ተገኝ ብሩ
ትውልድና እድገት
ባደገችበት አካባቢ ያለው ሌሊሶ የተባለው ሰፊ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ዛሬ እሷ በእግር ኳስ መስክ ታላቅ ስኬት ለመጎናፀፍ ያስቻላት መነሻዋ ነው።ከአቻዎቿ ጋር ጨርቅ ኳስ እያዘጋጁ በዚያ አቧራማ ሜዳ የእግር ኳስ ፍቅር ጥማታቸውን ማርካት ጀመሩ።ያሜዳ ለእርሷ ዛሬ ለተገኘችበት ቦታና ለተጎናጸፈችው ስኬት ምክንያት፣ ለጥበበኛ እግሮቿ ጥንካሬና ክህሎት ዋንኛ ትምህርት ቤትም አጋጣሚም ሆኗል።
የደቡብ ክልል ከምባታ ጥምባሮ ዞን ዋና ከተማ ዱራሜ ተወልዳ ያደገችበት ከተማ ነው። ልጅ ሆና እግር ኳስ ጨዋታ እጅግ ትወድ ስለነበር መጫወትና መምልከት ማዘውተርን ተያያዘችው።ከእግር ኳስ በተጨማሪ በልጅነቷ በትምህርት እጅግ ጎበዝና ፀባየ ሰናይ ተማሪ ነበረች።ክፍል ውስጥ በምታደርገው ንቁ ተሳታፎና የደረጃ ተማሪ በመሆኗ በመምህራኖቿ የምትወደድ ተግባቢና ታታሪ በመሆን ጥሩ የልጅነት ጊዜ አሳልፋለች።
እግር ኳስ ከስኬቷ ጫፍ ላይ የሚያደርሳት መክሊቷ መሆኑን ያኔ ፈፅሞ አታውቀውም።በትምህርቷ በርትታ ወደፊት የህክምና ሳይንስ በማጥናት የሰው ልጆችን ከህመም ለማዳን እና ከስቃይ ለመታደግ ሀኪም ለመሆን ተመኝታም ነበር።ህይወት ግን የአንቺ የስኬት ስፍራ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ነው አለቻት።በወረዳ፣በዞን፣ በክልል፣ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ታላቅ ዝናና አድናቆትን አትርፋለች።ኢንተርናሽናል የእግር ኳስ ተጫዋቿ ሎዛ አበራ።
ስኬት
በአገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ በምታደርገው ማራኪ ጨዋታ ብዙዎች አድናቆትን የቸሯት፣ በታላላቅ ውድድሮች ላይ ሽልማትና ክብር የተቀዳጀች ለአራት ተከታታይ ዓመታት ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን ተሸልማለች፣ አራት ጊዜ ከቡድኗ ጋር የሻምፒዮንነት ክብር ተቀዳጅታለች፣ ባለፈው ዓመት በሲዊዲን ሀገር በማልታ ባስመዘገበችው ድንቅ ችሎታ
የዓመቱ ኮከብ ተጫዋችነትና ኮከብ ግብ አግቢነት ክብርና ሽልማት ተበርክቶላታል፣ የኢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማት አሸናፊም ናት።ቢቢሲም ከዓመቱ 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል አንዷ አድርጎ መርጧታል።
በኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ የዞንና የክልል እግር ኳስ ቡድኖች ላይ በመሳተፍ ባሳየችው ድንቅ ብቃት ክለቦች ዓይናቸውን አሳረፉባት።በዚህም በሃዋሳ ከነማ፣ደደቢት፣አዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለቦች ተዛዋውራ ተጫውታለች።ወደ ሲውዲን በማቅናትም በሁለት የተለያዩ ክለቦች በመጫወት ስኬቶችን ተጎናፅፋለች።አሁን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጫወት ላይ ትገኛለች።
ዝነኛዋ የዕረፍት ጊዜዋን እንዴት ታሳልፋለች ?
በሥራዋ ታታሪ በተሰማራችበት መስክ ደግሞ ስኬታማ የሆነቸው ሎዛ፤ ተግቶ በመሥራትና በአግባቡ የዕረፍት ሰዓት መውሰድ ተገቢነት ላይ ታምናለች።የዕረፍት ጊዜዋን እሷን የሚያዝናናትና ለቀጣይ ስኬቷ ይበልጥ አዲስ አድርገው የሚያቃርቧትን መዝናኛዎች ትመርጣለች።እርግጥ ሥራዋም በደስታ የሚከውኑት በማዝናናት ስሜት ጥበብን እያሳዩ የሰውን ልብ በሀሴት ከፍተኛ ደስታ የሚያጎናጽፋት እግር ኳስ ነውና በእርሱ አብዝታ ትዝናናለች።
እቤቷ ውስጥ እረፈት ስታገኝ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን ትከታተላለች።መንፈሳዊ የሆኑ መፅሐፍትን አብዝታ ታነባለች።ከስብዕናዋ ጋር የሚሄዱና በመልካም ነገር መሰረት አድርገው የሚፃፉ መፅሐፍትም ሎዛ ደስ እያላት የምታነባቸው ናቸው።
የአገር ውስጥ ፊልሞችን በብዛት ከውጭ ደግሞ እየመረጠች መመልከትም በዕረፍት ሰዓቷ የሚያስደስታት መቆያዋ ነው።ከፊልሞች የድራማ ይዘት ያላቸውን መመልከት እጅግ ያዝናናታል።ባይበዛም አልፎ አልፎ የማይርቁና አቅራቢያዋ የሚገኙ መዝናኛ ቦታዎች ላይ ከቤተሰብና ከጓደኞቿ ጋር ተገኝታ የማይረሱ ቀናትን በመዝናናት ማሳለፍም ሌላው ምርጫዋ ነው።
የዕረፍት ጊዜዬን በአግባቡና በተገቢው መንገድ ማሳለፍ እንዳለብኝ አምናለሁ የምትለው ሎዛ፣ ቤተሰቦቿ ከሰው ጋር ተግባብቶ መኖር ያለውን ፋይዳ እያሳዩ፤ በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን ጥቅሙን እየነገሩ ያሳደጓት መሆኑን ትናገራለች።በዚህ የተነሳም ከሰዎች ጋር መልካም ጊዜን ማሳለፍና የተቸገሩትን በመጠየቅ በአቅሟም በመርዳት የታመመን በመጠየቅና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ በአካባቢዋ ተወዳጅም ናት።በሰዎች ኀዘን ላይ በመገኘት ማጽናናት፣ እንደ ሠርግ ባሉት የደስታ ወቅቶች ላይም በማጀብ አብሮ መሆን የለውዝ የማህበራዊ ተሳትፎ ማሳያዎች ናቸው።
ሴቶች በተለያዩ መስኮች የራሳቸውን ያልተቆጠበ ጥረት ካደረጉ ከፍ ያለ ውጤትና ስኬት ማስመዝገብ ይችላሉ፤ ለዚህም ማመንና ለስኬታቸው መጣር ይገባቸዋል የምትለው ለውዝ በዓለም ላይ ስኬታማና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎች በአንድ በተለየ መስክ ሳይሆን ተፈጥሮ ባደላቸው ክህሎታቸው በራሳቸው ጥረት ባደረጉት ጥረት ያገኙት ስኬት መሆኑን ትገልፃለች።በእግር ኳስ ስኬታማ ከሆኑ ሴቶች መሀከል የብራዚልዋ ማርታ አድናቂም ናት።
የዝነኛዋ መልዕክት
“ሁላችንም በዚህች ውብ አገር ውስጥ ነን ያለነው።ኢትዮጵያ ደግሞ ከሁላችንም ትበልጣለች።ይህች አገር ከፍ እንድትል የሁላችንም አብሮ መቆም፣ መፈቃቀርና አንድነት ያስፈልጋል።ሰውነትን አክብረን ሰውነትን ከሁሉ አስቀድመን ሰዋዊ ኑሮ እንኑር።አምላክም የሚወደው ያንን ነው።በመልካምነትና በቅንነት ለአገራችን እንሥራ።በየዘርፋችን ለአገራችን ለውጥና ዕድገት የምንችለውን ሁሉ አድርገን እንለፍ።”የሚለው ለዚህች ታላቅ አገር ህዝብ ከዝነኛዋ የተላለፈ መልዕክት ነው።እኛም ከዝነኛና ተጽዕኖ ፈጣሪዋ እግር ኳስ ተጫዋች ሎዛ አበራ ጋር በነበረን ቆይታ ያጠናከርነውን ፅሐፍ በዚህ አበቃን፤ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013