ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት በዊንዶውስ 10X ምርቱ ላይ ማሻሻያ ሊያደርግ መሆኑ ታወቀ፡፡
ኩባንያው የተሰረቁ ኮምፒውተሮች እንደገና ተስተካክለው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የሚያስችል አዲስ የፀረ-ሌብነት ጥበቃ በዊንዶውስ 10X ላይ እያዘጋጀ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ይህ ዊንዶውስ የተጫነባቸው ኮምፒውተሮች የፀረ-ሌብነት ጥበቃ ሞድ ከተጨመረላቸው በኋላ የግድ በተሰጣቸው የማይክሮሶፍት አካውንት የይለፍ ቃል የሚገለገሉ ይሆናል፡፡ ኮምፒውተር ዳግም ለማስጀመር የሚፈልግ ሰውም ይህን የይለፍ ቃል( PIN or password) የግድ ማስገባት ይኖርበታል፡፡
ይህ ደግሞ ማንኛውም የተሰረቀ ኮምፒውተር እንደገና ተስተካክሎ ወይም (reset) ተደርጎ ጥቅም ላይ እንዳይውል በማድረግ የሌብነት ወንጀልን ለመቀነስ ሊያግዝ ይችላል፡፡ በዚህ ዊንዶውስ የሚገለገሉ ሰዎች ንብረታቸው ቢሰረቅ እንኳን በአዲሱ ጥበቃ አማካኝነት ኮምፒውተራቸውን በማንኛውም ቦታ ሆነው መቆለፍ የሚያስችላቸው ሲሆን፤ ጎግል ባቀረበው ‘Find my device’ በተባለው የመፈለጊያ አማራጭ ደግሞ የኮምፒውተሩን መገኛ ሊረዱ ይችላሉ፡፡.
ይሁንና ዋነኛ ተጠቃሚ የሆነው ግለሰብ ራሱ የተሰጠውን የይለፍ ቃል በሚጠየቅበት ወቅት ትክክለኛውን ምላሽ ለመስጠት ከተቸገረ ፈታኝ ችግሮችን መጋፈጥ ግድ ይለዋልም ተብሏል፡፡
ካምፓኒው፣አዲሱ የፀረ-ሌብነት ጥበቃ አሁን ላይ ሊሰራበት የታሰበው የዊንዶውስ አይነት መደበኛው ዊንዶውስ 10 ሳይሆን በሱ ቨርዥን በቀረበው ዊንዶውስ 10X ላይ የሚሰራ ሲሆን ወደፊት በሌሎች የዊንዶውስ አይነቶች ላይ የመተግበር እቅድ እንዳለም አስረድተዋል፡፡
ማይክሮሶፍት ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት ዊንዶውስ 10X አደባባይ ለማውጣት የወሰነ ቢሆንም አልተሳካለትም፡፡ ይሁንና በዚህ አመት የበጋ ወራት ላይ ለገበያ እንደሚያቀርብ አሳውቃል፡፡መረጃው የተገኘው ከዊንዶው ሌተስት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 11/2013