ከገብረክርስቶስ
ነጻነት ሳያውቅ ህዝብን ነጻ አወጣለሁ ብሎ ደደቢት ላይ የተፈለፈለው እፉኝት በተከዜ በረሃ ውስጥ በመቀበሩ ለኢትዮጵያ ነጻነት ታውጇል።
ደጋግመን እንደገለጽነው “ቀን ያስጎነበሰውን ቀን ቀና ያደርገዋል” እንዲሉ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ኢትዮጵያን ያስጎነበሳት ጥቁር ቀን ነው። ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ ያዘመመችዋን አገር ቀና አድርጓታል።
የዘረኝነት ሴራ ጠንሳሾቹ፣ የዘረፋና የክህደት አብሾ ኮማሪዎቹ እንደ እሽኮኮና እንደ ዝንጀሮ ከስንጥቅ አለትና ከሰርጥ ውስጥ እየተጎተቱ ወጥተዋል። እኩሌቶቹ በለኮሱት እሳት ተቃጥለው እስከወዲያኛው አመድ ሆነው ቀርተዋል። የተቀሩትም ከሁለት አንዱን ዕጣ ለመቀበል ቀናቸውን እየጠበቁ ነው።
በአሁኑ ወቅት ታዲያ ድህረ-ሕወሓት ኢትዮጵያን ወደተሻለ የዴሞክራሲና የኢኮኖሚ ምዕራፍ ለማሸጋገር ከሚከናወነው ቁልፍ የሪፎርም እርምጃ ጎን ለጎን የዛን ድርጅት ሰንኮፍ ከምድሪቱ ነቃቅሎ ለማጽዳት የሚያስችሉ ወሳኝ ሥራዎች መከናወን አለባቸው።
በዚህ ረገድ በተለይም በድርጅቱ የፖለቲካ ሕልውና ላይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች እና አንድምታቸውን እንዳስሳለን።
ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰሌዳ ላይ መፋቅ ትህነግ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. ተወልዶ ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ሞተ የሚለው ታሪክ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
እፉኝት የሚባል መርዘኛ እንስሳ አለ። ይህ እንስሳ ሥነ-ተፈጥሮው እንደ እባብ እና ዳሞትራ (የሸረሪት ዘር) ዓይነት ያለ ሆኖ በመርዙ ሕያዋን ፍጥረታትን የሚጎዳ የምድራችን ክፉ እንስሳ ነው።
የእፉኝት ክፋት ይህ ብቻ አይደለም። እፉኝት ሲወለድ እናቱን ይገድላል። በዚህ መነሻ ለክፉነቱ ልኬት ያልተገኘለት አደገኛ እንስሳ ነው።
ሕወሓትም እንዲሁ ነው። የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም. ሲወለድ እናት ኢትዮጵያን ገድሏታል። የድርጅቱ መሪዎች ለግማሽ ክፍለ-ዘመን ኢትዮጵያ የሚለውን ስም መጥራት ተስኗቸው “ይህቺ አገር” እያሉ ስም አልባ አድርገዋት ኖረዋል።
በጥረትና በህብረታቸው የታፈረችና የተከበረች አገር የመሰረቱትን ሕዝቦች ከተጋመዱበት የአብሮነት ታሪክ ይልቅ የተጎዳዱበትንና የተበዳደሉበትን ሁነት አድምቆ በማሳየት መሼ ጠባ በዘር የሚናቆሩ ትውልዶች እንዲፈጠሩ አድርጓል – ሕወሓት።
ስለዚህ ይህ ድርጅት በዚህ ቀን ተወልዶ እናቱን ገድሎ በዚህ ቀን ሞተ የሚለው የመቃብሩ ላይ ጽሁፍ ጎልቶ ሊነበብ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ወሳኙ ርምጃ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰሌዳ ላይ ሕወሓት የሚለውን ስም መፋቅ ነው።
ይህንኑ መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ ሕወሓትን ከሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅት መዝገብ ላይ ሰርዞታል። ይህ መሰረታዊ እርምጃ ነው።
ሟች ከመሞቱ በፊት መቀሌ ተወትፎ የትግራይን ሕዝብ ዙሪያውን በጠላት የተከበበ በማስመሰልና የጠላቶች ጭራቅ በመሳል ሲያወናብድ ሰነባብቷል። የጦርነት ነጋሪት ሲጎስምና በዕብሪት ሲወጠር ከርሟል።
ወዲህ ለጦርነት እየተሰናዳ ወዲያ ደግሞ ምርጫ አካሂዳለሁ በማለት ለ27 ዓመት በመላ ኢትዮጵያ የሰራውን ድራማ ትግራይ ላይም ደግሞታል።
ሕወሓት ዓምና ያካሄደው ምርጫ ተብዬ ተውኔት ከቀደሙቱ በጣሙን ይለያል። ምክንያቱም ምርጫው ከመሰረቱ ሕገ-ወጥ በመሆኑ።
በዚሁ በጋዜጣችን ላይ ስለ ትግራይ ክልል ምርጫ “ከመርዛማ ዛፍ መርዛማ ፍሬ ይለቀማል እንደሚባለው እንዳይሆን ያሰጋል” በሚል ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት ሃሳባችንን አቅርበን ነበር።
ፍጻሜው እንደስጋታችን ሆኗል። ምርጫው ሕገ-ወጥ ስለነበር ውጤቱም ሕገ-ወጥ ሆኗል። ይባስ ብሎም ትግራይ ከኢትዮጵያ ውጭ ያለች ሌላ አገር እስክትመስለን ድረስ ሕወሓት ታሪክ የማይዘነጋቸውን ውርደቶች ፈጽሟል። በዕድሜው አመሻሽ ላይም ኢትዮጵያን ወግቶ ተወግቷል።
ሕወሓት ምርጫ አካሂዳለሁ ብሎ ሲፎክር ምርጫ ቦርድ ተገቢ አለመሆኑን ደጋግሞ አሳውቆት ነበር። አገራችንን እየመራ ያለው መንግስት ሥልጣኑ ባሳለፍነው መስከረም እንደሚጠናቀቅ ነበር የሚጠበቀው። እናም ዓምና ምርጫ ሊደረግ የግድ ነበር።
ይሁንና የምርጫ ቦርድ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ እንደማይችል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቆ፤ ፓርላማውም ምርጫውን ማካሄድ የማይቻል ከሆነ አገረ-መንግስቱን ሊያዘልቁ ይችላሉ ያላቸውን አማራጮች ተመልክቷል።
በዚሁ መሰረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ የሕገ-መንግስት ማሻሻያ ማድረግ፣ ፓርላማውን መበተን ወይም የሕገ-መንግስት ትርጉም መጠየቅ የሚሉ አማራጮች ቀርበው ሕገ-መንግስቱን መተርጎም የሚለው አማራጭ በአብላጫ ድምጽ ተመራጭ ሆኗል።
ለዚህ ዋነኛ መነሻው ደግሞ የሕገመንግስቱ ዝምታ ነው – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ምርጫ ሲገጣጠሙ አገረ-መንግስቱ በምን ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት የሚያስቀምጠው መፍትሔ የለምና።
በየአምስት ዓመት በሚደረግ ምርጫ መንግስት እንደሚመሰረት በሕገመንግስቱ የተደነገገ ቢሆንም ከኮሮና መከሰት በኋላ አገሪቱ በአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ ሰንብታለች።
በዚሁ መነሻም የፌዴራሉን ጨምሮ የሁሉም የክልልና የከተማ መስተዳድሮች መንግስታት (ትህነግ መራሹ የትግራይ ክልል መንግስትም ሳይቀር) ሥልጣናቸው ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞላቸዋል።
በወቅቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁ በአንድ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የሚመራው መንግስት አገርን ከዚህ ከባድ ጊዜ ለማሻር በአስተዋይነት የመረጠው ቀና መንገድ ስለመሆኑ ተነግሯል።
በሌላ በኩል ግን ሕገ-መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ በገዥው የብልጽግና ፓርቲ የሚመራውን መንግስት ስልጣን ለማራዘም የተቀመረ ዘዴ ስለመሆኑ ጥርጣሬያቸውን የገለጹም ነበሩ። የዚህ ጎራ መሪ ትህነግ ነበር።
ለተፈጠረው ችግር ከሕጋዊ መፍትሔ ይልቅ ዋነኛው መፍትሔ ፖለቲካዊ መሆን እንዳለበት የሚገልጹት ኃይሎች ደግሞ የሽግግር መንግስትን አማራጭ አቀንቅነዋል። በተመሳሳይ የዚህኛውም ጎራ መሪ፣ ማልያና ማርሽ ቀያሪው ወያኔ ነበር።
የሆነው ሆኖ ከግራ ከቀኝ ሲደመጡ የነበሩት ሃሳቦች ገሚሶቹ ገንቢ እና ኃላፊነት የተሞላባቸው ሲሆኑ፤ ጥቂት የማይባሉት ግን ሆነ ብለው ሕዝቡን የሚያሳስቱና ሕገ- መንግስቱን ሳይቀር አጣምመው የሚያቀርቡ ግብዝ አስተሳሰቦች ነበሩ።
ሕወሓት በአንደኛው ማልያ ሕገ-መንግስት ይከበር እያለ በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ-መንግስቱንና በሕግ የተቋቋሙ አገራዊ ተቋማት ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች ጥሶ ምርጫ አካሂዷል።
በወቅቱ ታዲያ የአገሪቱ ፌዴራሊዝም ጠባቂና የነፍስ አባት እየተባለ የሚጠራው የፌደሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልልን ምርጫ በተመለከተ ክልሉ የራሱን የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም ያወጣው አዋጅና በአዋጁ የተቋቋመው የምርጫ ኮሚሽንም ሕገ-መንግስቱን የጣሰ ስለመሆኑ ነበር የወሰነው።
አያይዞም የሚካሄደው የክልሉ ምርጫም ሆነ ምርጫውን ተከትሎ ሊቋቋም የሚችለው መንግስት ሕገወጥ መሆኑንና ተቀባይነት የሌለው እንደማይሆን ወስኗል።
የራሱን ምርጫ ኮሚሽን ያቋቋመ እኩይ ድርጅት ይህ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ታሪክ ውስጥ ሊዘነጋ የማይገባው ጥቁር አሻራ ነው። ሕወሓት ሕብረ- ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን በመተግበር አንድ የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ እንዲገነባ እታገላለሁ እያለ ሕገ-ወጥ ምርጫ ለማድረግ ሲል ሕገ-ወጥ የሆነ ክልላዊ የምርጫ ኮሚሽን ያቋቋመ የተኩላዎች ስብስብ ነበር።
በሕገ-መንግስቱ መሰረት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ምርጫን እንዲያካሂድ ብቸኛ ሥልጣን የተሰጠው አካል ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ነው። የተቋቋመውም እንደብዙዎቹ ተቋማት በአዋጅ አልያም በደንብ ሳይሆን በራሱ በሕገ-መንግስቱ ነው።
“በፌዴራልና በክልል የምርጫ ክልሎች ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት እንዲያካሂድ ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ተቋቁሟል” ይላል ሕገ-መንግስቱ የምርጫ ቦርድ ምስረታን ሲያበስር።
ከዚህ ድንጋጌ በግልጽ እንደምንረዳው በየትኛውም የአገሪቱ ጥግ ነጻና ትክክለኛ ምርጫ እንዲያካሂድ በራሱ በህገ-መንግስቱ የተቋቋመ “አንድ-ላገሩ” የሆነ ተቋም ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑን ነው።
ይህንን ድንጋጌ ይዘን ታዲያ ምርጫን በተመለከተ ሕግ የማውጣትም ሆነ ያወጣውን ሕግ የማስፈጸም ሕገ-መንግስታዊ ሥልጣን ያለው ማን እንደሆነ ማየቱ ጠቃሚ ነው።
በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጡትን የፖለቲካ መብቶችን ለማስፈጸም ቁልፍ መሳሪያ የሆነውን ምርጫን የተመለከተ ሕግን የማውጣት ሥልጣን ያለው የፌዴራል መንግስቱ ነው።
የፌዴራሉ መንግስትና የክልሎች ሥልጣን ደግሞ በሕገ-መንግስቱ ተወስኗል፤ ተለይቶም ተቀምጦላቸዋል። ለፌዴራሉ መንግስት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች፤ የክልሎችም በፌዴራሉ መንግስት መከበር እንዳለበትም ተደንግጓል።
ታዲያ በምን ሕገ-መንግስታዊ መሰረት ነው ክልሎች ወይም አንድን ክልል የሚመራ የፖለቲካ ፓርቲ “በምመራው ክልል ውስጥ ምርጫ አደርጋለሁ” ብሎ የሚነሳው!?
ሌላው የዚህ ሃሳብ ደጋፊስ እስከዛሬም ድረስ “የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል ምርጫን ክልሎች ማድረግ መብታቸው ነው” እያለ የሚያደነቁረን በምን የሕግ መሰረት ነው!?
እስኪ ሕገ-መንግስቱን አንቀጽ በአንቀጽ ተወያይቶ ያጸደቀውን የሕገ-መንግስት ጉባዔ ቃለ-ጉባዔዎችን በወፍ በረር እናስታውሳችሁ።
በወርሀ-ህዳር 1987 ዓ.ም ከተደረጉት የጉባዔው ስብሰባዎች እንደምንረዳው ምርጫና ሌሎችም መሰል ለፌዴራል መንግስቱ የተሰጡት ሥልጣኖች በሕገ- መንግስቱ መግቢያ ላይ በሰፈረው አግባብ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያግዙ ናቸው።
በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ሌሎቹ የሕገ-መንግስቱ አንቀጾች በተቃውሞ እየታጀቡ ሲጸድቁ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ የሆነው የህገመንግስቱ አንቀጽ ግን ያለአንድም ተቃውሞ ነው የጸደቀው።
በዚሁ አመክንዮ ነው እንግዲህ የምርጫ ቦርድ ብሔራዊ ተቋም ሆኖ የተቋቋመው። በመላ አገሪቱም ምርጫን የሚያካሂደው እሱው ብቻ ነው።
ከሁሉም በላይ ምርጫን በተመለከተ እንደ አገር የሚቋቋመው አንድ አካል ብቻ ስለመሆኑ፤ ይህም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑን፤ ቦርዱም በየወቅቱ ለሚደረጉ ምርጫዎች ወሳኝ አካል ሆኖ ተቋሙም ራሱን በቻለ አዋጅ ሳይሆን በራሱ በሕገ-መንግስቱ እንዲቋቋም መደረጉን በሕገ-መንግስት ጉባዔው ቃለ ጉባዔ ላይ ለታሪክ ተመዝግቦ እናገኘዋለን።
ስለዚህ ሕገ-መንግስቱን ያረቀቁትና ያጸደቁት የያኔዎቹ ሰዎች ሃሳብ ይህ ከሆነ ከምርጫ ቦርድ ውጭ ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ መነሳት ሕገ-መንግስቱን መጣስ ነበር ማለት ነው። የክልል የምርጫ ኮሚሽን ብሎ የይስሙላ ተቋም መመስረትም ሕገ-ወጥነት ነበር።
ከሁሉም በላይ የህገ-መንግስቱ ቁልፍ ማጠንጠኛ ከሆነው አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት ከሚለው መርህም ያፈነገጠ ነው። ለዚህም ነው “ከመርዛማ ዛፍ የሚለቀመው መርዛማ ፍሬ ነው” የሚባለው።
ደጋግመው በሚያወጡት መግለጫ ይገልጹ እንደነበረው ምርጫ እናደርጋለን የሚሉት የያኔዎቹ የትግራይ ክልል መሪዎች ሃሳባቸውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በሚል የወርቅ ቅብ በማቅረብ ቅቡልነት ያለው ለማስመሰል ጥረዋል።
እርግጥ ነው በሕገ-መንግስቱ እንደተገለጸው ክልሎች ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳድር ያዋቅራሉ። የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም የመገንባት ኃላፊነት አለባቸው።
ከዚህ ውጪ ግን ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ባልተገባ ሁኔታ በማቅረብና ሕዝብን በማሳሳት ከሕገ- መንግስቱ ውጭ ምርጫ ማድረግ ሕገ-ወጥነት ነው።
ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተግባራዊ የሚደረገው በሕገ-መንግስቱ አግባብ በፌዴራሉ መንግስት ሕግና ሥርዓት የሚመራ ምርጫ ተደርጎ እንጂ በሕገወጥ መንገድ በሚደረግ ሕገወጥ ምርጫ አለመሆኑን የወያኔ መሪዎች ለመረዳት ሕሊናቸው ታውሮ ነበር።
ትህነጎች ምርጫ እናደርጋለን ሲሉ ጠንቅቀው የሚያውቁት ግን ደግሞ በደንብ ሊገነዘቡት ያልቻሉት ሌላም ቁልፍ ጉዳይ ነበር። የየትኛውም አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ሕገ-መንግስቱን የሚጻረር ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በሕገ-መንግስቱ ተደንግጓል። በተጨማሪም ማንኛውም አካል ለሕገ- መንግስቱ ተገዢ ባለመሆን ተጻራሪ ውሳኔ ካሳለፈ ወይም ከተገበረ ተቀባይነት አይኖረውም።
በመሆኑም የፌዴራል መንግስቱም ሆነ ክልሎች ሕገ-መንግስቱን የመጠበቅና የመከላከል ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊዘነጉት ባልተገባቸው ነበር።
በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት ያ ምርጫ ሕገ-መንግስቱን የጣሰ በመሆኑ እንዳልተደረገ ተቆጥሮ ከታሪክ ገጽ ላይ ተሰርዟል። ምርጫውን ተከትሎ የተመሰረተው ያ የክልሉ ምክር ቤትም ሆነ የመንግስቱ አስፈጻሚ ሕገወጥ ነበር፤ እውቅናም አልተሰጠውም። አሁን ተራው የትህነግ ሆኗል።
ትህነግ ቀድሞም ቢሆን የፌዴራል መንግስቱን የሥልጣን መዘውር ጨብጦ መላ አገሪቱን በእጅ አዙር አሃዳዊነት ሲያስተዳድር በነበረበት የይስሙላ ፌዴራሊዝም ዘመን ሲያካሂድ በኖረው ምርጫ እንደለመደው ሁሉ በትግራዩ የይስሙላና ሕገ-ወጥ ምርጫ አሸንፌያለሁ ብሎ ክልላዊ መንግስት መስርቶ ነበር።
ይህንን ያደረገው ደግሞ በያኔው የፌደሬሽኑ ምክር ቤት ውሳኔ እና በሕገ-መንግስቱ አግባብ የሁሉም የክልል ምክር ቤቶች ሥልጣን ሲራዘም ሥልጣኑ ተራዝሞለት የነበረውን የቀድሞውን የትግራይ ክልል ምክር ቤት በማፍረስ ነበር።
ሥልጣናቸው የተራዘመላቸው የምክር ቤት አባላትንም አሰናብቶ በሕገወጦቹ ተመራጮች ተክቷል። የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወኪሎች ሆነው የፌዴራሉ ፓርላማ አባል የነበሩ ትህነጎችም የክልሉን ሥልጣን በአቋራጭ ለመቆናጠጥ በክልላዊው ምርጫ በመሳተፍ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የክህደት ሸፍጥ ነበር የፈጸሙት።
በእንዲህ ዓይነት የፖለቲካ ቁማር የተመሰረተው የያኔው የትግራይ ክልል መንግስት ከሌሎቹ የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎችና ከፌዴራሉ መንግስት ጋር ሊኖረው የሚገባው ግንኙነት ገና በውል እንኳን ሳይለይለት ታሪካዊዋ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. መጣች።
የሆነው ሆኖ የትግራይ ክልል የያኔው ምርጫ መርዛማ ዛፍ ነበር፤ ፍሬውም መርዛማ ሆኗል። መርዛማ ዛፉን የተከሉቱም፣ ፍሬውን የለቀሙቱም የመርዙን ጽዋ ተጎንጭተውታል። አብሾ እንዳለበት ሰው አስጡዞ፣ እንደጦስ ዶሮ አናውዞ ደፍቷቸዋል በመጨረሻው።
እናም ይህንን ድርጅት ከአገሪቱ የፖለቲካ መዝገብ መሰረዝ ትክክለኛ ውሳኔ ስለመሆኑ ጥርጥር የለም። አንዳንዶች ድርጅቱን በሽብርተኝነት መፈረጅ ያስፈልጋል ሲሉ ቢደመጡም ድርጅቱን ከፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው በቀይ ካርድ በማሰናበት እስከወዲያኛው የፖለቲካው ዓለም ተጫዋች እንዳይሆን ማድረግ ቀዳሚው ተግባር ነው። እናም የሕወሓትን ድርጅታዊ እውቅና መሰረዝ የጎላ አንድምታ ይኖረዋል ማለት ነው።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013