አዲሱ ገረመው
በሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ረጅም ሂደት ውስጥ በጽሑፍ ወይም በአፈ ታሪክ የሚተላለፍ ዕውቀት ትልቁን ድርሻ ይይዛል። የትውልድ ቅብብሎሹ የተሳካ ነው ባይባልም የዘርፉ አጥኝዎች መረጃ በድንጋይ፣ በእንጨት፣ በብራና፣ በቀንድና በሌሎችም ቁሳቁስ ይቀመጥ እንደነበር፤ ይህም ለጥናትና ምርምር እንደረዳቸዉ ያስረዳሉ።
የማወቅና የማንበብ ፍላጎት እየጨመረ ሲመጣ መረጃን በዕውቀት በቤተ-መጻሕፍት መሰብሰብ ተቻለ። ከሁለተኛው እስከ አምስተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ቤተ- መጻሐፍት መንግሥታዊና ሐይማኖታዊ በመባል ይጠሩ እንደነበረም ይነገራል።
በብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ የዳታቤዝ አድሚኒስትሬተር አቶ ግዛው ዋቅጅራ እንደሚሉት፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣው የቤተ መጻሕፍት ታሪክ የስነጽሑፍ ክምችት ፈርቀዳጅ የሆኑት አገሮች ማለትም ሮም፣ ቻይና፣ ግሪክ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ስፔን እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በርካታ ቤተ-መጻሕፈትን ማቆየት ችለዋል። ቤተ-መጻሕፍቱ በነገሥታትና ሐይማኖት ተቋማት ስር ስለነበሩ ከሰባተኛው እስከ 14ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ጠንካራ አደረጃጀት ነበራቸው። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ማደግ ችለዋል።
በቤተ-መጻሕፍት ታሪክ ውስጥ ከ17ኛው እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ይህ ዘርፍ ወርቃማው ዘመን ተብሎ የሚነገር ሲሆን፤ አውሮፓዊያን የሕንፃ ጥበባቸውን ጭምር በማሳየት ከፍተኛ መጠን ያለው ጎብኚን ያገኙበት ጊዜ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ የምናገኘው ቤተመጻሕፍት ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ዓለማችን ውስን የሆነውን ሀብት ተጋርቶ ለመጠቀም በዲጂታል ተክኖሎጂ በመበልጸጉ ነው።
እንደ አቶ ግዛው ማብራሪያ፤ ዲጂታል ላይብረሪ ማለት ዲጂታል ማከማቻ ወይም ዲጂታል ክምችት ጽሑፍን፣ ምስሎችን፣ ድምፅን፣ ቪዲዮን፣ ዲጂታል ሰነዶችን ወይም ሌሎች የዲጂታል ቅርጾችንና የዲጂታል እቃዎችን ሊያካትት የሚችል የመስመር ላይ የመረጃ ቋት ነው።
ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ይዘትን ከማከማቸት በተጨማሪ በክምችቱ ውስጥ የተካተቱትን ይዘቶች ለማደራጀት፣ ለመፈለግና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው። በመረጃ ቋት (Digital Database) ውስጥ ተጭኖ በአውታር መረብ አማካኝነት በድረገጽና በበይነመረብ አማካኝነት ለተገልጋዮች ተደራሽ ማድረግም ያስችላል።
የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት በዚህ ዘመን ተጀመረ ማለት ባይቻልም በርካቶች ግን ከጽንሰ ሃሳቡ መምጣት ጋር እንደሚያገናኙት አቶ ግዛው ይናገራሉ። ከቀደምቶቹ መካከልም ፖልኦትል እና ሄንሪ የተባሉ ምሁራን እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። እነዚህ ታወቂ ሰዎች እ.ኤ.አ በ1895 የዓለምን ሠላም ለማምጣት ተስፋ በማድረግ የዓለምን ዕውቀት ለመሰብሰብና በሥርዓት ለማደረጀት የተጀመረው ሙከራ የዲጂታል ላይብረሪ እድገት በአብዛኛው ከ100 ዓመት በኋላ በበይነ መረብ መስፋፋት ወቅት የተጀመረ መሆኑን ይጠቁማሉ። መጽሐፎቹን ማግኘትና በዓለም ዙሪያ ባሉ ድረ ገጾች ላይ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰነዶችን ሰብስቦ ለማስቀመጥ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለበት ጊዜ አንስቶ እንደሆነ ያመላክታሉ።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ተቀማጭ ዓይነቶች ተገንብተዋል። የብሪታኒያ ቤተ መጻሕፍት ፖርታል እና የጀርመን ቤተ መጻሕፍት አውታር መረብ መፍጠር ችለዋል። ይሁን እንጂ ለህዝብ ተደራሽ የሆኑት በቤተ መጻሕፍት ውስጥ በሚገኙ የንባብ ክፍሎች ውስጥ ብቻ ነው፤ አሁን ላይ በቀላሉ ሁሉም ማህበረሰብ እጅ ላይ መድረስ የሚያስችል አቅም ተገንብቷል።
ዓላማዎች
የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት፡- ዲጂታል እና ህትመት መረጃዎችን ለመሰብሰብ፤ የተሰበሰቡትን ወይም ዲጂታይዝድ የተደረገትን ለማደራጀት፤ ጥበቃና እንክብካቤ ለማድረግ (ኦሪጅናል የመረጃ ሀብቶችን ከሰዎች ንኪኪ ለመጠበቅ እና ዲጅታል ቤተ-መጻሕፍትን “ባከፕ” በማድረግ ከአደጋ መጠበቅ) ፤ ፈጣን እና ቀልጠፋ የመረጃ ተደራሽነት ለመፍጠር፤ አንድ የመዳረሻ ዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት ቤተ-መዛግብት ለማልማት፤ የሥነ-ጽሑፍ አጠቃላይ የመረጃ ቋት ለመፍጠር እና ለማዘመን፤ ለተገልጋዮች በቤተ-መጻሕፍት የሚሰጡ የመረጃ ሀብቶችን በብቃት እንዲጠቀሙ ለማስቻል የታለመ መሆኑን አቶ ግዛው ያብራራሉ።
ጥቅሞች
አቶ ግዛው እንደሚሉት፤ የዲጂታል ቤተ – መጻሕፍት ዋነኛው ጥቅም ሰዎች መረጃን በቀላሉ ለማግኘት ማስቻሉ ላይ ነው። የቦታ ውስንነት የለውም። በአካላዊ ድንበር ሳይገደቡ ከመላው ዓለም ካሉበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉትን የመረጃ ዓይነት ለማግኘት ይጠቅማል። በተመሳሳይ ሰዓት ከአንድ የዲጂታል መረጃ ቋት በርካታ ተጠቃሚዎችን እና የመዳረሻ ቦታዎችን ተደራሽ ለማድረግ ያገለግላል። ተጠቃሚው ካለው ስብስብ ውስጥ የሚፈልገውን የመረጃ ዓይነት ማንኛውንም የፍለጋ ቃል በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት ያስችላል። የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ውስንነትን ያስቀራል፤ በአነስተኛ አካላዊ ቦታ ብዙ መረጃዎችን የማከማቸት አቅም ይፈጥራል።
ተግዳሮቶች
ዲጂታል አገልግሎት በአሁኑ ሰዓት ጠንካራ ቁጥጥር ካልተደረገ የቅጂ መብት እንደሚያስጥስ አቶ ግዛው ይናገራሉ። ለዚህም መሰረታዊ ችግሮችን ያነሳሉ። የአንዱ ደራሲ ሃሳብ ይዘት ያለ እውቅናው ለሌሎች ሊተላለፍ እንደሚችል ይህም መረጃዎችን እንደሚፈለገው ወደ ዲጂታል በመቀየር ለአገልግሎት ማዋል አያስችልም ይላሉ። በሌላ በኩል የመዳረሻ ፍጥነትም አንዱ ተግዳሮት መሆኑን በማመልከት፣ ኮምፒዩተር ከበይነ መረብ ጋር የተገናኘ በመሆኑ የመዳረሻ ፍጥነቱ እየቀነስ ሊሄድ እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ክምችትና የተጠቃሚውም ቁጥር እየበዛ ሲሄድ ፍጥነት መቀነሱ፤ አዲስ የቴክኖሎጂ ችግሩን ለመፍታት ካልተሻሻለ በቀር በይነ መረብ በስህተት መልዕክቶች የተሞላ ይሆናል ሲሉ ያብራራሉ።
የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት የመሠረተ ልማት ወጪ ከፍተኛ መሆኑ፤ ዲጂታል ቤተ መጻሕፍት የመልቲሚዲያ ሀብቶችን ለማስተላለፍ ለመጫንም ሆነ አገልግሎት ላይ ለማዋል ከፍተኛ ባንድ ወይም የኢንተርኔትና አውታረ መረብ ዝርጋታ ማስፈለጉ የዘርፉ አሉታዊ ተጽእኖዎች መሆናቸውን አንስተዋል። ከዚህም ባሻገር በቴክኖሎጂ እድገት ምክንያት የዲጂታል ቤተ መጻሕፍት ክምችትን ደህንነት መቶ በመቶ አስተማማኝ ማድረግ አለመቻሉም ሌላኛው ተግዳሮት ነው።
የቴክኖሎጂ እድገት በጣም ፈጣን በመሆኑ ምክንያት የመረጃውን ቅጅ መብት ሳይጠብቅ ተደራሽ ሊሆን እንደሚችልም አቶ ግዛው ያመላክታሉ። በዚህም የቴክኖሎጂ ተለዋዋጭነት የቀደሙ መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግ አለመቻልም በራሱ ተደራቢ ችግር ነው ይላሉ።
በሀገሪቱ ውስጥ ዲጂታል ሆነው የተፈጠሩትንና ወደ ዲጂታል የተቀየሩትን መረጃዎች በዓለም አቀፍና በሀገሪቱ ህግ መሰረት የቅጂ መብት ተጠብቆ እንዲከማቹና እንደ እውቀት ባህሪያቸው እንዲደራጁ የብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጸሕፍት አጄንሲ እንደሚሠራም አቶ ግዛው ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013