አብርሃም ተወልደ
የእያንዳንዱ ሰው የፋሽን ህልም በኢጣሊያ ይሸጣል።እዚያ ፋሽን ሆኖ የማይመረት፤ ቦታ የማያገኝ ምርት የለም።ጣሊያን ለፋሽኑ ዓለም ጅማሮና ዕደገት ባበረከተችው አስተዋፅዖ የቀዳሚውን ስፋራ ትይዛለች።
ይህ እውነት ደግሞ ምንም አያስገርምም።ምክንያቱም የጣሊያን የንግድ ምልክት ያላባቸው ምርቶች ዛሬ በዓለም ላይ እንደ ዋናው ፋሽን ዓለም ምልክት የምርቶች የጥራት መለኪያ ተደርገው ነው የሚወሰዱት።
ጣሊያኖች በአገራቸው ለሚመረቱ ልብሶች ጫማዎች እና ለሌሎች የመዋቢያ እና መሰል ምርቶች ለእያንዳንዳቸው መስፈርቶች አሏቸው።በመጀመሪያ ደረጃ የአካባቢው ሰዎች ለምርቱ ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፤ በዚህም ምክንያት በዓለም አቀፉ ገበያ ተመራጭ ምርት እንዲመረቱ የሆኑት።ታዲያ እነዚህን የፋሽኑ ዓለም መለኪያ የሆኑ ምርቶች የምታመርተው ጣሊያን ለወትሮ በሰው የሚጨናነቁ የምርቶች ማሳያ መድረኮቿ በሰው ድርቅ ተመተዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት አርብ የጣሊያኑ ፋሽን የንግድ ምክር ቤት በሚላን ከተማ ባዘጋጀው የፋሽን ሳምንት ያለምንም የክብር እንግዶች ፕሮግራሙን ለማድረግ ተገድዷል።ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ነው።በቫይረሱ ምክንያት የክብር አንግዳ የሌለው ይህ የፋሽን ሳምንት በወቅቱ የቀረቡት የወንዶች አልባሳት በዲጂታል ቴክኖሎጂ በቨርቿል ታግዞ የቀረበም እንደነበር ኤቢሲ ኒውስ ዘግቧል።
የአገሪቱ የፋሽን ቻምበርስ በሐምሌ እና በመስከረም ወር ላዘጋጀው የፋሽን ሳምንት ግለሰቦች በቀጥታ የሚሳተፉበት ፕሮግራም ያቀደ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የፋሽን ሳምንቱ ሲከፈት ከቤት ውጭ ሆኖ ለእይታ እና ለግዥ የሚቀርቡት የፋሽን ቁሶች ደግሞ ከንክኪ ርቀው በተዘጋ የመስታወት ቤት ውስጥ ሆነው ነበር።ይህም በአገሪቱ በድምቀት ለማከናወን የታቀደውን የፋሽን ሳምንቱ እንዲደበዝዝ አድርጎታል።
በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት ዶልቼ እና ጋባና የተባለው የታወቀ አለም አቀፍ የንግድ ምልክት እና በተለይ የፋሽኑ ዓለም እንደ ዋና የንግድ ምልክት (ብራንድ) የሚቆጠሩት ይህ ግዙፍ የንግድ ድርጅት በከተማዋ በተዘጋጀው የፋሽን ትርኢት ለመሳተፍ ፍቃደኛ እንዳልሆነ የኤቢሲ በዘገባው ገልጸዋል።
ከዶልቼ እና ጋባና ውጭ በፋሽን ትርኢቱ ትልልቅ የንግድ ተቋማትን እና የንግድ ምልክቶችን የያዙ 36 ድርጅቶች ተሳትፈዋል።ሁሉም ግን ምርታቸውን ያስተዋወቁት እንደቀድሞ በሞዴሎች ሳይሆን በዲጂታል በታገዘ መሳሪያ ነው።
የአገሪቱ የቻምበርስ ፕሬዚዳንት ካርሎስ ካፓሳ እንደሚሉት በትርኢቱ እኛ የተቻለንን ነገር አድርገን ከወረርሽኙ መዛመትን በሚከላከል መልኩ ፕሮግራሙን ብናዘጋጅም የኮቪድ ህጉ ግን ይህንን ስለማይፈቅድ ዝግ በሆነ ፕሮግራም ማንኛውም ተመልካች ዲጂታል መሳሪያዎችን በመጠቀም እንዲመለከት ትርኢቱም በዚህ መልኩ እንዲሄድ ተገድደናል።
የጣሊያን መንግስት ካሳለፍነው አርብ አስከ የካቲት 15 ቀን ድረስ በአገሪቱ ከአንደኛው ከተማ ወደ ሌላው ከተማ መጓጓዝን የሚከለክል አዲስ የጉዞ ገደብ ህጎችን አውጥቷል።ይህም የፓሪሶችን የፋሽን ሳምንት አዘጋጆች ቀጥታ በአካል ሁሉም ግለሰቦች ሊሳተፉበት የሚችሉበት የወንዶች አልባሳት ለማሳየት የያዙት እቅድ እንደከሸፈም የወሬ ምንጩ ገልጸዋል።ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ የሴቶች የፋሽን ትርኢት የሚቀርብበት ጊዜ ላይም ጥላ እንደሚያጠላበትም ምንጩ አስነብቧል።
የቻምበርሱ ፕሬዚዳንት ካፓሳ አክለው እንዳሉት አለም አቀፍ በረራዎች መከልከላቸው አገር ውስጥም ያለው ጉብኚ በአካል ተገኝቶ ያለመጎብኘቱ ድርጅቶቹ ወደ ኢኮሜርስ ወይም የዲጂታል ግብይት በመግባት ይህንንም የቴክኖሎጂ ስልታቸውን እንዲያዘምኑ እና እንዲጠቀሙ እንዳደረጋቸው ጠቁመዋል።
እንደ ካፓሳ ገለጻ በቀጥታ የዲጂታል ሽያጭ ሸማቾች ከፍተኛ ግዢ እየፈጸሙ ሲሆን በዚህም የሚላንን የፋሽን ሳምንት ሚሊዮን ሰዎች እንዲጎበኙት ሆኗል።ይህም ትርኢት ከኮቪዱ አንጻር እጅግ የከፋ ችግር ያጋጥመዋል ቢባልም ከታሰበው ግን እጅጉን የላቀ እና አስደሳች ነበር።
ይህም ሆኖ ግን የፋሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አጋጥሞታል የሚሉት የቻምበርሱ ፕሬዚዳንት ካፓሳ የኢጣሊያ የፋሽኑ ኢንዱስትሪ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር የ2019 ውን የነበረው ከ2020 ጋር ሲነፃፀር 50 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 61 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።አገሪቱ ለፋሽኑ አለም ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው ገቢ 43 ቢሊዮን ዩሮ አጥታለች።ይህም ወደ ውጭ የሚላኩ ለፋሽኑ ኢንዱስትሪ የሚያገለግሉ ምርቶች 25 በመቶ እንደቀነሱ ተገልጸዋል።
በቻይና “የበቀል ገበያ” በሚል በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ቤት ይቆዩ የሚለው እገዳ ተነስቶ በተፈቀደላቸው ጥቂት ጊዜ በሚያስገርም ሁኔታ በኢኮሜርስ ወይም በቴክኖሎጂ ግብይት የተሳተፉ ሲሆን በጣም ቅንጡ የሚባሉ የመዋቢያ እና የማጌጫ ቁሶቹን ገዝተዋል የሚሉት ካፓሳ በአውሮፓ ግን የመጀመሪያ የጉዞ ክልከላ ሳይናሳ ሌላው አዲሱ የኮቪድ ቫይረስ በመገኘቱ ክልከላው በዚያው ስለጸና እና ሰውም ባለው ሁኔታ ፍርዓት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ስለሆነ ገበያው እጅጉን የተቀዛቀዘ እንዲሆን አድርጎታል።
የፋሽን ኢንዱስትሪው በጣሊያን በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ትልቅ ገቢ ከሚያስገኙ ዘርፎች አንዱ ነው፤ የሚሉት ካፓሳ ታዲያ ይህን ኢንዱስትሪ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ታሟል፤ ኢንዱስትሪው ከመንግስት የማገገሚያ የገንዘብ ድጋፍ ይፈልጋል።በተለይ በአነስተኛ በጀት እና በግል የሚሰሩ የግል ኢንዱስትሪዎች ከመውደቅ ለመታደግ ድጋፍ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው።
ካፓሳ በማጠቃለያቸው የኮሮና ቫይረስ ክትባት እየተገኘ ስለሆነ ስጋቶች ቀስ በቀስ እየቀነሱ ስለሚሄዱ የፋሽኑ ኢንዱስትሪም ወደ መደበኛ ሀኔታው እንደሚመለስ ተስፋ አለኝ ያሉ ሲሆን ክትባቱ ደርሶ ነገሩ እስኪረጋጋ ግን ዘርፉን ለመታደግ የሚመለከተው ሁሉ የተቻለውን ማድረግ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013