በኢትዮጵያ በአደባባይ ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ጥር 11 ቀን ላይ የሚውለው የጥምቀት በዓል ነው፡፡ በዋዜማው ከተራ፣ በማግስቱ ደግሞ ቃና ዘገሊላ የተባሉ ተያያዥ በዓላትን ያካተተ ነው፡፡ ዘንድሮም በዓሉ ከፍ ባለ ድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል፡፡ በዓሉንም አስመልክቶ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የጥምቀት በዓል ስናስብ ሁለት ነገሮችን እንድናስታውስ ያመላከቱን ሲሆን የመጀመሪያው በዓሉ የትህትና በዓል መሆኑን፤ ሁለተኛው ደግሞ በዓሉ የለውጥ በዓል መሆኑን። የእነዚህ ሁለት እሳቤዎች አንድምታም ሰው በቀድሞው አኗኗሩ ንጹሕ ሕሊና እንዲያገኝና አዲስ ሕይወት ለመጀመር ፍላጎት እንዲያድርበት ለማስገንዘብ ነው።
ሁሉን ቻይ፤ ሁሉን አድራጊ፤ ሁሉን ፈጣሪና ሁሉን ወሳኝ የሆነው አምላክ ራሱን ዝቅ አድርጎ በዮሐንስ እጅ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁ የትህትና ምሳሌ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ ለጥፋት የዋለውን ውኃ ለድኅነት፤ ለመቅሰፍት የዋለውን ውኃ ለበረከት መለወጡን ይህም የአዲስ ሕይወት ጅማሮ እንደሆነ አስገንዝበውናል።
ከጥምቀት የምንማረው በሀገራችን ለጥፋትና ለመቅሰፍት ለማዋል ሕዝብን በብሔር በመከፋፈልና እርስ በርስ በማፋጀት የተካኑ የመንግሥት ሥርዓቶች ምንጫቸው ውኃን ወደ መቅሰፍት ከቀየረው የሰው ልጅ ክፋት መሆኑን። ለነዚህ እኩይ ተግባራት ማስፈፀሚያ የነበሩት ሕጎችና አሠራሮች በማጤን የኢትዮጵያን ብልጽግና እና ዕድገት እንዲያመጡ አድርገን መለወጥ ያስፈልጋል።
በሀገራችን ውስጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት በየቦታው የተዘራው፣ የተቀበረውና የተበተነው መቅሰፍት ብዙ ነው። የምንፈልገውን ሰላም፣ ብልጽግናና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማምጣት የለውጥ ሥራችንን በሚገባ መስራት ይኖርብናል። ይህንንም ለውጥ ለማምጣት እያንዳንዱን የመቅሰፍት ዱካ እየተከተሉ ጥፋቱን ወደ ድኅነት መለወጥን ይጠይቃል።
ዛሬ የምናየው የወገኖቻችን ስቃይ፣ ግፍ፣ መከራና ስደት፣ በንጹሐን ላይ እየወረደ ያለው ውርጅብኝ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየው ጥላቻ አስተሳሰባችን ውጤት በመሆኑ አሁንም ወደፊትም መደረግ ያለበት የጠፋውን በማቃናት ወደ አዳዲስ እሳቤዎችን በማምጣት ለዕድገትና ብልፅግና መገስገስ ብቻ ይሆናል።
ዶክተር አብይ እንዳሉት ለውጡ ጊዜ ይጠይቅ ይሆናል፤ ትዕግሥት ይጠይቅ ይሆናል፤ ደካማ አስመስሎ ያሳይ ይሆናል፤ ዐቅመ ቢስ ያስመስል ይሆናል፤ ወደ ታች መውረድ ይጠይቅ ይሆናል፤ ግን እያንዳንዱን መርገም ወደ በረከት፤ እያንዳንዱን መቅሰፍት ወደ ምሕረት፤ እያንዳንዱን ጥፋት ወደ ድኅነት፤ እያንዳንዱንም ሞት ወደ ሕይወት መቀየራችን አይቀርም። እውነታው አይቀሬ ነው።
ኢትዮጵያ የዘመናት ፈተናዎቿ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸነፉና ብሩህ ተስፋዋ እየበዛላት በመሆኑ የተስፋ መንገዳችን በስኬት እንዲቋጭ ዛሬም ሆነ ነገ ፈተናውን በድል መወጣት ይኖርብናል። በየመንገዳችን የሚገጥሙን ፈተናዎች እንደ ተስፋ መሻገሪያ በሮች በመጠቀም እንደ ሀገር ለምናደርገው የዴሞክራሲ ጉዞ ከፊታችን የሚጠብቀን ምርጫ በድል ከተወጣነው አንዱ የተስፋ በራችን ይሆናል። ስለዚህ ሁላችንም ጥሩ ዝግጅት አድርገንና መንፈሳችንን አጠንክረን በድል መሻገር ይኖርብናል።
አሁን በሀገራችን በመጣው ለውጥ ያልተደሰቱ ኃይሎች ለውጡን ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየሰሩ ቢሆንም ጥምቀቱ አንዴ ተደርጓልና አገርን የማተራመስ ሴራቸው ሊሳካ አልቻለም። ኢትዮጵያ በትክክለኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ በመግባት ስኬታማ የብልፅና ጉዞ ማድረግ የጀመረችበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት መለወጥን ባለመፈለግ እዚህም እዛም የሚከሰቱ ግጭቶችና መፈናቅሎች ለኢትዮጵያችን ፈተና መሆናቸውን በማመን የኢትዮጵያን እድገትና ለውጥ ከመጥላት ወደ ተሻለ የትልቅነት ማማ መውጣት የሚሻል መሆኑን የጥምቀት በዓል አስተማሪ ሆኖ ያልፋል።
ኢትዮጵያን የማፈራረስ አጀንዳቸው የፈራረሰባቸው የውስጥና የውጭ ኃይሎች ሴራ እየፈረሰ ከመሆኑ ባለፈ ኢትዮጵያ ለውጡን ከዳር ለማድረስ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሷን በተግባር ያስመሰከረችበትም በመሆኑ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል ቀጣይ የቤት ሥራ ሆኗል። ስለሆነም እውን እየሆነ የመጣው ሀገራዊ ለውጥም ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሙትም ችግሮቹን በትህትና ተሻግረን የተዘራብንን መቅሰፍት ማስወገድና የተዘረጋብንን ወጥመድ በጣጥሰን መጣል ይኖርብናል።
የክርስቶስ ጥምቀት በዓል የለውጥና የትሕትና ተምሳሌት በመሆኑ በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር በልዩ ልዩ አጋጣሚዎች የተጎዱ ወገኖቻችንን በቸርነት ዓይናችን እያየን፣ የተቸገሩትን በድጋፍ እጃችን እየጎበኘን፤ ለመልካም ለውጥ ሳንሰንፍ፣ ከብልጽግና ጉዟችን ሳንደናቀፍ፣ የወቅቱን የኮቪድ-19 ስርጭት ችላ ሳንል፣ የወደፊት አዲስ ተስፋን በመሰነቅ ሊሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 11 ቀን 2013 ዓ.ም