በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ሰውዬው ምሬት ውስጥ ነው። የምሬቱ ምክንያት ደግሞ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ነው። በሥራው ውስጥ ግጭት አላጣ ቢለው ግጭት አልባ የሆነ ሥራን ያገኝ እንደሆን ጉዞ ጀመረ።በማለዳም ተነስቶ ጉዞ ጀምሮ የአንድ ሰዓት ያህል መንገድ ከሄደ በኋላ አንድ የሚያውቀው ሰው በመንገዱ ይገጥመዋል።
“ጋሽዬ እንዴት ከርመሃል ወዴትስ እየሄድክ ነው?” ይለዋል ተጓዡን ግለሰብ። ግለሰቡም ችግር የሌለበት ሥራ አገኝ እንደሆን ልሞክር ነው፤ የሚገጥመኝ ሥራ ሁሉ ችግር ያለበት ሆኖ ተቸገርኩ” ሲል ይመልሰልታል። መንገደኛውም “ለመሆኑ ከግንበኝነት ሥራ ውጭ አስቸጋሪ ሥራ አለ ብለህ ነው?” በማለት እርሱ ከሚሠራው ከአናጢነት ሥራ ውጭ ያሉ ሥራዎች በሙሉ ችግር አልባ ሆነው እንደሚታዩት ይመክረዋል።
ተጓዡ ስለ ግንበኝነት እያሰበ ጉዞውን ይቀጥላል። ግንበኝነት እንዴት የተለየ ችግር ያለበት እንደሆነም ያስባል። አሁንም ጉዞውን ቀጥሎ ከገብያ የምትመለስ ጎረቤቱን ያገኛታል። ይህች ጎረቤቱ በሥራዋ ታታሪ እንደሆነች የሚያስባት ሁልጌዜ ደስተኛም መስላ የምትታየው አይነት ነች።
ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ወይዘሮዋም “ እንደምን አረፈድክ ጎረቤቴ ከገብያ በመመለሻ ሰዓት ወዴት እየሄድክ ነው?” ብለው ትጠይቀዋለች። ግለሰቡም “የምሠራው ሥራ ሁሉ በችግር እየተተበተበ ግራ ቢገባኝ ችግር የሌለበት ሥራ አገኝ እንደሆን ጉዞ ጀምሬያለሁ። በእርግጥ የአንቺ አይነት ሥራ መሥራት ችግር የሌለበት መሆኑን ባውቅም እንዴት የጎረቤቴ ተቀናቃኝ እሆናለሁ ብዬ አስቤ ተውኩት።” ብሎ ይመልስላታል።
ወይዘሮዋም ግንባሯን ቋጠር አድርጋ “ማሽላ እያረረ ይስቃል አሉ። እርሱስ ጥሩ ነው የምትለው አይነት ሥራ ከተገኘ። አደራ ግን እኔ የምሠራውን ዶሮ አርብቶ የመሸጥን ሥራ እንዳትሞክረው።
የዶሮ በሽታ በመጣ ጊዜ እንዴት በአንዴ መናጢ ደሃ አድርጎኝ፣ ክፉውን ቀን በሰው መሻገሬን አንተም ታውቀዋለህ። ለማንኛውም ስለ እኔ ሥራ ያለህን የተሳሳተ ግንዛቤ አስተካክል። ኸረ እንደውም ከእኔ ሥራ ውጭ ሌላ ሥራ ምኑ ነው የሚከብደው?” ብላ በጥያቄ ሃሳቧን ሰጥታው ተለያዩ።
ሰውዬው ስለ ዶሮ ሥራ እያሰበ ጉዞውን ቀጠለ። እንዴት የዶሮ ሥራ እንዲህ አስቸጋሪ ሆነ። አስቸጋሪ ነገር እንዴት በግንባታውም ሆነ በዶሮ ሥራ ውስጥ ኖረ። ይሄ ነገር ችግሩ ምንድን ነው? እያለ ከራሱ ጋር እያወራ እግሮቹ ወደ ፊት ይራመዳሉ። በጉዞው በቅርቡ ትዳር የመሰረተ የሰፈራቸውን ወጣት አማቾቹ ቤት ሄዶ ሲመለስ አገኘው።
ወጣቱም “ጋሽዬ እንደምን ዋልክ ወዴት እየዘለክ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል። ችግር አልባ ሥራ ፈላጊው ተጓዥም ለቀደሙት ሰዎች የመለሰውን የጉዞውን መዳረሻ ይነግረዋል። ወጣቱም እርሱ ከሚሠራው የመምህርነት ሥራ ውጭ ያለው ሥራ መልካም እንደሆነ ነገረው። መምህርነት የተናቀ ሥራ ሆኖ ጊዜን ማሳለፊያ መሆኑ እንደሚያሳዝነው ገለፀለት። እንዲሁ እርሱ የሚሠራው ሥራ ውስጥ ያለውን የችግር ብዛት ነግሮት ሌላ ሥራ እንዲሠራ ተጓዡን መከረው። ተጓዡም የወጣቱ ሥራ እንዴት አስቸጋሪ ሊሆን እንደቻለ እያሰበ ቀጠለ።
ጉዞውን ቢቀጥልም የሞላ ውሃ ስለገጠመው ቆመ። ወንዙ ትላንት ማታ በዘነበው ዝናብ ምክንያት ማለፍ እስከማይቻል ድረስ ጢም ብሏል። በእዚህ ጊዜ ወንዙ ዳር ቁጭ ብሎ በሃሳቡ ሄደ። በሞላው ወንዝ ውስጥ የሚሆነውን ትኩር ብሎ ሲመለከት ከውሃ በተጨማሪ የእንጨት ጉማጅ፤ ጉቶ፤ ጭራሮ ወዘተ በወንዙ እየተወሰደ ይመለከታል። ተጓዡም ወንዙን ለመሻገር ቢሞክርም በወንዙ እየተወሰዱ እንዳሉት የእንጨት አይነቶች አንዱ እንደሚሆን ያስባል።
በእዚህ ጊዜ አንድ ጥያቄ ራሱን ይጠይቃል። አሁን እንደው ከሞት ለማምለጥ ቢሆን ወይንም ከኋላው አውሬ ቢያባርረው ኖሮ እንዴት አድርጎ ወንዙን ይሻገር እንደነበር ያስባል። ሃሳቡም ዝግንን አለው። ወንዙ ውስጥ ዘሎ ቢገባ በጎርፉ እንደ ጉቶው ከመወሰድ ውጭ አማራጭ እንደሌለው አሰበ።
በሞት ጣር ላይ ያለ ሰው በቃሬዛ ይዘው መጥተው ቢሆንም እንዲሁ እንዴት እንደሚያልፉት ሲያስብ ከእዚህ ቀደም በሞላ ወንዝ ምክንያት ህክምና ሳያገኙ ቀርተው ህይወታቸው ያለፉትን አጎቱን አስታውሶ አዘነ። ድልድይ ቢኖር ግን ወንዙን ማለፍ ችሎ ጉዞውን መቀጠል ይችል ነበር። ድልድይ የሚሰሩ የግንባታ ሰዎች እንዴት ባለውለታችን ነበሩ? ሲል አሰበ። እንዴት ነው ታዲያ በመንገድ ላይ የገጠመው የመጀመሪያ ሰው የግንበኝነት ሥራን በችግር ውስጥ የገለፀው? እያለ ራሱን ጠየቀ።
ጥያቄውን በመቀጠል ድልድይ የሚሰሩትስ ሰዎች የድልድይ አሰራርን ትምህርት አድርገው ባይወስዱ ኖሮ፣ ባይማሩ ኖሮ እንዴት ሊሰሩት ይችሉ ነበር። ስለሆነም መምህራን እንዴት ባለውለታዎቻችን ነበሩ አለ። መምህሩ ተረጋግቶ ማስተማር እንዲችል አርሶ አደሩ ማረስ፣ ዶሮ ማርባት፣ ወዘተ ባይችል ኖሮ እንዴት ይሆንስ ነበር ሲል ጎረቤቱ ዶሮ አርቢዋን አሰበ። አርሶ አደሩ ጤናው ተጠብቆ ማረስ እንዲችል የሕክምና ባለሙያው ባይኖር እንዴትስ ይታሰብ ነበር ሲል እንዲሁ ጠየቀ። እንዲህ እያለ ሲያስብ እያንዳንዱ ሥራ ውስጥ ያለውን የከበረ አስተዋፆ ተመለከተ።
ወንዙ ይዟቸው እንዳይሄድ ወንዙ እስኪጎድል መጠበቃቸው ወንዙ ይዟቸው እየሄደ እንዳለ ጉቶና ጭራሮዎች የሚለዩ መሆናቸውን ገለጠላቸው። እርሱ ሰው የመሆናቸው ነው። ሰው በመሆናቸው ውስጥ ያለው አስተውሎት ከግዑዝ ነገር በብዙ እንደሚለዩም አስረዳቸው። የሰው ልጅ ከችግር የሚሸሽ ሳይሆን ችግርን ተረድቶ መውጪያ መንገዱን የሚፈልግ መሆኑንም አሰቡ። የአንዱ ሥራ የሌላው ችግር መውጫ መሆኑንም ተረዳ።
ችግር የሌለበትን ሥራ ሳይሆን ልሠራው የሚገባኝን ለመሥራት በመነሳት ችግርም ካለ ችግርን ከምንጩ በመፍታት መራመድ ነው ሲል ከራሱ ጋር ተማማለ። አስተሳሰቡንም አስተካክሎ ጥሎት ወደ መጣው ሥራ በፍጥነት ደርሶ የእርሱ ሥራ የሌሎችን ችግር በመፍታት ውስጥ ሌሎች በሚሰሩት ውስጥ የእርሱ የሚፈታ መሆኑን ለራሱ ነገረ። የሚያስፈልገው አንድ ነገር ችግርን መሸሽ ሳይሆን ችግሩን ከምንጩ የመፍታት ባህል ነውና እነሆ ችግርን ከምንጩ። ከችግር መዝርዝር በመነሳት ወደ መፍትሄ መሄድ የችግር መፍቻው ቁልፍ ነው።
የችግር አፈታት መንገድ
ራሳችንን የሚመስል የችግር መዝርዝር የመፍትሄ ፍለጋው እርምጃ ቀዳሚው ተግባር ነው። ችግር ሲገጥመን በገጠመን ችግር ውስጥ የችግር አፈታት መንገዱ ምን ይሁን የሚለውን ማሰብ ይገባናል። አንድ አይነት የችግር አፈታት ቁልፍ ሊኖር አይችልም። እንደ ችግሩ ሁኔታ ግን የችግር መፍቻ ቁልፍ ይኖረዋል።
አንዳንዱ ችግር በራሳችን የምንፈታው ሊሆን ይችላል፤ ሌላውን ችግር ደግሞ ከሌሎች ጋር በመሆን። አንዳንዱን በሕግ የምንፈታው ይሆናል ሌላውን በሌሎች መንገዶች። በሕግ ብቻ ሊፈታ የማይችለውን ሕግ በወቅቱና አግባብነት ባለው መንገድ ወደ ሕግ መውሰድ ተገቢ ሊሆን ይችላል።
ግለሰባዊ ችግር ሲገጥመን በሕግ ሊፈታ አይችልም፤ እራሳችንን ልንከስ ስለማንችል። በህይወት አካሄዳችን ደስተኞች ሳንሆን ስንቀር እራሳችንን ላለንበት ችግር ተጠያቂ በምናደርግበት ጊዜ መፍትሄው ወደ ውስጣችን መመልከት፤ የእምነት አባቶችን ምክር መጠየቅ፤ እረፍት ማድረግ ወዘተ ሊሆን ይችላል።
የችግር አፈታት ቁልፉን እንደ ሁኔታው ቢለያየም ለሁሉም ችግሮች ሊተገበር የሚችለው አጠቃላይ ችግር አፈታትን ቀጥሎ እንመለከታለን፤ ችግሩን በሚገባ የመረዳትን አስፈላጊነት በማስቀደም።
1. ችግሩን ማወቅ፡- ችግሩ ምንድን ነው? እንዴት ሊፈጠርስ ቻለ? በችግሩ ውስጥ የእኔስ ድርሻ ምንድን ነው? ችግሩ ቢዘልቅስ ምን ሊከሰት ይችላል? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለማወቅ ትንታኔ ማድረግ ቀዳሚው ቁልፍ ነው። የችግሮች ሁሉ ምንጭ ድንቁርና / አላዋቂነት ነው ይላል ፈላስፋው ፕሌቶ።
በስብሰባዎች ላይ በተለየ ሁኔታ ችግርን ሆነ ስጋትን በማውራት የሚታወቁ ሰዎች ይገጥሙን ይሆናል። አንዳንዱ ፈጽሞውኑ መልካም ነገር የማይታየው ችግር ብቻ የሚታየው ሆኖ ሊገኝ ይችላል። እንዲህ አይነቱ ሰው የሚያቀርበው አይነት የችግር መዝርዝርን ማለታችን አይደለም።
ወደ ምግብ ቤት ገብተን ምግብ ከማዘዛችን በፊት የምግብ መዝርዝሩ/ሜኑውን ለማየት እንሞክራለን። የምንፈልገውን ምግብ አይነትና ዋጋውን በዋናነት እናያለን። ልክ በሜኑ ላይ እንደተዘረዘሩት ለሽያጭ የቀረቡ ምግቦች በዙሪያችን ያሉ ችግሮችን እንዘርዝር ብንል በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ላንጨርስ እንችል ይሆናል። ነገርግን የችግሩን አይነት እና ችግሩ የሚያስከፍለንን ዋጋ ልናስብው ይገባናል፤ ልናደርገው የግድ ይላል።
በቤተሰብ ውስጥ የበረከቱ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በሁሉም ቤተሰብ ውስጥ አይነቱ ይለያይ እንጂ ችግሮች አይጠፉም። በሥራ ቦታም ሆነ በማህበራዊ ህይወት ውስጥ እንዲሁ ችግሮች ይኖራሉ። የሀገራችንን ፖለቲካዊ ሁኔታ ባሰብን ቁጥር ልባችንን በሀዘን የሚሞሉ ብዙ ችግሮች አሉ። ችግሮች ሁሉ ጠፍተው ሀገራችን የፍፁማን ምድር መሆን የምትችልበት ዘመን ይመጣል ብሎ ማሰብ ዘበት ነው።
ችግሮችን መቀነስ የሚል ካልሆነ በስተቀር ማጥፋት የሚለው በተጨባጩ ዓለም ውስጥ የማይታሰብ ነው። የሰው ልጅ በሂደት ሰላማዊና ፍፁም የምትመች ዓለምን እውን ያደርጋል ተብሎ እሳቤ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም የዓለም ጦርነቶችን የሚያስተናግድ፤ ጦርነቶቹንም አንድ ሁለት እያለ ቁጥር ሠጥቶ ራሱ በሠራው መሣሪያ እራሱን የሚያጠፋ ሆኖ እሳቤውን ውሃ በልቶታል።
የችግር መዝርዝራችንን ማስቀመጥ መቻል የመፍትሄ ፍለጋው እርምጃው ጠቃሚ ነገር ነው። ችግር እኛ ጋር ብቻ ያለ አለመሆኑን መረዳት እንዲሁ ለመፍትሄ ፍለጋው ሌላ ተጨማሪ አቅም ነው። ከእንቅልፋችን ስንነቃ ወደ አዕምሮችን ፈጥኖ የሚመጣው ምንድን ነው? ጥሩ ስሜት እንዲሰማን የማያደርግ ጉዳይ ከሆነ ምናልባት እርሱ የችግራችን ዋናው ችግር አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን።
ስሜታችን እንዲዋዥቅ የሚያደርጉ፤ በራስ መተማመናችንን የሚነጥቁ፤ በምናደርገው ነገር እርካታ እንዳይሰማን የሚያደርጉ ወዘተ እያልን ውስጣችንን ብንፈትሽ የችግር መዝርዝራችን ራሳችንን የሚመስል ልናደርገው እንችላለን። እራሳችንን የሚመስል ማለታችንን ልብ ይሏል፤ እኛ ያለንበትን ችግር የሚያሳዩ ማለት ነው።
በጤና ማዕከል ውስጥ የተገኘ ህክምና ፈልጎ የመጣ ግለሰብ ለራሱ ህመም መድሃኒት ይሁን መርፌ እንዲታዘዝለት እንጂ የሌላው እንዲሰጠው አይጠብቅም። ከግለሰብ እስከ ሀገር የህመማችን ሁሉ ምንጭ የሚመስለው ለእኛ ችግር ለሌሎች የተሰራውን መድሃኒት መውሰድ ይመስላል። ችግር ሁሉም ቦታ ያለ ቢሆንም የችግሩ አይነትም ሆነ ባህሪ፤ የጥልቀት ደረጃም እንዲሁም መፍቻ መንገዱ የሚቀየስበት ከባቢ ሁኔታ አንድ አይነት ሊሆን አይችልም።
እራሳችንን የሚመስል የችግር መዝርዝር ማዘጋጀት የመፍትሄ እርምጃው ቀዳሚው ነው። ችግሮችን በመዘርዘርና ምንጫቸውን በመፈለግ ሂደት ውስጥ 5ቱ ለምኖች/5 Whys መንገድን አጥንቶ መተግበር እግዛ ያደርጋል።
2. ችግሩን ለመፍታት የሚያስፈልገውን ማወቅ፡- ችግር ብለን መዝርዝራችን የጠቀስነው የትኛው ችግር የምንለው ነገርን መፍታትን ስናስብ ችግሩን ለመፍታት ምን እንደሚያስፈልግ ማወቅ ተገቢ ነው። ችግር አድርገን የመዘገብነው ከግለሰብ ጋር ያለን ግጭት ከሆነ ከተጋጨነው ሰው ጋር ቁጭ ብለን በእርጋታ የምንነጋርበትን ድባብ በመፍጠር የተጋጨነውን ሰው ለውይይት መጋበዝ ሊሆን ይችላል የሚያስፈልገን።
ለችግሩ አፈታት የሚያስፈልገውን አካሄድም ሆነ ግብዓት ማወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው። ችግሩ የገንዘብ ከሆነ የሚያስፈልገንን ገንዘብ ለማግኘት የምንሄድበትን መንገድ መቀየስ እንዲሁ ሊሆን ይችላል። ችግሩ የጤና መታወክ ከሆነ ጤናችን ያለበትን ሁኔታ በሚገባ አውቀን ወደ ጤንነት ለመምጣት የሚያስፈልገን ምን እንደሆነ ማወቅም ማለት ነው። በችግር ውስጥ እንዲሁ በጭንቀት ከመኖር ችግሩን በሚገባ ከተረዳን በኋላ ችግሩን ልንፈታ የምንችልበትን መንገድ መቀየስ የችግር መፋቸው ዋናው ቁልፍ ነው።
3. የችግር መፍቻ ዕቅድ ማውጣት፡- መሆን እንደምንፈልገው እንዳንሆን ሆነን ተቸግረን የአዳኝ ያለህ በምንልበት ነገር ላይ ከችግሩ ጋር አብሮ ከመኖር መፍትሄ ፍለጋው ጤናማነት ነው። መፍትሄው ፍለጋው ውጤታማ የሚሆነው ችግሩን በማወቅ እና ችግሩን ለማወቅ የሚያስፈልገንን በማወቅ ብቻም ሳይሆን የችግር መፍቻ ዕቅድ በማውጣት ነው። ዕቅድ ማለት በጊዜ የተገደበ ዝርዝር የሚሠሩ ሥራዎች ያሉበት ነው።
እግዚአብሔር በፍጥረት ሥራ ውስጥ የመጀመሪያ ቀን የፈጠረውን በሁለተኛ እና በሦስተኛ ቀን ፍጥረት እየለየ ሲገልፀው በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ ውስጥ እናገኛለን። ዕቅድ ማለት እያንዳንዱ ሥራ ተሠርቶ ወደ ምናስበው ውጤት የሚያደርሰን ድልድይ መሆን አለበት።
ችግርን በማወቅ ውስጥ የተሠራ የችግር መፍቻ ዕቅድ ችግሩን ለመፍታት የሚረዳ ነው። ችግሩን ለመፍታት የሚያስፈልገንን በማወቅ ውስጥ የተሠራ ዕቅድ የመተግበር አቅሙ ትልቅ ነው።
የችግር መፍቻ ዕቅድን ማውጣት ችግሩን መፍታት እንደምንችል ማመናችንን እና ለተግባር እርምጃው ግማሽ መንገድ ያህል የመጣን መሆናችንን የሚያሳይም ነው። ዕቅድ ብቻውን ወደ ውጤት የሚያደርሰን አለመሆኑን ከተረዳን ዕቅድን ለመተግበር መነሳት የሚቀጥለው ቁልፍ ነው።
4. ዕቅድን በአዎንታዊ መንፈስና በፍፁም መሰጠት መተግበር፡- ከችግር ለመውጣት ማቀድ አስፈላጊ ቢሆንም ዕቅዱ ግን የሚተገበር ካልሆነ ለውጥ አያመጣም። ዕቅዱ በሚተገበርበት ጊዜ ማነቆ እንዳይገጥመው ገና ከጅማሬው በጥንቃቄ መታቀዱ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ወደ መተግበር ሲገባ በመሰጠትና በከፍተኛ ትጋት ሊሆን ይገባዋል፤ እንዲሁም በአዎንታዊ መንፈስ ውስጥ። ወደ መተግበር ስንገባ መመልከት ያለብን ችግሩን ሳይሆን ችግሩ ተፈቶ የምናየውን መልክ ነው።
ዴቪዲ ኮፕራይደር “ዕቅድን ስንተገብር የስኬትን ምንጭ እንጂ የውድቀትን ምንጭ ማየት የለብንም” እንዳሉት ማለት ነው። አዎንታዊነትን ሊጨምሩ ከማይችሉ ግንኙነቶች ሁሉ መታቀብ ተገቢነትም ይኖረዋል። መነሳሳትን ሊያቀዘቅዝ የሚችል ምክርም ሆነ ድምጽ መስማት በትግበራ ወቅት አስፈላጊ አይደሉም። መተግበር ጀምረሃልና ወደፊት እየተመለከትክ ተራመድ።
5. የዕቅድ አፈፃፀምን መገምገም፡- የታቀደው ዕቅድ ውስጥ ሊኖር የሚገባው የዕቅድ አፈፃፀሙን በተወሰነ የጊዜ እርቀት በመገምገም መጠነኛ ማስተካከያዎችን እንደ ሁኔታው ለማድረግ መፍቀድ አስፈላጊ ነው። ግምገማ ትምህርት መውሰጃ መንገድ ነው። ግምገማ ከትላንት ተምረን ለነገ ስንቅን መሰነቂያ እንጂ እራስንም ሆነ ሌሎችን የመውቀሻ መሣሪያ አይደለም። የሚወሰደው ትምህርት ለቀጣይ ጉዞ ግብዓት መሆን ያለበት ስለሆነ።
ችግርን ከምንጩ በመፍታት ውስጥ የምንሄድባቸው ሂደቶች እንደተጠበቁ ሆነው እሳቤ ውስጥ ሊገቡ የሚገባቸው ሦስት ቁልፍ ነጥቦች አሉ። እነርሱም በችግር አፈታት ውስጥ ሊኖረው የሚገባው ትልቅ ቦታ፣ ለህሊና ዳኝነት ተገዢ መሆን እና ችግርን ከምንጩ መፍታትን ባህል እያደረጉ የመጓዝን አስፈላጊነት።
ሰው በችግር አፈታት ውስጥ
የተጋጩ ሰዎችን ችግር መፍታት ሰላምን ለማውረድ ቢሆን፤ ትዳራችን እክል ገጥሞት የመፍትሄ መንገድ እየፈለግን ቢሆን፤ በትምህርታችን ሆነ በጤናችን ቢሆን፤ በማህበራዊ ህይወታችን ሆነ በቤተ-እምነታችን ውስጥ ባለ ጉዳይ ቢሆን ወዘተ ውስጥ ችግር መፍታትን ስንሄድ ሁሌም ማዕከላዊ ማድረግ ያለብን አንድ ዋና ጉዳይ – ሰው ነው! በችግር አፈታት ሂደቱ ውስጥ ሰውን ማከም ሰውን ማዳን ለሰው መፍትሄ መስጠት ላይ መድረስን ትልቁ ግብ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከእራሳችን ጀምሮ በችግር አፈታቱ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሊያመጣ የሚችል የችግር አፈታት መንገድን መሄድ አስፈላጊ ነው። ሰው በችግር አፈታት ውስጥ ትልቁ ቁምነገር ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዛሬም የሰውን ልጅ ደም እንደ ቀይ ብዕር ቀለም እየቆጠረ ነው።
ሰው እንዲህ የረከሰ ሆኖ በሚታይባት ሀገር ውስጥ ስንኖር የሰው ልጅ ዋጋው ቢዛባ ላይገርመን ይችል ይሆናል። ሰው በችግር አፈታት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ክቡሩ ሰው የትም፤ በየትም ሁኔታ ውስጥ የችግር አፈታቱ ማዕከል መሆን አለበት። አንዳንዴ የችግሩ መወሳሰብ ይህን ማሰብ እንዳንችል ሊያደርገን ይችላል።
ህሊና ታላቁ ዳኛ
ከንጉሣዊ ሥርዓት ወደ ወታደራዊ አገዛዝ ሀገራችን ስትመጣ በችኩልነት በተወሰኑ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ለሀገራቸው ብዙ የወጡና የወረዱ ግለሰቦች የሞተን ጽዋ ግራ ቀኝ በአግባቡ ባልታየበት ሁኔታ እንዲጎነጩ ተደርጎ ህሊና ቦታውን እንደሳተ እንደ ሀገር ምልክቱ ታየ።
ህሊናን ለማዳመጥ ፋታ ያጣ ትውልድ ቃታውን መሳብ የችግር መፍቻ መንገድ አድርጎ ጀምሮ እነሆ ከሃምሳ ዓመታት በኋላም በሀገራችን የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ እንዳንገባ የሚያደርጉ ክስተቶች ተከታተሉ። ከግለሰብ እስከ ሀገር ያሉ ችግሮች ሁሉ ሊፈቱ የሚችሉ እንዲሆኑ ህሊናን ማዳመጥና አንዱ በሌላው ቦታ ላይ መቀመጥ መቻሉ የተገባ ነው። መዳረሻውም ችግርን ከምንጩ የመፈታት ባህል ይሆናል።
ችግርን ከምንጩ የመፍታት ባህል
ባህል ያደረግናቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ቀጠሮን በ30 ደቂቃ ዘግይቶ መድረስ ባህል የሆነ ይመስላል። አብሮ መሥራት አለመቻልም እንዲሁ። በአሉታዊነት የሚጠቀሱ ባህሎታችን ማሻሻል የምንችለው አዎንታዊ ባህልን በመገንባት ነው። ችግርን የመፍታት አካሄዳችን አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ እንዳይሆን፤ ችግርን ከምንጩ መፍታትን እንድንለምድ ያስፈልጋልና እነሆ የዛሬ መልዕክታችን።
ጸሐፊና የእምነት ተናጋሪ የሆኑት መጋቢ ሪካ ዋረን ነገሮችን ከመሰረቱ ስለመፍታት ሲናገሩ “የፍቃዳችን ሃይል ለጊዜው የሚሆን ለውጥ ቢያመጣም ነገር ግን ችግርን ከምንጩ ስለማይፈታ ውስጣዊ ድባቴን ይፈጥራል።” ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013