ምህረት ሞገስ
ከዋናው የአስፓልት መንገድ ገባ ብሎ አንድ ፈርጣማና ጎረምሳ ወንድ እና አንዲት ሴት ልጅ ቆመው ይጨቃጨቃሉ። ወንድየው ልጅቷን አንገቷን አንቆ በቀኝ እግሩ ግራ እግሯን በካልቾ ሲመታት በጀርባዋ የኮብል ስቶን መንገዱ ላይ ተዘረረች። ይህን የተመለከተ መንገደኛ ወጣት ‹‹እንዴት ሴት ልጅን በጠረባ መትተህ ትጥላለህ?›› ብሎ ተማቺውን ጎረምሳ በመሀል ገብቶ ይይዘዋል።
‹‹በገዛ ሚስቴ ምን አገባህ?›› ደብዳቢው መልስ ይሰጣል። የአገላጋይ ጓደኛ ‹‹ሚስትህም ብትሆን ከአሁን በኋላ ከነካሃት ፖሊስ እጠራለሁ›› ይለዋል። ደብዳቢው ለጊዜው ከገላጋዮቹ ጋር የነበረውን የቃል ምልልስ ትቶ ስልክ መደወል ይጀምራል።
ደውሎ መልዕክቱን ካስተላለፈ በኋላ በድጋሚ ልጅቷን ሲመታ መጯጯህ ይጀመራል።በአካባቢው ያሉና የሚያልፉ ሰዎች ሲሰባሰቡ ደብዳቢው ‹‹ፖሊስ ነኝ›› ብሎ መታወቂያ ያወጣል። በዛው ፍጥነት የአዲስ አበባ ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች መሳሪያ እና ዱላ ይዘው ቦታው ድረስ ከተፍ ይላሉ።
በፍጥነት ለባልደረባቸው የደረሱት ፖሊሶች የነበረውን ሰው በዱላ በማባረር ለጓደኛቸው ድጋፍ ሆነው ‹‹ደርሰንልሃል›› ይላሉ። ሴቷን ሲደበድብ የነበረው ፖሊስ ‹‹ሴት እንዴት ትመታለህ›› ያሉትን ሁለት ወጣቶች ‹‹ያዙልኝ›› አለ። በዚህ አላበቃም ‹‹ሊዘርፉኝ ነበር›› ብሎ እንዲያዙ አዘዘ። ከስምንት ያላነሱት ፖሊሶች የመንደሩን ሰው ከበተኑ በኋላ መሳሪያ አቀባብለው ሁለቱን ወጣቶች ይዘው እያዋከቡ በቅርብ ወደ ሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው።
በፖሊስ ጣቢያው አስገብተው ‹‹ሚስትህም ብትሆን ለምን ትመታታለህ›› ብለው ሲገላግሉ የነበሩትን ወጣቶች በዱላ እየተቀባበሉ ይደበድቧቸዋል። የወጣቶቹ ቤተሰቦች ተንደርድረው ፖሊስ ጣቢያ ሲደርሱ ፖሊሶች ወጣቶቹን እየደበደቡ ነበር። በተለይ የአንደኛው ወጣት አባት ልጃቸው አይናቸው እያየ ያለጥፋቱ ሲደበደብ አይተው ከማዘንና ከመበሳጨት ውጭ ከዱላው ውርጅብኝ ሊያስመልጡት አልቻሉም።
ወደ ፖሊስ ጣቢያው የሚመጡ የወጣቶቹ ቤተሰብ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ፖሊሶቹ ፈሩ። ቤተሰብ ‹‹ፖሊስ ብትሆኑም ምንም ያላደረጉ ልጆቻችን መደብደብ አትችሉም›› እያሉ በአካባቢው ጩኸታቸውን አቀለጡት።
ጊዜው ከምሽቱ ሶስት ሰዓት አካባቢ ነበር። ቦታው ደግሞ ከጄነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ጀርባ ሲሆን፤ ቤተሰብ ‹‹ድርጊቱ በዕለት መዝገብ ይያዝ ክስ እንመሰርታለን›› አሉ። ግማሾቹ የተደብዳቢዎቹ ቤተሰቦች፤ የጣቢያው የዕለቱ ተረኞች በሙሉ ልጆቹን በመደብደባቸው ወደ ሌላ ፖሊስ ጣቢያ መሄድ አለብን አሉ። መንገድ ተጀመረ።
በመንገድ ላይ ልጃቸው ፊት ለፊታቸው ሲደበደብ ያዩት አባት የልጃቸው መደብደብ ውስጥ ውስጣቸውን እየበላቸው እየተጨቃጨቁ እና እየተነጫነጩ፤ መንገድ ላይ እየተጯጯሁ በተለምዶ ብርጭቆ ፋብሪካ አካባቢ ያለው ፖሊስ ጣቢያ ተደረሰ። የአንደኛው ተደብዳቢ ወጣት ወንድም ቀድሞ እዛ ደርሶ ነበር። ወንድሙ ተደብድቦ እያነከሰ ሲያየው ‹‹ፖሊስም ብትሆኑ ሰውን መምታት አትችሉም›› ሲል፤ ከአንደኛው ፖሊስ ጋር ተያያዘ።
አባት ቀድሞ አንደኛው ልጃቸው ሲደበደብ ቆመው አይተው፤ አሁን ሁለተኛው ልጅ ሲያዝ ‹‹ልጆቼን አትደብድቡ፤›› ብለው ጩኸታቸውን ሲያቀልጡት አንደኛው ፖሊስ እኝህ አባት ላይ በቦክስ መታቸው።አፋቸው አካባቢ ስለመታቸው የእርሳቸው ጥርስ ሲነቃነቅ የእርሱ እጅ ጣት ላይ መጠነኛ ጉዳት በመድረሱ መድማት ጀመረ።
በዚህ መሃል የነበረው መጯጯህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ አካባቢው በሰው ተከበበ። መሳሪያ የያዙ ፖሊሶች በሙሉ መሳሪያቸውን ለተኩስ አዘጋጁ። ‹‹እባካችሁ ተዉ›› ቢባሉም ሰሚ ጠፋ፤ አንደኛው ፖሊስ ቢለመንም አልሰማም ብሎ ወደ ሰማይ ተኮሰ። ሌሎቹ በስንት ልመና ተረጋግተው መሳሪያቸውን አወረዱ እንጂ ለምን ትመቱን አላችሁ ብለው የሚጠይቁ ወጣቶችን እግራቸውን በጥይት ምቷቸው ሲሉ የነበሩ ፖሊሶችም ነበሩ።
በዚህ ወቅት ነበር የጣቢያው አዛዥ በአጋጣሚ ለእራት ወጥተው ነበርና ወዲያው ከተፍ አሉ። ‹‹ ማን ነው ምንድን ነው?›› ሲሉ ተየቁ። ከዛኛው ፖሊስ ጣቢያ ‹‹ተደብድበናል›› ብለው የመጡትን ሰዎች ለይተው መሬት ላይ እንዲቀመጡ አዘዙ። ደብዳቢ ፖሊሶችም ‹‹ ወደ ጣቢያችሁ ሂዱ›› ተብለው ተሸኙ።
መጀመሪያ ሴቲቱን ሲመታ የነበረው ዩኒፎርም ያልለበሰ ፖሊስ ከነልጅቱ እንዲቆዩ ተደረጉ። መርማሪው የጉዳዩ መነሻ የነበሩትን ሴቷን ልጅ እና ሲደበድባት የነበረውን ፖሊስ የችግሩን መነሻ ጠየቁ። ፖሊሱ ‹‹ 24ሺህ ብር ተዘርፌያለሁ፤ ሞባይሌም ተወስዶብኛል።›› አለ።
ልጅቷንም ብቻዋን ጠርተው ጠየቁ ‹‹ፖሊሱ አልደበደበኝም›› ብላ ካደች። ነገር ግን መርማሪው ነገሩን ለማወቅ አልተቸገረም የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ተዘርፌያለሁ የተባለው ውሸት መሆኑን አረጋገጡ። የግጭቱን መነሻም መለየት ቻሉ።
‹‹ ወጣቶችንና የተወሰኑ ቤተሰቦችን የደበደቡ ደብዳቢ ፖሊሶችን ተጠያቂ እናደርጋለን›› እንዲሁም ጉዳዩ እስኪጣራ ድረስ ወጣቶቹም ማረፊያ ቤት ይቆያሉ። የሚል ምለሽ ሰጡ።ይህም ልጆቻቸው ያለ ጥፋታቸው በፖሊስ መደብደባቸው ሳያንስ ማረፊያ ቤት ይቆያሉ የሚለው ሀሰብ ላይ አልተስማሙም።
ቤተሰብ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ ሲከራከሩ ቢቆዩም፤ ልጆቹ ብቻ ሳይሆኑ አባትም ሳይቀሩ ማረፊያ ቤት እንዲያድሩ ተወሰነ። በመጨረሻ ቤተሰብ ‹‹ፖሊስ በፖሊስ ላይ ክስ አይመሰርትም፤ ቢመሰርትም ትርፉ መጉላላት እንጂ ፍትህ አይገኝም›› በሚል በሽምግልና ጉዳዩ እንዲያልቅ በመስማማት ጉዳዩ በዚሁ ተቋጨ።
ይህ በምሳሌነት የተጠቀሰ አጋጣሚ ቢሆንም፤ ከፖሊስ ድብደባ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ቅሬታዎች እየተሰሙ ናቸው። መኪና አስቁመው መንጃ ፍቃድ ጠይቀው መንጃ ፈቃድ አልያዝኩም የሚለውን የሚደበድቡ፤ ፍተሻ በሚል ስም የሚዘርፉ አንዳንድ ፖሊሶች መኖራቸው ይገለፃል። እርግጥ ህግ አስፈፃሚው ፖሊስ መብቱ እስከምን ድረስ ነው? ፖሊስ የመደብደብ መብት አለው ወይ? አሁን ላይ ይህ በስፋት እንደሚስተዋል መረጃው አለ? በማለት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ጠይቀናል።
ኮማንደር ፋሲካ እንደሚገልፁት፤ የአንድ መንግስት የመጀመሪያ ተልዕኮ ህግ ማስከበር እና ሰላም ማስፈን እንዲሁም የዜጎችን(የነዋሪዎችን) ደህንነትን ማረጋገጥ ነው። የእዚህ ተልዕኮ አንዱ ፈፃሚ ደግሞ ፖሊስ ነው። በዚህ መሰረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ለህገመንግስቱ በመታመን ፖሊሳዊ ተልዕኮውን ይወጣል። ህግ ያስከብራል። ህገ ወጥነትን ይከላከላል። ህግ የጣሱ ሰዎች ካሉ እንዲከሰሱ ያደርጋል።
‹‹ፖሊስም ሆነ ማንኛውም አካል በሰዎች ላይ ዱላ መሰንዘሩ አግባብ ነው›› ማለት አይቻልም። ነገር ግን ዱላ የሚሰነዘርበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ደግሞ መረሳት የለበትም በማለት፤ በምሳሌነት ብዙውን ጊዜ በወንጀል የሚሳተፉ ሰዎች ከዱላ በላይ ጦር መሳሪያ ይዘው ከፖሊሱ ትጥቅ በላይ መሳሪያ ይዘው ወንጀል ሊፈፅሙ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ፖሊስ ተመጣጣኝ እርምጃ የመውሰድ ስልጣን አለው። ወንጀል ፈፃሚው የሚተኩስ ከሆነ ፖሊሱ ቀድሞ ሊተኩስ እና ሌሎች ሰዎች ላይ አደጋ እንዳይደርስ የማድረግ ስልጣን እንዳለው ይናገራሉ።
እንደኮማንደር ፋሲካ ገለፃ፤ ከዚህ ውጪ ህግን የማስከበር ስራ ላይ የተሰማራ የፖሊስ አባል ህጋዊ በሆነ አግባብ ህግን ያስከብራል። እንዲሁ በሰዎች ላይ ዱላ መሰንዘር አይችልም። ነገር ግን በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው አደንዛዥ ነገር ተጠቅመው ወንጀል ለመፈፀም የሚነሳሱ ሰዎች ከፖሊስ ጋር የሚጋጩ እና ግልፍተኛ ሆነው መሳሪያ የያዘ ፖሊስን ‹‹ና ምታኝ ›› የሚሉ አሉ። ይህ በአደባባይ የሚታይ ነው ካሉ በኋላ፤ ፖሊስ ሰላማዊ የሆነ ሰው ምንም አይነት ወንጀል ሳይፈፅም እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ የሃይል እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ፖሊሱ የሚጠየቅበት ሥርዓት መኖሩንም ያብራራሉ።
በኮሚሽኑ ጥሩ የሆነ የዲስፕሊን መመሪያ አለው። በመመሪያው መሰረት ፖሊሱ አጥፍቶ ከተገኘ በጥፋቱ መጠን አቤት የሚል ሰው ከቀረበ አልያም አቤት ባይ ባይኖርም በጋራ አብሮ ህግ ሲያስከብር የነበረ ፖሊስ ‹‹ያለአግባብ ጥቃት አድርሷል›› ብሎ ከጠቆመ የፖሊሱ ሥራ ተጣርቶ የሚቀጣበት ራሱን የቻለ አሰራር መኖሩን ይናገራሉ።
ለኮሚሽኑ እስካሁን ‹‹በየመንገዱ ከሚደረጉ ፍተሻዎች ጋር ተያይዞ ድብደባ እና የተለያዩ ተግባራት ይፈፀሙብናል ብለው ቅሬታ ያቀረቡ ሰዎች የሉም።›› የሚሉት ኮማንደር ፋሲካ፤ እነርሱ ጋር የደረሰ ጥቆማ ባይኖርም ወደፊትም ቢሆን፤ በአሥሩም ክፍለ ከተማ በቅርብ ርቀት ፖሊስን የሚመሩ ሃላፊዎች በመኖራቸው ‹‹ የሃይል ተግባር ተፈፅሟል።
በፖሊስ ህግ በመተላለፍ ድብደባ ደርሶብናል፤ ወይም ሌላ ወንጀል ተፈፅሞብኛል›› የሚሉ ሰዎች ካሉ፤ አቤቱታ ለቅርብ ሃላፊ በማቅረብ ምላሽ ማግኘት የሚችሉ መሆኑን እና በቅርብ ምላሽ ባይገኝ እንኳ ተጎድቻለሁ የሚል አካል በየደረጃው የመጠየቅ መብት አለው በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013