ሰው በሙያው ይጠራል፤ አንዳንዴ ግን ሙያን የሚያስጠሩ ሰዎች ይታያሉ። ስማቸው ሙያቸውን ልቆ እናገኛቸዋለን፤ እነዚህም በየዘመናቱ አልፎ አልፎ የሚገኙ ናቸው። «እወቁልኝ» እያሉ አይለፍፉም፤ ሥራቸው ግን ምስክር ሆኖ ይቆያል። ያከበሩት ሙያና ተግባርም ያከብራቸዋል። እንግዲህ ያልተዘመረላቸው የምንላቸው እንዲህ ያሉትን ነው።
«ጋዜጠኛ እሆናለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም» የሚለው የዛሬው እንግዳችን፤ ጋዜጠኛና የኪነጥበብ ሰው አባተ ማንደፍሮ ነው። ስለራሱ ብዙ አያወራም፤ ትህትናን ያስቀድማል። በመድረክ መሪነት፣ በራዲዮ፣ በጋዜጣና በቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት፣ በሙዚቃ ገጣሚነት፣ በቴአትርና በመጽሐፍ አዘጋጅነት ስሙ ሰፍሯል፤ አሁንም ስሙን ለታሪክ እያኖረ ይገኛል። ዛሬ ደግሞ ተጠያቂ ሆኖ፤ ማራኪ በሆነ ድምጽና በተለቀመ አነጋገር፤ ብዙ ከሆነው የሕይወትና የሙያ ልምዱ፤ በጥቂት ሊያካፍለን በ«ሕይወት እንዲህ ናት» ዓምድ ብቅ ብሏል።
ነገርን ከስሩ
አባተ ትውልዱ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ፤ ይፋት የሚባል ቦታ በ1955ዓ.ም፤ ነሐሴ 5 ቀን ነው። ይሁንና በተወለደበት ከተማ አላደገም፤ ይልቁንም ገና የዘጠኝ ወር ልጅ ሳለ በእናቱ እቅፍ ሆኖ አዲስ አበባ ተገኘ። ፊት በር እና ገብርኤል ሰፈር የልጅነትና የእውቀት ዘመኑ ትዝታና ታሪክ ተጽፎባቸዋል።
በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥሮ ዳዊት ደግሟል። በዛም ለአራት ዓመታት ቆይታ ማድረጉን ያስታውሳል። እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ኢዮቤልዩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የገባው። ኢዮቤልዩ ትምህርት ቤት በቤተመንግሥት የሚያገለግሉ ሰዎች ልጆች የሚማሩበት ትምህርት ቤት ነበር። በዛው የሚሠሩት የአባተ እናትም ልጃቸውን ወደዚህ ትምህርት ቤት መላክ ችለዋል።
«የዛን ጊዜ ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ግብረገብ የሚባል ትምህርት አለ፤ ከእስጢፋኖስ የሚመጡ ቄስ ያስተምሩን ነበር።» የሚለው አባተ፤ በስነምግባር ታንጾ ለማደግ መሰረቱ ያ እንደነበርም ያነሳል። ከኢዮቤልዩ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ስድስተኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ ቅዱስ ዑራኤል መለስተኛ ትምህርት ቤት ገባ። ወቅቱ በአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ መረጋጋት ያልነበረበት በመሆኑ «እንዲሁ ተማርን ለማለት ያህል አለፍን እንጂ በአግባቡ አልተማርንም ነበር።» ሲል ወቅቱን ያስታውሰዋል።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ዘልቋል። ይህ ሲሆን ዘመኑ 1969ዓ.ም ነበርና በፖለቲካ መስመር ልዩነት መነሻነት የነበረው መገዳደልና እስር፤ ሰው ከየቤቱ በሰላም ስለመውጣቱ እንጂ ስለመመለሱ እርግጠኛ መሆን የማይችልበት ጊዜ ሆነ። ትምህርቱም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በሦስት ፈረቃ ይሰጥ ጀመር።
መምህራኑ ታድያ የጊዜው ማጠር ሳይገድባቸውና የአገሪቱ ሁኔታ ሳያደናቅፋቸው ለተማሪዎቻቸው በአግባቡ ትምህርት ይሰጣሉ። ይህም ወቅት ለአባተ እንዲሁም በዛ የትምህርት ደረጃና እድሜ ለነበሩ ልጆች በራሳቸው እንዲጥሩና እንዲያነቡ ገፋፍቷቸዋል። የአባተ የንባብ ፍቅርም የጀመረው ያንጊዜ ነበር።
ወደሥራ
አባተ በልጅነት እንዲሁም በወጣትነት ከቤተሰቡ በጥበብ ዘርፍ ገፍቶ አርአያ የሆነው ሰው አልነበረም። ከጠቀሰም ወላጅ እናቱ ዘፈን ይሞክሩ እንደነበር ያስታውሳል። «እናቴ ጥሩ ድምጽ ነበራት። ነገር ግን አገር ፍቅር ተፈትና እንዳላለፈች ነግራኛለች» ይላል። ከዚህ ውጪ በራሱ ጥረትና ብርታት፤ ይህም በተፈጥሮ ከታደለው ጸጋ ጋር ተዳምሮ መንገዱን አመላክቶታል።
ከትምህርት ዓለም ተሰናብቶ ወደ ሥራው ዓለም ሲቀላቀል፤ መጀመሪያ የተቀበለው የቀበሌ ኪነት ነበር። «በኪነት ቡድኖች በውስጣችን የነበረውን ለማውጣት ሰፊ እድል ነበር» የሚለው አባተ፤ በቀበሌ ኪነት ቆይታውም በተለይ መድረኮችን በመምራት በኩል እውቅናን አትርፏል። ብዙም ሳይቆይ ግን የእናት አገር ጥሪ መጣ፤ ብሔራዊ ውትድርና፤ ግዳጅ።
አባተ ወደ ብሔራዊ ውትድርና ካቀኑ ወጣቶች መካከል አንዱ ሆነ። «ያኔ የግድ የአንድ ሙያ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል፤ አለበለዚያ ስልጠናው ከባድ ነበር። ስለዚህ በትንንሽ እሞክራት የነበረውን የመድረክ ማስተዋወቅ ሥራ በዛም እሠራ ጀመር» ደግሞም ስኬታማ ነበር፤ ለካ ሳያውቀውም በቀበሌ ኪነት የነበረው ሥራ ታዋቂ አድርጎት ነበርና፤ ብዙዎች ያደንቁትና ያበረታቱታል። ግዳጅ እስኪጨርስ ድረስም የማዕከሉ ኪነት መድረክ አስተዋዋቂ በመሆን አገለገለ።
የማያልቅና የማያልፍ የለም፤ የብሔራዊ ውትድርና ግዳጁ አብቅቶ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ያም ሆኖ በቆይታ የተላመደውን መድረክ የመምራት ሥራ ሊገፋበት ፈልጎ አገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለፈተና ቀረበ፤ አላለፈም። በኋላ ወደ ባሌ ፖሊስ አቅንቶ ፈተናውን ወሰደና አለፈ። ከዚህ በኋላ በዋናነት በመድረክ አስተዋዋቂነት፤ በተጨማሪ በገጣሚነትና በተዋናይነት አገለገለ። ከባሌ ፖሊስ ሲወጣም ወሎ ላሊበላ ኪነትን ተቀላቅሎ ለጥቂት ወራት አገልግሏል።
የጋዜጠኝነት መነሻ
ለመድረክ አስተዋዋቂነት እንዲሁም ለጋዜጠኝነት ሙያው የመጀመሪያ በር የተከፈተበት የብሔራዊ ውትድርና ቆይታው እንደሆነ ይናገራል። ከዚህም በኋላ ነው ጋዜጠኝነቱና ሌላው ሁለገብ የሚያስብለው ሙያ የተከተለው። ጋዜጠኝነቱም ቢሆን በመድረክ አስተዋዋቂነቱ መነሻነት የተጠነሰሰ ነበር። እንዴት ቢባል፤ «ድምጽህ ለጋዜጠኝነት ጥሩ ነው» ይሉት የነበሩ ሰዎች ትኩረቱን ወደሙያው እንዲያዞር አንድ ምክንያት ነበሩ። እርሱም ከዚህ በኋላ ድምጹን በመቅረጸ ድምጽ እየቀዳ መላልሶ ያዳምጥ ነበር።
ከዛም በተጨማሪ በየወሩ በሚካሄድ የውይይት ክበብ መድረክ ላይ የሚቀርቡ፤ ከተለያዩ ጋዜጦች የሚሰበሰቡ ዜናዎችን ያቀርባል። ይህም በተጨማሪ ድምጹን መልሶ እንዲሰማው ረድቶታል። ይህንን በልቡ ያኖረው አባተ፤ በባሌ እንዲሁም በወሎ ላሊበላ ኪነት የነበረውን ቆይታ ጨርሶ አዲስ አበባ ሲከትም ቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ አመራ። በወቅቱ በቦታው የነበሩ ልጆች ችሎታ ላለው እድል የሚሰጡ በመሆናቸው መጣጥፍ በማንበብና በመሳሰለው በወጣቶች ፕሮግራም ላይ መሳተፍ ጀመረ።
አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ፤ የአባተን አንባቢነትና ጥሩ ጋዜጠኝነት ከሚያውቅ ዳንኤል ክፍሌ ከተባለ ሰው ጋር በአጋጣሚ ይገናኛሉ። ዳንኤል ክፍሌ በወቅቱ «ፈንድሻ» የሚባል ጋዜጣ ያዘጋጅ ነበርና ለጋዜጣ የሚሆን አንድ ጽሑፍ እንዲያበረክት አባተን ይጠይቀዋል። ወቅቱ በአባይ ጉዳይ ላይ ሁስኒ ሙባረክና መለስ ዜናዊ የሚነጋገሩበት ነበርና፤ በአባይ ጉዳይ ላይ የሚያውቀውን እንዲጽፍ ነበር የጠየቀው።
«እኔ የህትመት ጋዜጠኛ መሆን የምችል አይመስለኝም ነበር፤ የኤሌክትሮኒክስ እንጂ።» የሚለው አባተ፤ መጀመሪያ በጋዜጣ የሚታተም ጽሑፍ ባበረከተበት ጊዜ የተሰማውን ደስታ ያስታውሳል። ማክሰኞ እለት የወጣውን ያንን ጋዜጣም ከሁሉ ቀድሞ አራት ኪሎ ተገኝቶ እንደገዛ ይናገራል። ሰው ያነበዋል ብሎ ባያስብም፤ ጋዜጦች በአንባቢ እጅ እስከደረሱ ድረስ ሥራው መነበቡ አልቀረም። ከዛ በኋላም ምኒልክ፣ አስኳል፣ ሳተናው የተባሉ ጋዜጦች ላይ ሠርቷል። እስከ 1997 ዓ.ም ድረስም ስሙ ከጋዜጦች ላይ አይጠፋም ነበር።
አንጋፎችን ማፈላለግ
አባተ አሁን ጄቲቪ በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ እየሠራ ይገኛል። በዚህ ጣቢያና በአዘጋጁ አቅራቢነት የሚታዩ፤ ለብዙዎች የተሰወሩና የተዘነጉ፤ በየመስኩ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ካሉበት በማውጣት በኩል የአባተ ሚና ላቅ ያለ ነው። ምንም እንኳ አባተ ራሱን በዛ መልክ ባያስተዋውቅም፤ ብዙዎች ግን ለዚህ ምስክር ናቸው። ይሁን እንጅ እነዚህን በስም እንጂ በመልክ የማናውቃቸውን፤በሥራቸው ብንደነቅም ያሉበትን ያልጠየቅናቸውን ሰዎች እርሱ እንዴት አወቃቸው?
የእርሱ ምላሽ እንዲህ የሚል ነበር፤ «በፊት ጀምሮ ምንም ነገር ሳነብ አንድም ቀን ጋዜጠኛ እሆናለሁ ብዬ አልነበረም። ስለአንድ ሰው ሳውቅና በምንም ዘርፍ ላይ የበኩሉን ነገር ያደረገ ሰውን ታሪክ ለማወቅ ስፈልግ አንድ ቀን ጋዜጠኛ ሆኜ እጠቀምበታለሁ ብዬ እያሰብኩኝ አይደለም። ስለዛ ሰው ማወቅ አለብኝ ብዬ ለራሴ ስለምፈልግ ነው፤ አሁን ግን ጠቀመኝ።»
ይህ ለራሱ ሲል ያጠራቀመው ታሪክና እውቀት፤ በተፈጥሮ ከታደለው ድምጽና በውስጡ ከኖረው የሙያ ፍቅር ጋር፤ ሥራውን በአግባቡ የሚሠራ ባለሙያ አድርጎታል። እርሱም እድለኛ ነኝ ይላል፤ ለዚህ ምክንያቱ በሁሉም ጉዳይ ላይ መሥራት መቻሉ ነው። ማለትም በጋዜጣውም ሆነ በራዲዮን እንዲሁም በቴሌቪዥን ሠርቷል፤ መሥራትም ይችላል። አልፎም በማንኛውም ፖለቲካም ሆነ ኢኮኖሚ አንዲሁም ጥበብ ነክ ጉዳይ ላይ የሚናገረው መረጃና እውቀት አለው።
ማንበብ ማንበብ ማንበብ
አባተ በሙያው ሁሉገብና ሙሉ መሆን የቻለበትን ምስጢር ቢጠየቅ መልሱ አንድ ነው፤ ማንበብ። በተለይ በጋዜጠኝነት ሙያ የማንበብን ወሳኝነት ያነሳል። «ማንበብ ሱሴ ነው። ያላነበብኩ እንደሆነ ወይ ታምሜ ነው አልያም ሦስት ቢራ ጠጥቻለሁ» ይላል። በማንበቡም እጅግ ብዙ ማትረፉን ነው የሚናገረው።
ከሙያው ጋር በተያያዘም ምክረ ሃሳቡ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። አክሎም መማር ጠቃሚ ቢሆንም መጀመሪያ ፍላጎት ሊኖር ይገባል ባይ ነው። የጋዜጠኝነት እንዲሁም በጥበቡ ዘርፍ የቴአትር ትምህርትና የሌላውም ትምህርት ከፍላጎት ጋር ቢሆን፤ ባለሙያውም በድፍረት ከመሥራት ቢቆጠብ ሲልም ሃሳቡን ያካፍላል። ለጋዜጠኞችም መልዕክቱ ይህ ነው፤ «የህትመት ሚዲያው አንባቢ ፈልጎ የሚያነብ ሲሆን፤ የኤሌክትሮኒክስ ሲሆን ግን አድማጭና ተመልካች ፈለገም አልፈለገ ሊሰማና ሊያይ ይችላል። እናም ተመልካችን የሚንቅና ደፋር የሆነ ሥራ ባይሠራ መልካም ነው»
ነገሩን ከጋዜጠኝነት ጋር አነሳን እንጂ አባተ በቴአትር፣ በሙዚቃ ግጥም እንዲሁም በመጽሐፍ ሥራ ላይ ስሙ ይገኛል። ከመጽሐፍት ስንጀምር «የደም ምድር» የተሰኘ መጽሐፍ፤ የአባተ የመጀመሪያ የድርሰት ሥራው ነው። ከሌሎች ጸሐፍት ጋር ራሱን እያነጻጸረና ሁሌም በራሱ እይታ የራሱ ሥራ አንሶ እየታየው፤ መጽሐፉን ለህትመት ለማብቃት እንዳዘገየው ይናገራል። በኋላ በጓደኞቼ ትብብርና ግፊት መጽሐፉ ገበያ ላይ ዋለ። አሁን ላይም ሁለተኛና ሦስተኛ መጽሐፉን እያዘጋጀ ነው።
በቴአትር በኩል ከአዲስ አበባ ውጪ በክፍለሀገር ብዙ ሥራ መሥራቱን ይጠቅሳል። ጎባ ውስጥ ቴአትር ታየ ከተባለ የአባተ ተሳትፎ አለበት። በአዲስ አበባ ከሠራቸው መካከልም «ጣምራ ስሌት» ይጠቀሳል። በእርሱ የተጻፈውና ተስፋዓለም ታምራት ያዘጋጀው ይህ ቴአትር፤ አገር ፍቅር ተገምግሞ አላለፈም ተባለ። ይሁንና ቴአትሩ በዓለም ሲኒማ የታየ የመጀመሪያው ቴአትር ለመሆን በቃ። ለረጅም ጊዜ በሜጋ ቴአትር መድረክ ላይ መቆየቱንም ይናገራል።
ከዚህ ባሻገር ያለው የዘፈን ግጥም ማዘጋጀት ነው። ይህኛው ደግሞ እንዲህ ነው፤ በ1980ዎቹ አጋማሽ አካባቢ የሙዚቃ አልበም ለአድማጭ ሲቀርብ ማስታወቂያው የሚሠራበት የራሱ ስርዓት ነበር። ይህም አልበሙ የያዘው አስር ዘፈን ከሆነ፤ ከዛ መካከል ለተመረጡት ለአምስቱ አንድ ማስታወቂያ ይሠራል። ማስታወቂያውም ተቀድቶና ተባዝቶ በየሙዚቃ ቤቱ በር ላይ ይለቀቃል።ታድያ አባተ በተመሳሳይ አንድ ሙዚቃ እንዲያስተዋውቅ በአምስት መቶ ብር ይስማማል።
ሙዚቃውን ለማስተዋወቅ በግጥም አልያም በስድ ንባብ መጠቀም ይቻላል። ይህን መብቱን የተጠቀመው አባተም «ከዘፈኑ ግጥም ዘፈኑ የተዋወቀበት የማስታወቂያው ግጥም ይበልጣል» የተባለለት የማስታወቂያ ግጥሞችን ተጠቀመ። ከዚህ በኋላ ነው ለገነት ማስረሻ «ዘገየህ ምነው»፣ ለግዛቸው አማከለው «ተው አባባ» እና ለሌሎችም ሙዚቃ ግጥሞችን በመስጠት ሥራውን የጀመረው።
አይረሴ ጊዜያት
በስድስት ብር እንዲሁም ከፍ አለ ሲባል በአስራ አራት ብር አበል ከኪነት ቡድኖች ጋር ኪነጥበባዊ ሥራዎችን ይዘው ኢትዮጵያን የዞሩበት ዘመን አባተ አይረሳም። ይህም ጉዞ በአንድ በኩል ስለተለያዩ ከተሞችና ባህላቸው እንዲሁም ታሪክን በደንብ እንዲያውቅ አግዞታል። አሁን ላይ ግን ሁሉም ነገር በአዲስ አበባ ከመታጠሩ ጋር ሲያነጻጽረው፤ «ወደኋላችን ወደነበረው መልካም ጊዜ የምንመለስ አይመስለኝም» እስኪል ድረስ፤ አሁን ላይ ሙያውን ወድዶ የሚሠራው ብዙ እንዳልሆነ ታዝቧል።
እንዲህም ይላል፤ «ለምሳሌ ንዋይ ደበበ ራስ ቴአትር የመጣው ራስ ቴአትር ወላይታ ሄዶ ባዛር ሲሠራ ነው። የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ ብናንሳ፤ አገር ፍቅር ቴአትር ወሊሶ ሄዶ ሙዚቃ ባይሠራ ጥላሁን ገሠሠ ኢዮኤል ዮሐንስን አያገኝም ነበር። ይህ በየክፍለ አገር ላሉ ልጆች መነሻ ምክንያት ነበር» እናም ይህ በአዲስ አበባ የታጠረውን ነገር ሲመለከት፤ ጥበብ ያለው መሃል ከተማ ብቻ ነው ወይ? ሲል ይጠይቃል። «ያኔ ለሙያው ነው መስዋዕትነት የሚከፈለው» ይላል ጨምሮ።
በቅርብ ጊዜ የሆነውንና ያስታወሰውን ታሪክ በእርሱ ቃል ላካፍላችሁ፤ «የኃይሉ ከበደ ሮኆቦት ፕሮሞሽን “ቃልኪዳን” የሚባል ቴአትር ያዘጋጃል። ቴአትሩን ይዘን ጎሮ የሚባል አካባቢ ልናሳይ ሄድን። ቴአትር ለማሳየት አዳራሽና መብራት ያስፈልጋል። በጎሮ ደግሞ መብራትም ሆነ አዳራሽ የለም። እናም በአጋጣሚ አንድ የእርዳታ ማስተባበሪያ መጋዘን ተገኘ። በዛ የመድረክ ገጽ ግንባታ ተሠራና ቴአትሩ በማሾ ቀረበ። ቴአትሩ ሊታይ በሚችልበት አቅም ሠራን። ያ ሕዝብ እንዴት አክብሮ እንደሸኘንና ቴአትሩን እንዳየ፤ ከተማዋን ለቅቀን እስክንወጣ ድረስ እንዴት በፍቅር እንዳስተናገደን ልናገረው አልችልም። እና ያም ሰው ቴአትር ሊያይ ይፈለጋል። በቴሌቪዥን የሚያያቸውና በስም በዝና የሚያውቃቸውን ሰዎች ቢያያቸው ደስ ይሰኛል»
ሕይወት ሲቀጥል…
«ነገሮች ብዙ ጨልመውብኝ ያውቃሉ» የሚለው አባተ፤ ሕይወት እንደዛ አይደለች? አባተ ደግሞ ወታደር ቤት በየትኛውም ደረጃ ሆኖ መኖርን ስላወቀበት፤ ቢከብደውም የጣለው ፈተና አልነበረም። አንዱ ፈተናና ከባድ ጊዜ በአገር ጉዳይ ተፈጥረው የነበሩ አስከፊ መመሰቃቀሎች ናቸው። ቤተሰብ እንደገና ተሰባስቦ መተያየት የመቻሉ ነገር ህልም ያከለበትን ጊዜ ማሰብ እንደሚከብድ ይናገራል።
ሌላው በህመም ነው። ከስድስት ዓመት ገደማ በፊት አባተ በጠና ታምሞ ነበር። ታድያ አበቃ የተባለበት ጊዜም ይህ ነው። «እኔ ያኔ ራሴን አላውቅም፤ ለቤተሰቦቼ ግን ተስፋ አስቆራጭ ነበር።» ይላል ጊዜውን ሲያስታውስ። ከዛ ህመም ላይ ተነስቶ ለመቆሙም የፈጣሪውን እርዳታ፤ የቤተሰቡን ጥንካሬና ብርታትም እንዲያመሰግን አድርጎታል። ሕይወትም ሰው እንዳሰባት ብቻ አይደለችምና፤ ይሁን በተባለላት መንገድ ቀጠለች።
ቅድሚያ ለሥራ
የአባተ ትህትና ሥራውን እንጂ ስሙን ካለማስቀደሙ ላይ ይታያል። እርሱም በቃሉ «ሌሎች አባተ እንዲህ ነው ብለው እንዲነግሩኝ እንጂ እኔ ልናገር አልፈልግም። በምታወቅበት ደረጃ እና በሚሰጠኝ አክብሮት ልክ ነኝ ወይ ብዬ እጠይቃለሁ» ይላል። የሠራውም መሥራት ያለበት እንደሆነ፤ ስለራሱ በማውራት ማስታወቂያ መሥራት እንደማይችልበትም ይናገራል።
ይህ በወታደር ቤት ቆይታው ያገኘው ሰብእና ነው። «በወታደር ቤት ራስን ማስቀደም የለም። ወታደር አንዱ ለአንዱ ነው መስዋዕት የሚሆነው። እንጂ በአንዱ ላይ ተረማምዶ ራስን ማዳን የለም። ውትድርና አንዱ ሞቶ ሌላውን የማኖር ጉዳይና መስዋዕትነት መክፈል ነው። በዛ እኛ እንጂ እኔነት የለም» ይህ እንዳለ ሆኖ አስተዳደጉም የነበረውን ድርሻ አይረሳም። ግብረገብን በአግባቡ መማሩ፤ በትውልዱ የነበረው ስርዓትና ሁናቴም በእርሱ ማንነት ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ይመሰክራል።
ማንን ታደንቃለህ?
ብዙዎችንና ብዙ ነገር ያውቃልና እንዲህ ያለ ሰው «ማንን ታደንቃለህ?» ለሚለው ጥያቄ በእርግጥ ትክክለኛው ሰው ይሆናል። እርሱም አለ፤ «በሕይወት በኖሩበት ዘመን ሁሉ በአንድም በሌላም መልኩ ለአገርና ለሕዝብ መልካም ነገር ሠርተው ያለፉ ሰዎችን በጣም አደንቃለሁ»
በዋናነት ግን ስም ጥቀስ፤ ሰው ጥራ ቢባል ቀድሞ የሚያነሳው በላይ ዘለቀን እና ራስ አበበ አረጋይን ነው። በምን አደነቃቸው? «ስለአገራቸው ሲሉ በልጆቻቸው ላይ የወሰኑ ሰዎች ስለሆኑ። ሁሌም እኔ ያንን አደርገዋለሁ ወይ ብዬ እጠይቃለሁ። ስለእነርሱ ሳወራና ስጽፍም ደስ ይለኛል» ይላል። ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ በሥራ አጋጣሚ የጀግናው አብዲሳ አጋን ባለቤት ያገኘበት ጊዜ ደስ የተሰኘበት ነው። «አብዲሳን በአካል ያገኘሁት ያህል ተሰምቶኝ ነበር» ሲል ስሜቱን ያስታውሳል።
ገጠመኝ
«ብሌን» የሚባል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር። አንድ ጊዜ «አባተ ኪሾ ክልላቸውን ማስተዳደር ተሳናቸው» የሚል ዜና ይሠራል። ከዚህ በኋላ ነው የቢሮው ስልክ የተደወለው። «አባተ አለ?» ደዋይ ጠየቀ፤ «አልገባም» አባተ ራሱ ለደዋዩ ምላሽ ሰጠ። «አባተ ኪሾ እንደደወለ መልዕክት አድርሱልኝ» ስልኩ ተዘጋ።
ይህ ከመሆኑ ጥቂት ጊዜ አስቀድሞ፤ አንድ ጋዜጠኛ ጓደኛቸው በሥራው ምክንያት ከአዲስ አበባ ውጪ የመደብደቡ ዜና የታወቀ ስለነበር፤ በድፍረት «እኔ ነኝ» ለማለት ስጋት ነበር። ጭራሽ ይባስ ብሎ አባተ ወደ ቤቱ ሲደርስ ከበሩ ላይ ሁለት ፖሊሶች ቆመው ተመለከተ። አልቀረበም፤ በቅርብ ወዳለ የቤተሰብ ቤት አቀና፤ ሰው አላገኘም። ቀኑ ሲጨላልም ጠብቆ በርቀት ባለቤቱን ከቤት አስጠራ። «ቀን በዚህ በኩል በታክሲ ሳልፍ ከበራፉ ፖሊሶች አይቼ ነበር» አለ፤ ባለቤቱን። «ደከመን ብለው ለጥላ ቆመው ነውኮ!» ነበር የባለቤቱ መልስ። ይህ የማይረሳውን ገጠመኝ ነበር።
ቤተሰብ
አባተ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነው። ስለባለቤቱ ስለወይዘሮ ብዙነሽ ጀንበሬ ተናግሮ አይጠግብም። ከልጆቹ መካከል ደግሞ የመጨረሻ ልጁ የእርሱን ፈለግ ተከትሏል። በአሁኑ ወቅት በጄቲቪ አባትና ልጅ አብረው እየሠሩ ይገኛሉ። በየደረጃው ሆነ፣ ከባዱንም ቀላሉንም ጊዜ አሳልፎ መኖርን ያወቀበት ጋዜጠኛና የኪነጥበብ ባለሙያ አባተ ማንደፍሮ፤ ሕይወት እንዲህ እንደሆነችም አሳይቶናል። ቀድሞ ከሠራው በላይ ወደፊት የሚያበረክተው የበዛ እንዲሆን ተመኘሁ። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ሊድያ ተስፋዬ