ዳንኤል ዘነበ
በተለይ ከአፍላ ወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዞ ከሚከሰቱ እና የቆዳ ውበትን በመቀነስ የስነ ልቦና ጫና ከሚፈጥሩ ነገሮች መካከል አንዱ ብጉር ነው። በተለያዩ የቆዳ ህክምና መስጫዎች ለህክምና ከሚያቀኑ ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከብጉር ጋር በተያያዘ ነው። ብዙዎቹ ቆዳቸው በብጉር ምክንያት በተከሰቱ ጠባሳዎች ከተጎዳ በኋላ ነው ወደ ህክምና የሚያመሩት። በዚህ ደረጃ ላይ ደግሞ ህክምና ያን ያህል መፍትሄ የማይሰጥ በመሆኑ አጥጋቢ መፍትሄ ሳያገኙ ይመለሳሉ።
ብጉር በብዛት የሚታየው በትከሻ፣ የላይኛው የደረት ክፍል እና ጀርባ ላይ ሲሆን በሁለት የዕድሜ ክልል ውስጥ በብዛት ይገኛል። የመጀመሪያው በጨቅላነት ወይም የህፃንነት ጊዜ ሲሆን በዚህ ወቅት 20 በመቶ በሚሆኑት ላይ ይከሰታል። ይህም የሚከሰተው ከእናትየዋ በእርግዝና ወቅት ወደ ህፃኑ በሚተላለፍ ሆርሞን አማካኝነት ነው። ሌላኛው ወቅት ደግሞ አፍላ ወጣትነት ሲሆን አንዳንዴ ብጉር የዚህ ዕድሜ ክልል መግቢያ ማሳያ እየተደረገ ይወሰዳል። በዚህ ወቅት በወንዶች ከ16 እስከ 19 ዓመት እና በሴቶች ደግሞ ከ14 እስከ 17 ዓመት ባሉ ላይ በብዛት ይወጣል።
ብጉር ከ20 እስከ 25 ዓመት የዕድሜ ክልል (90 በመቶ) በሚሆኑት ሰዎች ላይ ቀስ እያለ በመቀነስ በመጨረሻ የመጥፋት አዝማሚያ የሚያሳይ ሲሆን በጥቂት ሰዎች ላይ ግን ከ25 ዓመት በኋላ በተለይም ሴቶች ላይ እስከ ሰላሳዎቹ እና ከዚያም በላይ ሊቆይ ይችላል።
ብጉር እንዴት ይፈጠራል?
ብዙ ጊዜ የሚከሰተው የዘረ መል ተጋላጭነት ከእናት ወይም ከአባት ወይም ከሁለቱም ባለ ጊዜ ነው። ይህ ሁኔታ ሁሌም ይከሰታል ማለት ግን አይደለም። የዘረ መሉ ውርስ ሙሉ ላይሆን እና የተወሰነ ትውልድንም ሊያልፍ (Genetic Skip) ይችላል። ከዘረ መሉ ተጋላጭነት ጋር ተዳምሮ ብጉር ለመከሰት አራት መሰረታዊ ደረጃዎች አሉት። እነዚህም፡-
1. በላይኛው የፀጉር መውጫ ህዋሳት በብዛት በመራባት እና አንድ ላይ በመያያዝ የቆዳ ቀዳዳዎችን መድፈን፤
2. ቅባት መሰል ፈሳሽ የሚያመነጩ እጢዎች በብዛት መመረት፤
3. የቆዳ መቆጣት እና
4. በተፈጥሮ በቆዳ ላይ የሚገኝ ባክቴሪያ መኖር እና በብዛት መራባት ናቸው።
የቆዳ ቀዳዳዎቹ በሚራቡት ህዋሳት ምክንያት በመዘጋታቸው በብዛት የተመረተው ቅባት መሰል ፈሳሽ ባክቴሪያ እና ሌሎችም በቆዳ ውስጥ በመከማቸት ትንንሽ እብጠቶችን ይፈጥራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ባክቴሪያው ትራይግላይስራይድ የሚባል የቅባት አይነት ወደ ቅንጣት ነፃ አይነት ቅባቶች በመቀየር ሰውነት እነዚህ ቅባቶች ላይ ጥቃት በሚያደርስበት ጊዜ የቆዳ መቆጣትን በማስከተል የሚያሙ ብጉሮች ይፈጠራሉ።
በቆዳ ውስጥ ክምችቱ ከመጠን በላይ የሚገባ ሲሆን የሰውነትን መቆጣት በማባባስ ትልልቅ እብጠቶች አንዳንዴም መግል አዘል የሚመስሉ እብጠቶችን በቆዳ ላይ ሊያስከትል ይችላል። በአጠቃላይ ብጉር ክፍት ትንንሽ እብጠቶችን (ጫፋቸው ጠቆር ያሉ)፣ ዝግ ትንንሽ እብጠቶችን (ጫፋቸው ነጭ የሆኑ)፣ ቀላ ያሉ፣ የሚያሙ እና መግል አዘል የሚመስሉ እብጠቶችን አንዳንዴም በጣም የከፋ ሲሆን ትልልቅ እብጠቶችን ሊያስከትል ይችላል። የእነዚህም ጦስ ቆዳ ላይ ቋሚ ጠባሳና ጥቁረት መከሰት ነው።
ብጉርን የሚያባብሱ ነገሮች ምንድናቸው?
• ብጉርን ማፍረጥ፡- ይህ ሁኔታ ብዙ ሰዎች ላይ የሚስተዋል ሲሆን ይኸውም የብጉር መንስኤ የሆነውን ባክቴሪያ ከአንድ የቆዳ ቀዳዳ ወደ ሌላ በማዛመት ብጉሩ እንዲባባስ ያደርጋል። በተጨማሪም ብጉሩ በሌሎች ቆዳ ላይ በሚገኙ አደገኛ ባክቴሪያዎች እንዲመረዝ በማድረግ እና በቆዳ ላይ ጠባሳና መጥቆር በማስከተል ዘላቂ የሆነ ችግር ይፈጥራል።
• ፊትን በተደጋጋሚ እና ቆዳው እስኪጎዳ ድረስ መታጠብ
• ቆዳን የሚጎዱ የቆዳ ማፅጃዎችን መጠቀም
• ቆዳን በጨርቅ መፈግፈግ
• ቅባት አዘል የሆኑ መዋቢያዎችን መጠቀም
• ፊትን በእጅ መደገፍ ወይም ስልክ ረዘም ላለ ጊዜ ፊት ላይ መያዝ
• ጭንቀት
• ቀዝቃዛ የአየር ጸባይ
• በቅድመ የወር አበባ ወቅት፡- ብጉር 70 በመቶ በሚሆኑ ሴቶች ላይ የወር አበባ ከ2 እስከ 7 ቀን ባሉ ቀኖች ውስጥ ከመምጣቱ በፊት የመባባስ ምልክት ሊኖር ይችላል። የሚቀጥለው የወር አበባ ዑደት ሲጀምር ግን ይሻሻላል።
• ለተለያዩ የበሽታ አይነት የምንወስዳቸው መድሃኒቶች ብጉርን ሊያባብሱም ይችላሉ።
የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያህል ኮርቲኮስቴሮይድ (በብዛት ለልዩ ልዩ የቆዳ በሽታ ይሰጣል)፣ የሚጥል በሽታ መድሃኒቶች፣ ፀረ ቲቢ መድሃኒቶች በተለይም አይሶናዚድ የሚባለው በተወሰኑ በሽተኞች ላይ ብጉር ሊያስከትል ይችላል፤ ለአዕምሮ ህሙማን የሚሰጡ መድሃኒቶች ወዘተ… ናቸው። አንዳንድ ሴቶች ላይ የብጉር መኖር የተወሰኑ በሽታዎች ማሳያ ምልክት ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ፣ አንዲት ሴት ከብጉር በተጨማሪ የወር አበባ ዑደት መዛባት፣ የወሲብ ፍላጎት መቀየር እና ባልተለመደ ቦታ ላይ ፀጉር ማብቀል ምልክት ካላት የሆርሞን መዛባት ችግር ማሳያ ሊሆን ይችላል። የብጉርን ህክምና በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።
መሰረታዊ የቆዳ እንክብካቤ ማድረግ
የቆዳ ንፅህናን በሚገባ መጠበቅ ብጉርን በመከላከል እና እንዳይባባስ በማድረግ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህም ፊትን በቀን ሁለት ጊዜ ሞቅ ባለ ውሃ እና ቆዳ ላይ ጉዳት በማያደርስ ሳሙና በጣታችን ጫፎች መታጠብ።
ቆዳ በሚደርቅበት ወቅት ብጉር አምጪ ያልሆኑ የቆዳ ማለስለሻዎችን መጠቀም በቅርብ ጊዜ ከቆዳ ብጉር ጋር ተያይዞ የሚመጣ የቆዳ መጥቆርን ለመከላከል የፀሐይ መከላከያ ወይም ‹‹ሰን ስክሪን›› ቅባቶችን መጠቀም እና ከላይ የጠቀስኳቸውን ብጉርን የሚያባብሱ መንስኤዎችን ማስወገድ ናቸው።
በመድኃኒት ማከም
የብጉር መድሃኒቶች በሐኪም የሚታዘዙ ሲሆን የመድሃኒቶቹ ምርጫ እንደየብጉሩ አይነት እና አፈጣጠር ምክንያት የተለያየ ነው። እነዚህም በቆዳ ላይ የሚደረጉ ወይም በአፍ የሚወሰዱ ሲሆን ተግባራቸውም አንዳንዶቹ የተደፈነውን የቆዳ ቀዳዳ የሚከፍቱ፣ የቆዳ መቆጣትን የሚቀንሱ እና ሌሎቹ ደግሞ የፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች ሊሆኑ ይችላሉ።
በመጨረሻም በብጉር ምክንያት በቆዳ ላይ ቋሚ የሆነ ምልክት ከመፈጠሩ በፊት ወደ ጤና ተቋማት በተለይም የቆዳ ሐኪሞች ወደሚገኙበት በመሄድ ተገቢውን ምክር እና ህክምና ማግኘት አስፈላጊ ነው።
ምንጭ፡- ጤናአዳም ዶት ኮም
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013