ጁንታው ተሓህት/ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ/ ይባል በነበረበት ወቅት ግገሓት/ ግምባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ/ ከተባለውና ከእሱ በፊት ተመስርቶ በትግራይና በኤርትራ አዋሳኝ መሬቶች ላይ ይንቀሳቀስ ከነበረው የታጠቀ ድርጅት ጋር ሙሉ በሙሉ ውህደት ለመፈፀም ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር፡፡
ይህንን ተከትሎም ሁለቱ ድርጅቶች ማለትም ተሓህት-ህወሓት እና ግገሓት ውህደት ወደሚፈፅሙበት ቦታ ምስራቅ ትግራይ ዘገብላ ተብላ ወደ ምትጠራው ቦታ ሰራዊታቸውን ወስደው ካሰፈሩ በኃላ አመሻሽ ላይ የተሓህት-ህወሓት አመራሮች ቀን ሲሸርቡት የዋሉትን ሴራ ለሰራዊታቸው በጠቅላላ በምስጢር እንዲተላለፍ አደረጉ፡፡
ሴራውም እያንዳንዱ የተሓህት-ህወሓት ታጋይ ከግገሓት ታጋይ ጋር ጥንድ ጥንድ እየሆኑ እንዲተኙና ግገሓቶች እንቅልፍ ወስዷቸው የተኩስ ትዕዛዝ እስኪተላለፍ በንቃት እንዲጠባበቁ የሚል ነበር፡፡
ከዚያም እኩለ ሌሊት ላይ የግገሓት ሰራዊት በእንቅልፍ ላይ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ የተሓህት-ህወሓት ታጋዮች ከጎን ከጎናቸው ከተኙ የግገሓት ታጋዮች ላይ እንዲተኩሱ በምልክት ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ለውህደት የመጣው የግገሓት ሰራዊት ከነመሪዎቹ በእንቅልፍ ላይ እንዳለ ተጨፍጭፎ ሙሉ በሙሉ ሊደመሰስ ቻለ፡፡ ይህ ታሪክ የጁንታው ውልደት ገና ከጅምሩ በሰይጣናዊ ሴራና ሸፍጥ የተሞላ እንደሆነ የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
በ1968 ዓ.ም ባሳተመው የፖለቲካ ፕሮግራሙ ሰፊው የትግራይ ሕዝብ ስራ አጥቶ በሴተኛ አዳሪነትና ስደት ብቻ ሳይሆን በርሃብ፣ በድንቁርና እና በሽታ እየተሰቃየ በመኖሩ ምክንያት ጠብመንጃ አንስተን በረሃ ለመውረድ ቻልን…” ብሎ ለትግራይ ሕዝብ ተናግሮ የነበረው ጁንታው ይህን ካለ ከ40 ዓመታት በኋላም ዛሬም ረሃብ፣ በሽታ፣ ስራ አጥነት፣ ሴተኛ አዳሪነት፣ እና ስደት የትግራይ መገለጫ እንደሆነ አለ፡፡ እንዲያውም ያን እሱ የተቸውን ዘመን በሚያስመሰግን ሁኔታ ታግየለታለሁ የሚለው የትግራይ ወጣት በየቀኑ ህይወቱን ለአደጋ አጋልጦ እየተሰደደ ስለመሆኑ በየቀኑ የሚሰማ ሀቅ ሆኗል፡፡
ጁንታው የህይወት ዘመኑን ያራዝምለት እንጂ የሕዝብ ሞትና ስቃይ ምኑም እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ካደረጋቸው ድርጊቶች የታወቀ ሀቅ ነው። ይልቁኑ ለህልውናውና ለስግብግብ ፍላጎቱ ዕድሜ መቀጠል ሆን ብሎ ሕዝብን ለስቃይ እንደሚዳርግ ከድርጅቱ በግፍ የተፈናቀሉና ጥንተ ባህሪውን ቁልጭ አድርገው የሚያውቁ ግለሰቦች ደጋግመው መስክረውታል።
ለዚህ እንደ ትልቅ ማሳያ የሚያነሱት ደግሞ ጁንታው ለሕዝብ ነጻነት በሚል መነሻ በረሃ ላይ እየተንቀሳቀሰ በነበረበት 1977 ዓ/ም የነበረውን ሁኔታ ነው። ለማንም ግልጽ እንደሆነው በዚያ ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የድርቅ አደጋ ተከስቶ ዘግናኝ ጉዳት የደረሰበት ዓመት ነው። በዚህ ወቅት ጁንታው ይንቀሳቀስበት በነበረው የትግራይ አካባቢ ለነበረው ሕዝብ ዓለም አቀፍ የምግብና መሰል ድጋፎች ተደርገው ነበር።
ይሁንና ለሕዝብ ደንታ የሌለው ይህ ስግብግብ ጁንታ ምንም አይነት ሰብዓዊነት ባልተሰማው መልኩ በዚህ ክፉ ወቅት የሕዝብን ህይወት ለመታደግ የተቀበለውን እርዳታ ለሽያጭ በማዋልና በዚያም መሳሪያ በመግዛት ታሪክ ይቅር የማይለው አሳፋሪ ተግባርን ፈጽሟል። በዚህም ምክንያት በምግብ እጦት የበርካቶች ህይወት ማለፉንም ታዋቂ ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበውት እንደነበር አይረሳም።
በሕዝብ ስም ሲምልና ሲነግድ የኖረው ይህ ጁንታ በሕዝብ ስቃይ መነገድ ሥራው ነውና አሁንም በዚሁ ተግባሩ እንደቀጠለበት በቅርቡ ከተስተዋሉ ድርጊቶቹ መረዳት ይቻላል።ይህ ዘራፊና ስግብግብ ኃይል ለችግረኛው ሕዝብ እንዲታደል ከፌዴራል መንግስት የተላከ የሴፍቲኔት እርዳታን ይዘርፍ አንደነበር በቅርቡ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁም ሩቅ ያልሆነ ትውስታ ነው።
በችግር ውስጥ የሚኖረው የትግራይ ህዝብ ዱቄትና ድርቆሽ ሳይቀር በግዴታ እንዲያዋጣ እያደረገ ለራሱ ስግብግብ ፍላጎት ያውል እንደነበርም በርካቶች የሚያነሱት እውነታ ነው። በሕግ ማስከበር ዘመቻው በተደረገ ኦፕሬሽን በመቀሌና የተለያዩ አካባቢዎች ጁንታው ደብቋቸው የተገኙ ስንዴዎችን ዱቄቶች ጁንታው ከራሱ ስግብግብ ከርስ በላይ የሚያሳስበው ምንም ዓይነት የሕዝብ ህይወት እንደሌለ ፍንትው አድርጎ አሳይቷል።
ጁንታው ትዕቢቱና በሕዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ ወደ ፍጻሜው መርተውት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ካደረሰው ጥቃት ጋር ተያይዞ በተወሰደ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሟል። ለዓመታት ሲፎክርበት የኖረው ቀረርቶም እንደጉም በኖ ጠፍቷል።
አሁን ላይ የጁንታው ርዝራዦች ፉከራና ቀረርቷቸውን አቁመው ለትግራይ ሀዝብ ተቋርቋሪ መሰለው አዞ አንባ ሲያነቡ ይስተዋላል። ለዚህ ደግሞ በሕዝብ ስቃይ መቆመር የጁንታው ጥንተ ተፈጥሮ ነውና ለማያውቃችሁ ታጠኑ ከሚል ምላሽ ውጪ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም!
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013