በዛሬው የእሁድ ገፅ የስፖርት ዓምዳችን አፍሪካ ውስጥ በቀዳሚነት መነጋገሪያ ስለሆኑ የሳምንቱ የእግር ኳስ ዜናዎች ዳሰሳ ለማድረግ ወደናል። በተለይ በዚህ ሳምንት በዋናነት ከእግር ኳሳዊ አጀንዳዎች መካከል የብዙኃኑን ቀልብ ይዞ የነበረው የቀድሞው የሰንደርላንድ ተከላካይ የተቃርኑ ቡድንን ተጫዋች አፍንጫ በመስበር ለስድስት ጨዋታ ቅጣት መዳረጉን የሚገልፀው ነበር።
ሴኔጋል
ሴኔጋላዊው የ30 ዓመት ኢንተርናሽናል ተከላካይ ፓፒ ጂሎባጂ አርጀንቲናዊውን የ31 ዓመት አጥቂ ፓብ ሎ ቻቫሪያ ሰርን በመስበሩ የስድስት ጨዋታ ቅጣት ተጥሎበታል። ጉዳቱም ከፍተኛ በመሆኑ ፓብሎ በህክምና የአፍንጫ ቀዶ ጥገና ባሳለፍነው ማክሰኞ እለት ተደርጎለታል።
በፈረንሳይ የመጀመሪያ ሊግ ውስጥ በጊንጋምፕ ክለብ በስድስት ወር ውል ስምምነት የፈረመው ፓፒ ለክለቡ ቅጣቱ ከመጣሉ በፊት ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ነበር ያደረገው። የተጣለበት የስድስት ጨዋታ ቅጣት ከክለቡ ጋር ካለው የቆይታ ስምምነት አንፃር ከፍተኛ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል። ተጫዋቹ ባሳለፍነው ክረምት ከሰንደርላንድ ጋር ያለውን የኮንትራት ስምምነት አቋርጧል። የነበረውን ውል ለማራዘም ፍላጎት ቢኖረውም የፊትነስ ፈተና በመውደቁ ኮንትራቱ ሊቋረጥ እንደቻለ ለማወቅ ተችሏል።
በአፍንጫ መሰበር ምክንያት ለቀዶ ጥገና የተዳረገው ፓብ ሎ ቻቫሪያ ከጉዳቱ በኋላ በቲውተር ገፁ ላይ ባሰፈረው ምልክት ህክምናው በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን እና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ገልፆ፤ መልካም ዕድል ለተመኙለት ወዳጆቹ እና የስፖርት አፍቃሪዎች ምስጋናውን አቅርቧል።
ሌላኛው አፍሪካን በተለይም ደግሞ ምዕራባዊቷን ሴኔጋልን የሚመለከተው የእግር ኳስ ዜና ወደ እንግሊዙ ኤቨርተን ክለብ ይወስደናል። በዚህ ክለብ እና በፓሪሰን ዤርመን መካከል በተፈጠረው ትልቅ የዝውውር ድርድር ላይ ዋንኛ ትኩረት ሆኖ የሰነበተው ደግሞ የ29 ዓመቱ ኢድሪስ ጉዬ ነበር። ይህን ተጫዋች በክረምቱ ወር ዝውውር በጥብቅ ለማስፈረም ፍላጎት የነበራቸው የፈረንሳይ ሻምፒዮናዎቹ ፓሪሶች የ2ነጥብ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ጥያቄያቸው ውድቅ ሆኗል። አይቬሪ ኮስት
በዚህ ሳምንት አነጋጋሪ ከነበሩ የአፍሪካ ዜናዎች መካከል የአይቬሪ ኮስታዊው የዊልፍሬድ ቦኔ የዝውውር ዜና ነው። ይህ የአጥቂ መስመር ተጫዋች እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በሚያዘልቅ የውሰት ስምምነት የኳታሩን ክለብ አል አረቢያን ተቀላቅሏል።
ቦኔ የስዋንሴ ሲቲ ከፍተኛው የደሞዝ ተከፋይ ሲሆን ይህን ደሞዙን ከፍሎ በውሰት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የሚወስድ ክለብ ሲፈልግ ቆይቶ በመጨረሻ አል አረቢያ ፍላጎቱን በማሳየቱ ምክንያት ተጫዋቹን በውሰት ሊያዘዋውረው ችሏል ። ከስዋንሴ ጋር ያለው ኮንትራትም በዚህ ዓመት መጨረሻ የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ ቀሪዎቹን ወራቶች በኳታሯ ዶሃ ከተማ መቀመጫውን ካደረገው ክለብ ጋር የሚያሳልፍ ይሆናል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ከማንችስተር ሲቲ ክለብ በ12 ሚሊዮን ፓውንድ የተዘዋወረው ቦኔ በግርሃም ፖተር በሚመራው ስዋንሴ ሲቲ ሰባት ጨዋታዎችን ብቻ ነበር ያደረገው። ላለፉት አስር ወራትም በጉልበቱ ላይ በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት ምክንያት ከህመሙ ለማገገም ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ክለቡ ከፍተኛ ደሞዝ እየከፈለው ተገቢውን ግልጋሎት ከተጫዋቹ ሳያገኝም ቆይቷል። ክለቡ ተጫዋቹ በጉዳት ምክንያት ከሜዳ ለብዙ ወራት መራቁ እና ያለው ብቃት ወደ ቀድሞው ባለመመለሱ በውሰት ለሌላ ክለብ መስጠትን እንደ አማራጭ ወስዶታል። ቦኔ በሳምንት 120 ሺ ፓውንድ ያገኝ ነበር። አሁን ላይ ሁለቱ ክለቦች በተስማሙበት ውል መሰረት የተጫዋቹን ደሞዝ አል አረቢያ የሚከፍል ይሆናል።
በሌላ የአይቬሪኮስት የሳምንቱ አነጋጋሪ የእግር ኳስ ወሬ የነበረው በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በክሪስታል ፓላስ ክለብ ውስጥ የሚጫወተው የዊልፍሬድ ዘሃ ጉዳይ ነበር። ተጫዋቹ በመሃል ዳኛው ላይ በሳየው ያልተገባ የእጅ እንቅስቃሴ በቀይ ካርድ የወጣ ሲሆን ከጨዋታው በኋላ ደግሞ የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ቅጣት የሚያስከትልበትን ክስ መስርቶበታል። ቅጣቱ ወደፊት ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ባሳለፍነው ሳምንት በነጥብ ጨዋታ ሳውዛምፕተንን ከክሪስታል ፓላስ ያገናኘው ጨዋታ ለተጫዋቹ ጥሩ እድል ይዞለት አልመጣም ነበር። ከሳውዝ ሃምፕተኑ ጃምስ ዋርት ፕራውስ ጋር በተፈጠረ አምባጓሮ የመሃል ዳኛው አንድሬ ማሪነር የቀይ ካርድ የመዘዙበት ዘሃ ከክስተቱ በኋላ ዳኛው ላይ በመዘባበቱ ከሜዳ የሚያስወጣውን ቀይ ካርድ አስመዝዞበታል።
ዘሃ ከጫወታ በኋላ በድርጊቱ እጅግ መፀፀቱን ገልፆ ክለቡን እና ደጋፊዎቹን ይቅርታ እንዲያደርጉለት ተማፅኗል። ‹‹በሁኔታው እጅግ አፍሬያለሁ። ክለቤን ዋጋ ያስከፈለ ድርጊት ፈፀሜያለሁ ያንን ማድረግ አልነበረብኝም። ሁኔታው ባይፈጠር ኖሮ ሙሉ ሦስት ነጥብ ከባላጋራችን ነጥቀን የምንወጣበት እድል ሊፈጠር ይችል ነበር›› በማለት ይህን ድርጊት በድጋሚ እንደማይፈፅም ቃል ገብቷል። ከሁኔታው እንደሚማርበትም ለጋዜጠኞች በሰጠው አስተያየት ተናግሯል።
ዘሃ በጨዋታው አንድ ጎል በማስቆጠር ክሪስታል ፓላስን መሪ ያደረገ ቢሆንም፤ ዋርድ ፕራውሰር ሳውዛምፕተኖችን አቻ ያደረገች ጎል በማስቆጠሩ ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ የግድ ብሏል። ዘሃ ለክለቡ ግብ ሲያስቆጥር ከመስከረም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሆንም የቀይ ካርዱን በማግኘቱ የፈጠረውን የደስታ እድል አበላሽቶት ወጥቷል።
የክሪስታል ፓላሱ አሰልጣኝ ሮይ ሁድሰን ዘሃ በሰራው ጥፋት ዙሪያ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ተጫዋቹን እረዳዋለሁ። ኳስ ከእግሩ ስር ተገፍቶ ሲቀማ ተስፋ ሊቆርጥ እና ጥፋት ሊሰራ ይችላል። ሆኖም ግን ለዳኛው ያሳየው የልተገባ ባህሪ ይቅር ሊባል የማይችል እና እርሱም በፍፁም ሊያደርገው የማይገባ ነበር›› በማለት ለድርጊቱ ምላሽ ሰጥተዋል።
በሌላ ተጨማሪ ዜና አይቬሪኮስት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት መስማማቷን ቢቢሲ አፍሪካ የስፖርት ድረ ገፅ አስታውቋል። አገሪቷ በ2021 የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት እድሉ የነበራት ቢሆንም ከፕሮግራም ሽግሽግ ጋር በተያያዘ ለሁለት ዓመት እንድትታገስ ከካፍ ጥያቄ ቀርቦላታል። በሁኔታው ላለመስማማት ፍላጎት አሳይታ የነበረው አገሪቷ በመጨረሻ ከካፍ ጋር በተደረገ ድርድር ስምምነት ላይ ደርሳለች።
ካሜሮን ዘንድሮ የሚደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት እድል ተሰጥቷት በዝግጅት በጊዜ አለመጠናቀቅ ምክንያት ተነጥቃ ግብፅ ኃላፊነቱን ተረክባለች። በዚህ ምክንያት ካሜሮን የ2021 ዝግጅቱን እንድታደርግ ከካፍ በድጋሚ እድሉ ተሰጥቷታል። ካሜሮን የወሰደችውን እድል ጊኒ ለማዘጋጀት አስባ የነበረ ቢሆንም ፕሮግራሙ በመፋለሱ ምክንያት የ2025ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ታሰናዳለች።
ናይጄሪያ
የባርሴሎና ክለብ የሴቶች ዋናው ቡድን አንድ እንስት የፊት መስመር አጥቂ በውሰት አስፈርሟል። ይህቺ እንስት ናይጄሪያዊቷ አሲስታ ኦሶላዋ ኦሾላ ስትሆን በቻይና ቻምፒዮን ሺፕ በሚሳተፈው ጃሊያል ኳንጂያን ክለብ ስትጫወት ነበር። የውሰት ውሉን ተጠናቆ በዓለማችን ላይ ትልቅ ዝና ባለው የባርሴሎና ክለብ ፈርማለች። የቻይና የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮን ሺፕ መጠናቀቁን ተከትሎ ባለው እረፍት ምክንያት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ከክለቡ ጋር የምትቆይ ይሆናል።
በቢቢሲ የዓመቱ ምርጥ አፍሪካዊ ኮኮብ ተብላ ከዚህ ቀደም የተመረጠችው ኦሶላዊ በቀጣይ በነሐሴ ወር በፈረንሳይ ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል አንደኛዋ ነች። የቻይናውን ጃሊያል ክለብ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ነበር የተቀላቀለችው። ከአገሯ ናይጄሪያ ጋር በመሆንም ሦስት የአፍሪካ ዋንጫን ማንሳት ችላለች። ባሳለፍነው ዓመት ጋና ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ 3 ጎሎችን በማስቆጠር አገሯ ናይጄሪያ ለዘጠነኛ ጊዜ ዋንጫውን እንድታነሳ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክታለች።
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ዳግም ከበደ