ሀገሯን ያስቀደመችው የማራቶን ንግሥት

ባለፈው ሚያዝያ በለንደን ማራቶን በሴት አሯሯጮች ብቻ የተመዘገበውን የዓለም የማራቶን ክብረወሰን ያሻሻለችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ በግል ውድድር ከምታገኘው ክብር ይልቅ ለሀገሯ ኢትዮጵያ ቅድሚያ መስጠቷን አረጋግጣለች።

የኦሊምፒክ ማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊና የወቅቱ የማራቶን ንግሥት የሆነችው ትዕግስት አሰፋ ከዓመት በፊት በርሊን ማራቶን ላይ ያሻሻለችው ሌላኛው የዓለም ክብረወሰን በ2024 የቺካጎ ማራቶን በኬንያዊቷ አትሌት ሩት ቺፕንጌቲች በ2:09:56 መሰበሩ ይታወሳል።

ትዕግስት በኬንያዊቷ የተሰበረውን ክብረወሰን በቀጣይ መስከረም በርሊን ማራቶን ላይ ለማስመለስ ጠንካራ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች። ይሁን እንጂ ለዚህም ከበርሊን ማራቶን በፊት በሚካሄደው የቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያን እንድትወክል መመረጧን ተከትሎ የመርሐ ግብር መጋጨት ገጥሟታል። በዚህም የተነሳ ክብረወሰኑን ለማስመለስ ካደረገችው ዝግጅትና ካደረባት ጉጉት የተነሳ በዓለም ሻምፒዮናው እንዳትሳተፍ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከትናንት በስቲያ እንዳስታወቀው በፌዴሬሽኑ አግባቢነት አትሌት ትዕግሥት አሰፋ በበርሊን ማራቶን የመሮጥ እቅዷን ትታ በቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና ለሀገሯ ለመሮጥ መስማማቷ ታውቋል። እንቁዋ የማራቶን ኮከብ አትሌት በበርሊን ማራቶን የዓለም ሪከርድ የመስበር እቅዷ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አግባቢነት ልትቀይር እንደቻለች ነው የተገለፀው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከአሠልጣኟ ጋር ባደረገው ስኬታማ እና ውጤታማ ውይይት ጀግናዋ አትሌት ትዕግስት በዓለም ሻምፒዮና ላይ ሀገሯን እና ሕዝቧን በመወከል የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በጃፓን ቶኪዮ ላይ ለማውለብለብ ከስምምነት ላይ ተደርሷል ።

በተደረገው ውይይት ላይም “ከሀገርና ከሕዝብ ምንም የሚበልጥ ነገር የለም” በማለት በሻምፒዮናው ላይ ለመሳተፍ እና ፌዴሬሽኑ ያቀረበላት የሀገር ጥሪ በፀጋ እንደምትቀበል አሠልጣኟ ገልጸዋል።

የአትሌት ትዕግስት አሰፋ አሠልጣኝ ገመዶ ደደፎ መጀመሪያ “በርሊን ማራቶን” ለመሮጥ የቀረበ ጥያቄ “በኬንያዊቷ አትሌት ሩት” የተያዘውን ክብረወሰን ለመመለስ እና በአሁኑ ሰዓት ትዕግስት በጥሩ አቋም ላይ በመሆኗ ክብረወሰን ቢሻሻል የኢትዮጵያ ስም ከፍ ለማድረግ የታሰበ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አትሌት ትዕግስት ያሳየችውን ታላቅ የሀገር ፍቅርና፣ ሀገርና ሕዝብ በማስቀደም ለቀረበላት ጥያቄ በጎ ምላሽ በመስጠቷ አክብሮትና ምስጋና አቅርቧል። ከአትሌቷ በተጨማሪም አሠልጣኟ ለሀገር እንድትሮጥ ያሳዩት ፍላጎት ፌዴሬሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል።

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በቶኪዮው የዓለም ሻምፒዮና በሴቶች ማራቶን በአራት አትሌቶች የምትወከል ይሆናል። ባለፈው የቡዳፔስት ዓለም ሻምፒዮና አሸናፊ የነበረችው አትሌት አማኔ በሪሶ ሻምፒዮንነቷን ለማስጠበቅ በቀጥታ ተሳታፊ የምትሆን አትሌት ናት።

በፓሪስ ኦሊምፒክ ሀገሯን መወከል ባለመቻሏ ትልቅ ቅሬታ ውስጥ የነበረችው አትሌት ሱቱሜ አሰፋ የ2024 ቶኪዮ ማራቶንን ማሸነፏ ይታወሳል። ይህን ውድድር ባሸነፈችባት ከተማ ቶኪዮ ሀገሯን በዓለም ሻምፒዮና ወክላ ቁጭቷን የመወጣት ዕድል አግኝታለች።

ሌላኛዋ ድንቅ የማራቶን አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው በቶኪዮው ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የምትወክል ሦስተኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሆናለች። ያለምዘርፍ በ2024 የአምስተርዳም ማራቶን አሸናፊ እንደነበረች ይታወሳል። የ2024 የዱባይና የበርሊን ማራቶን ውድድሮች አሸናፊዋ አትሌት ትዕግስት ከተማ ደግሞ በተጠባባቂነት የተመረጠች አትሌት ነች።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You