ዳንኤል ዘነበ
የዲስክ መንሸራተት ተብሎ የሚጠራው የአጥንት ህመም ብዙም ትኩረት ካልተሰጣቸው የአጥንት ህመሞች መካከል አንዱ ነው። የዲስክ መንሸራተት ማለት በሁለት የጀርባ አጥንቶች መካከል የሚገኘው እና የአጥንቶቹን መነካካት የሚቀንሰው ዲስክ ወደፊት እና ወደኋላ ወይም ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ በኩል ቦታውን ለቆ በሚንሸራተትበት ወቅት የሚከሰት ችግር ነው።
ተጋላጭነትዎን የሚጨምሩ ነገሮች
የሰውነት ክብደት፡- ክብደትዎ ከመጠን በላይ የጨመረ ከሆነ በጀርባ አጥንትዎና ዲስኩ ላይ ጫና ይፈጥራል።
የስራዎ ሁኔታ፡- የስራቸው ፀባይ ጉልበት የሚጠይቅ ስራ የሚሰሩ ሰዎች ከሌሎች ይልቅ ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ። በተደጋጋሚ ከባድ ነገር የሚያነሱ፣ የሚጎትቱ፣ የሚገፉ፣ ወደ ጎን መታጠፍና መጠማዘዝ የሚያበዙ ሰዎች ለችግሩ ተጋላጭ ይሆናሉ።
በዘር የሚመጣ፡- አንዳንድ ሰዎች ለመሰል ችግር ተጋላጭነታቸው መጨመር በዘር ሊወረስ ይችላል።
የአኗኗር ዘይቤ ለውጥና የቤት ውስጥ ህክምና
የህመም ማስታገሻ፡- ያለሐኪም ትዕዛዝ ሊወሰዱ የሚችሉ እንደ አይቡፕሮፌን/ አድቪል/ መውሰድ።
ሙቀት/ቀዝቃዛ ነገር መጠቀም፡- በመጀመሪያ ቀዝቃዛ ነገር ቦታው ላይ መያዝ ህመሙንና መቆጥቆጡን እንዲቀንስ ይረዳል። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ሙቅ ነገር መያዝ ምቾትና የህመም ፈውስ እንዲሰማዎ ስለሚያደርግ በቦታው ላይ መያዝ።
ከመጠን ያለፈ እረፍት ያለማድረግ/ማስወገድ፡- ከመጠን ያለፈ እረፍት የመገጣጠሚያዎች መጠንከር/መተሳሰር እና ጡንቻዎች መስነፍ እንዲመጣ ስለሚያደርግ የፈውሱን ጊዜ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል። ይልቁንም በሚመችዎ አቅጣጫ ለ30 ደቂቃዎች እረፍት ማድረግና ከዚያን ለአጭር ጊዜ ወክ ማድረግ አሊያም የተወሰኑ ስራዎችን ማከናወን። ከህመምዎ እያገገሙ ባሉበት ወቅት ህመሙን ሊያባብሱ ከሚችሉ ድርጊቶች/እንቅስቃሴዎች መቆጠብ።
የዲስክ መንሸራተት በሚኖርበት ወቅት የሚኖሩ የህመም ምልክቶች
የእጅ/የእግር ላይ ህመም፡- የዲስክ መንሸራተቱ ያጋጠመው በታችኛው የጀርባ አጥንቶች አካባቢ ከሆነ ከፍተኛ ህመም በመቀመጫዎ፣ በጭንዎና በባትዎ አካባቢ እንዲሁም መርገጫዎ/የእግር መዳፉ ላይ ሊሰማዎ ይችላል።
የዲስክ መንሸራተት ያጋጠመዎ አንገትዎ ላይ ከሆነ ህመሙ በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰማዎ በትከሻና በእጅዎ ላይ ነው። ሕመሙ በሚያስሉበት፣ በሚያስነጥሱበት ወቅት ወይም ወደ ተወሰነ አቅጣጫ የጀርባ አጥንቶችዎን በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት ሊባባስ ይችላል። የመደንዘዝ ወይም የመጠቅጠቅ ስሜት ይኖራል።
የእጅ/ እግር መስነፍ፡- በዲስክ መንሸራተት ምክንያት የተጎዳ ነርቭ ካለ ያ የተጎዳው ነርቭ እንዲሰራ የሚያደርገው ጡንቻ ሊደክም ይችላል። በዚህ የተነሳ መራመድ መቸገር፣ እቃ ማንሳት ያለመቻል ወይም መያዝ ያለመቻል ሊከሰት ይችላል።
የዲስክ መንሸራተትን እንዴት መከላከል ይቻላል?
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፡- የጀርባ ጡንቻዎችን ለማጠንከር ስለሚረዳ የጀርባ አጥንቶችን ለመደገፍና ለማረጋጋት ይረዳል።
ትክክለኛ የሰውነት አቋም/ Maintain good posture / እንዲኖርዎ ማድረግ፡- ጥሩ የሰውነት አቋም ካለዎ በጀርባ አጥንትዎና ዲስኩ ላይ የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ ይረዳዎታል። ለረጅም ጊዜ የሚቀመጡ ከሆነ ቀጥ ብለው ለመቀመጥ መሞከር። ከባድ እቃ በሚያነሱበት ወቅት ስራውን/ ክብደትዎን ከጀርባዎ ይልቅ በእግሮችዎ ላይ ማድረግ።
ክብደትዎን በትክከል መጠበቅ፡- ከመጠን ያለፈ ክብደት በጀርባ አጥንትዎና ዲስክዎ ላይ ጫና ስለሚፈጥር ክብደትዎን መቆጣጠር ያስፈልጋል።
ምንጭ፦ የዶክተር አለ
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013