ግብርናው የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑ በተደጋጋሚ ይገለፃል፡፡ ታዲያ ይህ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ካልቻለ ብሎም በዚሁ ፍጥነት ጥራቱን እያረጋገጡ ከአገር ውስጥ ፍጆታነት አልፎ የውጭ ገቢ በማስገኘት የሚጠበቅበትን ግብ እንዲመታ ካልተደረገ ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ሩጫ መግታቱ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ውጤቱን የማምጣት ተልዕኮም ለአንድ ዘርፍ ብቻ የተተወ ባለመሆኑ የተለያዩ ባለድርሻዎች አርሶ አደሩን ከማንቃት ጀምሮ በሚሰሩ ሥራዎች ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዛሬም በዚሁ ዙሪያ መጪው የበልግ ወቅት ለዘርፉ ምን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖዎች ይኖሩት ይሆን? በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ማዕከላት ኢሊኖ እንደሚከሰት የተሰጠው ማመላከቻስ እንዴት ይታያል? በሚል ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲና ግብርና ሚኒስቴር ጋር ቆይታችንን አድርገናል፡፡
ኤጀንሲው
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ፤ ወቅቶች ከመግባታቸው በፊት ኤጀንሲው ያለፈውን ወቅት ግምገማና የቀጣዩን ወቅት የሚጠበቀውን የአየር ፀባይና ሁኔታ መረጃዎችን ለተጠቃሚ ዘርፎች እንደሚያስተላልፍ ይናገራሉ፡፡ በዚህም 2011 ዓ.ም የበጋ የአየር ፀባይና ሁኔታ ግምገማውንና የ2011 የበልግ ወቅት የአየር ትንበያውን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት አቅርቧል፡፡
የበልጉ ዝናብ ለግብርናው ትልቅ ትርጉም እንዳለው የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በወቅቱ ዋነኛ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የአገሪቱ አርብቶ አደር አካባቢዎች በመሆናቸው የግጦሽ ሳር እንዲሁም የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ይጠቁማሉ፡፡ በሰብል ልማት ላይም በበልግ ወቅት የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ እርጥበታማ የአየር ሁኔታ እንዲኖራቸው ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህም ለግብርናው ሥራ የሚያግዝ ምቹና አዎንታዊ አስተዋፅኦን ያበረክታል፡፡ ከመስኖ ሥራዎች ልማት አኳያም በመስኖ ለሚጠቀሙ አካባቢዎች የውሃ መኖር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ መጥፎ የሚባል አይደለም፡፡
ከኢሊኖ ስጋት ጋር ተያይዞ በአንድ አካባቢ ላይ ሲከሰት አንድምታው ምንድነው የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ በበጋ ላይ እንዲሁም በክረምት ላይ ሲከሰትስ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል? የሚለውንም ማየት ያስፈልጋል፡፡ ኢሊኖ በዚህ ወቅት ቢከሰት ጎርፍ ሊከሰት ይችል እንደነበር በማንሳት፤ ግንቦት መጨረሻ ከተከሰተ ክረምቱን ደረቅ በአሁኑ ወቅት ሲከሰት ደግሞ በጋውን እርጥበታማ ሊያደርገው እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ማዕከላት ከሰጡት ማመላከቻ በመነሳት አካሄዱ እየቀነሰ የመሄድ አዝማሚያ ታይቶበታል፡፡ በዚህም ከ80 ወደ 65 በመቶ እየወረደ መሆኑ ይታያል፡፡
የትንበያና የአርሶ አደሩ ቅንጅትም ኤጀንሲው 11 የክልል ሜትዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላት አሉት፡፡ የተሰጠው ትንበያ መሠረት በማድረግ በዚህ ሳምንትና በቀጣይ ሳምንት ውስጥ የበልግ ትንበያ ምን እንደሚመስል ከዞን የግብርና ዘርፍ፣ ባለሙያዎችና ከአካባቢ መስተዳድር ጋር በመሆን ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያገናኘ መረጃውን ይሰጣል፡፡ በዚህ መሠረትም ከልማት ጣቢያ ሠራተኞች፣ የአካባቢው መስተዳድር፣ ውሳኔ ሰጪ አካላት፣ መንግሥታዊ መዋቅሩንና መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም መረጃውን በማሰራጨት በግብርናው የሚጠበቀው ውጤት እንዲመጣ ያግዛል፡፡
ሚኒስቴሩ
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ፤ ኤጀንሲው የበጋ ወቅት የአየር ጠባይና ሁኔታ ምን እንደሚመስል ትንበያ አውጥቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በአብዛኛው በሚባል ደረጃም ትንበያው ትክክለኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በወቅቱ አብዛኛው አካባቢዎች ላይ መደበኛ የአየር ጠባይና ሁኔታ እንደነበርና መኸር አምራች በሆኑ አካባቢዎች ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል መረጃ አውጥቶ ነበር፡፡
በየቀኑ በመተንተን የሚወጣውን መረጃ መሠረት በማድረግ ምርት ሳይባክን ለመሰብሰብ የደረሰውንም በመለየት እንዲነሳ ማድረግም ተችሏል፡፡ በሂደቱም አርሶ አደሩ የቤተሰቡን ጉልበት በመጠቀም እንዲያነሳና የጉልበት እጥረት ባለበት ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች፣ መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የተደራጁ ወጣቶች ህብረተሰቡን በተደራጀ መንገድ እንዲደግፉ በማድረግ ውጤት ማምጣት መቻሉን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የሚናገሩት፡፡
ምርትን ለማሰባሰብ የሚረዱ በአርሶ አደር ጉልበት የሚንቀሳቀሱ እስከ ኮንባይነር ድረስ ከቦታ ቦታ በማዘዋወር በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰራ የተደረገ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም 87 በመቶ ያክል ምርት ተሰብስቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኤጀንሲው የበልግ ወቅት የአየር ጠባይና ሁኔታን ትንበያ አውጥቷል፡፡ መረጃው እንደሚያሳየው፤ በልግ አምራች በሆኑ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ሊኖር ይችላል፡፡
አንዳንድ ደቡብ ምስራቅና ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች ከመደበኛ በታች የሆነ ዝናብ ሊኖራቸው እንደሚችልም መረጃው ያሳያል፡፡ አካባቢዎቹ በልግ አምራች ባለመሆናቸው ለእንስሳት መኖ ልማት መጠነኛ የሆነ ዝናብ ማግኘታቸው በችግር አይታይም የሚሉት አቶ ሳኒ፤ ለእንስሳቱ የሚሆን መኖና ውሃ ለማግኘት እንደሚያስችላቸውም ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም በዋናነት በልግ አምራች የሆኑት ደቡብ ትግራይ፣ ምስራቅ አማራ፣ ምዕራብ አፋር፣ አብዛኛው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም ደቡብና ማዕከላዊ ኦሮሚያ አካባቢዎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ያገኛሉ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው፤ አካባቢዎቹ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ማግኘታቸው ምቹ የበልግ ጊዜ እንዲኖር ያደርገዋል ይላሉ፡፡ ከመደበኛ በላይ የሚሆንባቸው የዝናብ ወቅቶች በመጀመሪያው ከፍ ያለ ዝናብ የሚያገኙ ሲሆን፤ ከዛም ዝናቡ ወደ መደበኛ ባህርይው እየገባ ይሄዳል፡፡ ይህም ማለት በወራቶቹ ሙቀቱ ከፍተኛ በማድረግ ትነት ስለሚኖር ከሰብሉ አኳያ የሚያስከትለው ጉዳት አነስተኛ ይሆናል፡፡
የግብርና ሥራ ለአንድ ዘርፍ ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ በዚህም ከታች ከአርሶ አደሩ ጀምሮ የሚሰራው ሥራ ለውጤቱ የራሱ ድርሻ እንዳለው ይታወቃል፡፡ ኤጀንሲው የሚያወጣው መረጃ ለግብርና ዋናው ግብዓት ሲሆን፤ ዝናብ መቼ ይጀምራል? መቼ ይወጣል? መጠኑስ ምን ያክል ነው? አገባብና አወጣጡ ብሎም በዝናብ መጠኑና ስርጭቱ ላይ ተመስርቶ ምን ዓይነት የሰብል ዝርያ መጠቀም አዋጪ ይሆናል? ዝናቡ ከፍና ዝቅ ሲልስ ምን ይደረግ? በሚል በዝርዝር ይታቀዳል፡፡ ይህንንም በሥልጠና መልክ ለባለሙያውና ለአርሶአደሩ በሥልጠና መልክ ይሰጣል፡፡
ኤጀንሲው የዕለት፣ የሶስትና የ10 ቀናት እንዲሁም የወር አድርጎ የሚያወጣው ዋቸ መረጃ በተለይ በግብርና ልማት ላይ የተሰማራው አርሶ አደርና ልማታዊ ባለሃብቱ እንዴት ይደርሰዋል በሚል አንዳንዱን መረጃ እንዲያውቅ አሰራር ተቀይሶ እየተሰራ ነው፡፡ በዚህም የተለያዩ አርሶ አደሩ ጋር ተደራሽ የሚሆኑ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮችን በመጠቀም መረጃው ይሰራጫል፡፡ ሚኒስቴሩ ኤጀንሲው ተደራሽ ከሚያደርግባቸው መንገዶች በተጨማሪ በየጊዜው የሚወጣው ትንበያ መረጃ በየአካባቢው ምን እንደምታ አለው? ምንስ መደረግ ይኖርበታል? በሚል ሚኒስቴሩ እስከ ባለሙያዎች ያወርዳል፡፡ ይህም ወደ አርሶ አደሩ ጋር በቀላሉ ይደርሳል፡፡
መረጃውን ወደ አርሶ አደሩ ማድረሻ መንገድ ተደርጎ የሚወሰደው ሌላኛው አማራጭ ደግሞ የሚኒስቴሩ የራሱ ሬድዮና ቴሌቪዥን መገናኛ ናቸው፡፡ በእነዚህ የግንኙነት አግባቦች በመጠቀም ትንበያው እንዲህ ነበር፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ያለበት ደረጃ ምን እንደሚመስል በሚያስረዳ መልኩ ከአርሶ አደሩ ጋር በጣም የተቀራረበ ግንኙነት በመፍጠር በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የምርት ብክነትን ለመቀነስ እየተሰራ ይገኛል፡፡
አንዳንዱ ምርትን ለማሳደግ የሚከናወን ተግባርም አርሶ አደሩ ጋር ደርሶ በማሳው ላይ መስራት ያለበትን ካልሰራ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ስለሆነም በየቀበሌ ያሉ የልማት ጣቢያ ባለሙያዎችና ሱፐርቫይዘሮች የአርሶ አደሩን መረጃ ማድረስ ብቻ ሳይሆን ማሳው ላይ መፈፀሙን የመከታተል፣ የመደገፍና የማገዝ ሥራ በመሥራት መረጃውን ተጠቅሞ ግብርናን ማልማት በሚያስችል መልኩ ይሰራሉ፡፡
ምን እየተሰራ ነው?
አልፎ አልፎ ለጉዳት ሊዳርጉ የሚችሉ የዝናብ ክስተቶች ሲኖሩ በእርሻው የመጀመሪያ ምዕራፍ ወይንም ጊዜ ላይ ስለሚያርፍ ትርፍ ውሃ የማስወጣት ሥራ ይሰራል፡፡ አስተራረሱ ላይ ከማሳ ውጪ ያለ ትርፍ ውሃ እንዳይገባ ሊያደርጉ የሚችሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን አጠናክሮ በመስራት ምቹ የበልግ ወቅት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ያመላክታሉ፡፡
ከመደበኛና መደበኛ በላይ ዝናብ በሚኖርበት ወቅትም የሚዘሩ የሰብል ዝርያ ዓይነቶች በቂ እርጥበት የሚጠይቁና ረጅም ጊዜ የሚወስድ የሰብል ዘሮችን በመምረጥ ይለማል፡፡ በተለይ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንዲሁም ኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በበልግ ወቅት በቆሎ ያለማ፡፡ በቆሎ ደግሞ እርጥበትንና ከፍተኛ ውሃ የሚፈልግ ሰብል በመሆኑ ከበቆሎም ረጅም ጊዜ የሚቆዩና ከፍተኛ እርጥበትን የሚፈልጉ የበቆሎ ዝርያዎች በመኖራቸው ይህን መርጦ በማልማት በላቀ ደረጃ ለመጠቀም መታቀዱን በቀጣይ ትንበያውን መሠረት አድርጎ ሊሰሩ የታቀዱ ተግባራትስ መሆናቸውን አቶ ሳኒ ይገልፃሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው ያወጣውን ትንበያ መሠረት በማድረግ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ መዋቅር ያሉ ባለሙያዎች በየአካባቢው ሊኖር የሚችለውን የበልግ የዝናብ ሁኔታና ስርጭት ታሳቢ ያደረገ ምን ሥራ ይሰራ በሚል እያቀዱ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይም ዕቅዱን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ በማድረግና በውይይት በማዳበር አቅርቦቱን በዚህ ደረጃ ቃኝቶ ይመራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው ትንበያ ለግብርናው የተመቸ በልግ ቢፈጥርም መኸሩ ግን ምን ሊሆን እንደሚችል ገና መረጃው ስላልወጣ መጪውን በልግ በላቀ ደረጃ መጠቀም በተለይ የማይለሙ አካባቢዎችም ቢሆኑ የዝናቡ ሽፋን ሰፊ ስለሆነ የበልግ የማሳ ሽፋኑን በማስፋት ለማልማት ታቅዷል፡፡
የበልግ ዝናብ ስርጭቱ የመዛባት ባህርይ ያለው በመሆኑ የኢሊኖ ክስተት እስከ 65 በመቶ ሊኖር እንደሚችል ያሳያል፡፡ ይህም ማለት ከፍተኛ የሆነ የዝናብ መጠን ሊኖር እንደሚችል ያሳያል፡፡ እየተዳከመ የሚሄድ ቢሆንም ይህ በራሱ የዝናብ ስርጭቱን ማዛባቱ ግን አይቀርም፡፡ ኢሊኖ በባህርይው ከፍተኛ ዝናብ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም መደበኛና ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያስከትላል፡፡ የዝናቡን መጠን ለሰብሉ በቂ ቢሆንም ሲበዛ ግን ምን ይደረግ? የሚለው ከወዲሁ በመነጋገር አስፈላጊውን የግብዓትና የሥልጠና ሥራ ተሰርቶ ስምሪት ይደረጋል፡፡ በዚህም ከፍና ዝቅ በማድረግ ረገድ የራሱ አስተዋፅዖ ስለሚኖረው ይህን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል? በሚል ከአርሶ አደሩና ከባለሙያዎች ጋር በጥልቀት ውይይት ተደርጎ መፍትሔ ይቀመጣል፡፡
ኤጀንሲው ይፋ ያደረገው መረጃና ሚኒስቴሩም በዕቅዱ አካቶ ለባለሙያው፣ ለአርሶ አደሩና ለልማታዊ ባለሃብቱ ለማድረስ እየተዘጋጀ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ከብዙሃን መገናኛና ከልማት ጣቢያ ባለሙያዎች የሚያገኘውን ምክረ ሃሳብ በመጠቀምም በተግባር እያዋለው ተጠቃሚም እየሆነ ይገኛል፡፡ በቀጣይም የኤጀንሲው አቅም በማደጉ የሚያወጣቸው የትንበያ መረጃዎች ትክክለኛነት እየጨመረ በመሆኑ አርሶ አደሩ ከምን ጊዜውም በላይ መረጃውን የመቀበል፣ በተግባር ደግሞ የመቀየር በሌላ በኩል ደግሞ ባለሙያዎችም ለአርሶ አደሩ መረጃውን የማድረስ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሚኒስትር ዴኤታው ያሳስባሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 27/2011
በፍዮሪ ተወልደ