
ዩክሬን በሩስያ ላይ የፈጸመቻቸውን የድሮን ጥቃቶች ተከትሎ በሞስኮ ከተማ የሚገኙ ዋና ዋና አየር ማረፊያዎች ለጊዜው እንዲዘጉ መደረጋቸውን እና ቢያንስ 140 በረራዎች መሰረዛቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር፤ ወደ ዋና ከተማዋ የተላኩ 27 ድሮኖችን ጨምሮ በአጠቃላይ 230 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።
የሩሲያ አቪዬሽን ተቆጣጣሪ እንደገለጸው ዋና ከተማዋን የሚያገለግሉ አራት ዋና ዋና አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚሰጡትን አገልግሎት አቋርጠዋል። ከ130 በላይ በረራዎች ደግሞ አቅጣጫቸው ለመቀየር ተገድደዋል። ኋላ ላይ ግን ሁሉም መደበኛ ሥራቸውን ቀጥለዋል ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሩሲያ አየር ኃይል በዩክሬን ላይ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ ሶስት ሰዎች እንደተገደሉ የክልሉ ባለስልጣናት ገልጸዋል። የሩሲያ የቱር ኦፕሬተሮች ማህበር እሁድ ዕለት እንዳስታወቀው በጥቃቶቹ ምክንያት በሞስኮ የሚገኙ አየር ማረፊያዎች በ 24 ሰዓታት ውስጥ 10 ጊዜ ተዘግተዋል።
ከሞስኮ በስተደቡብ ምዕራብ የሚገኘው የካሉጋ ክልልም የጥቃት ዒላማ ከነበሩ አካባቢዎች መካከል እንደሆነ ተጠቅሷል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ ጥቃት ለማድረስ የተሰማሩ 45 ድሮኖችን መጥለፉን ገለጸ ሲሆን በዚህ ጥቃት ምክንያት የካሉጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያምም በተመሳሳይ በጊዜው ተዘግቷል።
እንደ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ገለጻ፤ ሮስቶቭ እና ብራያንስክን ጨምሮ በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ባሉ ክልሎች እንዲሁም በጥቁር ባሕር ላይ ድሮኖች ተመትተዋል። ሮስቶቭ እና ባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በጥቁር ባሕር ላይ ድሮኖች መመታታቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል። በጥቃቶቹ የሰዎች ሕይወት ስለመጥፋቱ ግን አልተዘገበም።
የዩክሬን ድሮን ጥቃቶች ሩሲያ ውስጥ ጉዞዎችን ሲያስተጓጉሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በግንቦት ወር ኪየቭ በ24 ሰዓታት ውስጥ ከ500 በላይ ድሮኖችን ማስወንጨፏን ተከትሎ ቢያንስ 60 ሺህ መንገደኞች በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ ለመቆየት ተገድደው ነበር።
ሩስያ በዩክሬን በዶኔትስክ የተለያዩ አካባቢዎች በፈጸመችው የአየር ድብደባ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉ እና በሱሚ የመኖሪያ ህንጻዎች ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ተከትሎ አንዲት የ 78 ዓመት አዛውንት ሕይወታቸው ማለፉን የክልል ባለስልጣናት ተናግረዋል። የዩክሬን አየር ኃይል፤ ሩሲያ እሁድ ምሽት ከላከቻቸው 57 ድሮኖች ውስጥ 18 ያህሉን መትቶ መጣሉን አስታውቋል። ሌሎች ሰባት ድሮኖች ደግሞ ራዳሮቻቸው በመጠለፉ ጠፍተዋል ተብሏል።
ከሱሚ እና ዶኔትስክ በተጨማሪ እንደ ካርኪቭ፣ በኒፕሮፔትሮቭስክ እና ዘፖሪዢየ ያሉ የጦርነት ቀጣናዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል። እነዚህ ጥቃቶች ተፈጸሙት የክሬምሊን አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር ወደ የሰላም ስምምነት መንገድ ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸውን ነገር ግን ሞስኮ ቅድሚያ የምትሰጠው “ግቦቿን ለማሳካት” እንደሆነ እየገለጹ ባሉበት ወቅት ነው።
“ፕሬዚዳንት ፑቲን የዩክሬይን ጉዳይ በተቻለ ፍጥነት ወደ ሰላማዊ መደምደሚያ ለማምጣት ያላቸውን ፍላጎት በተደጋጋሚ ገልጸዋል። ይህ ረጅም ሂደት ነው፣ ጥረት ይጠይቃል፣ ቀላልም አይደለም” ሲሉ በቴሌቪዥን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረዋል።
የሩሲያ -ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ሶስት ዓመት ተኩል ገደማ ሆኖታል። ቅዳሜ ዕለት የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ባለፈው ወር የተቋረጡትን ድርድሮች እንደገና ለማስጀመር በማሰብ፤ ከሞስኮ ጋር አዲስ ዙር ውይይት እንዲያካሂድ ሃሳብ አቅርበዋል። ከዚህ ቀደም ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነቱን ለማብቃት በሚል ለመደራደር ያደረጉት ሙከራ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ባይችልም፤ የእስረኞች ልውውጥ እንዲካሄድ ምክንያት ሆኗል። ዜሌንስኪ፤ “ትክክለኛ ሰላምን ለማረጋገጥ በአመራር ደረጃ ስብሰባ ያስፈልጋል” ሲሉ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ፊት ለፊት ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውንም በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ለሩስያው መሪ ያላቸውን ድጋፍ እና አድናቆት በተደጋጋሚ ሲገልጹ የከረሙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ዋሽንግተን በኔቶ ሀገሮች በኩል “ከፍተኛ ደረጃ የጦር መሣሪያዎችን” ወደ ዩክሬን እንደምትልክ አስታውቀዋል። በተጨማሪም ትራምፕ በ50 ቀናት ውስጥ ጦርነቱን ለማቆም ስምምነት ካልተደረሰ በሩሲያ ላይ ከባድ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል። ትራምፕ፤ በፑቲን “መበሳጨታቸውን” ነገር ግን ጉዳዩ “አለማለቁን” መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም