ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት በአለማችን ከኢንዱስትሪ አብዮት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ መሆኑ ይታወቃል። በእኛ ሀገርም ዘመናዊ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ አንድ ክፍለ ዘመን እየተቃረበ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሃገራችን የሰዎችን ድካም ለመቀነስ እና የሃገሪቱን ማህበራዊ፤ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስራዎችን ለማሳለጥ በማሰብ መንግስታት የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ አይተናል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአጼ ሃይለስላሴ የተጀመረው የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ የትራንስፖርት አገልግሎት አሁን ላይ ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፉ ያደባባይን በጆሮ ነው። አሁን ላይም በከተማችን አሉ ከሚባሉ ለህዝብ አለኝታነታቸውን እሳያዩ ካሉ ድርጅቶች ግንባር ቀደሙን ስፍራ ይይዛል።
ይሁን እንጂ አገልግሎቱን የተሻለ ተደራሽ ለማድረግ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ሁለት ጥያቄዎችን ጠይቁልን በማለት ለአዲስ ዘመን የዝግጅት ክፍል አቅርበዋል። በዚህ መሰረት ለአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ሁለት ጥያቄዎችን አድርሰናል።
አንደኛው የአንበሳ አውቶቡስ ብዙ ጊዜ የሚጭነው ከመነሻ አካባቢ ያሉ ሰዎችን ነው። ስለሆነም መካከል ላይ የሚገኙ ዜጎች አገልግሎቱን ለማግኘት እየተቸገሩ ነው። እኛም ይህን ችግር እንዴት ተመለከታችሁት ስንል የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ቁጥጥር ዋና የስራ ሂደት ለሆኑት አቶ መላኩ ካሳየን ጠየቅናቸው።
በጥያቄውም መሰረት አቶ መላኩ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭም እስከ ኦሮሚያ ልዩ ዞኖችም ጭምር በመድረስ ለዜጎች አገልግሎት እየሰጠ ያለ ድርጅት መሆኑን አመላክተዋል። ይሁንና የአንበሳ አውቶቡስ ብዙን ጊዜ አገልግሎት የሚሰጠው ከመነሻ እና መድረሻ ላሉ ደንበኞች ነው።
ምክንያቱም በመነሻ አካባቢ ስለሚሞላ መካከል ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሰጠው ግልጋሎት ውስን እንዲሆን አድርጎታል። ይሁን እንጂ ይህን ችግር ድርጅቱ ስለሚገነዘብ ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አቶ መላኩ አመላክተዋል።
ለአብነት ያህል ከፒያሳ የሚነሱ ሃያ አውቶቡሶችን በመመደብ በወንበር ልክ ብቻ በመጫን የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ እና ከመካከል ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ አውቶቡሶች እየተመደቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አቶ መላኩ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአውቶቡሶችን ቁጥር በመጨመር ምልልሱን በመጨመር እና የአውቶቡስ የመጠበቂያ ጊዜውን በማሳጠር አውቶቡሶች ከመነሻቸው ብቻ የተወሰነ ሰው ብቻ በማንሳት መካከል ላይ ያለውንም ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አቶ መላኩ አመላክተዋል። ነገር ግን አሁን በኮቪድ 19 ምክንያት መነሻ ላይ ያለውን ህዝብ በሙሉ ማነሳት ስላልቻለ መካከል ላይ ይሰጥ የነበረው አገልግሎት በተወሰነ መልኩ ለተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ጠቁመዋል።
ሌላው የተባለውን ችግር ለመቅረፍ አንድ አውቶቡስ የጫነውን እያራገፈ ከመነሻው ሳይጭን በመነሳት መካከል ላይ ያለውን ህዝብ እንዲጭን እያደርግን ነበር። በዚህ ጊዜ ደግሞ ያጋጠመው ችግር መካከል ቦታዎች ላይ ያለው የአገልግሎት ተጠቃሚ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ነበር።
ይህ ደግሞ ድርጅቱን ለኪሳራ ይዳርገዋል ሲሉ አቶ መላኩ አመላክተዋል። የሆነው ሆኖ ብዙ ህዝብ ያለባቸውን አካባቢዎች እያጠናን እና ህዝቡ በሚሰጠው አስተያየት መሰረትም ችግሮችን በቅርቡ እናሻሽለዋለን ብለን እናስባለን ሲሉ አቶ መላኩ ተናግረዋል።
ሌላው ህዝብ ለአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ጠይቁልን ያለው የአንበሳ ትኬት ቀድሞ ቢቆረጥ አውቶቡሱ ሲመጣ ለሚፈጠሩ አላስፈላጊ ውጣውረዶች ከመዳረግ እንድን ነበር። ስለዚህ ይህ ቢታሰብበት የሚል ጥያቄ ቀርቦልናል። በዚህም መሰረት የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የብዙሃን ትራንስፖርት ቁጥጥር ዋና ስራ ሂደት የሆኑት አቶ መላኩ ካሳየ ጥያቄውን አደረሱን።
አቶ መላኩ እንደሚሉት መገናኛ አካባቢ ቀድሞ ትኬት በመቁረጥ የተሳፋሪውን ሰዓት የሚቆጥብ እና ተሳፋሪውን ላላስፈላጊ እንግልት እንዳይዳረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ይህንን ነገር ፒያሳ ላይ ሞክረነው ነበር። ነገር ግን አውቶቡስ ሳይመጣ ሁሉም ሰው ቆርጦ እንዲቆይ ሲደረግ አንድ ችግር እንዳጋጠማቸው አቶ መኮንን አመላክተዋል።
አንድ አውቶቡስ የራሱ የመጫን ልክ አለው የሚሉት አቶ መኮንን፤ ከኮቪድ በፊት የአንድ አውቶቡስ መጫን ልክ አንደኛው 70 ሰው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ 86 ሰው ነበር። ይሁን እንጂ አሁን በኮቪድ ምክንያት የመጫን ልኩ ተቀንሶ 55 እና 65 ሰው ብቻ ነው የሚጫነው። ፒያሳ አካባቢ ያሉ ተገልጋዮች ቀድመው ትኬት ከቆረጡ በኋላ ወንበር ከሞላ አልገባም ይላሉ። ወንበር ከሞላ የማይሄዱ ከሆነ ደግሞ ድርጅቱ ለኪሳራ ይጋለጣል። ስለሆነም ፒያሳ ላይ ቀድመን ትኬት የመቁረጥ ስራውን አቋረጥነው ሲሉ አቶ መላኩ ይናገራሉ።
ነገር ግን መገናኛ አካባቢ በተለይም መስመር ቁጥር 82 ላይ ረጃጅሞች አውቶቡሶች ስላሉ አንድ ትኬተር ለሁሉም ሰው ይቆርጥ እና ሰዎችም በተቆረጠላቸው ትኬት መሰረት አውቶቡሱ መያዝ እስከሚችለው ድረስ ለመሳፈር ፈቃደኛ ናቸው። ይህን ችግር ለመቅረፍ ሁለት ነገሮችን እየሰራን ነው።
አንደኛው ከአለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ኤቲስ እና ኤቲሲ ቴክኖሎጂ ደቨሎፕ እየተደረገ ነው ። ይህን ለማድረግ ጨረታዎች ወጥተው የእቃ ግዢዎች ለማስኬድ ስራ ላይ ነን። እነዚህ እቃ ግዢዎች ሲመጡ አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሮኒክ ይሆናሉ። በዚህም የአውቶቡሶችን አገልግሎት በማዘመን የቅድሚያ ትኬት ሽያጭ ችግር መቅረፍ ይቻላል።
ሁለተኛው ደግሞ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እየተከናወነ ነው የሚሉት አቶ መኮንን፤ ለምሳሌ ሜክሲኮ፣ ቱሉዲምቱ ፣ ወዘተ አካባቢዎች” የህዝብ ክንፍ አባላት” የሚባሉ አካላት ተመስርተዋል። እነዚህ አካላት ከተጠቃሚው ህብረተሰብ መካከል ራሱ ህዝቡ መርጦ የወከላቸው እና እኛ ደግሞ መታወቂያ ሰጥተናቸው ህዝቡን የሚያስተባብሩ ፣ ሰልፍ የሚያሲዙ፣ ትኬት እንዲቆርጥ የሚያደርጉ አካላት ናቸው። ይህንንም ተሞክሮ ለማስፋፋት እና በህዝብ የተጠየቀውን ችግር ለመቅረፍ እየሰሩ መሆኑን አቶ መላኩ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የመገናኛ አካባቢን ቀድሞ ትኬት በመቁረጥ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀው ፤በሌላውም አካባቢ የሚገኝ ህብረተሰብ አሁን ያለውን ትራንስፖርት ችግር አይቶ ራሱ ሰልፍ ይዞ አገልግሎቱን እንዲጠቀም ጥሪ አስተላልፈዋል።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013