ኢትዮጵያውያን በምን እንታወቃለን የተባለ እንደሆነ ከዓለም እንደቀደመ በምናምነው ስልጣኔ ብቻ አይደለም፡፡ የእኛ በሆኑ ሰዋዊ ሀብቶችም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ትህትና፣ ለሰብአዊ ፍጡር የሚሰጥ አክብሮት፣ በማንነት ኩራትና ክብር እንዲሁም ታዛዥነት የኢትዮጵያዊ መገለጫዎች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ አሁንስ? አሁንማ ሁሉም ነገር ውድ በሆነበት ጊዜ ይኸው እነዚህም ውድ ሆነውብናል፡፡
ነገሩን እንደልብ አንጠልጣይ ፊልም ግነት አበዛሁበት መሰለኝ፡፡ እሺ ሳላጋንን፤ «ታዛዥነት ወዴት ገባች?» የሚል መጽሐፍ ይዘጋጅ ይሆን? በጣም ውድ ከሆኑና እየጠፉብን ካሉ ሀብቶቻችን መካከል መታዘዝ አንዱ ይመስለኛል። በአገራችን ያለውን ሁኔታ እያንዳንዱን ስናይ መነሻውም አለመታዘዝ ነው፡፡ አንዱ ጅብ ሌላው ውሻ ሆኖ፤ መንገዱን ባለመታዘዝ እየቀደዱ መሄድ ብቻ፡፡
ይሄ ሁሉ ለአገሩ የማይታዘዝ ሰው ግን ቤቱ ገብቶ ልጆቹ እንዲታዘዙት ይፈልጋል? ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስብሰባ ስም የሚወጣው ወጪ አስደንጋጭ እየሆነ መምጣቱንና እንዳላቆመ ተዘግቦ ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ስብሰባ ቀንሱ፤ ደንበኛ እናንተን ብሎ መጥቶ በስብሰባ ሰበብ እንዳያጣችሁ፤ ከተሰበሰባችሁም በእረፍት ቀን አድርጉት ሲባሉ፤ ለካ «በአንድ አፍ!» ብለዋል፡፡
ከዛ ቅዳሜና እሁድ «ዊኬንድ»ን ከአዲስ አበባ ወጣ ብለው፤ አዳማ ላይ መሰብሰብ፡፡ «ለምን?» አጋጣሚውን ለመጠቀምና አገር ለመጎብኘት፤ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ከፍ ለማድረግ ማለት ነው። የሆነው ሆኖ እንደተቋምም አለመታዘዝ እንዳለ ተገልጾልኛል፡፡ ነገሬ ለምን ከከተማ ተወጣ ሳይሆን፤ በዚህ አካሄድ የአንድ ለአምስት ሳምንታዊ ግምገማ የሚባለው የስብሰባ ዓይነትም ከከተማ ወጣ ተብሎ ይከናወን በሚል ሰበብ፤ ጉዞው እለታዊ እንዳይሆን በመስጋት ነው፡፡
ጥሩ! መዋዕለ ነዋይን ከከተማ ወጣ ብሎ ማፍሰስ ተገቢ ነው፡፡ እንግዲህ ወይ ለብቻው በጀት መመደብ ነዋ! አስታውሳለሁ ከዓመት ወይም ከሁለት ዓመት በፊት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አንዳንድ አላስፈላጊ ወጪዎችን እንዲቀንሱ ተብሎ የኮፍያ፣ ካላንደር ወዘተ የመሳሰሉ የህትመት ወጪዎች እንዲሁም ድግሶች እንዲቀሩ ተብሎ ነበር፡፡ ይህን ባዩ ደግሞ ገንዘብና ኢኮኖሚውን የሚከታተለው ሚኒስቴር ነው፡፡
ተቋማቱ ለዚህ ትዕዛዝ ታዛዥ ነበሩ ወይ? አልነበሩም፡፡ በእርግጥ በጣም ቆጣቢ ይሁኑና፤ እንደእኛ መሥሪያ ቤት በአሥራ ዘጠኝ ሰማንያዎቹ መጨረሻ የተቋማቸውን ዓርማ ይዞ በታተመ ማስታወሻ ደብተር ይጠቀሙ እያልኩኝ አይደለም፡፡ ግን ቢያንስ በጥቂቱ መታዘዝ ጥሩ ነበር፡፡
ጭራሽ ስብሰባ ቀንሱ ሲባል ወጪ መጨመር? ጉድ!
በብዙ እንቅስቃሴዬ መገናኛ የሚሉትንና አንድ ወዳጄ ‹‹መጠፋፊያ እንጂ መገናኛ ሊሆን አይችልም!›› የሚለውን ሰፈር ሳልረግጥ አላልፍም፡፡ እውነቱን ነው! ብዛታችን ቁልጭ ብሎ የሚታየው እዚህ አይደለም እንዴ? ታድያ በዚህ መንገድ ትልልቅ ሰዎች፤ የሚገራው እንደሚፈልግ እንደ ትንሽ ልጅ ሲሆኑ ሳይ ብስጭት እላለሁ፡፡ ይህን ‹በጎ ፈቃደኛ የመንገድ ትራፊኮች› ይናገሩት፡፡
ጠዋት ቀድመው የሚወጡትና ጸባያችንን አውቀው ሳይሰለቹ የሚያስተናግዱት እነዚህ ወጣቶች ስንቱን አይተዋል? እንዴት ነፍስ ያወቀ ሰው፤ «መኪና ይበላሃል! አሁን የመኪኖች ተራ ነው፤ ጥቂት ታግሰህ ቁምና ታልፋለህ» ሲባል፤ አሻፈረኝ ይላል? በመስመር ሂዱ፣ ወደዳር አትውጡ፣ እያያችሁ ተሻገሩ፣ ተረጋጉ፣ ስትሻገሩ ዜብራውን የባለስልጣን ቢሮ ምንጣፍ እንደረገጠ ሰው አትጠንቀቁለትና ራመድ በሉ… ይላሉ አስተናባሪዎች፤ ሰሚ ግን የለም፡፡
ታዘቡን! ራሳችንን ታዘቡ! መሥሪያ ቤት ቢሄዱ ቁጭ ብሎ እስክርቢቶ እየበሉ የሻይ ሰዓት ለመጠበቅ ነው፤ ከፍ ካለ ለመሰብሰብና ፊርማ ሳይነሳ ለመድረስ፤ ወዲህ ደግሞ ቆም ብለው ከወዳጅ ጋር «እገሌ ፖስት ያደረገውን አየሽ? እንትና ያለውን ሰማሽ?» ሲባባሉ እልፍ የሚለውን ሰዓት ማንም ልብ አይልም። መንገድ ላይ ግን ሯጭ ነን፡፡ ሰዓት እንደረፈደበት፤ ጊዜውን በአግባብ እንደሚጠቀም ሰው «አሁን ደግሞ እኛ እንለፍ እንጂ ምንድን ነው፤ ሰዓት ገደላችሁብንኮ!» ይላል፤ መንገድ አስተናባሪውን እየተቆጣ፡፡
ሌላው ቀርቶ ቅጣት እንኳ አይመልሰንም፡፡ እንደልጅ መቆጣትና ተዉ ማለት አንድ ነገር ነው፡፡ መንገዱ ስርዓት እንዲኖረው የሚደክሙት በጎ ፈቃደኛ ትራፊኮች ዱላ ይዘው ‹ዋ!› እያሉ ቢያስፈራሩ እንኳ ሰዉ የሚታዘዝ አይመስለኝም፡፡ ትልቅ ሰው ግን ድሮም እንዲህ ያስቸግራል!?
በቀደም በኢትዮጵያ ሆቴል በኩል ሳልፍ ‹‹ዝርዝር ነው?›› አለኝ አንድ ወጣት፡፡ ‹‹እናንተ! አላችሁ እንዴ?›› አልኩት…በልቤ፤ ራሴን በአሉታ ነቅንቄለት እያለፍኩ፡፡ አንደኛ ምን ሆኖ ነው እኔን በዝርዝር የጠረጠረኝ? ዝርዝር ፈላጊ እመስላለሁ? ነው ወይስ አስዘርዛሪዎች እንደእኔ ዓይነት ሰው ልከው ነው የሚያዘረዝሩት? የሚለው ጥያቄ ተፈጠረብኝ፡፡
ሁለተኛ ደግሞ ድፍረታቸው ገረመኝ፡፡ እንዴት ሰው በቅጣት አይመለስም? ይህን «እንቢ ባይነት» አርበኞች አገርን ለጠላት አንሰጥም ያሉ ጊዜ ያሳዩት ነው፡፡ «ብትገድሉንም ንቅንቅ አንልም፤ አገራችንን ለባንዳና ጠላት አንተውም» ብለው እስከመጨረሻው ታግለውና ሞተው አገር አትርፈዋል፡፡ እነዚህ ወንድሞችና እህቶቻችን ደግሞ ገንዘብ ለማትረፍ «እንቢ» ብለዋል፡፡
አሁን የገባኝ ታዛዥነት የሚባል ኢትዮጵያዊና ሰዋዊ ሀብታችን መቀበሩ አልያም መሰረቁ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ልጆች ጋር ሳይጠፋ አዋቂዎች ጋር ነው ድራሹ የሌለው፡፡ መንገድ ላይ ተረጋጋ ሲባል፤ ያውም ለራሱ ጥቅም አልሰማ ያለ ጎልማሳ፤ አውቶቡስ ተሳፍሮ ወጣት ልጅ ለትልቅ ሰው ከወንበሩ ካልተነሳ ቁጣው ለጉድ ነው፡፡ ነገሩን አልኩኝ እንጂ በእርግጥ፤ እሾህን በእሾህ ብሎ የማይታዘዝን ባለመታዘዝ መቅጣት ልክ አይደለም፡፡
ግን ትልቅ ሰዎች ምን ነካችሁ ማለት ፈልጌ ነው፡፡ አንድ ሰው ነፍስ ካወቀና ራሱን መግዛት የሚችልበት ደረጃ ከደረሰ፤ ትልቅ ሰው ይባላል፡፡ እና እነዚህ ሰዎች ብርቅዬ ሊሆኑብን ይሆን? አሁን ስለመታዘዝ ለልጅ እንጂ ለትልቅ ሰው የሚነገር መስሎን ያውቃል? ድንቅ የሚለው ግን ረባሽና አስቸጋሪው ትልቅ ሰው መሆኑ ነው፡፡ ይሄኔ ነው ልጅነት ንፍቅ የሚለው፡፡ ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር26/2011