መጠሪያዋም፣ ምስረታዋም ከተንጣለለው ሐይቋ ጋር ተቆራኝቷል፤ ሞቅ ያለው የአየር ጸባይዋ ለኑሮ፣ ውብ የአስፓልትና የባለጌጥ ንጣፍ መንገዶቿ እንደልብ ለመዘዋወር ምቹ አድርገዋታል፤ የቱሪስትም ሆነ የኢንቨስተሮችን ልብ የሚስቡ በርካታ ሀብቶችም ተጎናጽፋለች፤ የሰላምና መቻቻል አውድ ስለመሆኗም «ትንሿ ኢትዮጵያ» የሚለው ቅጽል ስሟ እማኝ ሆኖ ይናገራል፤ ለሕዝቦቿ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየተጋች ስለመሆኗ የሚናገሩ በርካታ ማሳያዎችም አሏት፤ የደቡብ ኢትዮጵያዋ ፈርጥ ሐዋሳ ከተማ፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ለከተማዋና ነዋሪዎቿ ሁለንተናዊ ለውጥና ተጠቃሚነት ዙሪያ ምን እየሠራ ነው በሚለው ዙሪያ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ልዩ አማካሪ ከሆኑት አቶ አስፋው ጎኔሶ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሐዋሳ ከተማ አሁን ባለችበት ደረጃ እንዴት ትገለጻለች?
አቶ አስፋው፡- ሐዋሳ ከተማን በሚመለከት ከለውጡ በፊትም ቢሆን ከተማዋ በማህበራዊም ሆነ በሰላምና ጸጥታ አኳያ በአንጻራዊነት ከኢትዮጵያ ከተሞች የተሻለ ስምና ዝና ያላት ከተማ ነች፡፡ ለምሳሌ፣ በኢኮኖሚ መስክ በተለይም የወጣቱ ተጠቃሚነት ላይ በሥራ ፈጠራ የተሻለ አፈጻጸም አላት፡፡ ከተለያዩ ተቋማት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና ቴክኒክና ሙያዎች ጭምር ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች በሚፈልጉት የሙያ መስክ ተሰማርተው እንዲጠቀሙ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደሥራ የተሰማሩበት እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ለምሳሌ፣ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ሐዋሳ ከተማ በከተሞች ፎረም ላይ በከተሞች ውድድር ሁል ጊዜ አሸናፊ ነች፡፡ ለአሸናፊነቷ አንዱና ዋና ምክንያት ደግሞ በሥራ ፈጠራ ላይ የተሠራው ሥራ ነው፡፡ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ሌሎችም ተግባራትም የአሸናፊነት መመዘኛዎች ነበሩ፡፡
ከለውጡ በኋላም በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም ለወጣቶች ተጠቃሚነት በትኩረት እየተሠራ ነው፡፡ በዚህም ከአምስት በላይ የተያዙ ሼዶች ለሌሎች እንዲሸጋገሩና ተተኪዎች እንዲጠቀሙባቸው ተደርጓል፡፡ ለአሰራሩ ግልጽነትም ህዝብ ባለበት ዕጣ እንዲጣል ተደርጎ በእነዛ ሼዶች አዲሱ ወጣት እየገባበት ይገኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ወጣቱ ተደራጅቶ ወደሥራ እንዲገባና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል እየተሠራባት ያለች ከተማ መሆኗን ነው፡፡
ከሰላምና ጸጥታ ጋር በተያያዘም 2010 ሰኔ አካባቢ የተወሰኑ ግለሰቦች በፈጠሩት ችግር ያልተጠበቁ ክስተቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ ክስተቱ ግን ህዝብ የተሳተፈበት ባለመሆኑ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ተችሏል፡፡ ምክንያቱም ሐዋሳ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ብትሆንም በእነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አንድም ቀን ሰላምን የሚያናጋ ጠብና ቁርሾ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡ አሁንም የለም፡፡ ነገር ግን ብሔርና ብሔርን አጋጭተው ለመጠቀም ካላቸው ፍላጎት የተነሳ አስመስለው የሚያቀርቡ ቡድኖችና ግለሰቦች አሉ፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን በብሔርና ብሔር መካከል የተፈጠረ ግጭት ከአሁን ቀደም አልነበረም፤ አሁንም የለም፡፡ አሁንም ቢሆን በከተማዋ በተለይ የሲዳማና የወላይታ ሕዝብ በአንድነት አብረው ይኖራሉ፡፡
ምክንያቱም ምንም እንኳን ሁለቱ ሕዝቦች እንደተጋጩ ተደርጎ ቢወራም ባካሄዱት እርቀ ሰላም፣ አብሮነታቸው ቀጣይነት እንዲኖረው አድርገው ታርቀዋል፤ ተዋህደዋልም፡፡ ይሄን ውህደት ለማስቀጠል ሲባልም በሐዋሳም ሆነ ወላይታ ሶዶ ላይ የሁለቱም ሕዝቦች አገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም ባሉበት እርቀ ሰላም ወርዶ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ሰላም ሆኗል፡፡ እንደወትሮና እንደ በፊቱ ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት የሚችልበት ሁኔታ በመፈጠሩ አሁን ላይ በከተማችን የሰላምና ጸጥታ ችግር የለም፡፡
በጥቅሉ እነዚህ ለሐዋሳ መገለጫነት እንደ አብነት ተነሱ እንጂ ከተማዋ ከማህበራዊ አገልግሎት፣ ልማት፣ ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ አኳያም ጥሩ ሥራዎች የተሠሩባትና እየተሠሩም ያሉባት ከተማ ስለመሆኗ መግለጽ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በከተማዋ ተከስቶ በነበረው ግጭት ሰዎች ተጎድተዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ንብረትም ባክኗል፡፡ እነዚህን ሰዎች ወደነበረ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ከማድረግ አኳያ ምን ተሠርቷል?
አቶ አስፋው፡- በወቅቱ በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ፤ በፍርሃትም ከቤት የወጡ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህን ከቤታቸው የወጡ ሰዎችን መልሶ ለማቋቋምም የከተማ አስተዳደሩ፣ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት በጋራ ባከናወኑት ተግባር ወደቄያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ አሁን ላይ እንደ ወትሮውና እንደበፊቱ ከጎረቤቶቻቸውና ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በሰላም እየኖሩ ነው፡፡ ምክንያቱም መጀመሪያም ቢሆን ግለሰቦች በተለያየ መልኩ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘትና ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ የፈጠሩት ችግር እንጂ ከሕዝብ የተነሳ ነገር አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ አሁን ላይ በሰላም ችግሮችን ፈትቶና ተግባብቶ አብሮ እየኖረ ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በህዝቦች መካከል ይሄን መሰል ችግር የሚፈጥሩ አካላትና አጋሮቻቸውን ያልተገቡ የጥቅም መስመሮችና ኮንትሮባንዶችን ከመዝጋት፣ ሕገ ወጥ ተግባራቸውንም ከማክሰም፤ አጥፊዎችንም ለይቶ ተጠያቂ ከማድረግ አኳያ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ አስፋው፡- በተለያዩ ደረጃ የሚገለጹና በከተማዋ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥ ተግባራት አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር አልፎ አልፎ እንደ ክስተት ቢታይም የከተማዋ መገለጫ የሚሆን አይደለም፡፡ የኮትሮባንድ ንግድና ኮንትሮባንዲስቶች ግን አሉ፡፡ እንደውም ሕገ ወጥ ንግድን መከላከል ሲጀመር ነው የሕገ ወጥ ንግድ ተሳታፊዎች ለግጭቶች ትንስኤ እየሆኑ ያሉት፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ኔትዎርክ ፈጥረው የሕገ ወጥ ኮንትሮባንዶችን የሚጠቀሙ የመንግሥት አካላት በተለይ የጸጥታ አካል ላይ አሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ሴራ ነው በከተማችን ውስጥ ሁከት እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግን ሕገ ወጦች ወደ ሕጋዊነት የመጡበት፤ ከለውጡ ወዲህ በተለይ ከመስከረም 2011 ወዲህ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ አደብ እየገዛ የመጣበትና ትክክለኛ መስመር እየያዘ የመጣበት፤ የተከሰተ ካለም የከተማውና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ተቀናጅቶ በጥብቅ ክትትል በቁጥጥር ስር እያዋለ በመሆኑ ሕገ ወጥነት ሙሉ በሙሉ ወደ መቆም ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡
በተመሳሳይ አጥፊዎች፣ ግጭት ጫሪዎችና ሕገ ወጥ ተግባር ላይ ተሳታፊዎች እየተለዩ ተገቢው እርምትና እርምጃም እየተወሰደ ይገኛል፡፡ የጦር መሳሪያ ጭምር የሚያንቀሳቅሱ አካላት በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ የዛሬ ወር አካባቢ ሽጉጥ ወደከተማዋ በሕገ ወጥ መልኩ ሲገባ በመያዙ ለሕግ እንዲቀርብ እየተሠራ ነው፡፡ በተመሳሳይ በሞያሌ፣ ዲላ፣ አርባ ምንጭና ሻሸመኔ መስመር የሚመጡ ሕገ ወጥ ንግዶች በመኖራቸው ኮንትሮባንድ የጫኑ መኪኖች በተለይ ቦንዳዎች ተይዘው ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እየተሠራ ነው፡፡ በዚህና ሌሎች ተግባራት ላይ ተሰማርተው የተያዙ ሰዎችም ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ እርምጃም እየተወሰደ ነው፡፡
በከተማዋ ሁከትና ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሰዎችን በተመለከተም ከከተማ አስተዳደሩ ባለፈ ክልሉም ሆነ ፌዴራል ክትትል እያደረጉና መረጃ እየያዙ እየሠሩ ሲሆን፤ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ በከተማዋ አሮጌ ከተማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የእሳት አደጋ እንዲፈጠር አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩ ከ16 እስከ 40 የሚሆኑ ሰዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጎ ጉዳያቸው በሂደት ላይ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ በከተማዋ ሁከት በመፍጠርና ትምህርት ቤቶችን በድንጋይ በመሰባበር አደጋ የፈጠሩ ሰዎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ተጠርጥረው ለሕግ በቀረቡ ከ16 በላይ ሰዎችም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ውሳኔ አግኝቷል፡፡
ከዚህ አኳያ ከተማ አስተዳደሩ በተለይ ጸጥታን ከማስከበር አኳያ በትኩረት እየሠራ ሲሆን፤ ጸጥታ የሚያደፈርሱ አካላትን ለሕዝብ በማጋለጥና መረጃ እንዲቀርብ በማድረግ በሕዝብ ተሳትፎ በርካታ ሕግ የማስከበር ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ሥራውም በሕዝብ ተሳትፎ የሚሠራ እንደመሆኑ በቅድሚያ ከሕዝብ ጋር ውይይት በመደረጉ ሕዝቡም ሆነ ወጣቱ ጉዳዩን በመረዳት መንግሥት ይሄንን ከሠራ አካባቢያችን ሰላም ያገኛል በሚል እያጋለጠ እየሰጠ ነው ያለው፡፡ ውጤት መገኘቱም ከሕዝብ ጋር ከስምምነት ተደርሶ በመሠራቱ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወጣቶች የከተማዋ ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ በመሆን ለኮንትሮባንዲ ስቶችና የጥፋት ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን በተለይም የሥራ እድል እንዲፈጠርለት ከማድረግ አኳያ የሠራችሁት ሥራ በቂ ነው ማለት ይቻላል? በቀጣይስ እንዴት ለመሥራት አስባችኋል?
አቶ አስፋው፡- የወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ በከተማዋ ስምንቱም ክፍለ ከተሞች ውስጥ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በየክፍለ ከተማውም የተደራጁ ወጣቶችም በእጣ ሼድ እየተሰጣቸው ሲሆን፤ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በሌላ መልኩ አጋጣሚ ሆኖ ከተማዋ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ከተማ በመሆኗ እድለኛ ነች፡፡ በዚህም ተደራጅተው ከሚጠቀሙት ውጪ ባለው ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ የሚሆኑና በኢንዱስትሪዎች የሚቀጠሩ ወጣቶችም በብዛት አሉ፡፡
ይሁን እንጂ አጠቃላይ ካለው ፍላጎት አንጻር እነዚህ ሥራዎች በቂ ናቸው፤ ሥራውም የተሟላ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ወጣቱንም ሙሉ በሙሉ አርክተናል ማለት አንችልም፡፡ ሥራውም የተሟላ ስላልሆነ ገና መሥራት የሚጠበቁብን በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡
ምክንያቱም ወጣቱን ሥራ ማስያዝ ካልተቻለ ከሚፈጠረው ሁከት በኃይልና በጉልበት መመለስ አይቻልም፡፡ መመለስ የሚቻለው የሥራ እድል በመፍጠር፤ ወጣቱን በማወያየትና በማነጋገር ወደ አንድ ስምምነት ላይ መድረስ ሲቻል ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች ካልተሠሩ መንግሥትም ከችግር ውስጥ መውጣት አይችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በከተማዋ የሚፈለገው ለውጥና እድገት በተሟላ መልኩ እንዲመጣ ካስፈለገ ከወጣቱ ባሻገር መላው የከተማዋ ህብረተሰብም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ ሊረጋገጥለት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ለሕገ ወጥነት መስፋፋትና ለመሬት ወረራ ጭምር ከተማዋ መጋለጧ አይቀርም፡፡ በዚህ ላይስ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ አስፋው፡- ህብረተሰቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በተለይም ከመሰረተ ልማት አኳያ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል፡፡ ለአብነት፣ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት አሁን ላይ የከተማዋ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከ90 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ ከመንገድ አኳያም፣ አቅርቦቱ ጥሩ ነው፡፡ ከመብራት ጋር በተያያዘም ችግሩ አገራዊ የመሆኑን ያክል በሐዋሳ ያን ያክል የከፋ ነገር አለ ብለን አንወስድም፡፡
ከቤት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ግን ችግር አለ፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ ምቹና ተፈላጊ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በሥራ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ እንዲሁም ከገጠር ወደከተማ በሚደረግ ፍልሰትና በሌሎችም ምክንያቶች ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ በየጊዜው ሰው ይገባል፡፡ የሚገባው ሰው ደግሞ ቤት ይፈልጋል፡፡ ሆኖም ካለው ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የቤት አቅርቦት ላይ መድረስ አልተቻለም፡፡
ሆኖም ከተማ አስተዳደሩ በጀት መድቦ ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ገንብቶ እያቀረበ ሲሆን፤ በቅርቡ የሚቀርቡም በርካታ ቤቶች አሉ፡፡ በከተማዋ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውና የቤት ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተለይተው እንዲያገኙ የሚደረግበት አግባብም አለ፡፡ እነዚህ ጥረቶች ቢደረጉም በጥናት እንደተለየው የቤት አቅርቦቱ ብዙ ችግርና ክፍተት ያለበት ነው፡፡
ከሕገ ወጥ የመሬት ወረራና የቤት ግንባታን በተመለከተም በከተማዋ ጫፍ በተለይም በአርሶአደር አካባቢዎች ይህ ተግባር የለም ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም አሁን ላይ እንደ በፊቱ የከፋ ነገር የለም፡፡ ይህ ደግሞ አመራሩ በሕገወጥ የመሬት ወረራ ላይ ያሉ ተግባራትን ለመግታት በመሥራቱ የመጣ ውጤት ሲሆን፤ በተለይም ከተማዋ እየሰፋች ባለችበትና በአብዛኛውም አርሶአደር በሚኖርባት ስምንተኛ ክፍለ ከተማ ያሉ ችግሮች እንዲቃለሉ ከቀበሌ ጀምሮ የክፍለ ከተማና የከተማው አመራሮች በጋራ ተቀናጅተው እየሠሩ ነው፡፡ በዚህም የሆነ ነገር ቢከሰት እንኳን ወዲያውኑ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጎ በፋክስ ቁጥር 046 211 00 25/29/13ሕዝብ በማስተቸት ስህተት መሆኑን አምነው ግለሰቦቹ ራሳቸው አፍርሰው እንዲነሱ ከማድረግ አንጻር ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከላይ ያነሳናቸውም ሆኑ ሌሎች የከተማዋ ሁለንተናዊ እድገትና ለውጦች የከተማው አመራር ያለው ቁርጠኝነትና ትጋት ላይ ይመሰረታሉ፡፡ ታዲያ ሐዋሳ ለውጡን በማስቀጠልና የሕዝቡን ጥያቄ የሚመለስ አመራር በየደረጃው እንድታገኝ ከማድረግ አኳያ ምን ተሠርቷል? የወጣቶች ተሳትፎውስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አስፋው፡- አሁን በሐዋሳ ከተማ ያለው አመራር ከመስከረም ጀምሮ ያለ፤ ዘጠና በመቶ በሚባል ደረጃም አዲስ አመራር ነው፡፡ ይሄ አመራር ከመጣ በኋላም በተለይ በሰላምና ጸጥታው ላይ ሰፊ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ምንም እንኳን ከተማዋ ቀድሞም ሰላም ብትሆንም ከአዲሱ አመራር ወዲህ ግን ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ሰላም ሆናለች፡፡ ምክንያቱም አመራሩ ባለፈው የተፈጠረውን ክስተት ተከትሎ በከተማዋ ያሉ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው እስከ ከተማ ድረስ በማወያየት የጋራ አቅጣጫ ተሰጥቶበት ነው እየተሠራ ያለው፡፡
አዲሱና የለውጡ አመራር ደግሞ በአብዛኛው ወጣት አመራር ነው፡፡ የከተማውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ሰላምና ጸጥታውን ለማስፈንም እየሠራ ይገኛል፡፡ አሁን ያለው ልማት እንዲቀጥል ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ እየታዩ ያሉ ለውጦችም አዲሱ ወጣት አመራር የፈጠረው እንደመሆኑም፤ ይህ አመራር የከተማዋንና የነዋሪዎቿን ሁለንተናዊ ለውጥና እድገት የሚያስቀጥል እንደሚሆን ነው እኔም የምገምተው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ አመራር ምንም እንኳን ጠንካራ ቢሆንም ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ሊቸገር ይችላል፡፡ ታዲያ ከህዝቡ ባለፈ ከሌሎች አጋሮችና አጎራባች ከተሞች፣ ወረዳዎችና ዞኖች ጋር በምን መልኩ ተቀናጅታችሁ እየሠራችሁ ነው?
አቶ አስፋው፡- እንዳልከውም የከተማዋን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት፤ ሰላምና ጸጥታንም ለማስከበር አመራሩ ብቻውን ቢሯሯጥ ለውጥ አያመጣም፡፡ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው ሕዝብ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው ሕዝብ በሁሉም ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ሲሆን መልካም ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ መልካም ያልሆኑትና ተገቢነት የሌላቸው ደግሞ እንዲታረሙ ያስችላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከከተማው ህዝብ ጋር ውይይት እየተደረገ በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡
ከሕዝቡ ባለፈ ግን ከአጎራባች ወረዳዎች፣ ከተማዎችና ዞኖች እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ጋር በቅንጅት እየተሠራ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ከአጎራባች ዞን አኳያ ሐዋሳ የሲዳማ ዞን ዋና ከተማ እንደመሆኗ ከዞኑ ጋር ተቀናጅተን እየሠራን ነው፡፡ ከሲዳማ ዞን ጋር ከሚዋሰነው ከወላይታ ዞን በተለይም ሎካ ከሚባለው ወረዳ ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ለምን ቢባል፣ ሎካ ላይ አንድ ነገር ካለ እዚህ ሐዋሳና ሲዳማ ዞን ላይ ተመሳሳይ ችግር ይኖራል፡፡ ምክንያቱም አባት እዛ ካለ ልጅ እዚህ ይኖራል፤ ወይም አባት እዚህ ካለ ልጅ እዛ ይሆናል፡፡ ይህ የሕዝቦች ትስስር ደግሞ አብረን እንድንሠራ ያደርገናል፡፡
በክልሉ ካሉ አጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ባለፈ በኦሮሚያ ክልል ካሉ ከተሞችና ወረዳዎች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ፣ የሻሸመኔ ከተማ አመራርና የሐዋሳ ከተማ አመራር፣ እንዲሁም የሻሸመኔ ከተማ የጸጥታ ኃይልና የሐዋሳ ከተማ የጸጥታ ኃይል በቅንጅት ነው የሚሠሩት፡፡ ይህ ደግሞ ጠንካራ ትስስር እንዲኖራቸው እና በችግሮቻቸውም አንዱ ለአንዱ ቶሎ የሚደርስበትን እድል ፈጥሯል፡፡ ለአብነት፣ በቅርቡ በሐዋሳ ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ ከከተማ አስተዳደራችንና ከኢንዱስትሪ ፓርኩ እሳት አደጋ በተጓዳኝ የሻሸመኔ ከተማ የእሳት አደጋ ደርሶ አግዟል፡፡ የሻሸመኔ ፖሊስም መጥቶ ተሳትፏል፡፡
በተመሳሳይ የሐዋሳ ከተማም ሻሸመኔን ያግዛል፡፡ ለሌሎች አጎራባች ቀበሌዎችም ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ፣ የቢሻን ጉራቻ (ጥቁር ውሃ) ከተማ የመጠጥ ውሃ ከሐዋሳ ከተማ ታገኛለች፡፡ በዚህ መልኩ ከኦሮሚያ ክልል በተለይም ከሻሸመኔ ከተማ ጋር አብረን የምንሰራው ሥራ እርስ በርስ መደጋገፍን በመፍጠር ውጤታማ አድርጎናል፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ ከተማዋ ከአጎራባቾቿ ጋር በተሳሰረ መልኩ እየሠራች መሆኑን ያሳያሉ፡፡ ሥራዎቹም በጋራ እየተገመገሙ የሚሄዱ ብቻ ሳይሆን ትስስሩም የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ፤ እርስ በእርስም በእውቀትና ቁሳቁስ መደጋገፍን ፈጥሯል፡፡ በእነዚህ ተግባራት ድምር ውጤትም ነው ዛሬ በከተማችን ላይ ሰላምና ጸጥታን በማረጋገጥ እየሄድን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ብዙ የተባለ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ስጋቱ ቀጥሎ የህዝብ ጥያቄ በመሆኑ የሐዋሳ ሐይቅን ችግር ተረድቶ ሐይቁን ከአደጋ ለመታደግና የሕዝብን ስጋት ለመቀነስ የሚያስችል ምን ሥራ እየተሠራ ነው?
አቶ አስፋው፡- የሐዋሳ ከተማ መለያዋ የሐዋሳ ሐይቅ ነው፡፡ መጠሪያውም ከዚሁ የተወሰደ ነው፡፡ «ሐዋሳ» ቃሉ ሲዳምኛ ሲሆን፤ ትርጉሙም «ሰፊ» ማለት ነው፡፡ ይህ ከሐይቁ ውሃ ስፋት ጋር ተያይዞ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ እናም የሐዋሳ ሐይቅን መጠበቅና መንከባከብ ካልተቻለ የሐዋሳ ከተማም ሕልውና ከሐይቁ ጋር አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ምክንያቱም የሐዋሳ ውበቷም ሆነ ትልቁ የቱሪስት መዳረሻዋ ሐይቁ ነው፡፡ ሰፊ የዓሣ ሀብቱም የኢኮኖሚ ምንጭ ነው፡፡ ይሄን ታሳቢ በማድረግም ሐይቁን ከተደቀነበት አደጋ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡
ሐይቁን ከተጋረጠበት አደጋ ለማዳን እንዲቻልም በከተማ አስተዳደር ደረጃ የተቋቋመና በሐይቁ ላይ አተኩሮ የሚሠራ የአካባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት አለን፡፡ ይህ ተቋም ሲቋቋምም በሐይቁ ላይ የተለያዩ ጥናቶች እንዲሠሩ የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በሐይቁ ላይ ጥናት በማድረግና ለሚመለከታቸው በማቅረብ የሚመለከተው አካል በሐይቁ ላይ ሥራ እንዲሠራ ያደርጋል፡፡ ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሐይቁ ዙሪያ ይሠራሉ፡፡ ለምሳሌ፣ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ባለሥልጣን በቅርብ ጊዜ የከተማውን የአካባቢ ጥበቃ ጽሕፈት ቤት፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲን፣ ስምጥ ሸለቆና ሌሎችም የተካተቱበት በሐይቁ ላይ ብቻ የሚሠራ ፎረም አቋቁሟል፡፡
እናም ሐይቁን ለመታደግ የተለያዩ ጥናቶች ተካሂደዋል፤ መፍትሄ የሚሆኑ ነገሮችም እየተሠሩ ነው፡፡ ከተማ አስተዳደሩም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ተግባር ደግሞ የሐይቁን ደህንነት ለመጠበቅና ደህንነቱም ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል ነው፡፡ ስለዚህ ሐይቁ ከአደጋ፣ ከብክለትና ከደለል ነጻ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር ችግሮቹ ተለይቶ እየተሠራ ነው እንጂ የተዘነጋና የተረሳ ጉዳይ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሐዋሳ ከተማና ሕዝቦቿ ሰላምና ሁለንተናዊ የእድገት ጉዞ መሳካት ለሕዝቡ፣ ለአመራሩ፣ ለባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው?
አቶ አስፋው፡- ከመንግሥት ጎን ሆኖ ሰላሙን የሚጠብቅ ራሱ ሕዝቡ ነው፡፡ ሕዝቡ ሰላሙን ካልጠበቀ መንግሥት ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም፤ በፖሊስ፣ በልዩ ኃይል ወይም በሌላ የጸጥታ ኃይል ብቻ ሰላሙን ማስጠበቅ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን ከተማችን ሰላም እንደምትሆን በመገንዘብ እንደ እስካሁኑ ሁሉ በቀጣይም የሰላሙ ባለቤትነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በዚህ አግባብ በቀጣይነት ከተሠራም ከተማችን ሰላሟን ታስቀጥላለች የሚል እምነት አለኝ፡፡
በሌላ በኩል ሐዋሳ የኢንቨስትመንት ከተማ ናት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ማዕከል፣ የቱሪስት መዳረሻም ነች፡፡ ሰፊ የኢንቨስትመንት ፍላጎትም አላት፡፡ እናም በተለያዩ አማራጮችም ሆነ የቱሪዝም ሀብቷን ለማልማት የሚፈልግ ባለሀብት እንዲመጣ እንፈልጋለን፡፡ ለኢንቨስትመንት የሚሆን መሬትም በከተማዋ ተዘጋጅቷል፤ በተለያዩ መስኮች ለመሰማራትም ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች በርካታ ጥያቄ እየቀረበ፤ ለመጡትም እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም ባለሀብቱ ሳይጉላላ እንደ ቤቱ ቆጥሮ ያለቀጠሮ ጭምር ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት እየሠራ ሲሆን፤ በከተማዋ ያለውን እድልና ሰላም ተጠቅሞ በተለያዩ ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የሚፈልጉ ባለሀብቶች፤ በከተማዋ ጉብኝት ለማድረግ ያሰቡ ቱሪስቶች ወደ ሐዋሳ ያለስጋት እንዲመጡ ከተማ አስተዳደሩ ይጋብዛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቃለ ምልልስ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አስፋው፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 27/2011
በወንድወሰን ሽመልስ