ኢትዮጵያዊቷ አርበኛ – ሲልቪያ ፓንክርስት

ሲልቪያ ፓንክርስት እ.ኤ.አ በ1882 እንግሊዝ ሀገር ተወልዳ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው እ.ኤ.አ መስከረም 27 ቀን 1960 አዲስ አበባ ነበር። አስከሬኗ የተቀበረውም ወለተ ክርስቶስ ተሰኝታ እንደ ሌሎች ታላላቅ አርበኞች ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንና ሌሎች ክቡራን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነበር። የ50ኛው ዓመት መታሰቢያዋ መስከረም 17 ቀን 2003 ዓ/ም በቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ተከብሯል።

ከዚህ በታች በዝርዝር እንደሚቀርበው ፋሺሽቶችና በጊዜው የነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመቆራረስ የነበራችውን ዓላማ በመቃወም ለኢትዮጵያ ነፃነት በሙሉ ቆራጥነት ባከናወነችው ከፍ ያለ ተጋድሎና ላስገኘችው አመርቂ ውጤት በተጨማሪም፤ ሲልቪያ ፓንክርስት ካከናወነቻቸው ከፍተኛ ተግባሮች ውስጥ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታልን ለማሠራት የሚያስፈለገው ገንዘብ እንዲዋጣ ማድረጓ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት እንዲከበርና ፓርላማውም እንዲሻሻል ያደረገችው ጥረት ሁሉ ይጠቀሳል።

ሲልቪያ ፓንክርስት በዜግነት እንግሊዛዊት ብትሆንም በተጨባጭ ተግባሯ ግን የኢትዮጵያ ጀግና የነበረች ናት። ይህ ጽሑፍ ስለዚህች ጀግና በቂ ግንዛቤ እንዲኖር የሚጥር ከመሆኑ ሌላ ይህን ለመሰለ ከፍ ያለ ጥረትና ተጋድሎ ተገቢውን ዋጋ የሚከፍል ኢትዮጵያዊ ትውልድ ስላለ፣ ለወይዘሮ ሲልቪያ ፓንክርስት የፀረ–ፋሺሽትና ፀረ–ቅኝ አገዛዝ አቋም፣ ለኢትዮጵያ ያበረከተችው መስዋዕትነትና አርአያነት ታውቆና ተከብሮ እንዲኖር ተገቢው ልዩ መታሰቢያ እንዲቆምላትና በስሟ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም የሚያስገኝ የመታሰቢያ አገልግሎት ተቋም እንዲቋቋም ለማሳሰብ ነው።

በተጨማሪም፤ ታዋቂው የሲልቪያ ፓንክርስት ልጅ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክርስት፤ ለብዙ ዘመን በማስተማርና ስለ ኢትዮጵያ በመጻፍ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን ለማስታወስና ባለቤቱም ሪታ ፓንክርስት የቤተሰቡ የጀርባ አጥንት በመሆን ኑሯቸውን በአዲስ አበባ አድርገው ሁለቱም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ሲልቪያ እድሜዋ 20 ዓመት ሲሆን የሞዜይክ (mosaic) ሥነ ጥበብ ለማጥናት እ.ኤ.አ በ1902 ቬኒስ ከተማ፤ ኢጣሊያ ሄዳ ስለነበር ስለሀገሩ ያደረባት ልዩ ዝንባሌ ከዚያን ጊዜ ጀመረ። በወጣትነት እድሜዋ የነበራት ትኩረትና ስትታገልለት የነበረው ዓላማዋ የእንግሊዝ ሴቶች የመምረጥ መብት እንዲኖራቸው ለማድረግ ቢሆንም እ.ኤ.አ በ1919 ለጉብኝት ቦሎኛ ከተማ፤ ኢጣሊያ በነበረችበት ጊዜ የሙሶሊኒ ወንበዴዎች (“ስኩዋድሪስቲ”) ተራውን ሕዝብ ሲደበድቡ ተመልክታ የትግልዋ ትኩረት ፋሺሽቶችን በመቃወም ላይ አነጣጠረ። (2) የፀረ–ፋሺሽት አቋሟ ተጠናክሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያተኮረው ግን ኢጣሊያ እ.ኤ.አ ታኅሣሥ 5 ቀን 1934 ወልወል፤ ኢትዮጵያ ላይ በፈጸመቻቸው ወረራ ምክንያት ነበር።

የሙሶሊኒ ዓላማ ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር መሆኑን በመገንዘብ ሲልቪያ ፓንክርስት በጊዜው የነበረው የመንግሥቶች ማሕበር (League of Na­tions) ገብቶ በነበረው ቃል ኪዳን መሠረት፤ ኢትዮጵያን ከኢጣሊያ ወረራ እንዲያድን ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎች በመጻፍ እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባዎች በማካሄድ ከፍ ያለ ጥረት አድርጋ ነበር። ነገር ግን፤ በተጻራሪው በተለይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥቶች ከኢጣሊያ ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያድሙ ስለነበር ወረራውን የሚያበረታታው እንጂ የሚያቆመው ኃይል አልተገኘም። እንዲያውም ሲልቪያን እጅግ ያስገረማት ክስተት እ.ኤ.አ በ1935 የእንግሊዝ መንግሥት ስለ ጉዳዩ እንዲያጠና በሰር ጆን ማፊ የተመራ ኮሚቴ አቋቁሞ የቀረበለት አስተያየት፤ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ብትወር እንግሊዝን የሚጠቅማት እንጂ የሚጎዳት አለመሆኑን መጠቆሙ ነበር። ከመንግሥታቱ ማህበር አንዱዋ በነበረቺው ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ወረራ ድርጅቱ በነበረበት ግዴታ መሠረት ባለማስቆሙ ጠንቁ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በተከሰተው እልቂት፤ ለአውሮፓ ለራስዋም እንዲተርፋት ሆነዋል። ሲልቪያም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ እለተ ሞቷ ድረስ ለኢትዮጵያ መብትና ነፃነት ጸንታ ታገለች።

እ.ኤ.አ በ1935-40 ኢጣሊያ፤ ለአምስት ዓመቶች ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ በተፈጸመው ግፍ እጅግ ብዙ እልቂትና ውድመት ደርሶ ነበር። በጥይት፣ በቦምብ እንዲሁም በአውሮፕላኖች በተነሰነሰ የመርዝ ጋዝ ጭምር አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨፈጨፉ። ከነዚሁ ውስጥ በ3 ቀኖች ውስጥ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ 30,000 ሕዝብ ተገደለ። አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል እንዲሁም ሌሎች ብዙ አርበኞች ተሰው። 2000 ቤተክርስቲያኖችና 525,000 መኖሪያ ቤቶች ተደመሰሱ። በተጨማሪም በመርዙ ዝናብ 14 ሚሊዮን እንስሶችና ብዙ እጽዋት ወደሙ። ይህ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ ሲከናወን ኢትዮጵያ በአርበኞቹዋ አማካኝነት ከፋሺሽቶቹ ጥቃት የመከላከል ትግልዋን አላቋረጠችም ነበር። አጼ ኃይለ ሥላሴም በስደት አውሮፓ ሄደው የዲፕሎማሲ ጥረታቸውን አጠናክረው ቀጥለው ስለነበር ከሲልቪያ ፓንክርስት ጋር የተገናኙት በዚያን ጊዜ ነበር።

ኢጣሊያ ወልወል ላይ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ፤ በመጨረሻም እ.ኤ.አ በ1941 ድል ተመትታ እስከ ተወገደችበት ድረስ ሲልቪያ ሙሉ የሕይወቷ ዓላማና ተግባር ያደረገቺው ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ነበረ ማለት ይቻላል። ያከናወነቻቸው ተግባሮች እጅግ ብዙ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ይጠቀሳሉ።

ኢጣሊያ የወልወል ትንኮሳዋን አከናውና ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር በምትንቀሳቀስበት ጊዜ፤ ኢትዮጵያም መከላከል እንድትችል የመንግሥታት ማህበር በጋራ ደኅንነት (collective security) ግዴታው መሠረት ኢትዮጵያን እንዲደግፍ ከመጠየቋም በላይ ፋሺዝም ለዓለም ጠንቅ የሚያመጣ መሆኑን አስገንዝባ ነበር።

ሲልቪያ ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎችዋን ለእንግሊዝና ለሌሎች መንግሥቶች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሃን (ለምሳሌ ቢ.ቢ.ሲ፤ ዴይሊ ኤክስፕሬስ፤ ማንቸስተር ጋርዲያን፤ ዴይሊ ቴሌግራፍ፤ ኒውስ ክሮኒክል፤ ወዘተ) በመጻፍ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተቃጣው የፋሺሽት ወረራ ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝና ተገቢው ርምጃ እንዲወሰድ ከፍተኛ ጥረት አድርጋ ነበር። “የአውሮፓ ሕሊና ሞቷል ወይ? በእንግሊዝ ሀገር ታማኝ አስተሳስብ ጠፋ ወይ?” እያለች ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓን ሕዝቦች ስሜት ለመቀስቀስ ሞክራ ነበር።

በሌላም በኩል ኢትዮጵያ በባሪያ ንግድ ትጠቀማለች በማለት ፋሺሽቶች ያሰራጩ የነበረውን ሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመቃወም አጋልጣለች። ለአፍሪካም የዘለቄታ ጥቅም በማሰብ፤ በፀረ–ፋሺሽትና ፀረ–ኮሎኒያሊስት መርሆ ተሠማርተው የነበሩትን እነጆሞ ኬንያታን (ኬንያ)፤ ኤሚ አሽውድ ጋርቪ (ጃሜይካ) እንዲሁም የሙሶሊኒ ተቃዋሚ የነበሩ ጣሊያናዊ ታጋዮችን ጭምር በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲተባበሩ አድርጋ ነበር።

በጊዜው በለንደን የኢትዮጵያ ሚኒስትር (አምባሳደር) ከነበሩት ከዶ/ር ወርቅነህ እሸቱ (ቻርልስ ማርቲን) ጋር በመተባበር እንዲሁም ከእቴጌ መነን ጋር በመጻጻፍ በኢትዮጵያ በኩልም ስለነበረው ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራት ታደርግ ነበር።

ለኢትዮጵያ ነፃነት ታከናውነው በነበረው ትግል እንዲረዷት ታዋቂ ከነበሩ የእንግሊዝ ምሁራን፤ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ኤፍ.ኤል.ሉካስ፤ እንዲሁም እንደ ፊሊፕ ኖዌል ካሉ የፓርላማ አባሎች ጋር በቅርብ እየተመካከረች ትሠራ ነበር።

እ.ኤ.አ ከጥቅምት 1935 ጀምሮ ኢጣሊያ የኢትዮጵያ ወረራዋን ስትቀጥል በምዕራባውያን በኩል በተለይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥቶች የጦር መሣሪያ ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ማዕቀብ ሲጥሉ በሌላ በኩል ለኢጣሊያ ነዳጅ ጭምር በማቀበል የግፍ ወረራው እንዲሳካላት አድርገው ነበር። በመጨረሻም ኢጣሊያ አዲስ አበባንና አብዛኛዎቹን የኢትዮጵያ ከተሞች ስትቆጣጠር የእንግሊዝ መንግሥት የቅኝ ግዛት ሥልጣኗን አውቆላት ነበር። እ.ኤ.አ. ከ1935-40 ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከሞላ ጎደል በተቆጣጠረችበት ዘመን፤ ሲልቪያ ፓንክርስት ያላቋረጠ እጅግ ከፍ ያለ የተቃውሞ ጥረት ታከናውን ነበር። ካከናወነቻቸውም አያሌ ተግባሮች ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው፤

(ሀ) ለዓለም መንግሥታት ማኅበር፣ ለዊንስተን ቸርቺል፣ ለእንግሊዙ ሊቀ ጳጳስ፣ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልትና ለሌሎችም ኃያላን የአቤቱታ ደብዳቤዎች መጻፏ፤

(ለ) እ.ኤ.አ በ1936 “አዲስ ዘመንና የኢትዮጵያ ዜና” (5) የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁማ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረጓ፤

(ሐ) እ.ኤ.አ በየካቲት 1937 አዲስ አበባ ብቻ 30,000 ሕዝብ ሲጨፈጨፍ የጦር ወንጀሉ በይፋ እንዲታወቅ ማድረጓ፤

(መ) አጼ ኃይለ ሥላሴ ለንደን ሲደርሱ በክብር ተቀብላ በየጊዜው ቃለመጠይቆች እያከናወነች፤ ባቋቋመችው ጋዜጣ አማካኝነትና በነበራት ሰፊ ሕዝባዊ ግንኙነት ንጉሠ ነገሥቱ ድጋፍ እንዲያገኙ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

(ሠ) የዓለም መንግሥታት ማህበር ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ በሚወያይበት ጊዜ ጄኔቫ ድረስ በመመላለስ መልእክተኞቹን በማነጋገር ኢትዮጵያ ለጊዜው በኢጣሊያ ብትወረርም የማህበሩ አባልነቷ እንደተጠበቀ እንዲቆይና ሌላ ድጋፍም እንድታገኝ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

(ረ) ብዙ ምሁራንን፣ የሰብዓዊ መብት ደጋፊዎችን፣ የፓርላማ አባሎችን፣ የቤተክርስቲያን መሪዎችን፣ ወዘተ. በማስተባበር ብዙ አቤቱታዎችንና መግለጫዎችን በሰፊው በማሰራጨትና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማከናወን የእንግሊዝ መንግሥትን ፖሊሲ ለማስቀየርና እንዲያውም ከአርበኞቻችን ጋር በመተባበር ኢጣሊያኖችን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ እጅግ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

(ሰ) ያከናወነቺው ባለብዙ ዘርፍ ያላሰለሰ የፖለቲካ ትግል እንግሊዞች የኢትዮጵያን አርበኞች ጦር ደግፈው የኢጣሊያ ግፈኛ ጦር ድል ተመትቶ እ.ኤ.አ በ1941 የኢትዮጵያ ነፃነት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷና ሌሎችም ብዙ ምሥጉን ተግባሮቿ ሁልጊዜም የማይረሱ ናቸው።

(ሲልቪያ ፓንክርስት በጣሊያንና ኢትዮጵያ መካከል ከ1935-40 ዓ.ም በተደረገው ጦርነት ኢትዮጵያን በመደገፍ ታትመው የነበረ ጋዜጣ፤)

የእንግሊዞች መቋመጥና የሲልቪያ ትግል፤

እ.ኤ.አ በ1941 ኢትዮጵያ ከፋሺሽት ኢጣሊያ ነፃ ከወጣች በኋላ ቀጥሎ ያጋጠማት ከባድ ችግር የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን በቁጥጥሯ ስር (protectorate) ለማድረግ፤ ይህ ሳይቻል ደግሞ ኤርትራን፣ ኦጋዴንንና ቦረናን ለመቆጣጠር መወሰኗ ነበር። በዚህም ረገድ ሲልቪያ ከአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ትግል አከናውና የእንግሊዝ መንግሥት እኩይ ዓላማ እንዲከሽፍ እጅግ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አድርጋለች፤

(ሀ) በዚያን ዘመን ሲልቪያ ለእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለፓርላማው፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውና ለሌሎችም በምትጽፋቸው አቤቱታዎችና በምታከናውናቸው የማጋለጥና የተቃውሞ ተግባሮቿ እንደ ኮሎኔል ጊልበርት ማክበረት የነበሩ ቁልፍ ባለሥልጣኖች ስለ ሲልቪያ የሚሰማቸውን ቁጣ ይገልጹ ነበር። ቢሆንም ለኢትዮጵያ ነፃነት በነበራት ጽኑ እምነት ማንም ሊያንበረክካት አልቻለም።

(ለ) በጊዜው የነበሩት የእንግሊዝ መሪዎች ቢቃወሟትም ኤርትራ ከእናት ሀገርዋ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል አስደናቂ ጥረት አድርጋ ነበር። እ.ኤ.አ በኅዳር 1941 የእንግሊዝ መንግሥት ኤርትራን ለኢትዮጵያ ማስረከብ ይገባታል ብላ አጠንክራ ጠይቃ ነበር።

(ሐ) እንግሊዞች ኤርትራ ውስጥ በተለይ ምጽዋ የነበረውን ጠቃሚ ንብረት እያወላለቁ ሲያግዙ ሲልቪያ ተቃውሞዋን አሰምታ ነበር።

(መ) ኢጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ከተወገዱ በኋላ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ግዛቶች ለመቀራመት የነበራቸው ዓላማ በነሲልቪያ ጠንካራ የ14 ዓመት ትግልና በኢትዮጵያ መንግሥትም አልበገር ባይነት ሳይሳካ በመቅረቱ በመጨረሻው እ.ኤ.አ በ1954 ከኢትዮጵያ አካባቢ ለቀው ወጡ።

ከፋሺሽቶችና ከኮሎኒያሊስቶች ጋር በመታገል ካስገኘችው ከፍተኛ ውጤት በተጨማሪ፤

(ሀ) የኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲሻሻልና ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሀገሩ የፖለቲካና የማኅበራዊ ጉዳዮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር በማሳሰብ ለአጼ ኃይለሥላሴ በመጻፍ አመልክታ ነበር።

(ለ) ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባሕልና ሥልጣኔ እየጻፈች ስለ ሀገራችን ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝ አድርጋለች።

(ሐ) እ.ኤ.አ በ1956፣ በ74 ዓመቷ ከልጇ ከሪቻርድ ፓንክርስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ኑሮዋን በመቀጠሏ ከራሷ እጅግ አስደናቂ አገልግሎት በተጨማሪ ልጇም የልጅ ልጇም ቤተሰቡ በሙሉ ለኢትዮጵያ ከፍተኛና የሚያስመሰግን አገልግሎት አከናውነዋል።

(መ) ኢትዮጵያ ከመጣች በኋላም “Ethiopia Observ­er” የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁማ ነበር። ቀደም ብላ ግን ኢትዮጵያ ነፃነቷን ካገኘች አገልግሎቱ አብቅቷል በማለት እንግሊዝ ሀገር አቋቁማው የነበረውን “New Times and Ethiopia News” የተሰኘውን ጋዜጣዋን እንዲቋረጥ አድርጋለች።

(ሠ) አዲስ አበባ የሚገኘው እጅግ ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው የልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል የተሠራው በሲልቪያ ጥረት በተገኘው ገንዘብ ነበር።

ይህንን ጽሑፍ ስንጠቀም በዋነኝነት ሰምና ወርቅ ከተሰኘ ስለሲልቪያ ፓንክረስት ከተጻፈ ሰፊ ጽሑፍ ውስጥ ለጋዜጣ በሆነ መልኩ አጥሮ የቀረበ ነው፡፡ የጽሑፉን አዘጋጆች እናመሰግናለን፡፡

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You