የውሃ ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤት ከተቋቋመ በኋላ ከተለያዩ ፋይናንስ ምንጮች የሚያሰባስበውን ሀብት በክልሎች መካከል ለማዳረስ የፍትሀዊ ተጠቃሚነት መርህን ተከትሎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በከተሞች የሚታየውን ከፍተኛ የንፁህ መጠጥ ውሃና ሳንቴሽን አቅርቦት አገልግሎት ለማሻሻል ለሚረዱ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ በአነስተኛ ወለድ ለረጅም ጊዜ ብድር ይሰጣል፡፡ ጽህፈት ቤቱ በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ 103 ከተሞች ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ 114 የመጠጥ ውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክቶችንም ለማስፈፀም ዘጠኝ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በረጅም ጊዜ ብድር ሰጥቷል፡፡
የውሃና ሳንቴሽን ፕሮጀክት ለማከናወን ብድር የወሰዱ ከተሞች አብዛኛዎቹ የተፈለገውን ያክል ብድር እየከፈሉ አለመሆኑ ይገልፃሉ፡፡ ይህን በማስመልከት ሰሞኑን በአዳማ ከተማ የተበዳሪ ከተሞች ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ድርጅት አመራር ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱ ብድር የወሰዱ ከተሞች ፕሮጀክቶቹ ቢጠናቀቁም ብድር አለመመለሳቸው፣ ፕሮጀክቶቹ ሳይጠናቀቁ የተበደሩት ገንዘብ ማለቁ፣ የመብራት መቆጣጠር በመኖሩ ለህብረተሰቡ የታሰበውን ያክል ውሃ አለመሸጡ እንዲሁም የውሃ ክፍያ ታሪፉ አነስተኛ በመሆኑ ብድር ለመክፈል አለማስቻላቸው ተነስቷል፡፡
የውሃ ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋና ዋኬ እንደሚናገሩት፤ ብድር ተሰጥቷቸው ሥራ ከጀመሩ ፕሮጀክቶች ውስጥ 27ቱ ተጠናቀው ብድር መመለስ ጀምረዋል፡፡ ብድር ወደ መመለስ ከተሻገሩት ከተሞች ሁለት ነጥብ 86 ቢሊዮን ብድር የተመለሰ ሲሆን፣ እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ መመለስ ከነበረበት 639 ሚሊዮን ብር ውስጥ 529 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡ ያልተመለሰ 110 ሚሊዮን ብር ይቀራል፡፡
ብድራቸውን በወቅቱ የማይከፍሉ ከተሞች በህግ ጉዳያቸው እንዲታይ ከማድረግ በተጨማሪ ሌሎች ብድር ፈላጊ ከተሞች የእድሉ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው ህዝባቸውን ተጠቃሚ አለማድረጋቸውን ይገልፃሉ፡፡ በዚህም ፌዴራል መንግሥት ላይ እምነት ማጣት፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄና ብድሩ ሳይመለስ ሲቀር ወደ ፍርድ ቤት ስለሚሄድ የእርስ በርስ ግንኙነት እንደሚያሻክር ይገልፃሉ፡፡
እንድ አቶ ዋና ገለፃ፤ ከውጭ ብድርና እርዳታ ፋይናንስ ጥገኝነት ለመውጣት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲቻል ከውሃ ልማት ፈንድ የብድር ተጠቃሚ የሆኑ ከተሞች የብድር ጊዜያቸውን ጠብቀው መክፈል አለባቸው፡፡ ለብድሩ ዋስትና የሰጡ ክልሎችና ከተሞች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የውሃ አገልግሎት ሊደግፉና ሊከታተሉ ይገባል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው፤ ቀድመው ብድር ያገኙ ከተሞች በገቡት ውል መሰረት ገንዘቡን መመለስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በክልሎችና በከተሞች አካባቢ የብድር ወለድ ክምችት በየጊዜው እያደገ እንዳይሄድና የእዳ መጠኑ እንዳይጨምር የሚመለከታቸው አካላት በጥምረት መሥራት እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ከተጠቃሚው ከሚሰበሰው ገንዘብ ብድር መክፈል እንደሚቻል የተናገሩት ዶክተር ነጋሽ፤ ብድር ላለመከፈሉ ፕሮጀክቱ ቀድሞ ሲሠራ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ እንጂ በአበዳሪው አካል የተፈጠረ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ ብድር በመክፈል ጥሩ ተሞክሮ ካላቸው ከተሞች ልምድ መውሰድ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
በውሃ ልማት ፈንድ ጽህፈት ቤት የብድርና የበጀት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ተክሌ እንደሚናገሩት፤ ብድር ወስደው የውሃ ፕሮጀክት ሰርተው ያጠናቀቁ 27 ሲሆኑ፤ ስድስት ከኦሮሚያ፣ ስድስት ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ ዘጠኝ ከአማራ፣ ሶስት ከትግራይ እንዲሁም ሐረር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና አዲስ አበባ አንዳንድ ናቸው፡፡
ብድር ከወሰዱት ውስጥ ሐረርና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሙሉ ለሙሉ የተበደሩትን ገንዘብ መክፈል አለመጀመራቸውን በመጥቀስ፤ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ደግሞ ከግማሽ በላይ ብድራቸውን አለመመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልና አዲስ አበባ ከተማ በአግባቡ ብድራቸውን እየመለሱ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ አቶ አለማየሁ አባባል፤ የሚመለከታቸው የክልልና የከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ቢሮዎች ትኩረት አለመስጠታቸው፣ የውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አመራር ቶሎ ቶሎ መቀያየር፣ ውል ስምምነት የተደረገባቸውን ሰነዶች ማጥፋት፣ ከህዝቡ ተገቢው የውሃ ክፍያ አለመቀበል፣ መክፈል እየቻሉ በወቅቱ ብድር አለመክፈል እንዲሁም የመብራት መቆራረጦች እንደ ችግር ተነስተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 27/2011
በመርድ ክፍሉ