በሀሳብ መፎካከር፤ ስለሀገር መተባበር ḷ

ሁሉም ነገር ከሀገር በታች ነው።ግለሰቦችም፤ቡድኖችም፤የፖለቲካ ድርጅቶችም ሊኖሩ የሚችሉት ሀገር ስትኖር ነው።ተምሮ ለቁምነገር መብቃት ፤ወልዶ ማሳደግ ፤ሠርቶ መክብር የሚቻለው ሀገር ስትኖር ነው።በአጠቃላይ ሀገር የሁሉም ነገር ማጠንጠኛ አልፋ እና ኦሜጋ ናት።

ሆኖም በነባራዊው የሀገራችን ፖለቲካ አውድ ውስጥ ይህንን የመገንዘብ ችግር አለ።ወይንም ደግሞ ሆን ብሎ ከእውነታው የማፈንገጥ አካሄድ ይታያል።ሀገርን ከራስ በታች መመልከት፤ከጎጥ በታች ማውረድ፤ከፖለቲካ ድርጅት በታች አድርጎ መመልከት የመሳሰሉት አንሶ የማሳነስ አካሄድ እንመለከታለን።

በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ የሚቀነቀነው የፖለቲካ ዕሳቤ የፖለቲካ ፓርቲን ወይንም ድርጅትን አግዝፎ እና አተልቆ ከሀገር በላይ የማሳበጥ ስሁት አካሄድ ተጠናውቶን ቆይቷል።የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፈጠሩት፤የሚያድጉት እና የሚያብቡት በሀገር ውስጥ መሆኑ እየታወቀ ከሀገር በላይ ግምት እንዲሰጣቸው ማድረግ ፖለቲካን አለመረዳት ካልሆነም ደግሞ የሀገርን ምንነት በመረዳት ዙሪያ የዕውቀት ውስንነት መኖሩን የሚያመላክት ነው።

ሀገር የጋራ ነች።ዜጎች በጋራ የሚያንጿት፤በጋራ የሚገነቧትና በጋራ የሚያለሟት።ሀገር የጋራ ቤት ነች።ስትዘም ባጋራ የሚያቃኗት፤ጉድፏን የሚያነሱላት ፤አቧራዋን የሚያራግፉላትና ገበናዋን የሚደብቁላት።

ኢትዮጵያውያንም በሀገራች ለመጣ ቀልድ አያውቁም።አጥንታቸውን ይከሰክሳሉ፤ ደማቸውን ያፈሳሉ፤ህይወታቸን ይገብራሉ። ህይወታቸውን ሰውተው ጭምር የሀገራቸውን ዳር ድንበር ያስከብራሉ፤፤ሉአላዊነቷን ያስጠብቃሉ፤፤ባዕዳን ወራሪን አሳፍረው ይመልሳሉ።በሀገራቸው ለመጣ በአንድነት ይቆማሉ።

ይህ የቆየ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ግን ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መጥቷል።በተለይም ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ ባህል ስናይ በጎ ስራ ሰርቶ ሀገር እና ህዝብን ከመጥቀም ይልቅ የራስን ጥቅም፤ክሀዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስን ስሜት፤ከሀገር ህልውና ይልቅ የፓርቲ ህልውና ማስቀደም ላይ ትኩረት የሚደረግበት ነው።ይህ ደግሞ የጋራ ቤታችን የሆነችው ኢትዮጵያ ክብሯ ዝቅ እንዲል፤የጋራ ማንነት እንድናጣና እና አልፎ ተርፎም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድዘልቅ አድርጎን ቆይቷል።

የፖለቲካ ስርዓታችን ለሀገር በጎ ማሰብና አለፍ ሲልም ችግሮቻችንን በጋራ ከመቅረፍ በጋራ ችግሮችን መቀፍቀፍ ላይ እንድንጠመድ አድርጎናል።በጋራ ቆሞ ህዝብና ሀገርን ከመጥቀም ሀገር በትብብር እንዳትቆም የጥላቻ መርዝ መንዛት ነው። ተባብሮ ተደጋገፎ ሀገርን ማቆም ፖለቲከኞቻችን በሩቁ የሚሸሹት ጸበል ነው።

ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች የመለያየት እንጂ የአንድነት ተመስላት ሆነው አያውቁም።በሀገራችን ፖለቲካ ሲታሰብ ከአብሮነት ይልቅ መለያየት፤ከመደጋገፍ ይልቅ መገፋፋት፤ከውይይት ይልቅ መነቋቆር፤አብሮ ከመቆም ይልቅ አብሮ መውደቅ አመዛኙን ስፍራ ይይዛል።

ሆኖም በቅድሚያ ሁሉም ነገር ከሀገር በታች መሆኑን መተማመን ላይ መድረስ ይገባናል።ሀገር እና ህዝብን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ሙግት ማድረግ፤የሚጠቅመውን መያዝና ለሀገር ሉአላዊነት እና ብልጽገትና መስራት ፖለቲከኞችን ጨምሮ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ሀቅ ነው።ከዚህ በሻገር ሀገር እና ህዝብን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የስልጡን ፖለቲካ መገላጫችን ሊሆን ይገባል።

ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን የሚጋፉ፤ልማቷን የሚያደናቅፉ ችግሮች ሲገጥሟት በጋራ መቆም የሁሉም ዜጋ የውዴታ ግዴታ ሊሆን ይገባል።ዛሬ ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄን የህልውና ጥያቄ ነው ብላ ወስናለች።የአባይ ግድብን አጠናቆ ለልማት ማዋል ከድህነት መውጫዩ አንዱ መንገድ ነው ብላ አውጃለች።በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን መትከል በየአመቱ ከሚጠቃን ድረቅና ርሃብ ማምለጫ መንገድ መሆኑን ካወጀች ስደስት አመታት ቶቆጥረው ሰባተኛውን ይዘናል።ሀጋራዊ ምክክር ለዘመናት የተከማቹ አለመግባባቶችን ለመቅረፍ እና ኢትዮጵያን በአዲስ ጎዳና ለማራመድ ብቸኛው መውጫ መንገድ ነው ብላ ካወጀች ሶስት አመማት አለፉ። ስለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀልባቸውን ሰብሰብ አድርገው በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ አለባቸው።ሀገር የጋራ ነች እና የጋራ ጉዳዮችም እንዳሉን መዘንጋት የለበትም።

ሌላው ቢቀር በበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ መሳተፍ ላይ ለምን ሰነፉ።የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነትና መልካም ፈቃድ ለኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በማሳተፍ ነፃ አገልግሎት የሚያበረክቱበት ተግባር ነው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም አይነት ክፍያ የማያገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የህሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለምንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራሱ ተነሳሽነት የሚፈፅመው ተግባር ነው። ይህ ተግባር ሰዎች ዘር፤ቀለም ብሄርና ኃይማኖት ሳይለያቸው የሚሳተፉበት በጎ ተግባር ነው።

ሆኖም በገቢር እንደሚታየው የበጎ ፈቃድ በተነሳ ቁጥር ሁልጊዜ ግንባር ቀደም ሆነው የሚገኙት የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እና የመንግስት አካላት ብቻ ናቸው።ለቁጥር የሚያዳግቱት አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በጎ ፈቃድ ስራ ሲመጣ የት እንደሚገቡ አይታወቅም።

የፖለቲካ ፓርቲዎች መመስረት ዋነኛ ጉዳይ የሀገር ልማት እና እድገት እስከሆነ ድረስ አብዛኞቹ ፓርቲዎች በበጎ ፈቃድ ለመሳተፍ ዳተኛ የሆኑበት ምክንያት እንቆቅልሽ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምስረታቸው ጀምሮ እስከ ስልጣን ድረስ ያሰቡትን አላማ ማሳካት የሚችሉት ሀገር ስትለማ ነው።ሀገር የምትለማው ደግሞ በፖለቲካ ዲስኩር ወይም በፖለቲካ ሽኩቻ አይደለም።

በሰለጠኑት አለማት የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱና ዋነኛ መመዘኛ የበጎ ፈቃድ ስራ ነው።ተወዳድሮ ለማሸነፍና ስልጣን ለመያዝ የመጀመርያው መመዘኛ ፓርቲው ወይም ግለሰቡ የሰራቸው በጎ ፈቃድ ስራዎችና ያመጣው ውጤት ነው።ያለበለዚያ በፖለቲካ ፓርቲነት መመዝገብና የመንግስትን ህጸጽ እየፈለጉ ብቻ በመውቀስ ስልጣን ላይ ፊጥጥ ማለት አይታሰብም።

የእኛ ሀገር የፖለቲካ ፓርቲዎች እሳቤ የሚመነጨው በተገኘው አማራጭ ሁሉ ወደ ስልጣን መምጣት እንጂ ባከላቸው ግዜ ለህዝብ እና ለሀገር በጎ ስራ መስራት አይደለም ።ለማንም ክፍት የሆነውና ሁሉም በሰብአዊነት የሚሳተፍበትን የበጎ ፈቃድ ስራ ለፖለቲከኞቻችን የተከለከለ ይመስል በአጠገቡም ዝር አይሉም። እነሱ ስልጣን ካልያዙ በስተቀር ሀገር የሌለች ይመስል ከፖለቲካ ወቀሳና ማጣጣል በስተቀር አባሎቻቸውን አስተባብረው ይህ ነው የሚባል የበጎ ፈቃድ ስራ ሲሰሩ አይታይም።

አሁን በእጃቸው ያለውን የበጎ ፈቃድ ስራ ሳይሰሩ ነገ ስልጣን ጨብጠው የሚሰሩትን ስራ እና የሚለውጡትን ሀገር ያልማሉ።ይህ ደግሞ ህልም እንጂ እውን ሊሆን አይችልም።

ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያለውን የፖለቲካ ባህል ስናይ በጎ ሥራ ሠርቶ ሀገር እና ህዝብን ከመጥቀም ይልቅ የራስን ጥቅም፤ክሀዝብ ፍላጎት ይልቅ የራስን ስሜት፤ከሀገር ህልውና የፓርቲ ህልውና ማስቀደም ላይ ትኩረት የሚደረግበት ነው።ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ላልተገባ እሰጥ እገባና ግጭት አልፎ ተርፎም በማያባራ ጦርነት ውስጥ እንድትዘልቅ አድርጓታል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ ጉድለት ፖለቲካን ከሸፍጥ ጋር መቆራኘቱ ነው። ፖለቲከኛ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆኖ በጎ ስራ መስራት የተከለከለ ይመስላል ።ይልቁንም ሴራ መተንተንና መንግስትን መውቀስ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ጥንካሬ መለኪያ ተድርጎ እየተወሰደ ሀገር እና ህዝብም ከፖለቲከኞች ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም እያጡ ነው፤ይባሱንም ሀገርና ህዝብን በማያራምድ አጀንዳ ሰቅዘው የኋሊት እንድንጓዝ እያደረጉን ነው።

የፖለቲካ ሥርዓታችን ለሀገር በጎ ማሰብና አለፍ ሲልም በበጎ ፈቃድ ስራዎች ውስጥ ተሳትፎ ሀዝብና ሀገርን ከመጥቀም ሀገር በትብብር እንዳትቆም የጥላቻ መርዝ መንዛት ነው። ተባብሮ ተደጋገፎ ሀገርን ማቆም ፖለቲከኞቻችን በሩቁ የሚሸሹት ጸበል ነው። ተፎካካሪን እንደ ጠላት ማየትና ማሳደድ ለዓመታት የተፀናወተን ልማድ ነው።አንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሲመሰረት ሌሎችን አጥፍቶና አንቋሾ፤ጥላቻ ዘርቶና አኮስምኖ የራሱን ስብዕና ለመገንባት ሲሞክር ማየት የተለመደ ነው።

በጋራ ሰርቶ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ከማላቀቅ ይልቅ መልካም ስራ ሊሰራ የተነሳን ወገን ማንቋሸሽና በህዝብ ዘንድም በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረግ የኖርንበትና እየኖርንበት ያለ ሀቅ ነው። በየጊዜው ጥላቻና ግጭትን መፈብረክ ሀገርን የኋሊት እንድትጓዝ ማድረግ አንዱ ፖለቲካ ታሪካችን ነው።

ሀገርን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀምና የአቅምን ያህል ሃሳብ ከማዋጣት ይልቅ ሀገርበን በሚያፈርሱ አጀንዳዎች ውስጥ መጠመድ ፤አለፍ ሲልም ሃሳብን በነፍጥ ለመጫን ማዳከር አንዱ የእኛነታችን መለያ ሆኖ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፤ዛሬም የሚታየው ሀቅ ይኸው ነው።

እነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተቋቋሙ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ ስትጎዳ ተመልክተዋል።ድርቅ በየአመቱ እየደጋገመ እየመጣ በርካቶችን ከአካባያቸው ሲያፈናቅል፤ ሲያሰደድና ሰዎች በርሃብ ሲሞቱ ተመልከተዋል።ሆኖም የእኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግረን ቁጭ ብሎ ከመመልከት ወይንም ደግሞ ወቃሽ ከመሆን ድርቅን በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻልበትን አማራጭ ሲጠቁሙ አይታዩም።

አለፍ ሲልም ያላቸውን ዕውቀትና የአባላት ብዛት በመጠቀም አስተባብረው ችግኝ ሲተክሉ አይታዩም።አረንጓዴ አሻራ መትከል በጎ ፍላጎትንና ቅን አሳቢነትን እንጂ ስልጣንን ወይንም ገንዘብን አይጠይቅም።ስሙ እንዲህ የሚባል ፓርቲ አባላቱን አስተባብሮ ይሄን የሚያክል ችግኝ ተከለ የሚባል ዜና የምንሰማው መቼ ይሆን?

በተመሳሰይም አንድ ፓርቲ አባላቱን አስተባብሮ የድሃ ቤት ማደስ ለሀገር ለወገን ማሰብን እንጂ የተለየ ጥበብን አይጠይቅም።እነዲሁ ለአፍ እና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ለድሃው የቆምኩ ነኝ የሚለው ፕሮፖጋንዳ ተዝብትን ከማትረፍ ውጪ የሚያሰግኘው ፋይዳ የለም።

ኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በመረዳዳትና በመደጋገፍ የማለፍ ጥበብን የተላበሱ ሕዝቦች ናቸው።በርሃብም ሆነ በድርቅ፤በግጭትም ሆነ በጦርነት ወቅት በመረዳዳት አስከፊ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል።

ኢትዮጵያውያን ዘር ፤ቀለምና ኃይማኖት ሳይለዩ የተቸገረን መርዳት፤የተራበን ማብላት፤የተጠማን ማጠጣትና የታረዘን ማልበስ ያውቁበታል።እንኳን እርስ በእራሳቸው ይቅርና ባህር አቋርጦ፤ድንበር ተሻግሮ ለመጣ ስደተኛ ጭምር በራቸውን ክፍት አድርገው ፤ያላቸውን አካፍለውና ፍቅር ለግሰው ማኖር የሚችሉ ህዝቦች መሆናቸውን በርካታ የታሪክ መዛግብት የሚያወሱት ሃቅ ነው።

ይህ የመተሳሰብ ፡የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጠናክሮ ቀጥሏል።በተለይም አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ማዕድ ማጋራትና ድሃ ድሃ ቤት እድሳት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።

በየአመቱ ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅመ ደካማ ቤቶች እየታደሱ ከዝናብና ከጎርፍ ለመታደግ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።በዚህም በርካቶች ከስቃይና ከመከራ ተላቀው በጎ አድራጊዎችን ሲያመሰግኑና ሲመርቁ ተሰምተዋል።

በየዓመቱም ክረምት በመጣ ቁጥር የበርካታ አቅም ደካማ ዜጎች ቤቶች እየታደሱ ዜጎችን ከዝናብና ከብርድ የመታደጉ ተግባር በመንግስት፤መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በነዋሪው ተሳትፎ እውን እየሆነ ነው።

በዚህ በጎ ፈቃድ ስራ ውስጥ በርካታ ወጣቶችና ሴቶች አለፍ ሲልም በጎ አድራጊ ባለሃብቶች ሲሳተፉ ቢታዩም ፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ግን ከሰልፉ ውስጥ አልታዩም።በተለይም ተወዳድረን፤ ስልጣን ይዘን ፤ሀገር እንመራለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጎነታቸውንና ለሀገርና ለወገን ያላቸውን ተቆርቋሪነት ማሳያው ጊዜ አሁን ሊሆን በተገባ ነበር።ገን በእድሉ ሲጠቀሙ አይታዩም።

በሌላም በኩል በአቅም ማነስ ምክንያት በቀን አንድ ግዜ እንኳን እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በጋራ ማእድ እንዲቆርሱ በማድረግ ረገድ የተጀመሩት በጎ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን በጎ እሴቶች ማስቀጠያዎች እየሆኑ ነው።በበጎ ፈቃድ ወጣቶች ጭምር የሚከናወኑ የማዕድ ማጋራት በጎ ስራዎችን ለተመለከተ በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን መተሳሰብና መረዳዳት የሚያመላክት ነው።እዚህስ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን የታሉ?

የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰረትና ህልውና ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው።ወጣቱን ያልያዘ የፖለቲካ ፓርቲ ቀጣ ህይወት አይኖረውም።ሆኖም አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎቻን ወጣቱን በስሜት ከመቀስቀስና መንግስት ላይ ከማነሳሳት በዘለለ ዘላቂ የሆነ መርሃ ግብር ቀርጸው የወጣቱን ሕይወት ለማሻሻል ሲጥሩ አይታዩም።

በአሁኑ ወቅትበ ወጣቱ በመጤ ባህሎችና በአጓጉል ሲሶች እየተጠቃ ይገኛል።ይህ ደግሞ የነገ ሀገር ተረካቢ ብለን በየመድረኩ የምናነሳውን ወጣት ሕይወት በእጅጉ የሚጎዳና ጦሱም ለሁላችንም የሚተርፍ ነው።

ነገር ግን የወጣቱ በሱስ ውስጥ መዘፈቅና በመጤ ባህሎች መመረዝ አሳስቦት እንቅስቃሴ ያደረገ ፓርቲ አላጋጠመኝም።ቢያንስ ወጣቱ ከአጓጉል ሱስ እንዲበቅ ግንዛቤ የሚፈጥሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ማዘጋጀትና ወጣቱ ላይ ንቃት መፍጠር የተለየ ክህሎት የሚጠይቅ አይደለም።

በተመሳሳይም ስለሚደፈሩ ሴቶች መከራከርና ጥብቅና መቆምም የእነዚሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ መለያ መሆን ነበረበት።እዚህ ጉዳይም ላይ አልፎ አልፎ ከሚሰነዝሩት ትችት በስተቀር የሴቶችን መደፈርና ሰብአዊ መብት መከበር በተመለከተ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ጥረት ሲያደርጉ አላየናቸውም።

የኑሮ ውድነቱን ከፖለቲካ ፍጆታ ነጥሎ በመመልከት አባላቱን አስተባብሮ የሰው ኑሮ የሚቀነስበትን መላ መዘየድ እና ተግባራዊ እቅስቃሴ ማድረግስ እንደ ኒዩክለር ሳይንስ የከበደው ለምንድን ነው ?

ስለዚህም የፖለቲካ ባህላችን መቀየር ይኖርበታል።ሀገር እና መንግስትን ነጣጥሎ የሚመለከት የፖለቲካ ዕሳቤ ልናዳብር ይገባል።በዚህ ረገድ ኢዜማ ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ይህንን የቆየ ዕሳቤ የሚሰብር መልዕክት አስተላፏል።‹‹በሃሳብ እንፎካከራለን፤ስለሀገር እንተባበራለን›› በሚል ለሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ትምህርት የሚሆን መልዕክት አስተላልፏል።

በእስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You