ትኩረት ለንጽህና መጠበቂያ ፍጆታ

የተፈጥሮ ግዴታዋ እንደሆነ ታውቃለች። ወር በመጣ ቁጥር መዘጋጀት እንዳለባትም ትረዳለች። ሆኖም የሕመሙ ሁኔታ ‹‹ምነው ሴት ባልሆንኩ›› ያሰኛታል። ተፈጥሮን ልትገዳደርበት የምትችለውን ተግባር ለመከወንም ያስመኛታል። ሆኖም የሚቻላት አይደለምና የወር አበባዋን መምጫ ጊዜ ስታስብ አጥብቃ ትጠላዋለች። በዚያ ላይ የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን እንደልብ አለማግኘቷ ሁኔታዋን በእጅጉ የሚያከብድባት ስለሆነ ግራ ትጋባበታለችም። ሁሌም ይህ ጭንቀቷ ወር ብቻ ሳይሆን ቀናትን ጭምር የሚይዝ ይሆንና ከትምህርት ገበታዋ ያስቀራታል። በተለይ አንዳንድ ጊዜ በሚገጥማት የሁለት ቀን ሕመም ፈተና ጭምር አምልጧት እንደሚያውቅ ታስታውሳለች። ይህና መሰል ጫናዎቹ ደግሞ ውጤታማ ተማሪ እንዳትሆን ገድቧታል።

ሜላት መብራቱ ከወር አበባ ጋር ተያይዘው የሚመጡባት ችግሮችን ስታይ የምታማርርባቸው ወቅቶች እንዳሉ ብታምንም አንዳንዴ በእርሷ ላይ የሆነው ጥቂት እንደሆነ ትረዳለች። ምክንያቱም እርሷ ቢበዛ በወር ውስጥ ከሦስት ቀን በላይ ከትምህርቷ ቀርታ አታውቅም። ሕመሟም ቢሆን ለክፉ አይሰጣትም። የቤተሰብ ክትትሏና የንጽህና መጠበቂያ ለመግዛት ብላ ብር ከቤተሰብ ስትጠይቅ እንቢ አትባልም። በዚህም ጤናዋን ጠብቃ ጊዜዋን በአግባቡ ተጠቅማ ያለፏትን ትምህርቶች እንድታነብና መካከለኛ ተማሪ የመሆን እድሏን እንዳትቀማ አድርጓታል። ይህንን የምትረዳው ደግሞ ሌሎች ጓደኞቿን ስትመለከት እንደሆነ ታነሳለች።

‹‹አንዳንድ ተማሪዎች ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ የወር አበባ ሲታያቸውና በድንገት ሲመጣባቸው መሸማቀቅ ውስጥ ይገባሉ። ይህ ደግሞ በትምህርትቤቶች ውስጥ በስፋት ይታያል። ‹የተማሪዎችን ዓይን እንዴት አየዋለሁ› በማለትም ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ሴቶችን አግኝቻለሁ። አንዳንዶች በዚያው እንቢ ብለው ሲቀሩ አንድ አራት የሚሆኑ ተማሪዎችን ግን ትንሽ ግንዛቤው ያለን ሴቶች በመተባበር እንዲመለሱ ያደረግንበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ልጆች ደግሞ ዛሬ ለብዙዎች ትምህርት መቀጠል ተስፋ ሆነው አይተናቸዋል›› የምትለው ተማሪ ሜላት፤ የሴቶች ወር አበባ ማየት የተፈጥሮ ግዴታ መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ ማስገንዘብ ይኖርበታል። በተለይም ሴቶች ለሴቶች ቅርብ ሆነው በመነጋገር ችግሮቻቸውን መፍታት ይኖርባቸዋል ስትል ከገጠማት ተሞክሮ አንጻር በመነሳት ትመክራለች።

ኤዲስ ሄልዝ ኬር ፋዉንዴሽን ኢትዮጵያ (ኤ አፍ ኤች) ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ የወር አበባ ንጽህና ቀን በተከበረበት ወቅት ያገኘናት ተማሪ ሜሮን ታሪኩ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የምትለው ነገር አላት። የወር አበባ ማየት ጤናማ የመሆን ምልክት ነው። እርሱ ሲዛባ ጤናችንን እንድንጠራጠር እንሆናለን። ሀኪምን አማክረን ለመፍትሄው እንፋጠናለን። ስለዚህም ወር አበባ የመለምለማችን ምልክት እንጂ የምናፍርበት መለያ አይደለም። ዑደቱ በራሱ የሚነግረን ብዙ ነገርም አለው። ለምሳሌ ለመውለድ ጭምር መቼ ዝግጁ እንደሆንን የምናውቅበት መመሪያችን ነው። እናም ተፈጥሮ በቸረን የሴትነት ግዴታችን ልንሸማቀቅ አይገባንም ስትል ታስረዳለች።

እንደ ሜሮን ማብራረያ፤ የወር አበባ ፈታኝ የሚሆንበት አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። አንዱ የግንዛቤ እጥረት ሲሆን ባለማወቅ ተፈጥሯዊ ክስተቱ ሲጀምር ብዙዎች ይሸማቀቃሉ። ስለ እርሱ ለማውራትም ይፈራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ተፈጥሮ ለሴት ልጅ የሰጠቻት በረከት ሳይሆን እርግማን እንደሆነም ያስባሉ። በዚህም በነጻነት የማውራቱ ጉዳይ ሁሉም ላይ የተከለከለ እስኪመስል ድረስ ዘልቋል። በማኅበረሰቡ ዘንድም ያለው አመለካከት የተዛባ በመሆኑ በተለይም በገጠራማ አካባቢ ሴቷ ከሚመስሏት እናትና እህቷ እንዲሁም ጓደኞቿ ጋር ለማውራት ትፈራለች። ከዚህ ጋር ተያይዞም የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን ለመግዛት ጭምር ታፍራለች። መግዢያ ገንዘብ ለመጠየቅም ትሸማቀቃለች። በተለይም አሁን ላይ ዋጋው እየናረ ስለመጣ በራሷ እንኳን የማትሸፍንበት ሁኔታ ተደቅኖባታል ትላለች።

ሜሮን ‹‹በፊት ላይ ዋጋው ዝቅ ያለ በመሆኑ በቀላሉ ለሌሎች ወጪዎች ቤተሰቦቼ ሲሰጡኝ ለንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) መግዢያ ጭምር ይተርፈኛል። እናም ስጡኝ ለማለት አልገደድም ነበር። አሁን ግን ዋጋው የሚቀመስ ስላልሆነ ተናግሬ መግዛት ግድ ይለኛል። ይህንን ማድረጉ ደግሞ በራሱ ያስጨንቃል። እናም ሌሎች አማራጮችን ጭምር ለመውሰድ የምመርጥበት ሁኔታ ብዙ ነው። ለምሳሌ፡- ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ለመግዛት ሳስብ እንዲተርፈኝ በማድረግ በወር የማወጣውን ሞዴስ እገዛለሁ።›› ትላለች።

ይህን ማድረግ የማይችሉና የወር ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሴቶች በዚህ ጉዳይ በእጅጉ ይጎዳሉ። ምክንያቱም ከፍተኛ ወጪ ማውጣት ስለማይችሉ አንዱን ለብዙ ሰዓት መጠቀም አለዚያም ጥራት የሌለው ሞዴስ በዝቅተኛ ዋጋ መግዛትን ይመርጣሉ። ይህ ደግሞ ለከፍተኛ የጤና ችግር ይዳርጋቸዋል። በተለይ በቀላሉ ለኢንፌክሽን የመጋለጣቸው እድል ሰፊ እንደሆነ ታነሳለች።

የንጽህና መጠበቂያ ሴቶች ለቅንጦት የሚጠቀሙበት አይደለም። እንደ ምግብና መጠለያ ሁሉ ለሴት ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ነው። ስለሆነም ሁሉም ይህንን አምኖ ለሴቶች ጤናማ ሕይወት የተሻለውን ሁሉ ማደላደል ይጠበቅበታል። ሴትን ልጅ ጤናማ ማድረግ ሀገርን ከመገንባት አይተናነስም ሲባልም ይህንን በማድረግ የሚከወን ተግባር እንደሆነ መታሰብ አለበት። እናም እንደ መንግሥት በሁሉም ዘርፍ ላይ ያሉ አካላት ትኩረት ሰተውት እንዲሠሩበት አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል የምትለው ሜሮን፤ አሁን አሁን ግንዛቤው በብዛት እየሰፋ እንደመጣ ታነሳለች። ለዚህም በማሳያነት የምትጠቅሰው በሀገር አቀፍ ደረጃ ዓለም አቀፍ የወር አበባ ቀን እየተከበረ መሆኑን ነው።

ሜሮን እንዲህ አይነት ክብረ በዓላት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ይዘው ይመጣሉ ብላ ታምናለች። አንደኛው ማኅበረሰቡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ግንዛቤ እንዲጨብጥ ማድረጉ ነው። ሌላኛው ደግሞ በመንግሥት አካላት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ሁሉም እንዲረዳና በቀጣይም ይህ ትኩረት እንደሰፋ ለማድረግ ማስቻሉ ነው ትላለች። ይህ ሲሆንም ሰፊና ዋና ዋና ችግር ናቸው ተብለው የተለዩት ጉዳዮችም ወደ መፍትሄው እንዲገቡ መደላደልን ይፈጥርላቸዋል ስትል ታነሳለች።

ዓለም አቀፍ የወር አበባ ንጽህና ቀን በተከበረበት ወቅት የጤና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ዓለሙ ቀጄላ በኢትዮጵያ ስለ ወር አበባ ያለውን ግንዛቤና መሰል ነገሮችን በተመለከተ አንስተዋል። እርሳቸው እንዳሉትም፤ በሀገር ደረጃ ጤናማ የንጽህና መጠበቂያ የሚጠቀሙ ሴቶች ከ30 በመቶ አይበልጡም። ለዚህም ምክንያቱ ከወር አበባ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ያለው ግንዛቤ ችግር ነው። በተለይ በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል እጅግ በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል። የወር አበባ የጤናማነት ምልክት መሆንን በሚገባ የማያውቁ በርካቶች ናቸው። የምልከታው ችግር ደግሞ በተማረውም፤ ባልተማረውም ማኅበረሰብ ዘንድ በስፋት የሚታይ ነው። እንደ አሳፋሪ ነገር ይቆጠራልም። ይህም የንጽህና መጠበቂያ ፓዶችን እንዳይጠቀሙና ጤናቸውን እንዳይጠብቁ ገድቧቸዋል። ከዚያም ባሻገር የንጽህና መጠበቀያ (ሞዴስ) አቅርቦት እጥረት ለችግሩ መንስኤ ሆኖ እንዲጓዝ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ አጠቃላይ ካላት የሕዝብ ቁጥር የወር አበባ ማየት የጀመሩ ወይም በመዋለድ እድሜ ላይ የሚገኙ ሴቶች 23 ሚሊዮን ደርሷል። ሆኖም ከዚህ ብዛት ካለው የሴት ቁጥር ውስጥ የንጽህና መጠበቂያ የሚጠቀሙት ከ30 በመቶ አይበልጡም። ለችግሩ ደግሞ እንደ ዋና መንስኤነት የሚነሳው የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቱ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ ነው። በተጨማሪ ደግሞ የግንዛቤ ማነስ ጉዳይ ለችግሩ እልባት እንዳይሰጥ አድርጓል። በመሆኑም ይህንን ችግር ለመፍታት የጤና ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የጤና ሚኒስቴር የንጽህና መጠበቀያ (ሞዴስ) የመጠቀም ባሕልን ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የጤና ግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን በተለያየ መልኩ ያከናውናል። አንዱ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የሚሰራው ሥራ ነው። ተማሪዎች ስለ ወር አበባ ሲያውቁ ቤተሰብን የማሳወቅና ሁሉም ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ እንዲረዳ ከማስቻል አንጻር የማይተካ ሚና አላቸው። ግንዛቤው ያላቸው የሴቶችን ቁጥርን ከፍ ከማድረግ አኳያም ያለው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉም።

አክለውም፤ እንደ ጤና ሚኒስቴር ከግንዛቤ ማስጨበጡ ባሻገር ሌሎች ተግባራትንም ማከናወን የግድ ይላል። በዚህም ከዋጋ ንረቱ ጋር ይያያዛሉ የተባሉ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። አንዱ ቀረጥ ቅነሳ እንዲደረግ ማስቻል ነው። በዚህም ከዚህ በፊት ሚኒስቴሩ በሠራው ሥራ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ፓዶች ላይ የነበረው ቀረጥ 30 በመቶ ከነበረበት ወደ 10 በመቶ ማውረድ ተችሏል። ነገር ግን ይህ በቂ ነው ተብሎ የሚወሰድ አይደለም። ምክንያቱም ሴቶች የንጽህና መጠበቂዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻርም የንጽህና ፓዶችን ከቀረጥ ነጻ ማድረግ ይገባል። ለዚህም የተለያዩ አካላት ተሳትፎ ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

አቶ አለሙ፤ የወር አበባ ጉዳይን ከትምህርት አንጻርም ጥናቶችን አብነት በማድረግ ያነሱታል። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ አንዲት ሴት በአንድ ወር ከአንድ እስከ አራት ቀን ያህል በወር አበባ ምክንያት ከትምህርት ገበታዋ ልትቀር ትችላለች። ይህም አንድ የትምህርት ዓመት 10 ወር ቢሆን በእያንዳንዱ ወር አንዲት ሴት አራት ቀን የምትቀር ከሆነ፤ በዓመት 40 ቀናትን ከትምህርቷ የምትቀርበት አጋጣሚ ይኖራል። ይህም ሴቶች የሚገባቸውን እውቀት እንዳይቀስሙ፣ ተወዳዳሪ እንደሆኑ ብሎም የማለፍ ምጣኔያቸው ላይ ጥላ እንዲያጠላባቸው ያደርጋል። በአጠቃላይ በትምህርት ጥራት ላይ እና ተወዳዳሪነት ላይ የሚኖራቸውን አቅም ያሳጣቸዋል። እናም በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ችግሮቻቸውን ለይቶ መደገፍ ያስፈልጋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ግብዓት ተጨማሪና የቅንጦት እቃ አይደለም። ከመሰረታዊ ፍላጎቶች ከሚባሉት ውስጥ የሚካተት ነው። ስለዚህም ከዋጋው አንጻር የሚነሱ ችግሮች በአግባቡ መፍትሄ ሊቸራቸው ይገባል። ዋጋቸው እንዲሻሻልም ማድረግ ላይ ሁሉም የሚመለከተው አካል መረባረብ አለበት። ጉዳዩ የአንድ አካል ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። በመሆኑም የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታትና ሌሎች አማራጮችን በመፈለግ መፍትሄዎችን መስጠት የግድ ይላል።

የንጽህና መጠበቂያ የማግኘት እድል ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ ሴት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንደሚቀሩ ያነሱት ምክትል ሰብሳቢው፤ ይህም የተማረ የሰው ኃይል ከማፍራት አንጻር ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥር እንደሆነ መታሰብ አለበት። የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ሴቶች ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የቀረጥ ጉዳይም ሊፈተሽ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የንጽህና መጠበቂያዎች ልዩ ልዩ መሆናቸው ይነገራል። ይህንን ደግሞ የሚረዳ ማኅበረሰብ እንብዛም ነው። ስለሆነም ጤናማ ሆኑ የንጽህና መጠበቂያዎች ምን ምን አይነት ናቸው፣ ሴቶች ጤናማ ያልሆኑትን የንጽህና መጠበቂያዎችን ሲጠቀሙ ምን አይነት የጤና ጉዳት ይገጥማቸዋል? እና መሰል የጤና መጠበቂያ ዘዴዎችን ሁሉም ማኅበረሰብ እንዲያውቅ በተለይም ሴቶች እንዲረዱት ከማድረግ አንጻር ጤና ሚኒስቴር በትኩረት ሊሠራበት ይገባል። በሌላ በኩል ሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም የተለዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለችግሩ እልባት የሚሰጡ ተግባራትን ማከናወን ይኖርባታል። እከሌ እከሌ ሳይባል ሁሉም በወር አበባ ጉዳይ ላይ ለሁሉም ሴቶች ደራሽ መሆን አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።

የሴቶች ጤና ችግር ከሁሉም በላይ የሚፈታውና መፍትሄ የሚያገኘው ሁሉም ስለ ጉዳዩ በቂ እውቀትና መረዳት ሲኖረው ነው። በተለይም እንደ ሀገር ያለው ምልከታ መሻሻል ከቻለ ብዙዎቹ ችግሮች ይፈታሉ። እናም መረዳቱን ከራሳቸው ከሴቶቹ መጀመር እንደሚገባ የገለጹት ታደለ (ዶ.ር)፤ ለዚህ ሥራ ከፍተኛውን ድርሻ በመወሰድ ትምህርት ሚኒስቴርና ጤና ሚኒስቴር ቢሰሩበት የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያነሳሉ። ሁለቱም ተቋማት በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና በጥናቶች አስደግፈው ማቅረብ ቢችሉ የፖሊሲ አቅጣጫ ለማስቀመጥና ሕግ ለማውጣት እንዲሁም በተቻለው መጠን ሴቶችን ለመደገፍ ያስችላል ሲሉም ይመክራሉ።

አዎ የሴቶች ጉዳይ የሀገርን የማዳንና ወደ ከፍታው የማሻገር ጉዳይ ነውና አንዱ ችግራቸው የሆነውን የወር አበባን ምንነት ማሳወቅና ለዚያ ይበጃሉ የሚባሉ ግብዓቶችን በአግባቡ ማቅረብ ለአንድ አካል የሚሰጥ ስላልሆነ ሁሉም ያስብበት በማለት ለዛሬ የያዝነውን አበቃን። ሰላም!!

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You