በመፈታት ላይ ያሉ የቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ችግሮች

ወይዘሮ ራሄል ግርማቸው ትባላለች። የሞጆ ከተማ ነዋሪ ስትሆን፤ ሠርታ የትዳር አጋሯን ማገዝ ብትፈልግም ሥራና እሷ አልገጣጠም ብለው ቆይተዋል። ይህም ወጣት ሆና ሳትወድ የቤት እመቤት እንደትሆን አስገድዷታል። ባለቤቷ በሚያገኘው ገቢ ኑሮን ለመምራት እየጣሩ ባለበት ጊዜ፤ ሥራ የሌላቸው ይሁንና ሥራ የሚፈልጉ ወጣቶች ምዝገባ እየተከናወነ መሆኑን ባለቤቷ ሰማ። ለኑሯቸው መልካም ነገር ይዞ እንደሚመጣ በማሰብ አስመዘገባት።

በተደረገው ማጣሪያ ካለፉት ሥራ አጦች መካከል ተመራጭ ሆና ሥልጠና ጀመረች። በሥልጠናው ከቆዳ ቦርሳና የእጅ ጓንት ማምረት የሚያስችል እውቀት ቀሰመች። ከእሷ ጋር ከቆዳ ቦርሳ የማምረት ሥልጠና የወሰዱ 32 ሰልጣኞችና ቆዳ ጫማ ማምረትን የሰለጠኑ 41 ሰዎች በማኅበር ተደራጅተው አስፈላጊው ግብአት ተሟልቶላቸው ሥራ ጀመሩ።

ባለሥራ ሆነችና ሥራአጥ የሚለው የወል ሥም መጠሪያዋ መሆኑ ቀረ። ሥራ ፍለጋ በሀሳብም ሆነ በአካል አትንከራተትም፤ በማኅበሯ አማካኝነት የተለያዩ የቆዳ ውጤቶችን ማምረቷን ቀጠለች። ራሄልና መሰሎቿን አሰልጥኖ ለሥራ ዝግጁ ያደረጋቸው ፕሮጀክት በተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ላለፉት ሰባት ዓመታት ሲተገበር የቆየውና በቅርቡ የተጠናቀቀው የቆዳ ልማት ዘላቂ ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት ነው።

የቆዳ ልማት ዘላቂ ሥራ ፈጠራ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አውሪሊያ ፓትሪዚያ ፕሮጀክቱ በቆዳ ኢንዱስትሪው ላይ እሴት ለመጨመር እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት፤ ለቆዳ ኢንዱስትሪ ጥራቱን የጠበቀ ቆዳ ለማግኘት እንስሳቱ የሚታረዱበት ሁኔታ ወሳኝ በመሆኑ በአዳማ፣ በሞጆ፣ በቢሾፍቱና በአዲስ አበባ ለሚገኙ ስድስት ቄራዎች ዘመናዊ የማረጃ መሳሪያ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዘርፉ ባለሙያዎች ማፍራት የሚያስችል የሥልጠና ማንዋል ተዘጋጅቷል። ፕሮጀክቱ ቆዳ ከእርድ ሂደት አንስቶ እስከ መጨረሻው የምርት ሰንሰለት ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እንዲዘጋጅ ለሚመለከታቸው አካላት ሥልጠና በመስጠትና ግብአት በማሟላት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በዚህ ሂደት በሀገሪቱ ዓለም አቀፉ የሌዘር ሥራ ቡድን (ሌዘር ወርኪንግ ግሩፕ) እውቅና ከሰጣቸው ስድስት የቆዳ ኢንዱስትሪዎች አራቱ በፕሮጀክቱ ድጋፍ ያገኙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ይህም በአፍሪካ በቡድኑ እውቅና ካገኙ አሥር ፋብሪካዎች የስድስቱ መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ በዘርፉ ቀዳሚ መሆን የሚያስችላት ነው።

ፕሮጀክቱ በዋናነት 60 በመቶ የኢትዮጵያ የቆዳ ኢንዱስትሪ መገኛ በሆነችው ሞጆ ከተማ ላይ በማተኮር መሠራቱን ጠቅሰዋል። በዚህም በከተማው ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ የሚሆን የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ በመገንባት፣ ሥልጠና በመስጠትና የማምረቻ መሳሪያዎችን በማሟላት የሥራ እድል መፍጠር አስችሏል።

ሞጆ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ እሸቱ ሹሜ በበኩላቸው፤ በከተማው የሚገኙት የቆዳ ኢንዱስትሪዎች ከጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ከማምረቻ ማሽን እጥረትና ከምርት ጥራት ጋር የተገናኙ ክፍተቶች እንደነበሩባቸው ጠቅሰዋል። ክፍተቱን ለመሙላት የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት በቀረጸው ፕሮጀክት ለቆዳ ኢንዱስትሪዎች እገዛ ሲያደርግ መቆየቱንና በዚህም ለውጦች መታየታቸውን አንስተዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ፤ በከተማው በፕሮጀክቱ 120 ሥራ አጥ ወጣቶች የቦታ፣ የማምረቻ መሣሪያ እና የአቅም ግንባታ ሥልጠና በማግኘት ወደ ሥራ ተሰማርተዋል። በፕሮጀክቱ ሥልጠና ያገኙትና የሥራ ቦታ የተመቻቸላቸው ወጣቶች የቆዳ ጫማ፣ ቦርሳና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን በማምረት ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪ በፕሮጀክቱ በከተማው ቆዳና የቆዳ ምርቶችን መመርመሪያ ቤተመኩራ /ላብራቶሪ/ በሞጆ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል። ቤተመኩራው ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን የሚያሟሉ የቆዳ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል።

ዓለም አቀፉ የሌዘር ሥራ ቡድን የቆዳ ምርቶችን በሚገዙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተቋቋመ ነው። እነዚህ ሸማቾች የሚገዙት ቆዳ ከመነሻው ያለፈበትን ሂደት ማወቅ ይፈልጋሉ የሚሉት የፕሮጀክቱ የሀገር ውስጥ አስተባባሪ አቶ ወንዱ ለገሰ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቶቹ በትክክለኛ መንገድ ያመርታሉ ብለው ለሚያስቧቸው አምራቾች እውቅና ይሰጣሉ። እውቅናውን ለማግኘት ቆዳው የት ተመረተ? እንዴት ተመረተ? በምን ያህል ጥራት ተመረተ? ፋብሪካው እንዴት ይሠራል? ሠራተኞቹን እንዴት ይዟል? የሚሉና መሰል ዶክመንቶችን በሙሉ ፋብሪካው መያዝ አለበት። ባላቸው ሰነድና በሌሎችም መስፈርቶች አስፈላጊው የምርት ሂደት ማሟላታቸው ለተረጋገጠ ፋብሪካዎች የሚሰጥ ዓለም አቀፍ የእውቅና ማረጋገጫ ነው።

እውቅናው በቆዳ ገዢዎች ዘንድ የሚፈለግ ሲሆን፤ ዓለም አቀፍ ቆዳ ገዢዎች ግብይት ከመፈጸማቸው በፊት ድርጅቱ ይህን እውቅና ማግኘቱን ይጠይቃሉ። ለዚህም ፕሮጀክቱ ቴክኒካል ባለሙያዎችን በመቅጠር ከፋብሪካዎቹ ጋር አብሮ በመሥራት፣ ፋብሪካዎቹ ማሽኖችን እንዲቀይሩ፣ የፋብሪካውን ጽዳት እንዲጠብቁና የጎደሏቸውንና ማሟላት የሚጠበቅባቸውን በመለየት እንዲያሟሉ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ተሠርቷል።

በፕሮጀክቱ መሰል ድጋፍ ተደርጎለት አሁን በብር ደረጃ እውቅና ያገኘው ኮልባ ታነሪ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ደጀኔ፤ ድርጅታቸው እውቅናውን እንዲያገኝ ከፕሮጀክቱ ድጋፍ ማግኘቱን ይናገራሉ።

ከ50 ዓመት በላይ በቆዳ ዙሪያ የተሰማሩ ቢሆንም በቡድኑ ስለሚሰጠው እውቅናና እውቅናው ስለሚያስገኘው ጥቅም ጥልቅ ግንዛቤ አልነበራቸውም፡: የቆዳ ንግድ ሲጀምሩ ከድሬዳዋ፣ ከሐረር፣ ከጎጃም፣ ከሰላሌ እና ከወለጋ እንዲሁም ከሌሎችም አካባቢዎች ቆዳ ይሰበስቡ ነበር። ይህ የቆዳ ንግድ ፍሬ አፍርቶ አሁን በፋብሪካ ለቆዳ ምርት ግብዓት የሚሆን የለሰለሰ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ወደ ማምረት ተሸጋግሯል። በዚህ ሂደት የተበላሸውን ከጤነኛ ቆዳ የመለየት ልምድም አግኝተዋል። ከተለያዩ አካባቢዎች ቆዳ የሚሰበስቡ ነጋዴዎች “ሳላጉላላ ክፍያ ስለምፈጽምላቸው ይመርጡኛል” ብለዋል።

አቶ አየለ ከቆዳ በተጨማሪ ወደ ውጭ ሀገር ሥጋ የሚልክ ድርጅት አላቸው። በሁለቱ ድርጅቶች 800 ሠራተኞች ያላቸው ሲሆን፤ በፋብሪካው ቆዳ ሂደቱን ጠብቆ አልቆ ልብስ ሆኖ ይወጣል። ፋብሪካው በሀገር ውስጥ ለራሱ ከሚጠቀመው ግብዓት በተጨማሪ በርካታ አነስተኛ ጫማ አምራቾች የሚያስፈልጋቸውን የቆዳ ግብዓት የሚያገኙበት ቦታ ነው። በፋብሪካው የሚመረቱ የቆዳ ግብዓቶችና ያለቀላቸው የቆዳ ውጤቶች ለዓለም አቀፍ ሸማቾች ተሽጠው የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ ነው።

ፋብሪካው ጥቅም ላይ የሚያውለውን ቆዳ የሚያገኘው ከሀገር ውስጥ ቢሆንም፤ ቆዳውን ወደ ሚፈለገው ምርት መቀየር ይቻል ዘንድ በርካታ ኬሚካሎች ከውጭ ይመጣሉ። ሰርተፍኬቱን ለማግኘት በርካታ መስተካከል ያሉባቸው አሠራሮች ከመቀየር ጀምሮ አስፈላጊ ማሽኖች መሟላታቸውንና በዚህም በውጭ ገበያ ያላቸው ተፈላጊነት እንደሚጨምር ይናገራሉ።

“የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራት ከአስተራረዱ እንዲሁም ከአገፋፈፉ ይጀምራል” የሚሉት የፕሮጀክቱ የሀገር ውስጥ አስተባባሪ አቶ ወንዱ፤ ለቆዳው ጥራት ወሳኝ የሆኑ የእንስሳ አራጆችና ቆዳ ገፋፊዎች በሥራ ላይ የተሰማሩትም ሆነ ለመሰማራት የሚፈልጉ የሚማሩበት ካሪኩለም አለመዘጋጀቱንና ስልጠና አለመኖሩን ያነሳሉ።

እንደእሳቸው ገለፃ፤ የቆዳውን ጥራት ለማስጠበቅና በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመቅረፍ የአንድ ጊዜ ሥልጠና መስጠት በቂ አለመሆኑን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ከመግባባት ላይ ተደርሷል። ለባለሙያዎቹ የሚያስፈልገው ሥልጠና በትምህርት ተቋማት መሰጠት አለበት በሚል ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ከግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም ከቆዳ ኢንስትቲዩት ጋር ተማሪዎች የሚማሩበት ካሪኩለም ተዘጋጅቷል።

ካሪኩለሙ ጸድቆ ተግባራዊ ሲደረግ በጥሬ ቆዳና ሌጦ ላይ እመርታ ያመጣል። ከባለሙያዎቹ በተጨማሪ በቄራዎች ያሉ መሳሪያዎች የቆዳና ሌጦ ጥራት ድርሻ አላቸው። የሚሉት አቶ ወንዱ፤ ቆዳው በሚገፈፍበት ወቅት ጥቅም ላይ የሚያውሉት አግባብነት የሌላቸውና ለዚህ የተዘጋጁ ቢላዎች አለመሆናቸውን በማንሳት፤ ፕሮጀክቱ ለእዚህ የሚሆኑ ቢላዎችን ለተወሰኑ ቄራዎች ማቅረቡን ያስረዳሉ። ቆዳው ከእንስሳቱ የሚላቀቅበት ዘመናዊ ማሽን ለስድስት ቄራዎች ተሰጥቷል ይላሉ። ይህን ያደረጉት ለቆዳው ጥራት በማሰብ መሆኑንና ጥራት ያላቸው ቆዳዎች ከቄራዎች ወደ ቆዳ ፋብሪካዎች እንዲሄዱና የተሻለ ቆዳ ለማውጣት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ከቄራዎቹ የሚወጡት ቆዳዎች ጥራታቸውን የጠበቁና እሴት ተጨምሮባቸው ምርት ሆነው የሚሸጡ ማድረግ መቻሉን ይጠቁማሉ።

በአሁኑ ወቅት የበሬ ቆዳ በሽሚያ እንደሚገዛ የተናገሩት አቶ ወንዱ፤ የበሬ ቆዳ በሙሉ ወደ ፋብሪካ የሚገባበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል። ‹‹አልፎ አልፎም ቢሆን አሁንም በየቦታው የወደቁ ቆዳዎች ይታያሉ። ቆዳ ለምን ይወድቃል? የሚለውን መጠየቅ አለብን።›› ያሉት ኃላፊው፤ “ብዙ ቦታ ቢላዋ ያረፈበትና የተቆራረጠ ቆዳን የቆዳ ፋብሪካዎች አይገዙም።” ይላሉ። የተበሳሳ ቆዳ ማሽን ውስጥ ሲገባ የሚበጣጠስ በመሆኑ ፋብሪካዎች ገዝተው ኬሚካል ጨምረው ለተጨማሪ ኪሳራ መዳረግ አይፈልጉም። ይሁንና ከመጀመሪያው ጥራት ያለው ቆዳ ከተዘጋጀ ቆዳ ፋብሪካዎች ይወስዱታል።

እንደ አቶ ወንዱ ማብራሪያ፤ አሁን ማረድ የሚችለውም ሆነ ማረድ የማይችለው “አራጅ ነኝ” እያለ ገንዘብ ብቻ ለማግኘት የፈለገ እርድ ሲያከናውን ቆዳው ስለሚበሳሳ ቆዳዎቹ ገዢ አያገኙም። በመሆኑም የሀገር ሀብት በየቦታው ይወድቃል። ለዚህ መፍትሄው ቆዳውን በትክክል መግፈፍ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማዘጋጀት ነው። ለዚህም ተገቢውን ሥልጠና የወሰደና ማረጋገጫ ያለው እርድ የሚያከናውንበትን ሁኔታ ማዘጋጃ ቤቶች እንዲፈጥሩ ማድረግ ያስፈልጋል። በአራጅነት ሰርተፍኬት የሌለው ሰው አራጅ ነኝ ብሎ ቢለዋ ይዞ እንዳይዞር መከልከል አለበት። ለዚህም ሕግ ሊወጣለት ይገባል፤ አስገዳጅ ሲሆን ሁሉም ሰው ወደ ሥልጠና ይመጣል።

በተመሳሳይ ሕብረተሰቡ ላይም የግንዛቤ ሥራ ሲሠራ ሕብረተሰቡ የሰለጠኑትን አራጆች ብቻ መጠቀም ይጀምራል ያሉት አስተባባሪው፤ ሽግግሩ በአንድ ጊዜ ባይመጣም መጀመር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ሁሉም እርድ በዘመናዊ መንገድ በቄራ መከናወን ይኖርበታል። በየቤቱ የሚካሄድ እርድ መቅረት አለበት። ለዚህም ቄራዎች አሁን በቋሚነት ካሉበት በተጨማሪ በበዓልና መሰል የእርድ ፍላጎት በሚጨምርበት ወቅት በየቦታው እየተንቀሳቀሱ እርድ የሚያከናውኑበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል። ከዚህ ቀደም ሰፈር ውስጥ የሚያርዱም ቢሆኑ እርዱን ይችሉ እንደነበር በማንሳት፤ አሁን ግን ገንዘብ የፈለገ ሁሉ ለበዓል ቢላዋ ይዞ የሚዞርበት ሁኔታ መፈጠሩንና ይሄም ቆዳውን እያበላሸው መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን ያሉት ቄራዎች በቂ አለመሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ወንዱ፤ ለዚህም 90 በመቶ የፍየልና የበግ እርድ በየቤቱ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። ሆኖም በቄራ እርድ ለማከናወን ከውስንነታቸው አንጻር ረዥም ሰዓት የሚያስጠብቅ መሆኑንና ረዥም ርቀት የሚያስጉዝ መሆኑን በማንሳት በአጭር ሰዓት ግልጋሎት ለማግኘት ቄራዎች ወደ ሕብረተሰቡ መቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሚልኬሳ ጀገማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራት እንዲጨምር ለቄራዎች ድርጅትና ለቆዳ ሰብሳቢ ነጋዴዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በተናጠልና በመድረክ በመደበኛነት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውቀዋል። በተለይ የቆዳ አቅራቢዎችን ከፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር ሥራ እየተሠራ ነው። ቆዳ ላይ ዕሴት በመጨመር ያለቀላቸው የተለያዩ የቆዳ ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ ጓንት እና ሌሎች ምርቶችን በማዘጋጀት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመዋል።

በቀጣይም በተቋማቸው የቆዳና ሌጦ ጥራትን በማሻሻል ከትምህርት ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን የተማሪዎች ቦርሳ አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው ወደ ሥራ ገብተዋል። ከዚህ ቀደም ሌዘር ላይ የድጋፍ ክፍተቶች እንደነበሩ በማንሳት፤ ለዚህም በአዲስ መልክ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ የነበሩ ማነቆዎችን በመለየትና መፍትሄ በማስቀመጥ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You