
በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጄሪያ አቡኩታ በተከናው የአፍሪካ ከ18 ዓመትና 20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ለተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን የዕውቅና ሽልማት መርሃግብር መዘጋጀቱ ታውቋል።
በሁለቱም የዕድሜ ገደብ 10 ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ወጣት አትሌቲክስ ቡድን ትናንት ምሽት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የእንኳን ደህና መጣችሁ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ይህንንም ተከትሎ ዛሬ ለቡድኑ አባላት የማበረታቻ ሽልማትና ዕውቅና መርሃግብር የሚከናወን መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የአትሌቲክሱን ዓለም በቀጣይ የሚረከቡ ተተኪ አትሌቶች ያገኙትን ስልጠና በተግባር የሚመዝኑባቸው ውድድሮች አስፈላጊ ናቸው፡፡ የውድድር መድረኮች በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ ሲዘጋጁ ደግሞ ለቀጣይ ሕይወታቸው መሠረት የሚሆናቸውን ልምድም ለመቀመር ያስችላቸዋል፡፡ በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን አዘጋጅነት የሚካሄደው አህጉር አቀፉ ከ 18 እና 20 ዓመት በታች ቻምፒዮናም ዓላማው ይህ ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት አትሌቶችን ለቀናት ሲያፎካክር ቆይቶ ማጠቃለያውን አግኝቷል፡፡
የአትሌቶች ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያም ተስፋ ባላቸው ታዳጊና ወጣት አትሌቶቿ መወከሏ የሚታወቅ ነው፡፡ በናይጄሪያ ደቡብ ምዕራብ ክፍል በምትገኘው የአቡኩታ ከተማ በተከናው በዚህ ውድድር ላይ በአትሌቲክስ ስፖርት አጭርና ረጅም ርቀት እንዲሁም በርምጃ ውድድሮች 28 አትሌቶቿን ስታሳትፍ ቆይታለች። በዚህም 2 የወርቅ፣ 3 የብር እና 5 የነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎች ተመዝግበዋል፡፡ ለአምስት ቀናት በተከናወነው በዚህ ውድድርም ወጣት አትሌቶቹ የሀገራቸውን ስም በድል ለማስጠራት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሲሆን፤ በዚህም ተተኪነታቸውን ለማስመስከር ችለዋል ሊባል ይችላል፡፡ በሁለቱ የዕድሜ ገደቦች በተደረገው ፉክክርም ከ18 ዓመት በታች ቡድኑ በርካታ ሜዳሊያዎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
ለኢትዮጵያ የተመዘገቡት ሁለቱ የወርቅ ሜዳሊያዎች በ18 ዓመት በታች ሴት አትሌቶች የተገኙ ሲሆን፤ የ5ሺህ ሜትር ተፎካካሪዋ ሕይወት አምባው እና የ800 ሜትር ተስፈኛዋ አትሌት ኤልሳቤጥ አማረ አሳክተዋቸዋል፡፡ በ 1 ሺህ 500 ሜትር ኤልሳቤጥ አማረ እንዲሁም በ3 ሺህ ሜትር አትሌት ደስታ ታደሰ ደግሞ የብር ሜዳሊያዎቹን በማስመዝገብ ኢትዮጵያ በሁለቱ ርቀቶች ያላትን አቅም ለማሳየት ችለዋል፡፡ በ 1 ሺህ500 ሜትር ደስታ ታደሰ፣ በ 3ሺህ ሜትር ብርነሽ ደሴ እና በ 400 ሜትር ባንቺአለም ቢክስ የነሃስ ሜዳሊያውን በሴቶች ዘርፍ ሲያስገኙ አትሌት ሳሙኤል ገብረሃዋር ደግሞ በ1 ሺህ500 ሜትር በወንዶች የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ከ20 ዓመት በታች በተከናወነው ውድድር ደግሞ በ 3 ሺህ ሜትር ርቀት በአትሌት ትርሃስ ገብረሕይወት ብቸኛው የብር ሜዳሊያ ሲመዘገብ በ800 ሜትር ወንዶች ደግሞ ሲሳይ አለቤ የነሃስ ሜዳሊያውን አጥልቋል፡፡ በአጠቃላይ ውጤት ሲለካ ከ18 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን የተሻለ ውጤታማ ሲሆን፤ ሴት አትሌቶች አብላጫውን በመውሰድም ብቃታቸውን አስመስክረዋል። አትሌት ደስታ ታደለ ደግሞ በሁለት ርቀቶች የሜዳሊያ ዘንጠረዥ ውስጥ በመግባት ተደናቂ አትሌት ልትሆን ችላለች፡፡ ቻምፒዮናው በሩጫ፣ የሜዳ ተግባራትና ርምጃ የተካሄደ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አብዛኛው ትኩረት በመካከለኛና ረጅም ርቀቶች ላይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ቻምፒዮና ግን ከ18 ዓመት በታች በ400 ሜትር ርቀት የነሃስ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለች አትሌት መታየቷ በርቀቱ ቢሠራበት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያስመሰከረ ሆኗል፡፡
በ 1 ሺህ 500 ሜትር እንዲሁም 3 ሺህ ሜትር የተገኙት በርካታ ሜዳሊያዎች በርቀቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን የበላይነት እንደሚያስቀጥል የሚጠቁምም ነው፡፡ በአንጻሩ ከ20 ዓመት በታች በተካሄደ ውድድር ኢትዮጵያውያን ያገኟቸው ጥቂት ሜዳሊያዎችና ከውድድሩ አስቀድሞ በተከናወነው የእድሜ ማጣሪያ ወቅት የታየው የተገቢነት ችግር ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ዘርፍ ስለመሆኑ በግልጽ ያመላከተ ሆኗል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም