ሰላማዊት ውቤ
ግብርና ለሀገራችን ኢኮኖሚ መሰረት ነው።እንደ ሀገር ይህን ዘርፍ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን፣ሥራውን የሚያቀላጥፉ ቴክኖሎጂዎችን እና የተሻሻሉ ግብዓቶችን መጠቀም ዘርፉን ውጤታማ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል።ባለፉት ሁለት አመታት በቴክኖሎጂ በታገዘ የሰብል ልማት፣የእንስሳት እርባታና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ አርብቶና አርሶ አደሮችንም መፍጠር ተችሏል።የግብርና ሥራውን በማገዝ በቅርቡ በአዳማ ከተማ በተከናወነው የዕውቅና ሽልማት የኦሮሚያ ክልል በግብርናው ውጤት ካስመዘገቡት መካከል አንዱ በመሆን ለሽልማት በቅቷል።
የክልሉ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊው አቶ ዳባ ደበሌ በክልሉ ስለተሰሩት ሥራዎች እንደገለጹት፣ ምርትና ምርታማነት የሚጨምሩ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተከናወነ ሲሆን፣ለአሰራሮቹ የዘርፉ አመራር ሚና ጉልህ ነበር።እንደ ዩሪያ፣ዳፕ፣ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ በማድረግ ሕብረት ሥራ ማህበራት፣የተጫወቱት ሚናም ቀላል አልነበረም።
ባለሙያዎች፣ የመስኩ ተመራማሪዎች፣ባለሀብቶች፣ባለ ድርሻ አካላትም የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ የተሻሻሉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማፍለቅና በማቅረብ ትልቅ አስተዋጽ አበርክተዋል።
በዚህ መልክ 350 የእርሻ ትራክተሮችና 80 ኮንባይነሮች እንደ ክልል ለአርሶ አደሩ ቀርበዋል።አርሶ አደሩ እነዚህን በመጠቀም ሥራውን በማቅለልና ጉልበቱን በመቆጠብ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግብ አስችለዋል።
የስንዴ መዝሪያ፣ የጤፍ፣ስንዴና ገብስ መውቂያ፣የእርሻ ማረሻ ትራክተር ውጤት ማስመዝገብ ከቻሉት መካከል ይጠቀሳሉ።በቀጣይም አርሶ አደሩ እነዚህን የግል ባለሀብቶች አርሶ አደሮችን ለመደገፍ የመርሐ ግብሩ አንድ አካል በሆነው የግብርና አውደ ርዕይ ይዘዋቸው የቀረቡትን ጭምር ቴክኖሎጂዎች በስፋት በመተዋወቅና በመጠቀም የግብርና ሥራዎችን የላቀ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል አቶ ዳባ።
በክልሉ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች ጭምር በመታገዝ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የተገኘው የግብርና ሥራ ውጤት ከዚህ ቀደም በነበሩ ዓመታት ከተገኘው በእጅጉ የተለየና የላቀ ነው።መንግሥት ቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ እንዲውል ፍኖተካርታ በማዘጋጀት ጭምር እገዛው ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።
እንደየክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ ሁሉም ክልሎች ፍኖተ ካርታውን መነሻ በማድረግ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣የኦሮሚያ ክልልም የባለፉት ሁለት ዓመታት የግብርና ሥራውን ውጤት ልዩ የሚያደርገውም ይሄንኑ አቅጣጫ በመከተልና በዕውቀት የተመራ ሥራ በማከናወኑ ነው።ኃላፊው ሌላውን በክልሉ ውጤት ማስመዝገብ የቻለውን ጉዳይም አጫውተውን ነበር።ይሄውም በክልሉ አርሶና አርብቶ አደሩ ውጤታማ እንዲሆን አራት ዋና ዋና ግቦች መቀመጣቸው ነው።
አንደኛው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ሁለተኛው ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችን በጥራት ማምረት፣ሦስተኛው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን ማስቀረት የሚሉ ናቸው።ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደ ክልል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ሀገር የሚገባውን የስንዴ ምርትና ሌሎችንም በሀገር ውስጥ በማምረት ወጭና ማዳን ነው።በዚሁ መሠረትም ስንዴን በሀገር ውስጥ በስፋትና በጥራት የማምረት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል።
ሌላው በዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ሲሰራበት የነበረው በእነዚህ በተቀመጡ ግቦች መሠረት ለክልሉ ሕዝብ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ነበር።ክልሉ በሁለት ዓመት ውስጥ የክልሉ አርሶና አርብቶ አደሮች ፣ የግብርናውን ውጤት የሚጠቀሙ የንግዱ ማህበረሰቦች፣ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡ እንዲሁም ከሀገር ወደ ውጪ የሚልኩ ጭምር በሰፊው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።በአጠቃላይ በሁለት ዓመት በክልሉ ግብርናው ወደ ስርዓት ገብቶ ውጤት አስመዝግቧል።
‹‹የግብርና ውጤት ገበያውም ቢሆን ከካች አምና፤ አምና ፤ከአምናም በተለይ በዘንድሮ ዓመት ጥሩ በሚባል ሁኔታ መረጋጋት እያሳየ ነው›› ያሉት አቶ ዳባ ምክንያቱ የምርት መጨመር እንደሆነ ይገልጻሉ።‹አርብቶ አደሩንና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ምርት በየጊዜው መጨመር አለበት ብለን እናስባለን› ሲሉም ለምርት መጨመር ምክንያት የሆነውን ጉዳይ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።አሁን ላይ አርሶ አደሩ የልፋቱን ዋጋ እያገኘ እንደሆነ አመልክተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ከዚህ በፊት የነበረው የገበያ ስርዓት ግን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነበር።አንዱና ዋንኛው ችግር ደግሞ በግብይት ስርዓቱ ውስጥ ደላሎች የገቡበት ሁኔታ መኖሩ ነው ።እነዚህ ደላሎች ከአርሶ አደሩ እየገዙም ቀጥታ ለአዲስ አበባ ያቀርቡ ነበር።ትልቁን ጥቅም ወይም ትርፍ የሚያገኙትም በብዙ ድካምና ልፋት ምርቱን ያመረተው አርሶ አደር ሳይሆን እነዚሁ ደላሎች ነበሩ።
በዚህ የተነሳ አብዛኛው አርሶ አደር በኑሮው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሳያመጣ ‹እዛው ሞላ እዛው ፈላ› የሚሉት ሕይወት ዓይነት ለመግፋት ተገዶ ቆይቷል።የሥራ ተነሳሽነቱም ቢሆን ከዚሁ የተሻለ አልነበረም።
‹‹በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ›› እንዲሉት እኔ በደከምኩት የሚጠቀመው ሌላው ወገን ከሆነ ብሰራም ባልሰራም ለውጥ አላመጣም በሚል ትጋቱን ያሳነሰበት ተጨባጭ ሁኔታ ገጥሟል። በተጨማሪም አርሶ አደሩ ጋርና በገጠር የነበረው የምርት ዋጋ እጅግ ሰፊ ልዩነት ያለው ነበር።በገጠር ደላላው እጅግ በዝቅተኛ ዋጋ ነው ከአርሶ አደሩ ምርት ይገዛ የነበረው።ሆኖም ምርቱን አዲስ አበባ ላይ የሚሸጠው በውድ ዋጋ ነበር።ይሄ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ትልቅ የኑሮ ውድነት ጫና ፈጥሮ ቆይቷል።
አሁን ላይ ቢሮው በማሀል ያለውንና ችግሩን የሚፈጥረውን ደላላ አውጥቷል።አርሶ አደሩና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበትን ድልድይም አመቻችቷል።በዚህም በገጠርና በአዲስ አበባ ያለው የምርት ዋጋ ተቀራራቢ ሆኗል።የነበሩት ችግሮች በሁለት ዓመቱ በዕውቀት የተመራ አሰራር ሙሉ በሙሉ ተፈትተዋል። እነዚህን ችግሮች መፍታት እንዲሁም አርሶና አርብቶ አደሩ ቀላል፣ ሥራውን የሚያቀላጥፉና ጉልበቱን የሚቆጠቡ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀምና ምርቱን እንዲያመርት መደረጉ ባለፉት ሁለት ዓመታት ለመጣው ዕድገት ጉልህ ሚና ተጫውቷል በማለት ኃላፊው አቶ ዳባ ሀሳባቸውን ቋጭተውልናል።
በእውቅና ሽልማት ሥነሥርአቱ ላይ ካገኘናቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂ አስመጪና አቅራቢዎች መካከል አቶ መልኬሶ ገነሞ ከኬንያ የእርሻ መሣሪዎች አቅራቢ ድርጅት አነጋግረናል።አቶ ሜልኬሶ እንዳስረዱት ድርጅታቸው ከኦሮሚያ ክልል ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት የሚሰራ ሲሆን፣ከእርሻ ማረሻ እስከ ምርት መሰብሰቢያ ድረስ አርሶ አደሩን የሚያገለግሉ የእርሻ መሣሪያዎችን ለአርሶ አደሩ ያቀርባል። ባለ ሦስት፣ባለ አራትና ባለ አምስት ማረሻ ትራክተሮች ከምርቶቻቸው መካከል ይጠቀሳሉ።
ለትራክተሩ የሚመጥኑ ማረሻና መከስከሻዎችም ተካትተውበታል። በቆሎ፣ ስንዴና ሌሎች የዘር ዓይነቶችን በመስመር የሚዘራ ቴክኖሎጂም ተገጥሞለታል።በዚሁ ላይ ኬሚካል የሚረጭም ማሽን በጋራ ይዟል።የአርሶ አደሩን ጉልበትና ጊዜ በሚቆጥብ ሁኔታ ገለባውን ቤለር በተባለው ማሽን አማካኝነት የመለየት ተግባር ይከናወናል።
በማሽኑ እገዛ እህሉ ከገለባው የተለየውም ታስሮ ለከብት መኖ ይውላል።በነዚህ መሣሪዎች 70 በመቶ የሚሆኑ የኦሮሚያ፣ደቡብና አማራ ክልል አርሶ አደሮች ተጠቅመው ውጤት አግኝተውባቸዋል። በነዚህ አካባቢ ያሉ በመሳሪያው ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በአስተራረሳቸው፣በምርት አሰባሰባቸው፣በአኗኗራቸው መቶ በመቶ ለመቀየር ችለዋል።
የዛሬ ሦስት ዓመት እነዚህን ማሽኖች በጋራ የገዙ አርሶ አደሮች አሁን ላይ እራሳቸውን ችለው ማሽኖቹን ገዝተው መጠቀም ጀምረዋል።በጣም አነስተኛ የሚባለው ትራክተር እስከ ዘጠኝ መቶ ብር፣ከፍተኛው እስከ ሦስት ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሲሆን አርሶ አደሩ ማሽኖቹን በዚህ ዋጋ በመሸመት እየተጠቀመ ይገኛል።ይሄን የኢኮኖሚ አቅም የፈጠረላቸው ደግሞ ራሱ ማሽኑ ነው። ማሽኑ ምርታማ ባያደርጋቸው እንዲህ ዓይነት እሱን መልሰው እስከ መግዛት የሚያደርስ አቅም እንደማይኖራቸው መልኬሶ አጫውተውናል።
እርሳቸው እንዳሉት በዘንድሮ ታህሳስ ወር ምርት ለመሰብሰብ ከውጪ ያስገቡት ኮንባይነሮች 80 ሲሆን፤ 77ቱ ወደ ማሳ በመውጣት በሥራ ላይ ውለዋል።በምርት ስብሰባው የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ወረታ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ግሩፕ ትራክተር አስመጪ ድርጅት ወደ ሥራ ከገባ ሁለት ዓመቱ ነው።የሽያጭ ሠራተኛዋ ወጣት ሕይወት እንዳለው እንዳስረዳችን ድርጅቱ በሁለት ዓመት ውስጥ 300 ትራክተሮች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለአርሶ አደሩ አስረክቧል። ደንበኞቻቸው በኦሮሚያ ክልል ባሌ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ናቸው።ለእነዚህ አርሶ አደሮች 60 ትራክተሮች ተሰራጭቷል።126 ኤች ፒ የተሰኘው ትራክተር ሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሲሆን፤እንዲህ ዓይነቱን ትራክተር አርሶ አደሮች በጋራ ተደራጅተው ነው የሚገዙት።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013