ኢያሱ መሰለ
ገብረመድህን ካሰኝ (ኳሻ) ይባላል። ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ቀበሌ 18 ልዩ ስሙ ቤላ አካባቢ ነው። ነፍስ እስኪያውቅ ድረስ ያደገው አያቶቹ ጋር ነው። ከዚያም ወላጅ አባቱ በ1989 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ሲያልፉ የ15 ዓመት ታዳጊው ገብረመድህን ትምህርቱን ከስድስተኛ ክፍል አቋርጦ አስፋልት ዳር ማሳለፍ እንደጀመረ ይናገራል።
ከልጆች ጋር መደባደብ፣ መስረቅ፣ ጫት መቃምና ሲጋራ ማጨስን እየለመደ መጣ። ከሁሉ በላይ የእጅ አመል ሱስ በረታበት።
ገብረመድህን ለአካባቢው ማህበረሰብ ስጋት ሆነ፤ ሁሉም በዓይነ ቁራኛ እየተመለከተው ዓይንህ ላፈር ይለው ጀመር። ከሰዎች አንገት ላይ ሀብል እየበጠሱ መሮጥ ዋና የስርቆት ተግባሩ እንደነበር የሚገልጸው ገብረመድህን ጨለማን ተገን እያደረገ ቤት ሰብሮ ወደ መስረቅ ተሸጋገረ።
ከዚያም የቆሙ መኪኖችን ዕቃ እየፈታ መሸጥ ጀመረ። ማታ ማታ ይሰርቃል፤ ቀን ቀን አድፍጦ ይተኛል። አንዳንዴም ጫት በመቃም ያሳልፋል። እጅ ከፍንጅ እየተያዘ አንዳንዴም እየተጠረጠር ለአጭርና ለረዥም ጊዜ የታሰረባቸው ጊዜያት ስፍር ቁጥር የላቸውም።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እስር ቤቶችን አዳርሷል፤ በዝዋይ እና ሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤቶችም ተፈርዶበት ታስሯል። ገብረመድህን የስርቆት ተግባርን እንደ ሥራ በመመልከት ደጋግሞ እየሰረቀ ደጋግሞ ታስሯል።
የተለያዩ ስርቆቶችን በመፈጸም ግማሹን ዕድሜውን በእስር ቤት እንዳሳለፈ የሚናገረው ገብረመድህን በአንድ ወቅት የደረሰበትን ሁኔታ እንዲህ ያስረዳል።
‹‹እኔና ጓደኛዬ በበርካታ የስርቆት ክስ ተከሰን ፖሊሶች ሲፈልጉን ፈረንሳይ ለጋሲዎን ጀርባ በሚገኘው ጫካ ተክልለን ተሸሸግን። ቀን ቀን ጫካ እየዋልን ስንመለስ በግ እየሰረቅን እቤት እያስገባን እናርድ ነበር።
አንድ ቀን እንደለመድነው ሀገር አማን ብለን በግ ይዘን ወደ ቤት ስናስገባ ባለቤቱ አየንና በፌዴራል ፖሊስ አስከበበን።
ከዚያም ፖሊሶቹ መሣሪያ እያቀባበሉ ኑ ውጡ ሲሉን አብረውኝ የነበሩ ጓደኞቼ እንዳይያዙ በማሰብ ከቤት ወጣሁና በፖሊሶቹ እግር ስር መሮጥ ጀመርኩኝ። ፖሊሶቹ እኔን ተከትለው ሲሮጡ አብረውኝ የነበሩ ጓደኞቼ አመለጡ።
በመጨረሻ ግን እኔን ያዙኝና ከኢጣሊያን ኤምባሲ እስከ ፈረንሳይ ኤምባሲ ድረስ የታረደውን በግ አሸክመውኝ እስር ቤት አስገቡኝ። በስርቆት ታሪኬ እንደሞት ከምቆጥራቸው ክስተቶች አንዱ ይህ ነው።
በዚህ የተነሳም ከአንድ ዓመት በላይ ታስሬ ተፈታሁ። ከዚያ በኋላ ወደ ሰፈሬ መምጣት አፈርኩና ደጃች ውቤ ሰፈር ተከራይቼ መኖር ጀመርኩኝ። እዚያም ስኖር እንደገና በመኪና ዕቃ ስርቆት ላይ ተሰማራሁ። ከምኖርበት ሰፈር እርቄ እስከ ኮተቤ አዲሱ ገበያ እየሄድኩኝ ሌሊት አጥር ዘልዬ በመግባት የመኪና ዕቃ እየሰረቅሁ መኖር ጀመርኩ።
በመጨረሻ የካቲት 2001 ዓ.ም ሌሊት አራት ኪሎ ማስተር ማተሚያ ቤት ግቢ ገብቼ ከቆሙ መኪኖች ላይ ዕቃ ስፈታ ተያዝኩኝ እና ተፈርዶብኝ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ታስሬ ተፈታሁ። እንደገና አሁንም ሌላ ሰፈር ተከራይቼ መኖር ጀመርኩና አሁንም መስረቅ ጀመርኩኝ፤ ለመጨረሻ ጊዜ ተይዤ ሸዋ ሮቢት እስር ቤት ገብቼ በ2004 ዓ.ም ተፈታሁ።
ከዚያ በኋላ ዳግም ወደ ስርቆት ላለመግባት ለራሴም ለቤተሰቦቼም ቃል ገብቼ መኖር ጀመርኩኝ። ከጓደኞቼም ጋር ተራራቅሁ፤ በዚህ ሁኔታ እያለሁ ግን በጣም ተቸገርኩኝ፤ እስከመራብ ደረስኩኝ፤ ከኅብረተሰቡም ጋር መግባባት አቃተኝ። አምኖ ሥራ የሚያሰራኝ ሰውም አጣሁ፤ ዘበኝነት ሥራ ለመቀጠር ፈልጌ ዋስ እስከማጣት ደረስኩኝ።
አንድ ቀን ቀበሌ ሄድኩና ከስርቆት ሕይወት እንድወጣ ነግጄ መኖር የምችልባትን ትንሽ ቦታ እንዲተባበሩኝ ጠየኳቸው። እነርሱም ያሳለፍኩትን ታሪክ ስለሚያውቁ አንተ ብቻ የመስራት ፍላጎት ይኑርህ እንጂ እንተባበርሃለን ብለው ጥር 2007 ዓ.ም መንገድ ዳር ትንሽ ቦታ ሰጡኝና መሬት ላይ ላስቲክ ዘርግቼ በሦስት ሺ ብር መነሻ ማስቲካ፣ ውሃ፣ ሶፍት እና የመሳሰሉትን መቸርቸር ጀመርኩኝ።
ከዚያ በኋላ የአካባቢው ማህበረሰብ ከማስበው በላይ ተቀበለኝ። በመለወጤ ብቻ እየተደሰቱ 10 እና 50 ብር ሰጥተውኝ የአንድ ብር ማስቲካ ከወሰዱ በኋላ መልሱን ትተውልኝ ሲሄዱ የበለጠ አቅም ፈጠሩልኝ። አንዳንዶችም ሥራ በመጀመሬ ደስ እያላቸው እንድጠናከር ብር ይሰጡኛል።
የሚያበረታታኝ፤ የሚደግፈኝና ከጎንህ ነን የሚለኝ ሰው በረከተ። ከችርቻሮው ሥራ ጎን ለጎን ጫማ እሰፋለሁ፤ አንዳንዴም እደልላሁ። በምሰራው ሥራ ሁሉ ሰዎች ይተባበሩኛል። ገቢዬ ጨመረ፤ ኑሮዬም ተለወጠ። ሜዳ ላይ ዘርግቼ በምሸጥበት ቦታ ላይ መጠነኛ ኪዮስክ ከፍቼ መስራት ጀመርኩኝ። «ከዚህ ሁሉ ስኬት ጀርባ የአካባቢው ማህበረሰብ መልካም አቀባበልና የባለቤቴ ታታሪነት ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው» ይላል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ መከሰት በንግድ ሥራዬ ላይ ተጽእኖ ሲያሳድርብኝ የወዳደቁ የውሃ መያዣ ፕላስቲኮችንና ሌሎች ቁሳቁስን እያስዋብኩ አበቦችንና የምግብ አትክልቶችን እየተከልኩባቸው በመሸጥ አዲስ የሥራ ዘርፍ ፈጠርኩ ይላል ኳሻ።
አትክልቶችን እየተንከባከቡ በልምላሜ ውስጥ ማሳለፍ ከፍተኛ የመንፈስ እርካታ እንደፈጠረለት በመናገር ለጊዜው ሱቁን ዘግቶ የድለላና የአትክልት ሥራውን እያጠናከረ እንዳለም ይናገራል። ባለቤቴ ሰርተን እንድንለወጥና ኑሯችንን አሸንፈን እንድንኖር ትጥራለች የሚለው ገብረ መድህን እርሷ ሻይ ቡና እያፈላች ከመሸጥ ባሻገር እኔንም በሥራ ታግዘኛለች ይላል።
ለአብነትም በኮሮና መከሰት ምክንያት የኪዮስክ ንግዱ ሲቀዛቀዝ ለግል ቤታችን ማስዋቢያ የሰራናቸውን የአበባ ማስቀመጫ ዓይነቶች እየሰራሁ ለገበያ እንዲያቀርብ ሀሳብ የሠጠችው እርሷ መሆኗን ያስረዳል። በዚህም ከሥራ ሰዓቷ ስትመለስ አፈርና ኮምፖስት እያዘጋጀችለት ሥራውን እንዳስጀመረችው ይገልጻል።
ዛሬ በእርሱ ሰርቶ መለወጥ ጥርጣሬ የነበራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎችና የቀበሌው አመራሮችን በሥራ አሳምኗል። እንዲያውም በሥራ ዕድል ፈጠራ የተጣሉና ጥቅም የማይሰጡ ቁሶችን ጥቅም ላይ በማዋል ከቀበሌው ተጠቃሽ መሆን ችሏል። በዚህም ሥራዎቹን በኤግዚቢሽን በማቅረብ የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል።
ኳሻ ያለፈ ታሪኩን እያስታወሰ ከሚቆጭባቸው ነገሮች ውስጥ አንዳንዶቹን እንዲህ ይጠቅሳል። ኳሻ «አራዳ ነው፤ ደፋር ነው፤» የሚል ተራ ስም ዋጋ የሚያስገኝለት እየመሰለው በከንቱ ያሳለፈው ጊዜ ያስቆጨዋል። አራዳ ማለት ሰርቶ እራሱን የለወጠ እንጂ የሰውን ገንዘብ የሚዘርፍ አለመሆኑን የተረዳው አሁን ነው።
ለባህሪው መበላሸት የመጀመሪያው ተወቃሽ እራሱ እንደሆነ ቢያምንም በጥፋት ሕይወት ውስጥ እያለ በዙሪያው ሆነው ሲያደንቁትና ሲያወድሱት የነበሩ አድናቂዎቹን ተጠያቂ ያደርጋል። መልካም ጓደኛ መጥፎ ነገርን አያበረታታም። እየመከረ ቀናውን መንገድ ያሳያል። አንዳንድ ሰዎች ለመሳቅና ለመዝናናት ሲሉ የሰው ሕይወት መበላሸት ግድ አይሰጣቸውም።
ሰው ወንጀል ሲሰራ ያንን እንደተአምር እያወሩ ከመንቀፍ ይልቅ ያደንቃሉ። እነርሱ ግን ስማቸውን ጠብቀው ዓላማቸውን ያሳካሉ። ዛሬ እነርሱ ተምረው የተሻለ ሕይወት ሲመሩ ሲያይ እርሱ በተራ ሌብነት ያሳለፈው ጊዜ ያንገበግበዋል።
በውድቅት የሰረቀውን ዕቃ ተሸክሞ ከአውሬ ጋር እየተጋፋ ወንዝ ለወንዝ ሲዳክር የነበረውን ሲያስታውሰው ይገርመዋል። ተተኩሶበታል፤ ተደብድቧልም። ሰርቶ ማግኘት እና መለወጥ እየቻለ ባልባሌ ነገር ያባከነውን ሰርቶ የመለወጥ ዕድል ዛሬ ላይ ቆሞ ሲያስታውስ ይናደዳል።
እንደገብረመድህን አገላለጽ ያ በስርቆት ያሳለፈው ዘመን በሕይወት ያልኖረበት ዘመን ነው፤ ዕድሜው 38 ቢሆንም ቀልቡን ሰብስቦ ሕይወቱን አረጋግቶ እንደሰው መኖር ከጀመረ ገና አምስትና ስድስት ዓመት እንደሆነው ይሰማዋል።
ዛሬ ኳሻ ለአካባቢው ወጣቶች እንደጥሩ ምሳሌ የሚጠቀስ ሆኗል። ከራሱም አልፎ ለሚላላኩት ሰዎች የአገልግሎታቸውን እየከፈለ መጥቀም ችሏል።
ለአካባቢው ወጣቶች ትምህርት ቤት ነኝ የሚለው ባለታሪኩ የነበረኝን መጥፎ ባህሪ ቀይሬ ሌላ ሰው ሆኜ ሲያዩኝ ሊማሩብኝ ይችላሉ ይላል። እርሱም ቢሆን የሚሸጣቸውን የአበባ ችግኞችና አትክልቶች እዚያው ትቷቸው ሲሄድ ማንም ሳይነካበት እንደነበሩ ሲያገኛቸው መመልከቱ የታማኝነትን ዋጋ የበለጠ ለመረዳት እንደረዳው ይገልጻል።
የአካባቢው ሰዎች ታማኝነትንና ፍቅርን እያስተማሩኝ እኔም እየተለወጥኩ መጣሁ ይላል። በአንድ ወቅት ታሞ ጳውሎስ ሆስፒታል ተኝቶ በነበረበት ወቅት የአካባቢው ማህበረሰብ ያደረገለት እንክብካቤ ያልጠበቀውና የማይረሳው ነው።
‹‹ያ ያስቀየምኩት የአካባቢዬ ሰው ያንን የችግር ወቅት አቅፎና ደግፎ ያሳለፈኝ ባህሪዬ ስለተሻሻለ ነው። ያ አጋጣሚ የሰዎችን መልካምነት የበለጠ እንድረዳ የእኔንም ባህሪ የበለጠ እንዳስተካክል ረድቶኛል» ይላል።
ሰው ለሰው ፍቅርና ክብር ከሰጠ፣ ካልሰረቀና ለማደግ ከተጣጣረ ሰው ይወደዋል፤ ሰው ከወደደውና ከደገፈው ደግሞ ያሰበበት ይደርሳል ይላል ገብረመድህን። የሰውን ገንዘብ ከመስረቅ ይልቅ አዕምሮንና ጉልበትን አቀናጅቶ ነገሮችን ወደ ገንዘብ መለወጥ የሚቻልባቸው በርካታ ምስጢሮች መኖራቸውን ተረድቻለሁ ይላል።
ዛሬ ገብረመድህን የ38 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ነው። በባለቤቱ ወላጆች ግቢ ውስጥ ለራሳቸው የሚበቃ መኖሪያ ቤት ሰርተው ደስተኛና ተስፋ የተሞላበት ሕይወት በመምራት ላይ ይገኛሉ። ነገ የተሻለ ነገር ለመስራት የሚያስችል እቅድ እንዳለውም ነግሮናል።
የቀበሌው መልካም ትብብር ሰርቼ እንድበላ አድርጎኛል የሚለው ገብረመድህን ከዚህ የተሻለ ውጤታማ ለመሆን አሁንም የሚመለከተው አካል ያለበትን የቦታ እጥረት ተመልክቶ ለማምረቻ የሚሆን ሰፋ ያለ ቦታ ቢሰጠው ለራሱም ለሌሎችም እንደሚተርፍ ይገልጻል። በተጨማሪም የገበያ ትስስር ቢፈጠርለት ይመርጣል።
እኛም የገብረመድህንን የሕይወት ዝቅታና ከፍታ ይዘን መቅረባችን ሌሎች ይማሩበታል ብለን በማሰብ ነው። ሰው በሕይወት ዘመኑ የሚያልፍባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ ጋሬጣ ሆነው ወደ ኋላ የሚጎትቱ ሲሆኑ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ በተስፋና ደስታ የታጀቡ ናቸው።
ከፊታችን የሚገጥሙንን ጋሬጣዎች በጥበብ ካልተሻገርናቸው መንገድ ላይ ያቆሙናል። የእኛ መቆም ደግሞ ሌሎች እንዳያልፉት መተላለፊያውን ዘግተን እንድንቆም ያደርጋል።
በራሳችን ሕይወት ላይም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ እንቅፋት የሚሆኑ አላስፈላጊ ባህሪዎቻችን ማረም ከራስ አልፎ የሌሎችን ሰላም ማወጅ መሆኑን ከባለታሪኩ መማር ይቻላል። ሳይሸማቀቁና ሳያፍሩ ያለፈ ታሪካቸውን ለማስተማሪያነት ይሁን ብለው በቅንነት የሚናገሩ እንደ ገብረመድህን ያሉ ባለታሪኮችም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። የተሻለ ስኬት ተመኝተናል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013