለዓለም ወጣቶች ስፖርት ትልቅ ድርሻ አበርክተዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በስፖርት መስክ ካፈራቻቸው ዕውቅ ሰዎች አንዱ የሆኑት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ከ1989 –1993 ዓ.ም የዓለም አቀፍ (ኢንተርናሽናል) ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ሁዋን አንቶንዮ ሳማራጅ አማካሪ፣ ከ1994 – 2002 በዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ትብብርና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና የ‹‹ኦሎምፒኮ ሪቪው›› መጽሔት ዋና አዘጋጅ በመሆን አኩሪ ሥራቸው ዘለዓለማዊ ሆኖ እንዲቀመጥ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ያልተዘመረለት ዓለም አቀፍ የስፖርት ጀግና፣ አዋቂና አስተዋይ ፍቅሩ ኪዳኔ በሀገር ውስጥ ካከናወናቸው ሥራዎች በተጨማሪ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማትና ድርጅቶች ውስጥ በነፃ አገልግለዋል። ከ1967–1976 ዓ.ም ሀገሩ ኢትዮጵያን በተለያዩ ፌዴሬሽኖች በተለይም የእግር ኳስ፣ የቴኒስ፣ የብስክሌትና የብሔራዊ ኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ በመሆንም ሙያዊ አስተዋኦዋቸውን አበርክተዋል፡፡

አቶ ፍቅሩ ከ1970–1974 ዓ.ም የአፍሪካ ስፖርት ጋዜጠኞች ሕብረት (USAG) መሥራችና አንደኛ ጸሐፊ በመሆን ማሕበሩ በእግሩ እንዲቆም አድርገዋል። በኋላም የዩኔስኮ (Fair) lay) አባል፣ የኢንተርናሽናል ስፖርት ጋዜጠኞች ማሕበር (AIPS እና UGSA) የክብር አባል ነበሩ።

እኚህ ታዋቂ የስፖርት ሰው የኦሎምፒክ ጌምሴ (የኦሎምፒክ ጨዋታዎች) የሚል መጽሔት በማዘጋጀት በ1960 ዓ.ም በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት አሳትመዋል። በአውሮፓና በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ለተካሄዱት የውይይቶች እንዲሁም ለምርምርና ጥናት የሚረዱ ጽሁፎችን በጥሩ ሁኔታ አቅርበዋል፡፡

አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በሥራ ዘመናቸው ለስፖርቱ በተለይም ለእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ ብሎም በዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ስፖርት እድገት፣ አፍሪካውያን በሁሉም ስፖርት ዓይነቶች እምቅ ችሎታ ያላቸውን ወጣቶች በዓለም አደባባይ ወጥቶ እንዲያሳዩ የከፈቱት መድረክ ምን ጊዜም ሲታወስ ይኖራል፡፡

አቶ ፍቅሩ ሁሌ ለሀገሩ ኢትዮጵያ ስፖርት ማደግ ከመመኘታቸውም በላይ ኢትዮጵያ በሁሉም ተጠቃሚ እንድትሆን በማሰብ ከአፍሪካ አልፋ ከዓለም ጋር ግንኙነት እንዲኖራት ለኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማሕበርን በመመሥረት የአፍሪካ ጋዜጠኞች ማሕበር አባል እንዲሆን አድርገዋል። ለዚህ ማሕበር ዓመታዊ የአባልነት ክፍያ ሁሉ ከራሳቸው ኪስ በማውጣት ረድተዋል፡፡

አቶ ፍቅሩ የስፖርት ጋዜጠኞች በሀገር ውስጥ በማሕበር ከመደራጀታቸውም በላይ በየጊዜው እራሳቸው ጭምር በመመላለስ የዕውቀት ክሕሎት እንዲያዳብሩ የተለያዩ የዓለም የስፖርት ምሁራንን በመጋበዝ ትልቅ የሙያ እገዛ አድርገዋል።

አቶ ፍቅሩ የስፖርት ጋዜጠኞች ማሕበርን ከመመሥረታቸው በፊት የማሕበሩን ዓላማ ለመንግሥት አቅርበው ለማሳመን የወጡበት እና የወረዱበት መንገድ በወቅቱ አስቸጋሪ እንደነበረ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ይናገራሉ፡፡

ነዋሪነታቸው ፈረንሳይ ሀገር የነበሩት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ለዓለም ሠላም፣ ለስፖርት ዕድገት፣ በተለይም ወጣቶችን በአንድ ጥላ ሥር በማሰባሰብ ሠላም ፣ ፍቅር ፣ ወንድማማችነት የጾታ ፣ የቀለምና የእምነት ልዩነት ሳይኖር በአንድነት በአንድ መድረክ ላይ እንዲዘምሩ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

በስፖርት ጋዜጠኝነት፤ በአመራርነት እና በደራሲነት የሚታወቁት አንጋፋው የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ የእግር ኳስ ጨዋታን በቀጥታ በሬዲዮ በማስተላለፍ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ በተለያዩ ቋንቋዎች የተለያዩ የስፖርት ዘገባዎችን በማቅረብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በካፍ እና ኦሎምፒክ አመራርነት በጋዜጠኞች ማሕበር መስራችነት እና አመራርነት ከፍተኛ አገልጋሎት ሰጥተዋል። የፒያሳ ልጅ የሚለውም መጽሃፋቸው እውቅና ካገኙበት ሥራዎቻቸው አንዱ ነው፡፡

በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያውን የእግር ኳስ ግጥሚያ በሬዲዮ ከማስተላለፍ አንስቶ፣ በሬዲዮና በጋዜጣ ላይ ስፖርትን የሚመለከቱ ዘገባዎች ቦታ እንዲያገኙ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ የመጀመሪያው የእግር ኳስ ግጥሚያ በሬዲዮ ከማሰራጨት እስከ ፀሐፊ እና የስፖርት ሕትመቶች ዋና አርታዒነት ደርሰዋል። በስፖርት እውቀታቸው ዓለም አቀፍ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሴክሬታሪያት ፀሐፊ ሆነው አገልግለዋል። በዘርፉ ላስመዘገቡት አስተዋጽኦ በዓለም አቀፉ የስፖርት ፕሬስ ማሕበር የሕይወት ዘመን ስኬት ሽልማትን ተቀብለዋል።

ጥቅምት 01/2015 ዓ.ም. ፈረንሳይ ውስጥ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን አንጋፋውን የስፖርት ሰው ፍቅሩ ኪዳኔ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ እና የሱዳን ብሔራዊ ቡድኖችን የእግር ኳስ ግጥሚያን ለመጀመሪያ ጊዜ ማስተላለፋቸውን ይገልጻሉ።

አቶ ፍቅሩ ይህን ጨዋታ እንዴት በሬዲዮ እንዲያስተላልፉ የተደረገው በድንገትና ሳያስቡት ነበር። ይህም ጨዋታውን ለሕዝብ ጆሮ እንደሚያደርሱ ሳይነገራቸው እና ምንም አይነት ዝግጅት ሳያደርጉ ቀጥታ ስርጭት ውስጥ መግባታቸውን የተናገሩ ሲሆን ሆኖም ስርጭቱ ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ሱዳኖች የእግር ኳስ ጨዋታውን ከአዲስ አበባ በቀጥታ በሬዲዮ እንደሚያስተላልፉ የተረዱት አቶ ይደነቃቸው ተሰማ፣ እኛስ ለምን አናስተላልፍም? በማለት ሀሳቡን በድንገት እንዳመጡት ይነገራል።

ከዚያም ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር የቀጥታ ሥርጭቱ በመፈቀዱ ጨዋታው ከመጀመሩ ከደቂቃዎች በፊት አቶ ፍቅሩ እንደሚፈልጉ በድምጽ ማጉያ በድንገት ተጠርተው የቀጥታ ሥርጭት ውስጥ ገብተው ማስተላለፍ ጀመሩ።

አቶ ፍቅሩም “ጨዋታው ሊጀመር 10 ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩት ትፈለጋለህ ተብዬ ተጠርቼ ስሄድ፣ አቶ ይድነቃቸው አንተ እኮ ነው የምትፈለገው ብሎ የተጫዋቾችን አሰላለፍ ሰጥቶ ጨዋታውን እንዳስተላልፍ ነገረኝ” ሲሉ አስታውሰዋል።

ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ የስፖርት ውድድር ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ስታዲዮም (በ1948 ዓ.ም.) የእግር ኳስ ጨዋታ በሬዲያ በቀጥታ በማስተላከፍ አቶ ፍቅሩ ቀዳሚው ሆኑ። በሕትመት ውጤቶች ላይም ቢሆን ስፖርታዊ ጉዳዮችን መዘገብ የተጀመሩት በአቶ ፍቅሩ ጥረት ነበር። ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ለቢቢሲ ሲናገር፤ “በጋዜጦች ላይም ስፖርት የሚባል አይታወቅም ነበር። ከ1950 በኋላ ፍቅሩ ነበር መጻፍ የጀመረው።”

ቢቢሲ አማርኛው ክፍል እንደዘገበው በኒውዮርክ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ሲሰሩ የቆዩት አቶ ፍቅሩ፣ ወታደራዊው መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጣበት ጊዜ እንደወጡ ቀርተው ለበርካታ ዘመናት በተለያዩ ሀገራት ውስጥ ኖረዋል።

ነገር ግን ባሉበት ሆነው በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፖርቶች እንዲጎለብቱ የሚችሉትን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ቆይተው፤ አብዛኛውን እድሜያቸውን በቆዩባቸው የውጭ ሀገራት ውስጥ ሆነው እንኳን ለኢትዮጵያ ስፖርት ሲሰሩ ቆይተዋል።

አቶ ፍቅሩ በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፖርቶች ውስጥ ፍቅሩ ያልገቡበት ዘርፍ የሌለ ሲሆን አሁን ትኩረትን እየሳበ ያለው የሴቶች እግር ኳስ እንዲጎለብት የአቶ ፍቅሩ ሚና ጉልህ እንደነበር ይጠቅሳል።

ፍቅሩ ከእግር ኳስ ባሻገር በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ውስጥ ኢትዮጵያ ውክልና እንዲኖራት በግሉ የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ እንደቆየ እና ብዙም አቅም የሌላቸው የስፖርት ፌዴሬሽኖችን በመወከል በእራሱ ወጪ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ ይሳተፍ ነበር።

እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የዘር መድልዎ (አፓርታይድ) ሥርዓት በመቃወም ሀገሪቱ ከዓለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች እንድትታገድ ከአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር ከፍተኛ ጥረት ከማድረግ ባሻገር፤ በዓለም አቀፍ ሕትመቶች ላይ ፀረ አፓርታይ የቅስቀሳ ጽሁፎችንም ሲያቀርብ ቆይቷል።

አቶ ፍቅሩ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስለኦሊምፒክ ጨዋታዎች ያለው እውቀት እምብዛም ባልነበረበት ወቅት ውድድሩን ለሀገሬው ለማስተዋወቅ መጽሐፍ እስከ ማሳተም ደርሰው ነበር።“የኦሊምፒክ ጨዋታ የሚል መጽሐፍ በ1960 አሳተምኩ። ይህን መጽሐፍ ያዘጋጀሁት ሕዝቡ ስለ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እውቀት እንዲኖረው ነው።” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ይህን መጸሐፍም ለትምህርት ሚኒስቴር በመስጠት በሀገሪቱ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንዲታደሉ በማድረግ ወደ ወጣቶች እንዲደርስ አድርገዋል።

አቶ ፍቅሩ ከስፖርት ጋር በተቆራኘው ሕይወታቸው በበርካታ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። የኢትዮጵያ የብስክሌት ፌዴሬሽን፣ የቴኒስ ፌዴሬሽን፣ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ፀሐፊ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

አቶ ፍቅሩ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማኅበርን አቋቁመው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት በመሆንም ሠርተዋል። ከኢትዮጵያም ውጪ አቶ ፍቅሩ ከኦሊምፒክ ውድድር ጋር ባላቸው ቁርኝት ትልቅ የሥልጣን ደረጃ ላይ መድረስም ችለው ነበር። አቶ ፍቅሩ የመጀመሪያው ጥቁር የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ ሆነው በመሾም ሰርተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የፕሬዚዳንቱ ልዩ አማካሪ፣ የአፍሪካ የሰፖርት ጋዜጠኞች ማኅበር ዋና ፀሐፊ በመሆን አገልግለዋል። የፊፋ የፕሬስ ኮሚቴ አባል የነበሩ ሲሆን እንደ ቢቢሲ፣ የአሜሪካ ድምጽ፣ ሬዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ላሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን ይሰሩም ነበር።

ለረጅም ዓመታት ለዓለም ሰላምና ደህንነት ላበረከቱት የላቀ አስተዋጾኦ በ1961 ዓ.ም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሜዳልያ በ1962 ዓ.ም ከኢትዮጵያ መንግሥታት ከፍተኛ አግልግሎት ላበረከቱት የሚሰጥ የክብር ኮከብ ሜዳሊያ ፣ በ1968 ዓ.ም ከትሪንዳድና ቶቤጎ የወርቅ ሜዳልያ ፣ በ1976 ዓ.ም ከፈረንሳይና ወጣቶች ስፖርት ሚኒስትር የወርቅ ሜዳልያ፣ በ1999 ዓ.ም ከዩናይትድ ስቴት ስፖርት አካዳሚ የላቀ አገልግሎት ሽልማት ተቀብለዋል በሜክሲኮ ሁለት ከተሞችም (oxaca እና monterrey) የክብር ነዋሪነት ፍቃድ ተሰጥቶአቸዋል።

ይህንን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የቢቢሲ አማርኛን እና ሌሎች ደረገጾችን እንዲሁም መጽሃፍትን ተጠቅመናል፡፡

ተሾመ ቀዲዳ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You