ጌትነት ምህረቴ
የዛሬን አያድርገውና ቀደምት አባቶቻችን የሚያደርጓቸው እርቆች፣ ህዝባዊ ውይይቶችና ማበረታቻዎች ፍሬ አፍርተው የህዝብን አብሮነት የሚያጠናክሩ፣ መተሳሰብን፣ መከባበርንና አንድነትን የሚያዳብሩ ሆኖው ቆይተዋል። ግጭቶችና መቃቃሮች ቢከሰቱም እንኳን በሰዎች ላይ የሚያደርሱት ጉዳቶች እምብዛም አይሆኑም ነበር። ጉዳቶች ቢደርሱም ወዲያው መፍትሄ ያገኛሉ። ችግሮችን የመፍታት ብልሃታቸው በፅኑ ይተገበራል።
ዛሬ ግን በተቀራኒው በየቦታው የሚታዩ ግጭቶች መፍትሄ አጥተው ሲደጋገሙ ይስተዋላል። በተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የመንግስት አመራሮች፣ የጸጥታ መዋቅሮች፣ ታዋቂ ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች በቦታው ያሉ አይመስልም። ዛሬ ዛሬ በፖለቲካ አመራሮች አማካኝነት በየቦታው የሚደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች፣ እርቆችና መሽላለሞች ሰላምን ሲያሰፍኑ ግጭትን ሲያስወግዱ አይታይም። ይልቁንስ የሚስተዋለው ሲያባብሱ ብቻ ነው።
አሁናዊ የግጭት ክስተቶችን ስናይና ስንሰማ በየቀበሌው በየወረዳው፣ በየዞኑና በየክልሉ ያሉ የፖለቲካ አመራሮቻችን ግጭትን የመፍታት አቅም ፈርጣማነት ‹‹ታምራዊ ነው›› ያስብላል። ምክንያቱም እኔ የሚያስደንቀኝ እነሱ ባሰፈኑልን ሰላም፤ እነሱ ባስቀርሉን ግጭት ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይልቅ የምናገኛቸው ስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው። አርሶ አደሩ ስንት የለፋበትን ሰብሉን ሊሰብስብ ሄዶ እዚያው ተገድሎ ይታያል።
ህጻናት ሲቦርቁ ከመመልከት ይልቅ በቀስት ተመትተው ሲሰቃዩ እናያለን። ቤቶች በጅምላ ይቃጠላሉ። ከብቶች ሜዳ ላይ ሳር ሲግጡ ሳይሆን፤ ተዘርፈው በየጎዳናው ሲነዱ ይስተዋላል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ንጹሃን አዛውቶች፣ ወጣቶች ፣ ህጻናት ከቀያቸው ይፈናቀላሉ። ይህ ሲታይ ጠንካራና ብርቱ ካባ የተሸለሙት ሰዎች፤ ግጭቱን ማስቆም ስላቃታቸው እና ስለተሳናቸው የተሸለሙት እኮ ነው ያስብላል።
‹‹ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም›› እንዲሉ ግጭቶች መከሰት የለባቸውም ማለት ባይቻልም መፍትሄ ሊያገኙ ግን ግድ ይላል። ሆኖም የእኛ አገር የፖለቲካ አመራሮች ህዝቡን ሰብስበው በየጊዜው የሚያደርጓቸው እርቆችና ውይይቶች ሰላምን እያመጡ ከተደጋጋሚ ግጭቶች እየታደጉን አይደሉም።
ይልቅስ ሰላምና ጸጥታን ማስጠበቅ ያቃታቸው አመራሮች በአደባባይ ካባ ይሸለማሉ፤ ይሞገሳሉ። ግጭት በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የህዝቦችን መልካም እሴት በመጠቀም ራስን ለአደጋ አጋልጦ ማስታረቅ፤ አጥፊውን መገሰጽ፤ ትብብርና ወንድማማችነትን የሚያስተምሩ ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች የውሃ ሽታ ሆነዋል። ህዝባቸውን ወገናቸውን ለመታደግ ማንኛውም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆኑና ቃል የገቡ ፖሊሶች ቃላቸውን ማክበር ተስኗቸዋል።
በዚህ ምክንያት በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ግጭቶች ፣ግድያዎች ይፈጸማሉ። ‹‹አንተም ተው አንተም ተው›› የሚሉ አስታራቂዎች እና አስተዳዳሪዎች አቅማቸው ከድቷቸዋል። ይልቁንስ የግጭት ንግድ ተጧጡፏል። በክልል፣ በዞንና በወረዳ አመራሮች መካከል ሴራው እየጦዘ እርስ በእርስ መወጋገዝ እየጨመረ ነው።
እነዚህ አመራሮች፣ ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች ‹‹ህዝባችንን እንደ ቅጠል ከመርገፍ የሚታደጉ ውይይቶችና እርቆች አድርገናል›› ቢሉም ውጤቱ ተቃራኒ ነው። ለምሳሌ በተለይ ታኅሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 10 ሰዓት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ የታጠቁ ኃይሎች፣ በነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳትና በከፈቱት ተኩስ በርካቶች ከመሞታቸውም በተጨማሪ፣ ብዙ ቤቶች መቃጠላቸውንና የተሰበሰበና በማሳ ላይ ያለ እህል መቃጠሉን እንዲሁም ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ መሰደዳቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገልጿል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ እስካሁን በተከሰቱ ግጭቶች ከ500 በላይ ንጹሀን ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባደረገው ክትትል አረጋግጧል።
የኢሰመኮ ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፤ በመተከልና በአካባቢው ያለው የሰላምና ደኅንነት ችግር ከአሳሳቢ በላይ ሆኗል። አሁን ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በሥጋት ላይ ያሉትንም የሚታደግ ፈጣን የፀጥታ መዋቅር ሊኖር ይገባል። ይኼንን ለማድረግ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኖ በመገኘቱ፣ ጠንካራ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሚጠይቅ የመፍትሄ ሀሳብ ጠቁመዋል።
በተመሳሳይ የኮንሶ ጉዳይም ሌላው መፍትሄ ያላገኘ ጉዳይ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው በተገኙበት ጭምር እርቅ ቢደረግም ግጭቱን ማስቆም አልተቻለም። በየጊዜው በሚያገረሽ ግጭት ሰዎች ይገደላሉ፤ ቤቶችና ንብረቶች ይቃጠላሉ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ታኅሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በደቡብ ክልል የኮንሶ ዞን ከኅዳር 1 እስከ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እንደገና ባገረሹ ተከታታይ ግጭቶች አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት መድረሱን አስታውቋል። 66 ያህል ሰዎች መገደላቸውንና 132 ሺህ 142 ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸውን ገልጿል። የአካባቢው ሰብዓዊ ቀውስ ዘላቂ ዕልባት ባለማግኘቱ እየተባባሰ በመሄዱ ዘላቂ መፍትሄ ያሻዋል ብሏል።
እንዲሁም ኢሰመኮ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የባለሞያ ቡድኖቹን ወደ 40 የክልሉ አካባቢዎች ልኮ ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የምርመራ ግኝቶች መሰረት፤ በኦሮሚያ ክልል የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ 500 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራ እና በመጥረቢያ ተጠቅመው ሰዎችን ደብድበዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል። ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማሰቃየት እና በማረድ ጭምር ሰዎችን ገድለዋል።
“የጠፋብህን በሬ ማግኘት ከፈለግህ ከሌባው ጋር አትፈልግ“ እንዲሉ ተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትባቸው አካባቢዎች አመራሮችን በየጊዜው እየፈተሹ ማስተካከልና የእርምት እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። ተጠያቂነት ማስፈንና ህጋዊ ርምጃ ወዲያውኑ መውሰድ ወሳኝ ጉዳይ ነው። አለበለዚያ ንጹሀን ዜጎች በየጊዜው ከቀያቸው መፈናቀላቸው አይቆምም። በየጢሻው ከመገደል አይድኑም፤ ከስቃይና ከጉዳት መታደግ አይቻልም።
ሌላው ተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትባቸው በዞኖች ስር በሚገኙ ሁሉም የቀበሌ ነዋሪዎች ጸጉረ ልውጥ ወይም ማንኛውንም የአካባቢውን ሰላም የሚያደፈርስ ክስተት ሆነ እንቅስቃሴ ስያጋጥም ለሚመለከተው የጸጥታ አካል በማሳወቅ ችግሩን ማስቀረት አልያም የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠርና መከላከል ይቻላል። የጸጥታው አካል ደግሞ በተደረገለት ጥቆማ መሰረት ሀላፊነቱን ሊወጣ ካልቻለ ተጠያቂ የሚሆንበትን አሰራር መፍጠር አስፈላጊና ግዴታም ነው። ይህን መተግበር ቢቻል ምንም አይነት ችግር አይፈጠረም ባይባልም ጉዳቱን ቀላል ማድረግ ይቻላል።
የእኛዎቹ አመራሮች ግን የቀበሌያቸውን እና የወረዳቸውን ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ ይልቅ ወደ ሌላ አካል መጠቆም ላይ ተክነውበታል። ችግሩን በማደፋፈን ደግሞ የሚያህላቸው የለም። የእዚህን ያህል ሩጫ ችግሩን ለማስቀረትም ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ ህዝባዊ ተቀባይነትና ድጋፍ መላበስ በቻሉ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ይልቅ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ግጭትን እንደ ሸቀጥ የሚቸረችሩ ትንሽ አይደሉም።
ለጊዚያዊነት ይመስላቸዋል እንጂ ከግጭት የሚገኘ ትርፍ የለም። ከትርፉ ይልቅ የኋላ ኋላ የሚስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም ሽናሻ ይሁን አማራ ፣ ኦሮሞ ይሁን ጉምዝ ንጹህን ሰዎች በማንነታቸው ብቻ ያለጥፋታቸው መገደል የለባቸው። ይህ ተደጋጋሚ ጥቃትና ግጭት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሊያወግዙት ይገባል። ለመፍሄውም ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል። ምክንያቱም የእኔ ቤት ሲንኳኳ ነገም የሌላው ቤት እንደሚንኳኳ መረዳትና መገንዘብ ያስፈልጋል።
የቀበሌ፣ የወረዳ፣ የዞኑ አመራሮችን እና የፖለቲካ አመራሮቻችን ያለጥፋታቸው፣ ያለ ሀጢያታቸው በማንነታቸው ብቻ እየሞተ ያለውን ህዝብ መታደግ ቀዳሚ አጀንዳቸው ሊሆን ይገባል። በተለይ በሚመሩት ክልል፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ያሉ አመራሮች ይህን ችግር መፍታት የማይችሉ ከሆነ ስልጣን ላይ ለአፍታም ቢሆን መቆየት የለባቸውም። ምክንያቱም የህዝብን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅና ህዝብን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ማስተዳደር ቀዳሚ ስራቸው በመሆኑ ነው።
ወደ ዋናው ጉዳይ ስመለስ ግን በተለይ ተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትባቸው በቀበሌ ፣በወረዳ፣ በዞንና በክልል ያሉ አመራሮች የንጹሃን ሞት እና መከራ ስቃይ ስደት የሚያሳስባቸው አይመስልም። ቁጭትና ጸጸት የሚሰማቸው አይደሉም። ምክንያቱም የሚያደርጓቸው ውይይቶችና የሚፈጸሙ እርቆች ግጭትን ሊያስቀሩ አልቻሉም። ይልቁንስ ግጭት ሊያስቆሙ ያልቻሉ አመራሮችን ካባ ይሸልማሉ፤ እውቅናን ያበረክታሉ።
ይህ የይስሙላ አካሄድ ለህዝቦች ሰላምና ደህንነት ሲባል መቆም አለበት። ነገ ተጠያቂነትን ፣ የህሊና ጸጸትን ይዞ እንደሚመጣ መገንዘብ ያሻል። ከግጭት ነጋዴው የጁንታ ቡድንም ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል።
ችግሮች ካሉ በግልጽ ተወያይቶና መተማመን ፈጥሮ በህዝቦች ላይ የሚደርስን እንግልት፣ ሞትና ስቃይ ማስወገድ ያስፈልጋል እንጂ የክልላቸውን ሰላምና ጸጥታ ማስጠበቅ ለተሳናቸው አመራሮች መሸለም፤ የአካባቢያቸውን ግጭት በዕርቅ መፍታት ላቃታቸው የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ዕውቅና መስጠት በየጢሻው ለሚሞቱ፣ ከቀያቸው ተፈናቅለው ለሚንገላቱና ረጅም ርቀት በእግራቸው በመጓዝ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው ለሚገኙ ንጹሀን ሰዎች ስሜትን ያለመረዳት ነው ።
በተለያዩ ቦታዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በመንግሥት መዋቅር ተደግፎ የሚፈጸም መሆኑን ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ምስክርት ሰጥተዋል።እነዚህ ሰዎች ባሉበት ውይይት፣ ምክክርና እርቅ ተደርጎ ዘላቂ መፍትሄ ይገኛል ተብሎ መጠበቅ ዘበት ነው። እንዲያውም በዚህ ምክንያት ጸጥታ ለማስከበር የሄዱ የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በተሳሳተ መንገድ እየተነገራቸው በታጣቂዎች ተገድለዋል ። ይህ ውስጣዊ ችግሩ፣ ድብብቆሹና ሴራው ምን ያህል የገነገነ መሆኑን ያሳያል።
ኮሚሽኑም ቢሆን ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ግጭቶች የሚስተዋሉበትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተደጋጋሚ ማውገዙ እና መወሰድ ስለሚገባቸው የእርምት እርምጃዎች ማመላከቱ አበረታች እና መልካም የሚባል ቢሆንም በሚመለከታቸው አካላት ተተግብረው መፍትሄ አምጥተዋል የሚለውን ማየት አለበት።
ነገር ግን የዜጎችን በህይወት የመኖር ፣ የአካል ደህንነት እና የንብረት ባለቤትነት መብቶችን ጨምሮ በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውሮ የመስራት እንዲሁም በነፃነት የመኖር መብቶችን ሁሉም አመራር በየአካባቢው ማረጋገጥ አለበት። ለችግሮችም ዘላቂ መፍትሄ መስጠትና አስተማማኝ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ የማይችሉ አመራሮች ላይም ፈጣን ተጠያቂነት ማስከተል ይገባል።
የቀበሌያችን፣የወረዳችን፣ የዞናችንና የክልላችን የጸጥታ ችግር ምንጩን አውቀነዋል፣ በንጹሃን ሰዎች ላይ ዳግም መሰል ጥቃት አይከሰትም፤ አጥፊዎችን እንቀጣለን እያሉ በየአደባባዩ የሚምሉና የሚገዘቱ አመራሮች በተቃራኒው ከስብሰባው ወይም ዕርቁ ከተፈጸመ በኋላ ወደ ቢሯቸው ሲሄዱ ከጀርባ ሆነው ግጭት የሚለኩሱትንና የሚያቀጣጥሉትን አመራሮች መመንጠርና ማጥራት ጉዳይ ለነገ የሚባል አይደለም።
የዛሬው ክስተት ትምህርት ተወስዶበት ነገ በማያዳግም መልኩ መፍትሄ መስጠት ካልተቻለ ጦሱ ከባድ ነው።ከወዲሁ ከአድርባይነትና ከአስመሳይነት የተላቀቀ አመራር መፍጠር ካልተቻለ ብልጽግና ማምጣት ሳይሆን ግጭትን ማስፋፋት ነው የሚሆነው።
ነገን ለዜጎች አስተማማኝ ለማድረግ ዛሬ ግጭትን በቀላሉ የሚፈታ፣ ለዜጎች ደህንነት ከፊት የሚቆም አመራርን፣ ችግሮችን በዕርቅ ለመፍታት የሚሯሯጥ ሽማግሌዎችና ለህዝብ አንድነትና አብሮነት የሚታትሩ ሽማግሌዎችን ፣ከህዝብ ህልውና ፊት የሚቆሙ ፖሊሶችን ማፍራት ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013