የህውሓት ጁንታ በህግና በህጋዊነት፣ በውይይትና በሀሳብ የበላይነት የማያምን ስለመሆኑ ገና ከውልደቱ ጀምሮ የሄደባቸው የጥፋት እና የሴራ መንገዶች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው። በአንድ በኩል ስለ ዴሞክራሲ፣ የህግ የበላይነትና ከአቅሙና ከልኩ በላይ እየጮኸ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ድርጅት ለዴሞክራሲ ባይተዋር ከመሆኑ የተነሳ ሀሳቦችን በውይይትና በድርድር ከመስጠትና ከመቀበል ይልቅ ሀሳቦቹንና ሃሳቢዎቹን እስከ ምንጫቸው በሀይል ለማጥፋት ለባለፉት 40እና 50 አመታት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
በእነዚህ ዓመታት የመረጠው የጥፋት መንገድ አልፋና ኦሜጋ የሆነለት ያህል ከፍ ያለ የተሳሳተ የአሸናፊነት መንፈስ በውስጡ መፍጠር የቻለ ቢሆንም መንገዱ ገና ከጅምሩ የተሳሳተ ስለነበር ሀገርና ህዝብን ካስከፈለው ዋጋ ባልተናነሰ በመጨረሻው ራሱን ላቅ ያለ ዋጋ አስከፍሎታል።
የተሳሳተው የአሸናፊነት መንፈስ የፈጠረው እብሪት፣ እብሪቱ የፈጠረው መታወር ፣መታወሩ የፈጠረው አለማስተዋል በትናንትና እና በዛሬ መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት አጥፍቶበት ፤በትናንት ማንነቱ ለያዥ ለገላጋይ ሳይመች ቀርቶ የክፉ ታሪክ መማሪያ የታሪክ ገጽ ለመሆን ተገድዷል።
በርግጥ ህወሓት ፍጥረታዊ ለሆነው ለሰው ልጅ የሀሳብ ብዝሃነት የተገዛ አይደለም። ግለሰባዊም ሆነ ማህበረሰባዊ ለውጥ ፣ ከዚህም የሚመነጨው ዕድገት ከሀሳብ ብዝሃነት የሚፈጠር ስለመሆኑ የመጣበት የሴራና የጥፋት መንገድ የፈጠረበት ትምክህትና እብሪት ጋርዶታል።
ከዚህ በመነጨም ህወሓት ለምርጫ ፖለቲካ የሚሆን ፍጥረታዊ ማንነት እንዳይኖረው አድርጎታል። ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ዘመኑ ባካሄዳቸው አምስት ምርጫዎች በተጨባጭ የታየና የማንንም የምስክርነት ቃል የሚፈልግ አይደለም። በእነዚህ ምርጫዎች አሸናፊ ሆኖ ለመቅረብ የሄደባቸው የሴራ መንገዶች ሀገርና ህዝብን የቱን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ እንዳስከፈሉ ከማንም ሊሰወር የሚችል አይደለም።
የተለየ አስተሳሰብ አላቸው የተባሉ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆኑ የተለየ የፖለቲካ አመለካከት አላቸው የተባሉ ግለሰቦች ሳይቀሩ ስለ አሰቡት ሀሳብ ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርጓል። ለከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዳርጓል፣ ገድሏል፣ ከሀገር እንዲሰደዱ አድርጓል። ከራሳቸው አልፎም በቤተሰቦቻቸው ላይ የከፉ ድርጊቶችን ፈጽሟል።
እወክለዋለሁ ለሚለው የትግራይ ህዝብ ሳይቀር ከሰላማዊ ፖለቲካ አስተምህሮ ባፈነገጠ ፣ የትግራይን ህዝብ ባሳነሰና በናቀ መልኩ ካለእኔ ሊያስብለት የሚችል የለም፣ ካለም ሊኖር የሚችለው በመቃብሬ ላይ ነው እያለ ሕዝቡን ምርጫ አልባ አድርጎ፤ የሴራ አስተሳሰብ ባሪያ በማድረግ ሲያሰቃየው ቆይቷል።
በትጥቅ ትግሉ ወቅት እጅግ ብዙ ዋጋ የከፈሉ፣ በትግሉ ዘመን አንቱ የተባሉ የቡድኑ አባላትን ሳይቀሩ የተለየ ሀሳብ በማሰባቸው ብቻ ጠላት አድርጎ ከመፈረጅ ባለፈ በህዝቡ ያላቸውን ተቀባይነት ለማጥፋት አዳዲስ ትርክቶችን በመፍጠርና በየአደባባዩ ባልተገባ መልኩ እንዲወገዙ በማድረግ የሰቆቃ ሕይወት እንዲያሳልፉ አድርጓል።
ላለፉት 27 አመታት በየመድረኮች ይነሱ የነበሩ የለውጥ አስተሳሰቦችን የተለየ ገጽታ በመስጠት ከማጠልሸት ባለፈ ለሀሳቡ ባለቤቶች የተለያዩ ስያሜዎችን በመስጠት ሲያሳድድ ቆይቷል። ሀገሪቱ የሀሳብ መካን እስክትመስል ድረስ የተለዩ ሃሳቦች አደባባይ እንዳያገኙ አጥብቆ ሲሰራና ሀሳቦችን ሲያመክንም ቆይቷል።
በለውጡ ማግስትም ሀገርን አይደለም ፓርቲውን እንደ ፓርቲ ወደ አዲስ ዘመን የፖለቲካ አስተሳሰብ ማሻገር የማይችሉ ተቸንክሪ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችን ለመጣል ፈቃደኝነት አጥቶ ያንኑ አስተሳሰብ በሀገርና በህዝብ ላይ ለመጫን የሄደበት የጥፋት መንገድ ሞቱን አፍጥኖለታል ።
ቡድኑ በስልጣን ዘመኑ በጸደቀው የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ከሰላማዊ አማራጭ ውጪ የኃይል እና ጉልበት አማራጭን እንደትግል ስልት በመውሰድ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚሞክሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ከፖለቲካው መድረክ እንደሚገለሉ በግልጽ አስቀምጧል።
ይህን ህግ ሕግ አድርጎ ያስቀመጠው ለህግ የበላይነት ካለው ከፍ ያለ እሳቤና ቁርጠኝነት ሳይሆን ሕጉ በእጄ ነው ከሚል የማናለብኝነትና የእብሪት መንፈስ ስለመሆኑ ማሰብ አይከብድም። ለዚህም ይህንኑ ህግ ጠቅሶ ሲያሳድዳቸው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።
አዲሱ ነገር ትናንት ሌሎችን ጠልፎ ለመጣልና ለማሳደድ ይጠቀምበት የነበረው ያ ሕግ ዛሬ እራሱን ተጠያቂ በማድረግ ከሀገራዊ የፖለቲካ መድረኩ መሰናበቱ ነው፤ በዚሁ ህግ የመጨረሻው ስርአተ ቀብሩ መፈጸሙ ብቻ ነው። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ጅማሬው ይህንኑ ፍጻሜውን የሚጣራ እንደነበር የውልደት ማንነቱ ይመሰክርበታል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 13/2013