
“ውድ ልጄ ይህ ደብዳቤ ካለህበት በሰላም ይድረስህ። የት ነህ? የት ነህ ደስታዬ? የት ነህ ልጄ? ተወልደህ ትናንሽ እጆችህን እጆቼ ላይ የያዝኳቸው ቀን፤ ለዘለዓለም ላለቅህ፣ ልወድህ፣ ሕይወቴ ላንተ እንዲሆን፣ ልደግፍህ፣ ላነሳህ፣ ላድንህ፣ ልጠብቅህ፣ ልሞትልህ ቃል ገብቻለሁ። አንተን ፍለጋ ድባብ ከመጣሁ ሳላስብህ፣ ሳልፈልግህ የመሸ ቀን የነጋ ሌሊት የለም። ያለህበትን የሆንከውን ሳላውቅ አላርፍም። ድባብ ውስጥ ባንተ መጥፋት እጃቸው ያለበትን በሙሉ አስከፍላቸዋለሁ!…” ይህ በ‹ልጄስ?› ድራማ ውስጥ ከመግቢያው የምናደምጠውና የምንመለከተው የማጀቢያ ምስልና ድምጽ ነው።
በደብዳቤው ውስጥ የምናገኛቸው የሃሳብ ሰበዞች፣ ከጅምር እስከ ፍጻሜው ላለው ታሪክና ጭብጥ እንደ ግዙፍ ጠጣር ተደርገው ተቀምጠዋል። በአዕምሯችን የተቀረጸውን በእናትና ልጅ መካከል የምናውቀውን የሚያስንቅ ፍቅር፣ በ‹ልጄስ?› ድራማ ውስጥ ልብን ከሚንጥ ስሜት ጋር እናገኘዋለን። አባት ለልጁ የሚከፍለውና የሚሰጠው አጋፔ ፍቅር ነው።
በሀገራችን የተከታታይ ድራማ ታሪክ በሰፊው ተመልካች ዘንድ ሰፊ እይታን ካገኙና ከተወደዱ፣ ብዙ ከተወራላቸው፣ እንዲሁም ከተወራባቸውም ጭምር መሆኑ ነው። የድራማውን ባህር እየቀዘፈ በመሄድ ከነበረው መርከብ ፊት ድንገት የተነሳ ወጀብ ገጥሞት ነበር፤ ግን አምልጦ ከዳርቻው ሊደርስ ችሏል። ደራሲውም ዳይሬክተሩም የነበረው ካፒቴን የመጣበትን ሁሉ ተቋቁሞ፣ በስተመጨረሻ በምን ተአምር ከማዕበሉ ሊያመልጥ ቻለ…የተወራበትን ፍራቻ ፍጻሜውን ሌላ አደረገው ወይንስ አስቀድሞም እንዲሁ ነበር? ነገም መሰል ክስተቶች ውስጥ እንዳንገባ፤ ይህን ጅራት ከወደኋላ እንመለስበታለን።
የ‹ልጄስ?› ድራማ ደራሲና ዳይሬክተር ወጣቱ ሰማኝ ጌታ አይችሉህም ነው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በብዙ ማስደመሙን ተያይዞታል። በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ኤርክራፍት ኢንጀነር ሆኖ ለሁለት ዓመታት ያህል ሲያገለግል ከቆየ በኋላ፣ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ፊልምና ድራማው ዓለም ገብቷል። “ጉዞ ፊልምስ” የተሰኘ የራሱን ፕሮዳክሽን በመክፈት የጥበብ ሩጫውን ጀምሯል። በጥቂት ዓመታት ብቻ ሲትኮምና ተከታታይ ድራማዎችን፣ የሙሉና የአጭር ጊዜ ፊልሞችን ሠርቷል። ደራሲ፣ ዳይሬክተር፣ ሲኒማቶግራፈር፣ ኤዲተር እና ፕሮዲዩሰርም ጭምር ነው።
የድራማው መቼት አንዲት “ድባብ” ከተሰኘች ነውጠኛ መንደር ውስጥ ይዳክራል። ራሷን ከሁሉ አግልላና ተገላ በራሷ ዛቢያ የምትማስን ምስኪን መንደር ነች። ሕዝቦቿ ከችግር ወደ ችግር፤ መከራን የሚያፈራርቁ እንጂ ከመከራ የሚነጠሉ አይደሉም። “ድባብ መጥፎ ብቻ ሳይሆን ጥሩም ነገር አላት” ይሏታል። ደራሲው፤ ድባብን ኢትዮጵያ ወይንም የኢትዮጵያ አካል አድርጎ መቁጠሩን ለተመልካቹ የተወው ይመስላል።
“ልጄስ?” የሚለው ገዛኸኝ ልጁን ፍለጋ ‹ልጄ› የተባለው ደግሞ አንድያ ልጁ መላኩ ነው። መላኩም ከሚሳሳለት አባቱ በእንባ ተለይቶ፣ ለትምህርትና ለሥራ ወደ ድባብ ገብቷል። አባቱ ገዛኸኝ በቀድሞው ሕይወቱ ብዙ በደል የሠራ አደገኛ ሽፍታ ነበር። አሁን ግን በዚያ ድርጊቱ የሚጸጸትና በደሉን ለማከም የሚጥር ገበሬ ነው። ገዛኸኝ ከልጅነቱ አንስቶ ያለ እናት በፍቅር ላሳደገው መላኩ ያለው ፍቅር ከብረት የጠነከረና የጋለ ነው። የናፈቀውን ልጁን ፍለጋ ድባብ ቢመጣም፤ ልጁ መላኩ ግን እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ የውሀ ሽታ ሆኗል። የድባብ ነዋሪ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ‹የመላኩ አባት› እያለ በገበሬነቱ የሚያውቀው ሰው ግን፤ በልጁ ምክንያት ድባብን በአንድ እግሯ ሲያቆማት እንመለከታለን።
ደራሲው ከርዕሱ ጀምሮ የድራማውን መልህቅ ያኖረው ልጁን በሚፈልገው ገዛኸኝ በተባለው ገጸ ባህሪ ላይ ቢሆንም፤ ታሪክና ጭብጡ ግን ከርዕሱ እጅግ የሰፋ ነው። አባት ልጁን ፍለጋ የሚሄድባቸው መንገዶች ሁሉ ከድባብ ሕዝብና የውስጥ አጀብ ጋር እየተሳሰሩ፣ የድራማው ሴራ በውስብስብ ምስጢሮች የታጨቀ መሳጭ ያደርገዋል። አንዱ ከሌላው ጋር ያለው ግንኙነት በማይገመቱ ጠንካራ ሰበዞች የተደወሩ በመሆናቸውም፤ ቀጣዮቹ እያንዳንዱ ገቢሮች ልብ አንጠልጣይነታቸው ከፍ እያለ አርባ ሁለቱም ክፍሎች በአንድ ትንፋሽ ፉት! ማለትን ያስመኛሉ።
በድባብ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ በ‹ቢስ› ጫካ እንደሚገኝ በአፈ ታሪክ ሲነገርለት የቆየ ነው። ነገር ግን አፈታሪኩ እውነት ሆነና ‹የድባብ ሀጢያት በዛ› በማለት በአንድ ምሽት፣ ሁለት የክብር አባቶችን ጨምሮ ብዙ የድባብ ሕዝብ በሞት ረመረመ። ሰዎቹ በሞቱባቸው በእያንዳንዱ ቤት ግርግዳ ላይም በደምና በቀለም ተመሳሳይ ምልክት ተስሎ ተገኘ። ነገሩም ‹የቢስ ቁጣ ነው› በማለት መላው የድባብ ሕዝብ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለቁጣው ማብረጃ ግብር ይገብርለት ገባ።
ከሆነ ጊዜ በኋላ ደግሞ፤ ‹የክቡር አባት ድባብን መምራትም ሆነ የቢስን ትዕዛዝ መፈጸም አልቻሉም› የሚል ጉልበተኛ ቡድን ተነስቶ “ሀገሬ” የተባለችውን መድኃኒት ቀማሚን አነገሠ። “ቢስ እያናገረኝ ነው… ድምጹን ሰማሁ” የምትለው ሀገሬም፤ መንፈሳዊውን አብዮቷን “ንዳድ” በሚል ቀይ ካባ ለባሽ ቡድን አዋቅራ ነውጡን አቀጣጠለችው። ከቁጣው ለመዳን የሚፈልጉም ንዳድን እንዲቀላቀሉና በግንባራቸውም የቢስን ምልክት እንዲያኖሩ መልዕክተ ትንቢቷን ብታስተላለፍም ከድባብ ሕዝብ ይህን አንቀበልም አሻፈረኝ ያሉም ነበሩ። “ልጄስ?” የሚለው ገበሬው ገዛኸኝ ‹ልጄ እዚያ ነው ያለው› ከሚልበት የቢስ ጫካ የተነሳ ከአንዳንዶች ጋር ይፋጠጣል።
ደራሲው ድባብን ከመንደሮች ሁሉ የተለየች መንደር አድርጎ ሲያበቃ፤ በድባብ ውስጥ ለሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ “የኢትዮጵያ ፖሊስ” የሚል ታፔላ መስቀልን ለምን ፈለገ? በዚህም ሳያበቃ፤ ከጅምር እስከ ፍጻሜው በፖሊስ ጣቢያው ውስጥ የሚታየው አንድ ፖሊስ ብቻ ነው፤ ለምን? የጣቢያው አስር አለቃና ኢንስፔክተሩም፣ ወንጀል መዝጋቢና ወንጀለኛ አሳዳጁም፣ አሳሪና ዘብ ጠባቂውም…አንድ ግርማ ብቻ ነው። ‹ከሺህ ልጥ አንድ ፍልጥ› ብለን እንዳንቀበል ደግሞ፤ ፖሊሱ እንኳንስ ለድባብ ለራሱም የማይበቃ እንቅልፋም መሆኑ ነው። ብዙኀኑ ከመጤፍ የማይቆጥረውና ቀረብ የሚሉትም “ዘ ፖሊስ” እያሉ እንደ ቆሎ ጓደኛቸው የሚመለከቱትም ጭምር ነው።
ቅቤ ላይወጣት እንደ ወተት በምትናጥ ድባብ ውስጥ አንድ እንቅልፋም ፖሊስን የማቆሙ አንደምታ ምን እንበለው? ‹የሰው ኃይል ላለማባከን› ካልን ደራሲና ዳይሬክተሩን የሚያስወቅስ ስህተትም ጭምር ነው። ከዚያ ይልቅ ግን ለማሳየት ወይንም ለመናገር የፈለገው አንድ ነገር አለ ብለን እንውሰደው። ድባብ መንግሥትም ጭምር የረሳትና ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ የሆነች ከተማ ናትና ከዚህ አንጻር፣ የህግ መመናመንን ለማመልከት ተጠቅሞበት ሊሆንም ይችላል። ይህ ደግሞ ቀጣይ ለሚመጡት እንደ ‹ንዳድ› ላሉ ታሪክና ሴራዎች ጡዘትን ለመስጠት አመቺ ነው። በዚህ መልኩ አሳማኝ ፈጠራ ሆኖ እንድንቀበለው ከተፈለገም፤ “የኢትዮጵያ ፖሊስ” ከማለት ይልቅ ‹የድባብ ፖሊስ› ቢባል ኖሮ የተሻለ ቅቡልነት ይኖረዋል።
የድራማው ደራሲና ዳይሬክተር በአዲስ እይታ አንድ የተለየ ነገር ለመፍጠር የሄደበት ርቀት ከልቡ መጠበቡ የሚያጠራጥር አይደለም። እጅግ ጠባብ በሆነ መቼት ውስጥ ታሪኩን የማይገመትና ልብ ሰቃይ ያደረገበት ጥበብ ይመሰክራል። የአንድ ደራሲ የመብቃቱ መለኪያ፣ ገጸ ባህሪያቱ ጥሩም ይሁኑ መጥፎ በየራሳቸው ማንነት አይረሴና ሳቢ አድርጎ መሳል መቻሉ ነው። የወደድናቸውን እስከ ጥግ እንድንወዳቸው፣ የጠላናቸውንም እስከ ጥግ እንድንጠላቸው ማድረግ ከቻለ፣ በደንብ አሳምኖናል ማለት ነው። ከተዋንያኑ ችሎታ አንስቶ፣ በተንቀሳቃሽ ምስሎቹ ውስጥ የምንመለከታቸው ነገሮች አንዳች ገሀዳዊ ተመስጦ ውስጥ እንድንገባ ካደረጉን ዳይሬክተሩ ብዙ ደክሞ፣ ብዙ እንደተጠበበት ይናገራል።
የተዋንያኑ መረጣ ‹ምንኛ የተሳካለት ነው!› የሚያስብል ነበር። ከመሪ ተዋናንያን አንስቶ ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ ፊታቸውን እምብዛም ያልለመድናቸው ናቸው። አብዛኛዎቹ በተለያዩ የተሰጥኦ ውድድሮች ላይ አሸናፊ የነበሩ አዳዲሶች ናቸው። ብዙ ጊዜ ድራማና ሲኒማዎቻችን አዳዲስ ፊቶችን ከማሳየት አንጻር ያቆሙትን ግዙፍ ግንብ ለመደርመስ ችሏል። የእያንዳንዱ የትወና ብቃት ደግሞ፣ መረጣውን ስኬታማ አድርጎታል።
የድምጽና ምስል ጥራት በተከታታይ ድራማ ታሪክ ከግንባር ቀደሞቹ ፊት ያሰልፈዋል። ምንም እንኳን መቼቱ ጠባብ ቢሆንም፤ ቦታ መረጣው ልዩ ያደርገዋል። ቀረጻው የተካሄደው በአንዲት የኢትዮጵያ መንደር ውስጥ እንጂ፤ እንደ ሆሊውልድ ባለ ራሱን የቻለ የፊልም መንደር ውስጥ አይደለምና የቦታ ነገር በ‹ልጄስ?› ውስጥ ከባድ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ከቦታው ባሻገር፤ ከቤቶቹ እስከ ቁሳቁሶችና ሌሎችንም ግብአቶችን አሳክቶ፣ በዘላቂነት 42 ተከታታይ ክፍሎችን በመቅረጽ፣ ቀጣይነትን(ኮንቲኒቲ) መጠበቅ መቻል በእርግጥም ብዙ ዋጋ መክፈልንም የሚጠይቅ ነው። በቀረጻ ወቅት ከተዋንያኑ ጀርባ ወደ ካሜራው እይታ የሚገባው እያንዳንዱ ምስል የድባብን መንደርና ሕዝብ መምሰሉ ግድ እንደመሆኑ፤ በዚህም ጥንቅቅ እንዲል ያደረጉትን የካሜራ ባለሙያዎች እንድናመሰግናቸው ያስገድደናል።
በ‹ልጄስ?›ድራማ ውስጥ ሁሉም በአንድ ድምጽ አድናቆታቸውን ካሳረፉባቸው አንደኛው “ሀገሬ” እና “ቀሰም” በተሰኙት መንትያ ገጸ ባህሪያት መካከል ይገኛል። ሁለቱንም ወክላ የተጫወተችው የሳምራዊት ትወና ነው። በመልክ እንጂ በባህሪም ሆነ በግብራቸው ፍጹም ለየቅል መሆናቸውና ሁሌም የማይለያቸው የየራሳቸው የሆነ መገለጫ ያላቸው መሆናቸው ነው። እዚህ ላይ አድናቆታችን ለተዋናይዋ ብቻ ሳይሆን፣ ለዳይሬክተሩና ለኤዲተሩም ጭምር ነው።
በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ጥንቅቅ ተደርገው ተሠርተዋል። ሁለቱ ገጸ ባህሪያት በሚገናኙባቸው ገቢሮች ሳይቀር፣ የእውነትም በሁለት የተለያዩ ተዋንያን መካከል የሚደረግ አድርገን እስክንቀበል ድረስ አሳምኖናል። ይህ ጥበብና ችሎታ በደንብ ሊመሰገንና ሊደነቅ ይገባዋል። ገዛኸኝን ወክሎ መሪውን ገጸ ባህሪ የተጫወተው ዳንኤል፣ ትወናው ምንም የማይወጣለት ነበር። ከገጸ ሰብ አሳሳሉን አንስቶ የተመልካቹን የልብ ትርታ የደረሰ መሳጭና ተወዳጅ ነው። በአጠቃላይ በድራማው ውስጥ ያለ ቦታው የተገኘ አንድም አይታይበትም።
አንድ የፊልም ወይም የድራማ ታሪክ ‹እኛን አይመስልም…አያስተምርም› የምንለው መቼ ነው? ኢትዮጵያዊ አይደለም ለማለትስ መስፈርቱ ምንድነው? …ልጄስ? ድራማ የገጠመውስ ምንና እንዴት ነበር…ደራሲውን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባው አንደኛው ነገር “ቢስ” የተሰኘው መንፈስ ነበር። ‹ቢስ ማለቱ ’ቢስት’› የሚባለውን ሰይጣናዊ አማልዕክትን ለመግለጽ ነው› ያሉም አልጠፉም። መድኃኒተኛዋና በኋላም የቢስ መልዕክተኛ የሆነችው “ሀገሬ” የተሰኘችው ገጸ ባህሪም ‹ጠንቋይ ነች› ከሚል ድምዳሜ ተደረሰ። ከንዳዶች ቀይ ካባ አንስቶ፣ የተጠቀሙት ምልክት ሰይጠናዊ እንደሆነም ለማሳየት የሞከሩ ነበሩ። በአጠቃላይ ‹ባዕድ አምልኮን ለማለማመድ ሆነ ተብሎ የተሠራ ነው› ሲሉ አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ አዋቂዎቻችን ጉዳዩን ጥበባዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ጦርነት ለማድረግም ታትረውበታል።
በዚህ ማዕበል ውስጥ እያለፈ እስከ ፍጻሜው የዘለቀው ልጄስ? መጨረሻው ከታሰበውና ከተገመተው ሌላ ሆነ። ትልቁ ገላጋይ የነበረው ‹ቢስ› የሚባል መንፈስ አለመኖሩ ነበር። እንግዲህ ‹ቢስት ነው› ያሉም ፉርሽ! መሆናቸው ነው። በደራሲው ፍራቻ መጨረሻው ተቀይሮ ነው እንዳንል ደግሞ፤ የ42ቱም ክፍሎች ቀረጻ ተጠናቆ የተጀመረና አስቀድሞም የታየ መሆኑ ነው።
ያ ሁሉ ግብር፣ ያ ሁሉ መበዝበዝና መንቀጥቀጥ ውሸት ነበር። የሀገሬ ‹ቢስ አናግሮኛል›፣ የቀይ ለባሾቹ ንዳዶች ግፍና ጭካኔ ለቢስ መንፈስ ሳይሆን፤ ለግል ጥቅም በሕዝቧ ላይ ሲደረግ የነበረ አዕምሯዊና ስነ ልቦናዊ ቁማር ነበር። በአንዲት ሌሊት ያንን ሁሉ የድባብን ሕዝብ በሞት የረፈረፈውም ቢስ አልነበረም ማለት ነው።
በስተመጨረሻ፤ ሀገሬ በገዛ ጠባቂ ወታደሯ ተገደለች። ታዲያ ከዚህ ሁሉ ጀርባ ማን ነው የነበረው? ይህ ሁሉ ግፍ ሲደረግ የነበረው በቢስ ጫካ ውስጥ በነበረ የሽፍታ ቡድን ነበር። በድባብ ሕዝብ የድባብ አደራ የተሰጣቸው የክቡር አባት፣ ይህን ሁሉ ምስጢር እያወቁ ‹ቢስ ነው› ማለታቸው፤ ከሞቱት ጋር ሞተዋል የተባሉትንና በሌላ ከተማ ደብቀው የሚያኖሯቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ነበር። ያኔ ከጥንስሱ ከሦስቱ ክቡር አባቶች ሁለቱ ሴራውን አልቀበልም በማለት ስለ ቆሙለት ሕዝብ፤ በሽፍቶቹ ከነቤተሰቦቻቸው ሲሰዉ፣ እኚህ አባት ግን የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ነብስ መርጠው ድባብ ሲኦል እንድትሆን አደረጉ። ታዲያ ይህ ነው ኢትዮጵያን የማይመስለው?
በሰማይ በምድር ፊታችን ተገዝተው አደራችንን የተቀበሉን ስንት ፖለቲከኞቻችን፤ አደራችንን ቅርጥፍ! አድርገው በልተው፣ ስለ ግል ጥቅማቸው ሽጠውን የለም እንዴ? ስንቱ አፈታሪክ ጉድ ሠራን…ከጥንት አንስቶ ‹እንዲህ ለሚሉት መንፈስ…እንዲህ ብታደርጉለት ይህን ታገኛላችሁ› እየተባለ የዋህነቱ ቂል ያደረገው ምስኪን ማኅበረሰባችን በየአካባቢው ሲገብር አልኖረም ወይ? ድሮውን እንተወውና ዛሬስ ‹አምላካችሁን አናገርኩት…እንዲህ ብሏል…እንዲህም አምጡ› እየተባለ በስመ እምነት የምእመኑ ኪስ እየታጠበ አይደለምን? በየእምነቱ በሃይማኖት ስም እስከ አጥንታችን የሚገጠግጠን መች አጣን። ጠንቋይና አስጠንቋይ፣ ገባሪና አስገባሪ፣ ካዳሚና ታዳሚው ሁሉ በአንዲት መንደር ተደባልቆ፣ መንጋው ራሱን ለመለየት እየተሳነው ተምታቶበታል እኮ። ልክ እንደ ድባብ መሪ ሁሉ፣ የስም ወንበር ላይ ተቀምጠው የሕዝቧን ጤናና መሠረተ ልማት ሲገምጡ የሚኖሩ አስተዳዳሪዎች ዓይኖቻችን ስር ሞልተው ታጭቀዋል።
በየዘመናቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የማይታለልበት ምን አለ? ሀገሬ ከጥንት አያቶቿ አንስቶ፣ ከእናቷ የወረሰችው ልዩ ዕውቀትና ጥበብ ነበራት፤ ግን የበግ ለምድ ለብሰው በስስ ጎኗ የገቡ ተኩላዎች፣ ጠንቋይ መስላ እንድትታይ ሲያጠናቁሏትና የጥንቆላን ዛር ሲዘሩባት፤ በመጨረሻም ያላትን ጥበብ ሁሉ እንድታጣ አድርገዋታል።
በእጽዋት ቅጠሎቿ በተረጨው መርዛማ ኬሚካል፣ ማዳንን ትተው የመዳንን ጥበብ ሰውረዋል። ከነበረው የልጅ አዋቂነትና መልካምነት ጋር ተምሮ፣ ለድባብ ብርሃን ሊሆን ይችል የነበረው መላኩ፤ መልካም በሚመስለው የፍቅር ጦስ ተታሎ በስተመጨረሻ እሱም ሽፍታ ሆኖ ተገኘ፤ የአባቱንም ታሪክ ደገመ። እኛም እኮ እንዲሁ ነን፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተምረን መፍትሄ እንሆናለን ተብሎ ሲጠበቅ፣ ተምረን ተምረን ጠመንጃ ለመሸከም ይሆናል። ትናንት በአባቶቻችን የደማውን ታሪካችንን የምናክም ልንሆን ሲገባ፣ ይባስ ቁስሉን የምናመረቅዝና የምናመግል ባለጊዜ ሆነን እንታያለን።
ታዲያ ይህ ድራማ እኛን ላይመስል፣ እኛን ላያስተምር ምን ጎደለው? ጥበብ እንደወረደ የምትቀዳ ቡና አይደለችምና ‹ለምን?› ማለታችን ጥሩ ቢሆንም፤ ጥቁር ነጥብ ሁሉ ‹ጠባሳ ነው› ብለን ባንተረጉመው መልካም ነው። እንዲህ ወጣ ያሉ ነገሮችን ይዘው የሚመጡትና ደራሲና ዳይሬክተሮቻችንን የምናስደነግጥ ከሆነ፣ የጥበብ ኢንዱስትሪያችን በኦና ቤት ውስጥ ሲንፏቀቅ መኖሩ ነው። እንደተመልካች በዚህ ደረጃ ያገባኛል ብለን ለባህልና ሃይማኖታችን ቃፊር መቆማችን የሚያስመሰግነን ቢሆንም፤ ሁላችንም ሰከን ብለን በትዕግስትና በበሳል አዕምሮ፤ ጥበብን በጥበባዊ መንፈስና ስሌት ልንቃኝ ይገባል።
ልጄስ ከተወዳጅነት ያለፈ ላቅ ያሉ ሽልማቶችን ያገኘም ጭምር ነው። በአፍሪካ ተከታታይ ድራማዎች ሁለት ሽልማቶችን አግኝቷል። እይታው ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገና ወደ ‘ኔትፍሊክስ’ የመድረስ እቅድ እንዳለውና የተሠራበት የጥራት ደረጃም ይህንን እንዲመጥን ተደርጎ ስለመሆኑም፣ ደራሲና ዳይሬክተሩ ሰማኝ ጌታ አይችሉህም ቀደም ሲል ገልጾት ነበር።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም