የትግራይ ሕዝብ በህወሓት ጁንታ ምክንያት ከአራት አስርት ለሚበልጡ ዓመታት የተለያዩ ችግሮችን፤ ከችግሮቹ የመነጩ መከራና ስቃዮችን ተሸክሞ ኖሯል። በነዚህ ወቅቶች ለከፋ ድርቅ፣ ከድርቁ ለመነጨ ረሀብ ፤ ለጦርነት፣ ጦርነት ሊፈጥር ለሚችለው መከራና ስቃይ እንዲሁም ለሞትና ስደት ተዳርጓል። ለድህነት፣ ድህነት ለሚፈጥረው የከፋ ጉስቁልናና ጠባቂነት ተላልፎም ተሰጥቶ ቆይቷል።
በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን መጨረሻው የአምባገነኖችና የጁንታዎች መፈልፈያ ለሆነው የነፃነት ትግል ገብሯል። በበረሃ ትግሉም የመጀመሪዎቹ ዓመታት ስም ባልተሰጠው ትግራይን ከአስተሳሰቦች የማጥራት ዘመቻ ብዙ ተስፋ ያደረጋቸውን የአብራክ ክፋዮቹን አጥቷል። ምድሪቱ በነፃነት ትግል ስ ም የደም ምድር ሆናለች።
በዚህ የንጹሀን ደም ጉልበትና አቅም አግኝተው በድል እብሪትና በሴራ ትምክህት ወደ መሀል ሀገር የመጡት የጁንታው አመራሮች፤ ባለፉት 27 ዓመታት የስልጣን ዘመናቸው ምድሪቱን ከደም ምድርነት ወደ ጉስቁልና ምድርነት ቀይረዋታል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉን ነዋሪዎች ሕይወት ከእጅ ወደ አፍ እንዲሆን አድርገውታል፡፡
ሕዝቡን በነገር ሁሉ ጠባቂ በማድረግ የስልጣናቸው ማራዘሚያ አቅም እንዲሆን የሄዱበት እርቀት ለትግራይ ሕዝብ ክብር እንደሌላቸው፣ የክፋታቸው ጥግ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ በተግባር ያሳየ እንዲሁም ለቡድኑ ስልጣን አልፋና ኦሜጋ መሆኑን በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
በአንድ በኩል የትግራይ ሕዝብ ክፉ ቀንን የሚሻገርበት ጥሪት እንዳይኖረው በማድረግ፣ ሕዝቡ በየትኛውም ጊዜ ለክፉ ቀን የተጋለጠ እንዲሆን አድርገውታል። ችግር ኮሽ ባለ ቁጥር ችግሩ ሊፈጥርበት ከሚችለው መከራና ስቃይ እራሱን መታደግ በማይችልበት ቁመና ላይ እንዲሆን በአላማ ሰርተውበታል። በሌላ በኩል ደግሞ የሥርዓቱ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲመስል ለማድረግ ረጅም ርቀት ሄደዋል።
ጁንታው በትግራይ ሕዝብ ላይ የሰራው ክፋት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ዓይኑን አፍጥጦ የመጣበት ወቅት ነው። ቡድኑ ላለፉት 27 ዓመታት ያለ ከልካይ የሀገርና የሕዝብ ሀብት ሲዘርፍ ቆይቷል። ግለሰቦችን በአንድ ምሽት ሚሊየነር የማድረግ አቅምና ብቃት ፈጥሮ የቆየባት ሀገር ነች።
ድንገት ብቅ ያሉ ግለሰቦች አደባባይ ሞልተው ለያዥ ለገላጋይ ባስቸገሩበት፤ ልደት ባንኮክ፣ ክርስትና ዱባይ፣ የጫጉላ ሽርሽር ፓሪስ የሚያደርጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከመፍጠር አልፎ ማህበራዊ እውቅና እስኪያገኙ ድረስ የሄደ የፖለቲካ ሥርዓት ‹‹ታግዬለታለሁ፣ እወክለዋለሁ›› የሚለው የማህበረሰብ ክፍል ግን ጥቂት ክፉ ቀናትን የሚሻገርበት ጥሪት ባለቤት እንኳ መሆን አልቻለም።
በስልጣን ዘመኑ ‹‹ይህን ያህል የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል፤ የሕዝባችን ሕይወት በዚህ ደረጃ ተለውጧል …›› ሲል የነበረው ይህ ቡድን፤ ሲያወራውና ሲያስወራው የኖረው የኢኮኖሚ እድገት ትርክት በዘመኑ ከፈጠራቸው የሴራ ትርክቶች የከፋ ስለመሆኑም አሁን በትግራይ ክልል የሚታየው እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ዛሬ ግን ሁሉም የአደባባይ ምስጢር ነው። ብዙ እንዲነገርበት ያደረጉት የትግራይ ሕዝብ ባለፉት 27 ዓመታት ከቡድኑ አገዛዝ ጠብ ያለለት አንዳች ነገር እንደሌለ ከምንምና ከማንም ይልቅ ሕዝብ እየተናገረ ነው። ሕዝቡ ከሥርዓቱ ድህነትና ጉስቁልናን ብቻ ማትረፉ አሁናዊ ችግሮቹ ማሳያዎች ናቸው።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ከክልሉ ሕዝብ አንድ አራተኛ የሚሆነው በሴፍቲኔት ፕሮግራም የዕለት ጉርሱን ያገኝ የነበረ ነው። ይህ ደግሞ አእምሮ ላለው ለሚያስብ ጤነኛ ሰው ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት የሚቸግር አይደለም። ከዚህ ቁጥር ያልተናነሱ የክልሉ ነዋሪዎች ደግሞ የዕለት ጉርሳቸውን ተሯሩጠው ለመሸፈን የሚገደዱ ናቸው።
በእርሻ የተሰማራው የክልሉ ነዋሪ ክልሉ ለእርሻ ያለው አመችነት ጉዳይ ሲታሰብ፣ የእርሻ ሥራው የሚከናወንበት መንገድና ከዚህ የሚገኘው ምርት ምን ያህል ይሆናል የሚለው ሲገመት በርግጥም የትግራይ ሕዝብ ባለፉት 27 ዓመታት በምን ዓይነት ሕይወት ውስጥ እንዳለፈ ለመገመት አይከብድም፡፡
የሚከብደውና ለማሰብ የሚያስጨንቀው ነገር ይህ ቡድን በዚህ ዓይነት የሕይወት መንገድ ላይ ያለን ሕዝብ በመጨረሻው ሰዓት ሳይቀር ዕድሜውን ለማስረዘም እና የማይቀረውን ሞቱን ላለመሞት ሲል ሕዝቡን ወደ ጦርነት ለማስገባት የሄደበት መንገድ እንዲሁም ከሞተም በኋላም ርዝራዦቹ በዚህ ሕዝብ ስቃይና መከራ ለማትረፍ ዛሬም ሊሄዱበት የሚሞክሩት መንገድ ነው፤ ዛሬም በክፉ ቀናቶች ሊነግዱበት የመሞከራቸው እውነታ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 15/2013