አሌክሳንደር ጎልዲንስኪ ይባላል፤ ነዋሪነቱ አሜሪካ ኒው ጀርዚ በተባለች ከተማ ነው፡፡ ታድያ በቀደም ምን እንዳሳሰበው አይታወቅም አንድ ተንኮል ያስባል፡፡ ይህን ተንኮሉንና አስከትሎ ያመጣበትን መዘዝ የዘገበው ደግሞ ዩፒአይ የተሰኘ ድረገጽ ነው፡፡
የሆነው እንዲህ ነው፤ በጥንት ዘመን ስማቸው በጦር የናኘ ሰዎችን ስም የያዘው አሌክሳንደር፤ በመሥሪያ ቤቱ መተላለፊያ መንገድ ላይ በጀርባው ይወድቃል፡፡ አወዳደቁ እንዴትም ሆነ እንዴት በእድሜም ተለቅ ያለ የሃምሳ ዓመት አካባቢ ጎልማሳ ስለሆነ፤ ያስደነግጣል። ነገሩን ያዩ የመሥሪያ ቤቱ ሰዎች ደርሰው አንቡላንስ ይጠራሉ፡፡ ተንከባክበውም ሆስፒታል ያደርሱታል፡፡
በአካባቢው በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና ያገኛል፡፡ የወደቀው መሥሪያ ቤቱ ውስጥ በመሆኑ የህክምናውን ወጪና ተጨማሪ የኢንሹራንስ ክፍያ ይገባሃል ይባላል፡፡ የኢንሹራንስ ገንዘቧን ቅርጥፍ አድርጎ መሄድ። ‹‹በቃ! አለቀ፡፡›› ብሎ ነበር፤ ግን ታሪኩ አላለቀም፡፡ ለካ መሥሪያ ቤቱ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ የሚከታተልበት ካሜራ በየጥጋጥጉ ላይ አኑሯል፡፡
ካሜራው ታድያ አንድ እውነት አሳየ፡፡ ምን ያሳያል? አሌክሳንደር በረዶ መሬቱ ላይ ሲጥልና የጣለው በረዶ አውቆና ሆነ ብሎ ረግጦ እንደወደቀ ሰው ራሱን ሲያስተካክል። ነገሩ ከመሥሪያ ቤቱ ይወጣና ፖሊስ ጋር ይደርሳል። ፖሊስም አሌክሳንደርን በሀሰት በማታለልና ኢንሹራንስ ለማጭበርበር በመሞከር ጠየቀው፤ ተከሰሰም፡፡
አስቡት! አሌክሳንደር ወገቡ የተረፈ አይመስለኝም፤ እንደው ሆነ ብሎ ወደቀ መስሎ የታየ ቢሆንም፤ ሆስፒታል ሲደርስ የተጎዳው ነገር ካለ ሊፈታትሹ ሲያገላብጡት መጎሳቆሉ ይቀራል ብላችሁ ነው! እድሜውም ቀላል አይደለም። በዛ ላይ ከመከሰስና ወንጀለኛ ከመባልም አልዳነም፡፡ እንግዲህ የአገሬ ሰው ሁለት ያጣ የሚለው እንዲህ ያለውን ነው፡፡
የአገሬ ሰው ስል፤ እንዲህ ያለ ታሪክና ክስተት ስንሰማ ምን እንደምንል ልብ ብላችሁልኛል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ታሪክ መጀመሪያ አጭበርባሪው ያናድደናል፡፡ «አያፍርም እንዴ! በዚህ እድሜው?» እንባባላለን፡፡ ከዚህ ቀደም ስለገጠመን ተመሳሳይ ደፋርና አጭበርባሪ ሰው እንተርካለን፡፡ «ወይ ጊዜ!» እያልን ባለጉዳዩን የዘመን መተርጎሚያ እናደርገዋለን፡፡
መቼስ ደግ ነንና ደግሞ አንጨክንም! ቀጥለን አጭበርባሪው ሊያመልጥ ስለሚችልበት፤ ነገር ግን ስላልተጠቀመበት አጋጣሚ እናትታለን፡፡ «እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ አይያዝም ነበር» እንላለን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በዚህ ታሪክ፤ «ወይ አሌክሳንደር! ምን ሆኖ ነው ግን ካሜራ እንዳለ የረሳው? ተጋለጥ ሲለው ነው እንጂ ካሜራ የሌለበት ቦታ ጋር ሄዶ አያታልልም ነበር!» እንላለን፡፡ ለማንኛውም! አንዳንድ ሰው ራሱ በቋጠረው ራሱ ተሳስሮ ቁጭ ይላል፤ እናም የሌለውንም የነበረውንም ያጣል፡፡ ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ሊድያ ተስፋዬ