የጁንታው ርዝራዦች በተለይ ከሀገር ውጪ የሚኖሩት ጁንታው ሞቶ ተቀብሮም ማላዘናቸውን ቀጥለዋል። የህግ የበላይነትን አሻፈረኝ በማለት በከፈቱት ጦርነት እንዳይጠገኑ ተደርገው ተሰባብረዋል፤ በየዋሻው በየጫካው ከተወሸቁት አንዳንዶቹ እጅ አልሰጥ በማለታቸው ተደምስሰዋል፤ ሌሎች ደግሞ አውራቸውን ጨምሮ እየተለቀሙ ህግ ፊት ቀርበዋል። ወንጀለኞችን የመልቀሙ ተግባር አሁንም ቀጥሏል። በጁንታው መንግሥት ለተቀዳጀው ድል ሙሉነት የወንጀለኞቹ መደምሰስና በቁጥጥር ስር መዋል ፋይዳው ከፍተኛ ነው።
ርዝራዦቻቸው ግን አሁንም ተስፋ አልቆረጡም። «መካሪ የሌለው ንጉስ አለ አንድ ዓመት አይነግስ» እንዲሉ መካሪም የላቸውም፤ የሕይወትን ምክርም አልተቀበሉትም። በበሬ ወለደ ትርክታቸው አሁንም ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ፣ ሀገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚያሳስት የቁጥር መረጃ እየረጩ ናቸው።
ሰሞኑን የትግራይ ሕዝብ ለከፋ ረሀብ ተዳርጓል እያሉ ሲያላዝኑ፤ «ተርቧል» ብለው የለቀቁት አሀዛዊ መረጃም ይህንኑ ያመለክታል። የሚገርመው የእነሱን ተልካሻ መረጃ ይዘው በታዋቂ መገናኛ ብዙኃኖቻቸው የሚዘግቡት ሲሆን፤ ሰሞኑን ኢኮኖሚስት የተሰኘው ታዋቂ መጽሄት ይህን የትግራይ ህዝብ ተራበን ዘገባ ይዞ ወጥቷል። መሬት ላይ ያለውን እውነታ መዘገብ ሲቻል የበሬ ወለደዎችን ዘገባ ይዞ መውጣት ሙያዊም አይደለም።
የጁንታው ርዝራዦችና አጫፋሪዎቻቸው ከዚህም በላይ ሊሉ ይችላሉ። ጁንታው በሀሰት ሪፖርቱና በማይደረስበት የቅዠት እቅዱ በሚገባ ይታወቃል። ያልተፈጸመውን ተፈጸመ ብሎ ቁጥር በመቀመር የሚደርስበት እንደሌለ ይታወቃል። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። ርዝራዦቹ መላ የትግራይ ህዝብ ተርቧል፤ መንግሥት ትግራይን እያስራበ ነው እያሉ የሌለ አሀዛዊ መረጃ መንዛት ውስጥ መግባታቸው አይገርምም።
ይህ ሁሉ ጩኸት ዓለም አቀፍ እርዳታ አቅራቢዎች በትግራይ እንዳሻቸው እንዲንሸራሸሩ በዚህም መካከል መፈናፈኛ አግኝተን መንግሥት በክልሉ እያከናወነ ያለውን ጁንታው ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶች መጠገንና መልሶ ሥራ ማስጀመር እንዲሁም የመንግሥትን መዋቅር እንደገና የማዋቀር ሥራ ማሰናከል ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።
የጁንታው ርዝራዦች አሁንም እርማቸውን አለማውጣታቸው በእጅጉ ይገርማል እንጂ ወደኋላ ሊመለስ የሚችል ነገር ግን የለም። የጁንታው ጀንበር ጠልቃለች። ነገ የምትወጣው ሌላ ጀንበር ናት። እየተሰራ ያለውም ይሄው እንዲሆን ነው። የሚበጀው መንግሥት እያቀረበ ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ ድጋፍ በሁሉም አካባቢ በተሳለጠ መልኩ ለማቅረብ ርብርብ ማድረግ ነው። ለእዚህም ድጋፍ መስጠት ነው።
በትግራይ የተካሄደው ህግ የማስከበር ሥራ ግዙፍ ነው። ጁንታው ያወደማቸውን መሰረተ ልማቶች እየጠገኑ ወደ ስራ ማስገባትም እንዲሁ ታላቅ ሥራ ነው። ጁንታው በፈጠረው ቀውስ ሳቢያ ለአስቸኳይ እርዳታ ፈላጊነት ለተዳረጉ የክልሉ ነዋሪዎች የምግብ የመድኃኒትና የመሳሰሉት ድጋፍ የማቅረቡም ሥራ ግዙፍ እና በከፍተኛ ርብርብ እየተካሄደ ያለ ነው። ማውራት ለዓለም መንገር የሚያስፈልገው ይህን ነበር። ዛሬም በህዝብ ስም ለመነገድ ይህን ያህል አፍራሽና መሬት ላይ የሌለ ዘመቻ ውስጥ መግባት ያለፉትን ስህተቶች መድገም ነው።
መንግሥት የህግ ማስከበር ሥራ በተጠናቀቀባቸው አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የማቅረቡን ሥራ የጀመረው ሳይውል ሳያደር ጎን ለጎን ነው፤ ይህን አጠናክሮ በመቀጠልም በመላ ትግራይ የአስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቸ በአደጋ ስጋት አመራር በኩል እያከናወነ ነው። በዚህም እህል መድኃኒትና የመሳሰሉት ማቅረቡን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የጁንታው ርዝራዦች እንደሚሉት ሳይሆን በትግራይ ረሀብ የለም። ጁንታው እያለም በትግራይ ከአንድ ሚሊዮን የሚልቅ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ /ተረጂ/ነበር። ተጨማሪ ተረጂ የተፈጠረው እዚህ አሀዝ ላይ በፍጹም አይደርስም። የእርዳታ ፈላጊ ቁጥርን በማሳበጥ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ማሳሳታቸውን መቀጠላቸው እንደለመዱት በቀውስ ውስጥም እናተርፋለን ብለው ነው።
በትግራይ አሁን ቀውስ የለም፤ ነገሮች በታሰበው መልኩ እየሄዱ ናቸው። ጁንታው ሞቶ ተቀብሯል፤ ይህ መረጃም በተለያየ መልኩ ለእነዚሁ አካላት ደርሷል። እናም «እርማችሁን እንድታወጡ ነው። እርማችሁን አውጡ፤ አሀዛዊ መረጃ እየቀመራችሁ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ሀገሮችን የትግራይን ሕዝብ ጭምር አታሳስቱ» ብለን ማስገንዘብ እንወዳለን።
እናንተ ርዝራዦች እንደ ወላጆቻችሁ እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ መሬት ላይ የሌለ ቁጥር እየሰራችሁ ማውራታችሁን ቀጥላችኋል፤ መንግሥት እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ መስራት ያለበትን ሁሉ እየሰራ ነው። በትግራይ የጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናቅቆ ወደ መልሶ ግንባታና አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ ገብቶ ብዙ ሰርቷል። አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር በመሰየምም ክልሉን በአዲስ እያዋቀረ ይገኛል።
የጁንታውን ቀንደኛ መሪዎች እና ጋሻ ጃግሬዎቻቸውን በወረንጦ እየለቀመ ነው፤ በዚህም እጅ አልሰጥም ያሉት ተደምስሰዋል፤ እጅ የሰጡት ህግ ፊት እየቀረቡ ናቸው። እናም የጁንታው ርዝራዦች ውሻ በበላበት ይጮኸል ነውና ነገሩ ያደጉበትን ቁጥር መስራት በዚህ በሞተ ሰዓትም መቀጠላቸው አያስደንቅም። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው እነሱ በከንቱ እየጮኹ፣ መንግሥትም ሥራውን መቀጠሉን ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013