ቆንጆን ልጅ ሁሉም ይስመዋል!

እናት ዘጠኝ ወር አርግዛ፣ አምጣ እና ተጨንቃ ልጅ ትገላገላለች። ከእዚያም ጡት አጥብታ፣ በጀርባዋ አዝላ እና እሽሩሩ ብላ እስኪድህ እና ቆሞ እስኪራመድ ድረስ ሲወድቅ አብራ ወድቃ፣ ሲያለቅስ አብራ አልቅሳ በሁለት እግሩ እንዲቆም ታደርገዋለች።

ከፍ እስኪል ድረስም እሷ ሳትበላ ጠቃሚ ምግቦችን ትመግበዋለች፤ ንጽሕናው እንዳይጓደልም እጥብ እጥን ታደርገዋለች። በእዚህ መልኩ ተጨንቃ ያሳደገችው ልጅም ሲያዩት የሚያምር በመሆኑ የሁሉም ዓይን ውስጥ ይገባል፤ ሁሉም “ውይ ሲያምር” እያለ አገላብጦ ይስመዋል።

ሆኖም ይህንን ሕጻን ሁሉም ሊስመው የቻለው እናት በከፈለችው መስዋዕትነት ነው። እናት ጡቷን አጥብታ ባታሳድገው፣ ንጽሕናውን ባትጠብቅለት እና እንክብካቤ ባታደርግለት ልጁም በሽተኛ ይሆናል፤ ሰዎችም ይርቁታል። ስለዚህ ከልጁ ማማር ጀርባ በርካታ መስዋዕትነት የከፈለች እናት እንዳለች ማስተዋል ይገባል። ልጁም የእናቱ፤ እናትም የልጇ ነች።

የዓባይ ግድባችንም ልክ እንደእዚሁ ነው። ዛሬ ዓባይ ግድብን ለመሳም የማይፈልግ፣ እኔ ነኝ ለእዚህ ያበቃሁት የማይል ወገን የለም። ቆንጆን ልጅ ሁሉም መሳም እንደሚፈልገው ሁሉ የዓባይ ግድብንም “እኔም አለሁበት” የሚሉ ግለሰቦች፣ መሪዎች እና ሀገራት ቢኖሩ የሚያስገርም ሊሆን አይገባም።

ሆኖም የዓባይ ግድብን አርግዘው፣ በሆዳቸው ተሸክመው፣ መከራ እና ስቃይን ተሸክመው የወለዱት እና ለቁም ነገር ያበቁት ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ግን መካድ ከተፈጥሮ ጋር መጣላት ነው። ስለዚህ የዓባይን ግድብ ማድነቅ፣ የዓባይን ግድብ መሳም፣ የዓባይን ግድብ ማቀፍ ይቻላል፤ የዓባይ ግድብ የእኔ ነው ማለት ወይም የዓባይ ግድብ በእኔ ገንዘብ ነው የተሠራው ማለት ግን ጸሐይ በምሥራቅ ወጥታ በምዕራብ እንደምትገባ መካድ ነው።

ኢትዮጵያውያን የዓባይ ግድብን ከጥንስሱ እስከ ውልደቱ እንዲሁም እስከ እድገቱ ድረስ ተንከባክበው አሳድገውታል፣ ከሌላቸው ላይ ቀንሰው መግበውታል፣ ነገን አልመው የትናንትን እና የዛሬን ኑሮ መስዋዕት አድርገዋል። የዓባይ ግድብን ገንብተው ታሪክ ሠርተዋል።

ኢትዮጵያ ታሪካዊት ሀገር፤ ሕዝቧም የእዚህ ታላቅ ጀብዱ ባለቤት ነው። ይህ ጀግና ሕዝብ የብሔር፣ የሃይማኖት፣የጾታ እና ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ሳይበግሩት ታሪክ ሠርቷል፤ የዘመናት ብሶት የነበረውን ወንዝ በቁጥጥሩ ስር አውሎ እራት እና መብራት እንዲሆን አስችሎታል።

ኢትዮጵያ ከድህነት ለመላቀቅ እና በብልፅግና ማማ ላይ ለመውጣት በትልቁ ዓባይ ወንዝ ላይ በራስ አቅም ግድብ ለመገንባት መጋቢት 24 /2003 ዓ.ም ቆርጣ ተነሳች። ሕዝቧንም አስተባበረች። መሐንዲሱም፣ የገንዘብ ምንጩም ኢትዮጵያውያን ሆነው የግድቡን ግንባታ የዛሬ 14 ዓመት ጀመሩት።

የግድቡ ይፋ መደረግ የዘመናት ቁጭትና ወኔ ሊቋጭ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ዓድዋ ጦርነት በመላው ሀገሪቱ ከተሞች አደባባይ በመውጣት አጥለቀለቁት። አንድም ሰው የቀረ እስከማይመስል ድረስ ግልብጥ ብሎ በመውጣት “በተፈጥሮ ሀብታች መጠቀም ሉዓላዊ መብታችን ነው!” “ያለማንም ድጋፍ እና ብድር ተባብረን ዓባይን እንገድባለን!”፣ “ዓባይን በፍትሐዊነት በጋራ እንጠቀማለን!”፣ “ድሮም ተካፍሎ መብላት ባሕላችን ነው!” ሲሉ በአደባባይ በመፈክር፣ በሆታ እና በዜማ ገለጹ።

ዓባይ ሁሉንም በጋራ አንድ አድርጎ በማሰለፉ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል፣ ሀብታም ድሃ ሳይል፣ ምንም ዓይነት የፖለቲካ፣ ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ ልዩነት ሳያግደው ለግድቡ ድጋፍ ለማበርከት ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ተሰለፈ።

ሠራተኛው ከወር ደመወዙ፣ አርሶ አደሩ ከምርቱ፣ አርብቶ አደሩ ከሚያረባቸው እንስሳቱ፣ ነጋዴው ከንግዱ፣ ባለሀብቱ ከጥሪቱ፣ ምሁሩ በእውቀቱ፣ የኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ባለሙያው በሙያው፣ ተማሪው ከወር ቀለቡ፣ የቀን ሠራተኛ ከእለታዊ ገቢው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሠማራበት መስክ ከሚያገኘው ቆጥቦ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን በመደገፍ ግንባታውን ጀምሮ ለመጨረስ ተነሳ።

በመላው ሀገሪቱ ያለው ሕዝብ ያለምንም የውጭ ሀገራት ብድርና ዕርዳታ በራሳችን አቅም ግድባችንን መገንባት እንችላለን ሲል ለግድቡ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በሙያና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። የዓባይ ግድብ ላይ በራስ አቅም መሥራት የልማት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነትና የማንነት ጉዳይ መሆኑን ሕዝቡ በተጨባጭ ድጋፍ አረጋገጠ።

የሀገር ውስጡን የሕዝብ የድጋፍ ማዕበል ተከትሎ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እና በትውልድ ኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሩ ልማት በጋራ በመነሳት ታላቁ የሕዳሴ ግድብን መገንባት ሀገራዊ ግዴታ ነው ሲል በገንዘቡ፣ በዕውቀቱ እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲው መስክ ለሀገሩ አምባሳደር በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። ዲያስፖራው ለሀገሩ ግድብ የውጭ ምንዛሪ ቦንድ በመግዛትም ሆነ በስጦታ ሲያበረክት ርቀትም ሆነ ድንበር አልገደበውም።

የኅብረተሰቡ ድጋፍ በዓይነትም ሆነ በብዛት ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ተሳትፎውን በዘላቂነት ለማስቀጠል እና በትክክል ለታለመለት ግብ እንዲውል ለማስቻል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ቦንድ በተግባር ላይ በማዋል ለግድቡ በየወሩ ከደመወዙ ላይ እስከ አስር በመቶ እየቆረጡ በመደገፍ እግረ መንገድም የዜጎችን የቁጠባ ባሕል ማሳደግ ተቻለ።

ለታላቁ ሕዳሴ ግብ በብሔራዊ ደረጃ እና በክልሎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በሚከናወኑ የንቅናቄ እና ሀብት ማሰባሰቢያ ሁነቶች ከሕዝብ በስጦታ የሚመጡ ልዩ ልዩ ድጋፎችን (የቀንድ ከብት ግመሎች፣ ሌሎች እንስሳት፣ አዝርዕቶች፣ የቅባት እህሎች፣ ማዕድናት፣ ቁሳቁሶች፣ ወዘተ…) በገንዘብ ተለውጠው በልገሳ እንዲገቡ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ቀጠለ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ እስካለፈው ሰኔ 30ቀን2017 ድረስ 23ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በማዋጣት ግድቡን ከዳር ለማድረስ ተረባረበ።

ባለፉት ዓመታት የሀገራችን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የታላቁ ዓባይ ግድብን ጠቀሜታ በመረዳት ግድቡ ከተያዘለት የአገልግሎት ዘመን በላይ ተሻጋሪ እንዲሆን ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በማለት በመላው ሀገሪቱ የተፋሰስ ልማት (የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ) ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ ሕዝብና መንግሥት ለተፋሰስ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል።

ከግብርና ሚኒስቴር በመጣ መረጃ መሠረት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በማለት በየዓመቱ በአማካኝ 30 ቀናት በተፋሰስ ሥራ ላይ ያዋለው ጉልበት በገንዘብ ሲተመን ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ግድቡ በሀገሪቱ ዕድገት ላይ ምን ያህል የለውጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረ ማሳያ ነው።

ከእዚሁ ጎን ለጎንም ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚቃወሙት አካላት የሚነሱ ክሶች ስም ማጥፋቶችና አሉታዊ መረጃዎችን በመመከትና በመድፈቅ ኢትዮጵያውያን፣ በትውልደ ኢትዮጵያውን እና ወዳጆቻችን የሆኑትን በዓለም ዙሪያ በማስተባበር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጫና በማሳደር የተሠራው ሥራም ለመደበኛ ዲፕሎማሲው ቀላል የማይባል እገዛ አድርጓል።

“አንድ ድምጽ ለግድባችን!” “One Voice for Our Dam!” በሚል በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያውያን ለግድባቸው ድጋፋቸውን እንዲገልጹ በማድረግና ፒቲሽን ፊርማ በማሰባሰብ እንዲሁም ለግድቡ የድጋፍ ሰልፍ በማድረግ የምዕራባውያን ሀገራትን ከተሞች በማጨናነቅ ዲያስፖራው የሠራው በውጭ ሀገር ሆኖ ለሀገሩ የመቆም ተግባር በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር፣ ትውልድን የሚያኮራ ታላቅ ገድል ነው። ለእዚህም ነው እስከ የተ.መ.ድ ጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ተከሰን በድል የተወጣነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያዊ “ዓባይ የእኔ ነው!” በሚል በባለቤትነት እየገነባው ያለው የግንባታውን ሂደት ለማየት የሚመኘው ግድብ ነው። በእዚህ የተነሳ ቦታው ከመሐል ሀገር እጅግ ርቀት ቢኖረውም፤ ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ እና ምሥራቅ ጫፍ ተነስተው በርካታ ዜጎች በቡድን እና በግል ጭምር ግድቡን ጎብኝተውታል። ዲያስፖራዎችም ባገኙት አጋጣሚ በቡድን ሆነው ግድቡን ጎብኝተዋል።

ከኢትዮጵያውያንም በዘለለ የግድቡ ዜና በመላው ዓለም የተናኘ በመሆኑ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ የሉዑካን ቡድኖች እና መሪዎች ግድቡ ድረስ በመሄድ አይተዋል፣ ተደንቀዋል፣ ከመደነቅም በላይ ግድቡ የማይቀለበስ እና ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የተሰለፉበት፣ ለሀገሪቱ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል። በእዚህም ያለ ምንም ዓለም አቀፍ ድጋፍ ኢትዮጵያ በሕዝቦችዋ እና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ማደግ እንደምትችል ግድቡ ራሱ መስክሯል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የውሃ ሀብቷ ተጠቅማ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከምትገነባቸው ፕሮጀክቶች ግንባር ቀደም የሆነው ከላይ በተዘረዘሩትና ተነግረው በማያልቁ በርካታ ድጋፎች እንዲሁም በሀገሪቱ ያስነሳው የይቻላል ስሜት እና የድጋፍ ማዕበል ጭምር ነው።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የዘመናት ቁጭትና ምኞታቸውን በትውልድ ቅብብሎሽ ያሳኩበት ሲሆን፤ ግድቡን ከጥንት ነገሥታት ጀምሮ ለመገደብ ሲያልሙት የነበረ ግድብ ነው።የዓባይ ግድብ በአጼ ኃይለ-ሥላሴ ቢጠናም ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሙከራ ቢያደርጉም በአቶ መለስ ዜናዊ ግንባታው ተጀምሮ፣ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመርህ ስምምነት ተፈርሞ፣ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የግድቡ ችግሮች ተፈተው ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ነው። በእዚህም የሀገራችን መሪዎች ግድቡን በቅብብሎሽ በመገንባት አሁን ለደረሰበት የፍጻሜ ደረጃ አድርሰውታል።

ይህ ትውልድም ከመሪዎቹ ጎን በመሰለፍ ያለምንም ልዩነት ባለው አቅም ተረባርቦ ግንባታው በተግባር እውን እንዲሆን በማድረጉ በታሪክ ማህደር በትልቅ ስፍራ ተመዝግቦ ትውልድ በኩራት የሚዘክረው ባለ ታላቅ ገድል የሆነበት ልማት ነው።

ሆኖም ግድቡ ተጠናቆ ለምርቃት በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅትም ቢሆን፤ የግድቡን ዝና ለማውረድ የሚደረጉ ጥረቶች እና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ርብርብ የሚያሳንሱ መረጃዎች ዛሬም ቢሆን አልጠፉም። በተለይም በመግቢያችን ላይ እንዳነሳነው በኢትዮጵያውያን ተረግዞ፣ ተወልዶ እና በእንክብካቤ አድጎ ለሙሽርነት የበቃውን ግድብ በእኔ ገንዘብ ነው የተሠራው የሚሉ ድምጾች ቢበዙም ግድቡ ግን የኢትዮጵያውያን አንጡራ ሀብት ነኝ እያለ እውነታውን እየተናገረ ነው።

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You