
ያለንበት ወቅት በአንድ በኩል ትልቁ የሰላም ጠንቅ የተወገደበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጁንታው ለበርካታ ዓመታት የተከላቸውና ጥሎ የሄዳቸው ጋሬጣዎች ሙሉ ለሙሉ ያልፀዱበት ነው፡፡ እነዚህ ሰንኮፎች ደግሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ካልተነቀሉ አገርን ወደብልጽግና ለማሸጋገር ከባድ ፈተና መግጠሙ አይቀርም ፡፡
በአሁኑ ወቅትም መንግስት የጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ በማገባደድ አብዛኞቹን የሴራው ጠንሳሾችና መሪዎች ከፊሎቹን በመደምሰስና ከፊሎቹንም ለህግ በማቅረብ በሽታውን የማከም ስራውን እያካሄደ ይገኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚሁ የሴራ ቡድን ሲደገፉ የነበሩ ጥቂት ሃይሎች በየቦታው የሞት የሽረት ጥረታቸውን በንፁሃን ላይ ሲያደርሱ ይስተዋላል፡፡
ለአብነትም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የሚፈጸመው ግድያና በምዕራብ ወለጋና ጉጂ አካባቢዎች በአነግ ሸኔ ታጣቂዎች የሚፈፀሙ ጥቃቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህ ሃይሎች በተለይ መንግስት በህወሓት ጁንታ ላይ የጀመረው የህግ ማስከበር ስራን ተከትሎ የመንግስትን ሃይል ለማዳከም በማሰብ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ቢሆንም ያሰቡት ግን አልተሳካላቸውም፡፡ በትግራይ ከሚካሄደው የህግ ማስከበር ስራ ጎን ለጎን በነዚህ ሃይሎች ላይ የሚካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም በተለይ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ላይ በተከታታይ እየተካሄደ ያለው ህግ የማስከበር ስራና የተገኘው ስኬት ማሳያ ነው፡፡
ይህ ቡድን ለበርካታ ዓመታት በትግል ላይ የቆየና በ27 ዓመታት የህወሓት ጁንታ አመራር ዘመንም በስደት ቆየ ቡድን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ቡድን ልክ እንደታላቅ ወንድሙ የህወሓት ጁንታ በኦሮሞ ህዝብ መካከል ሆኖ መልሶ ለኦሮሞ ህዝብ ጠላት የሆነ የሰላም ጠንቅ ነው፡፡
ቡድኑ ከራሱ የትግል አጋሮች ጋር እንኳን መስማማት ያቃተውና እንደፈሪ ዱላ ከኦሮሞ ህዝብ መካከል ወጥቶ የኦሮሞን ልጆች የሚገድል፤ የኦሮሞን እናቶች እምባ የሚያፈስ ፈሪ አካል ነው፡፡
በአገራችን በተካሄደው የለውጥ ሁደት ወቅት እንደማንኛውም ከዚያ ቀደም በውጭ ሀገር ሲንቀሳቀሱ እንደቆዩ አካላት እድል ቢሰጠውም በእድሉ ሊጠቀም አልቻለም፡፡ ከአንድም ሁለትና ሶስት ጊዜም በእድሉ ተጠቅሞ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዲገባ ጥያቄ ቢቀርብለትም ይህንንም ሊቀበል አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ቡድኑ ገና ወደ አገር ሲገባ ጀምሮ በነአቦይ ስብሃት አማካይነት መቀሌ ላይ እረፍት ወስዶ እና የቤት ስራ ተቀብሎ የመጣ ከመሆኑም ባሻገር በሰላማዊ መንገድ ወደፖለቲካው መድረክ ገብቶ የህዝቡን የሰላም፣ የልማትና የእድገት ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችል ቁመና፣ አደረጃጀትም ሆነ አቅም የለውም፡፡ በመሆኑም ልክ እደ አሸባሪ ድርጅቶች ሁል ጊዜ እየዘረፈና እየገደለ በሽፍትነት መኖር ያደገበት እና ብቸኛው የሚያውቀው አማራጭ መንገዱ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ወደ አገር ቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ምንም አይነት ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ይልቅስ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ አንዴ መሳሪያ አልፈታም፤ ሌላ ጊዜ ማነው የሚያስፈታኝ በሚል ከመንግስት ጋር አተካራ ውስጥ የገባ ነው፡፡ ከዚያም አልፎ መንግስት ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲመለስ ጥረት ቢያደርግም ወደ ህዝቡ ውስጥ በመግባትና የህዝብን ሰላም በማወክ ለዓመታት የኖረበትን የትርምስና የጫካ ኑሮ ይዞ ቀጥሏል፡፡
ቡድኑ በመጨረሻ ለይቶለት ከሰላማዊ መንገድ ወጥቶ በየጫካው በመግባት እንደ አውሬ ሌሊት ሌሊት ብቻ እየተጓዘ ሰላማዊ ዜጎችን ማሸበር የዘወትር ስራው ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ሌሎች ዋጋ የከፈሉለትን የለውጥ አየር በነፃ እንዲቋደስ የተሰጠውን እድልም ሳይጠቀም እንደለመደው የዝንጀሮ ህይወትን መርጦ ጫካ ለጫካ መሯሯጥ መደበኛ ህይወቱ አድርጎታል፡፡ ከታላቅ ወንድሙ የህወሓት ጁንታ የተማረው ይህን የቆቅ ኑሮ ነውና ዛሬም እየደነበረ በየጫካው ሲዘዋወር ይውላል፤ እንደ ፈሪ ውሻም በድንገት ሰላማዊ ሰው ሲያገኝ እየተናከሰ ይሮጣል፡፡
የአካባቢው ህዝብ ግን ይህንን ቡድን አንቅሮ በመትፋት ድርጊቱንም በአደባባይ እየኮነነው ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ፣ እንዲሁም በጉጂ አካባቢዎች ዜጎች የኦነግ ሸኔን ድርጊት በመቃወም ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር አባገዳዎች የዚህን የሽብር ቡድን ድርጊት በማውገዝ ተግባሩ የኦሮሞን ህዝብ እንደማይወክል በይፋ አውግዘዋል፡፡ በኦሮሞ ባህል ደግሞ የአባገዳ እውቅና የተነፈገው እቅስቃሴ በህብረተሰቡ ዘንድም ተቀባይነት የለውም፤ የህዝቡንም ስነልቦናና ማህበራዊ እሴት አይወክልም፡፡
የክልሉ ፖሊስና ሚሊሻም በዚህ ሃይል ላይ ብቻ ሳይሆን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው አንድ እግራቸውን ከዚህ ቡድን ጋር ሌላኛውን እግራቸውን ደግሞ ከመንግስት መዋቅር ውስጥ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ላይ ጭምር የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ በዚህም ሰሞኑን ከአንድ ሺህ በሚበልጡ የክልሉ የፖሊስ አባላትና ሌሎች የክልሉ ሃላፊዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
አገራችን በቀጣይ ያለባት ከባድ የቤት ስራ ድህነትን ማሸነፍ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እነዚህ የሰላም ጠንቆች ከመስመሩ ላይ ገለል ሊሉ ይገባል፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡም እነዚህን የሰላም ጠንቆች ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት አሁን እንደጀመረው ከመንገስት ጎን በመሆን ሰላማዊ ሁኔታ ለመፍጠር የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል ፡፡ ፍቅር አስከ መቃብር እንዲሉ የቡድኑ የመጨረሻው ሥርዓተ ቀብር ከጁንታው ወዳጁ ጋር አብሮ ሊፈጸም ይገባል ።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013