ከጥር 19 እስከ 20 /2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ሄልዝ ኢንቴርናሽናል ሆቴል በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባላት እና ተሳታፊ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል። ይኸውም የኤች አይ ቪ /ኤድስ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ግምገማ 2011ዓመት እቅድ አፈፃፀም፤ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ፥ በ2030 ከኤች አይ ቪ ነፃ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር ሁላችንም ኃላፊነታችንን እንወጣ፤ ከኤች አይ ቪ ነፃ የሆነ ትውልድ በመፍጠር የለውጥ ጉዟችንን እውን እናድርግ የሚሉ ባነሮች የተስተዋለበት ነዉ።
የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ አሁንም ድረስ ዋነኛ የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዲሞግራፊያዊ ባላንስ መዛባት እንዲሁም ፖለቲካዊ ጉዳይ በመሆን በከፍተኛ ሁኔታ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ እየሆነ ነው። በመዲናዋ 90 በመቶ የሚሆነው የእድሜ ክልል አምራች የሆነው ማህበረሰብ ነው። ኤች አይ ቪ/ኤድስ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት የሚያደርሰው ይህንኑ አምራች የሆነውን ክልል በመሆኑ በሃገር ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት ያደርሳል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ 107 ሺህ ህዝብ ቫይረሱ በደሙ የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል ነው፤ በየዓመቱም በከተማዋ 1000 ያህል ሰው በቫይረሱ ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ይለያል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ ያለው የስርጭት መጠን 68 በመቶ መሆኑ ተፈጥሯዊ የሆነውን የስነ-ህዝብ ምጣኔ በማዛባት የዲሞግራፊክ ቀውስም እያስከተለ ይገኛል።
በሀገሪቷ ያለው የኤች አይ ቪ የስርጭት ሁኔታ እየቀነሰ ያለ ቢሆንም፤ የአፍሪካም ሆነ የዓለም የዲፕሎማቶች መቀመጫ እና የሀገሪቱ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ እና በጋምቤላ የቫይረሱ የስርጭት ምጣኔ ከፍተኛ እንደሆነ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ያስጠነቅቃሉ።
በአዲስ አበባ የስርጭት መጠኑ ከፍተኛ መሆንም ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የዘርፈ ብዙ ምላሽ ስራዎች እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እንዲሁም በሀገራችን የሕዝቡን ጤንነት የሚፈታተኑ፥ የማምረት አቅሙን የሚቀንሱና ውጤታማነቱን የሚያደናቅፉ በርካታ ችግሮች በመከሰት ላይ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ካለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ጀምሮ በሕብረተሰቡ በተለይም አምራችና ሀገር ተረካቢ በሆኑት ዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴና ሕይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ ዋናው ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር ብርዛፍ ገብሩ፥ የማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት በከተማዋ ያለውን የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከጽ/ቤቱ ጎን በመቆም በትኩረት እንዲሰሩ ጠይቀዋል። አክለውም በአዲስ አበባ የሚገኙ ከ700 በላይ እድሮች በቀጣይ የስድስት ወር እቅድ ላይ በጋራ ለመስራት መታሰቡን ገልፀዋል። በሴተኛ አዳሪነት ህይወት ላይ ያሉትንም ከዚህ ህይወት ለማውጣት ተደጋጋሚ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ፤ በዚህም ባለው የአመለካከት ችግር መቅረፍ ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ጠቁመው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት አልተሰራበትም ይህም መሻሻል አለበት ብለዋል።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሆኑት ወ/ሮ አበበች ነጋሽ በበኩላቸው የምክር ቤት አባላት በሙሉ ለመረጠን ህዝብ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አለብን ብለዋል። የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቫይረስም የህብረተሰባችን በተለይም አምራች የሆነውን እድሜ ክልል (ከ15-45) ስለሚያጠቃ የበለጠ ወደ ድህነት የሚመልስ ተግዳሮት ስለሆነ በጋራ መከላከል እና መቆጣጠር ይኖርብናል፤ እንዲሁም እንደ የአንድ ጊዜ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የሁል ጊዜ አጀንዳ አድርገን በትኩረት ልንሰራበት ይገባል ብለዋል።
በአዲስ አበባ ካሉት አጋላጭ ሁኔታዎችም እየተካሄዱ ካሉት ሰፋፊና ፈጣን የልማት እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን መዝናኛዎችና የወሲብ ግብዓቶች የሚስፋፉበት ዕድል ሰፊ ነው። የተለያዩ የኤች አይቪ መርሐ ግብሮች ሽፋንና ተደራሽነትን በተመለከተ ያሉ ክፍተቶችን በማህበረሰቡ ዘንድ በኤች አይቪ ዙሪያ ያለው የተሟላ ግንዛቤ የዕውቀት መጠን ማነስ እራሱን የቻለ ችግሩን የሚያባብስ ሁኔታ ነው። እንዲሁም ተጋላጭ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮረ የፀረ ኤች አይቪ መርሐ ግብሮችና አገልግሎቶች አለመጠናከር በዋናነትም ባለፉት ጊዜያት በተገኙ ውጤቶች መርካት ኤች አይቪ/ኤድስን በመከላከሉና በመቆጣጠሩ ዙሪያ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እንዲቀዛቀዙ ተፅዕኖ አድርጎ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት የስርጭት ምጣኔው በአዲስ አበባ ከተማ ወደ ሶስት ነጥብ አራት በመቶ ከፍ ማለቱም አሳሳቢ ሊሆን ችሏል።
እንደ ሲስተር ብርዛፍ ገለፃ በአሁኑ ወቅት ጽሕፈት ቤቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ ተግባራቶችን እያከናወነ ይገኛል። በዚሁ ዙሪያ እ.ኤ.አ በ2030 ራዕይ መቀመጡን አስታውሰዋል። ሲስተር ብርዛፍ እንዳከሉት ይሄን ራዕይ እውን ለማድረግ በ2020 ሊሳኩ የሚገቡ የሦስቱ ዘጠና ግቦች ለማሳካት የትኩረት አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። እነዚህም የትኩረት አቅጣጫዎች ተጋላጭነትን ትኩረት ያደረገ የላቀ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል የመከላከል መርሐ ግብር መተግበር፤ ይበልጥ ተጋላጭ የማሕበረሰብ ክፍሎችን ትኩረት ያደረገ የኤች አይቪ ምክርና ምርመራ አገልግሎቶችን ማጠናከር፤ ኤች አይ ቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ማስቻል፤ ጥራትና ተደራሽነት ያለው የፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስ ሕክምና አገልግሎትን አጠናክሮ ማስቀጠል።
እንዲሁም ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህፃናትን እንዲሁም በቫይረሱ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የድጋፍና እንክብካቤ አገልግሎት ማጠናከር፤ ማግለልና መድሎ በመታገል ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ወገኖችን በመከላከሉና በመቆጣጠሩ ተግባር ላይ ተሳትፏቸውን ማሳደግ ናቸው።
የአዲስ አበባ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ጽ/ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሽ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በበኩላቸው በተለይ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ከዋነኛ አጋላጭ ሁኔታዎች ስለሚመደብ በተለይ የሴቶች የልማት ቡድንን በማጠናከር በየክፍለ ከተማውና በየወረዳው ያሉ 2760ዎቹ ባለድርሻ አካላት ጋር በሰፊው መስራት እንደሚያስፈልግ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ደስታ ፊሊዾስ የተባሉ ተሳታፊም ያልኖርንበትን ህይወት ብናስተምር ሰሚ አናገኝም እና ከራሳችን በመጀመር ምሳሌ መሆን አለብን፤ በተሰጠን ኃላፊነት የቼክ እና የባላንስ ስራ ሰርተን ተግባራዊነቱንም መከታተል አለብን ብለዋል። በማከልም ስለሶስቱ ዘጠናዎች እቅድ የሰማሁት ከሶስት ቀን በፊት ነው፤ እኔ አስፈጻሚውን አካል የምቆጣጠር አካል ሆኜ አልሰማሁም፤ ስለዚህ በጉዳዩ ያለው ዝምታ ይህን ያህል ደርሷል እና መሰበር አለበት የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።
ሌላው ከጉለሌ ወረዳ 7 አፈጉባኤ የሆኑት የውይይቱ ተሳታፊ በሰጡት አስተያየት የውይይቱ ወቅታዊነት ገልጸው፤ በሜይንስትሪሚንግ የሚቀመጠው በጀት ለተባለለት ዓላማ መዋሉን የማመሳከር (ክሮስቼክ የማድረግ) ችግር አለ። እንዲሁም ቅንጅታዊ የአሰራር ማኑዋል ቢኖር፤ ምን ከማን ይጠበቃል፥ ለምሳሌ የስራ እድል መፍጠር በሚለው ላይ በምን መልኩ ተቀናጅቶ መሰራት እንዳለበት መታየት አለበት ብለዋል።
የንፋስ ስልክ ወረዳ 6 አፈጉባኤ የሆኑት አቶ ዮሴፍ ገ/ስላሴ በበኩላቸው በሁሉም ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች በስፋት መሰራት አለበት፤ በየትምህርት ቤቱ ዙሪያ ያሉ ፔኒስዮኖች ላይ ቁጥጥር መደረግ አለበት፤ መንግስትም ቆራጥ እርምጃ መውሰድ አለበት፤ እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ተጽኖ ፈጣሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በሰፊው መሰራት አለበት፤ ወላጆችም ልጆቻቸው ሞባይል የሚጠቀሙበት አላስፈላጊ ቀስቃሽ ፊልሞችን የሚመለከቱበት ሁኔታ ላይ ቁጥጥር ቢያደርጉ ልጆችን በጥበብ እና በሞገስ የማሳደግ ባህላችንን ማዳበር የራሱ ሚና ይኖረዋል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ሌላ አስተያየት ሰጪም ከአራዳ ፒያሳ አካባቢ ከየሃገሩ እንጀራ ፍለጋ ፈልሰው የሚመጡ ጨቅላ ህፃናት አሉ፤ በዚህ ጉዳይ ካሁኑ ትኩረት ካልተሰጠው ችግሩ እንደገና ሊያገረሽ ይችላል። እንዲሁም በየክፍለ ከተማው ባሉ የኤች አይ ቪ መከላከል እና መቆጣጠር ጽ/ቤቶች በተገቢው አልተሰራባቸውም ብለዋል።
በውይይቱ ላይም በወቅቱ የኤች አይ ቪ የስርጭት ሁኔታ እና በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫ በያንዳንዱ የአዲስ አበባ ክፍለ-ከተማዎች እንዲሁም የወረዳ መዋቅር ላይ የኤች.አይ.ቪ /ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር እንደ ዋነኛ ጉዳይ ትኩረት አግኝቶ በከፍተኛ መነሳሳት ተጠናክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ፤ እንዲሁም በከተማ ደራጃ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክር ቤት ለማቋቋም ከስምምነት ተደርሷል።
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
በሃይሉ አበራ
This is such an informative and well-written post! I learned a lot from reading it and will definitely be implementing some of these tips in my own life
Your posts are always so well-written and thought out It’s evident that you put a lot of effort into each and every one
This is exactly what I needed to read today Your words have given me a new perspective and renewed hope Thank you
Your blog has become my go-to source for positive and uplifting content Thank you for consistently delivering high-quality posts