ግርማ መንግሥቴ
ምን ጊዜም ህይወት ሩጫ ነው። አልጋ ባልጋ ብሎ ነገር፤ ወይም ሰይፈ መታፈሪያ ፍሬው እንደሚሉት “ሙዝ ላጥ ዋጥ” አይነት ህይወት መኖር ለሰው ልጅ የተሰጠው የአርባ ቀን እድሉ አይደለም። ታላቁ መጽሐፍም “ጥረህ ግረህ በወዝህ ብላ” ነው የሚለው።
በመሆኑም ጥሮ፣ ግሮ፣ ለፍቶና እላይ እታች ብሎ መኖር ለሰው ልጅ ስቃይ አይደለም። መከራም ሆኖ አያውቅም። ችግሩ ያለው “ጥሮ፣ ግሮ፣ ለፍቶና እላይ እታች ብሎ” የሚሉትን በመተርጎምና ስራ ላይ በማዋል ሂደቱ ነው።
“ጥሮ፣ ግሮ፣ ለፍቶና እላይ እታች ብሎ” ሲባል አገር ለቆ መሰደድ ማለት አይደለም፤ “ጥሮ፣ ግሮ፣ ለፍቶና እላይ እታች ብሎ” ሲባል በማያስፈልገው ሁሉ ላብን ማፍሰስና ጊዜን ማባከን አይደለም።
“ጥሮ፣ ግሮ፣ ለፍቶና እላይ እታች ብሎ” ሲባል ከእነዚህ በተቃራኒ በሆነ መልኩ ጊዜን፣ እውቀትን፣ ክሂልን፣ ሀብትን፣ ጉልበትን ወዘተ በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ መሆን ማለት ነው።
ነገር ግን ይህ ሁሉ ሳይሆንና ሳይደረግ እየቀረ እዚህም እዚያ ብክነት ይታያል፤ የዜጎች ጉስቁልና ይስተዋላል። የአገር ሀብትና ንብረት ይባክናል ብቻ ሳይሆን ሲወድም ሁሉ ይታያል። በእነዚህ ሁሉ መሀል ደግሞ ዜጎች ላልተፈለገና ለማይገባ ሰቆቃና እንግልት ይዳረጋሉ።
ይህ ደግሞ በፋንታው ጦሱ ለአጠቃላይ ህብረተሰቡ ሁሉ ይተርፍና ስቃይና ጉስቁልናው ሁሉ የጋራ ይሆናል ማለት ነው። “አይደለም” እንኳን ከተባለ ምቾትና ተድላው የጥቂቶች ከመሆን አይዘልምና አያስኬድም።
የላይኛው መንደርደሪያችን የአምዳችንን የእስከዛሬ፣ የዛሬና የነገን ይዘትና አቅጣጫ ያሳይልን ይሆናል ብለን ያሰፈርነው ሲሆን፤ አጠቃላይ ምልከታችን ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ለጉስቁልና የተዳረጉና ከዛ ለመውጣት እንደ ግለሰቦቹም፣ እንደ አገርም ምን እየተደረገ እንዳለ ማየት ነው።
በተለያዩ ጊዜያት በዚሁ አምድ ላይ ለማመልከት እንደምንሞክረው ህይወት መልኳ ብዙ ነው፤ አይደለም እንደ አገር እንደ ቤተሰብ እንኳን ለቃኛት ዥንጉርጉርነቷ ግልፅ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ነው።
እርግጥ ነው ህይወት በራሷ ችግር አይደለችም፤ እንደውም ፀጋ ናት። በተለይ ከተፈጥሮ አኳያ ለመረመራት ጉዳዩ ግልፅ ነው። “ለምን?” ቢሉ ለማንም ምንም የምታዳላው፣ አንዱን ለመጉዳት ወይም አንዱን ለመጥቀም ብላ የምታደርገው ምንም ነገር የላትም። ችግሮች ሁሉ የሚመጡት እኛ ህይወትን መምራት ከጀመርን በኋላ ነው።
እየመራንበት ያለው መንገድ፣ እየመራንበት ያለው ብልሀትና ዘዴ፣ እየመራንበት ያለነው ሥርዓት፤ ወይም እየመራን ያለው ሥርዓት ወዘተ ሁሉ ህይወትን ቡራቡሬ፤ ከፍና ዝቅ፤ ጎስቋላና ምቾት የተሞላበት ወዘተ ከማድረግ አኳያ ያለው ድርሻ እጅጉን ሰፊና ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው ብዙ ጊዜ የአሰራር፣ የአመራር፣ የአፈፃፀም ችግር … እየተባለ እሮሮ የሚሰማውና ጉዳዩ ቀላል አይደለም።
እነዚህ ሁሉ ተዳምረው እንግዲህ ወዴት ያመራሉ ያልን እንደሆን የሚያመሩት ወደ አንድ አቅጣጫ ሲሆን፤ እሱም በርእሳችን “የተሻለ ህይወትን ፍለጋ” ወዳልነው አቅጣጫ ነው።
ኢትዮጵያዊያን፣ በተለይም ከ70ዎቹ ወዲህ እንደጉድ በዓለም ዙሩያ ባሉ አገራት ሁሉ ተበትነን እንገኛለን።
“ስደት” እንደማያውቀን ሁሉ መለያችን ሆኗል። ዓለም በ”ዲያስፖራ” ምድብ ውስጥ ገና ባያስገባንም እኛው እራሳችን አስቀድመን በ”ዲያስፖራ ሰንጠረዥ” ውስጥ እራሳችንን አስገብተናል።
ይህ ሁሉ ሲሆን የቀድሞ ምክንያቱ “ፖለቲካዊ” ሲሆን አሁን አሁን ግን “ኢኮኖሚያዊ” መሆኑ በ”ሁሉም መስክ” ተረጋግጧል። (“ፖለቲካዊ ተፅእኖ” የለም እያልን ግን አይደለም።)
ድሮ ድሮ በብዙዎቻችን ዘንድ አረቡ ዓለም አገር መሆኑ እንኳን በቅጡ የማይታወቅበት ሁኔታ እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ እየተገፈተርን “ተመለሱ፣ ሂዱ፣ ጥፉ …” እስክንባልና ከዛም ባለፈ አካላዊና መንፈሳዊ ጥቃት እስኪደርስብን እየተንገላታንም ቢሆን ወደዛው እየተግበሰበስን እንገኛለን። ባጠቃላይ ባራቱም ማእዘን እኛ አለን።
“ለምን?” ከተባለም የአብዛኞቻችን መልስ “የተሻለ ህይወትን ፍለጋ” ሲሆን ይህንኑ ምክንያትም በአንድ ቃል ስንገልፀው “ኢኮኖሚያዊ” ሆኖ ይቀመጣል። ይህ ሁሉ ከላይ በ”ጥሮ፣ ግሮ፣ ለፍቶና እላይ እታች ብሎ” ካልነው አንፃር ትክክል ሊሆን ወይም ሊመስል ይችላል።
መሬት ላይ ካለው እውነታና ተጨባጩ ዓለም ጋር ስናስተያየው ግን ውጤቱ አኩሪ ሳይሆን አንገት አስደፊ ነው። ክብረ-ነክ ብቻ ሳይሆን ለስነ ልቦና ቀውስና ለቅስም ስብራት ሁሉ የሚዳርግ ነው።
እንደ አህጉራዊው የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት (IOM) (2018 እ.ኤ.አ) ጥናት በተደረጉት የህገ-ወጥ ስደተኞች የየብስ ጉዞ ወቅት ሃይለኛ የውሃ ጥም፣ ርሃብ፣ የተሽከርካሪዎች ብልሸት፣ አስገድዶ መድፈርና (ፆታዊ ጥቃት) አካላዊ ግርፋት፤ እንዲሁም በተለያዩ በሽታዎች መጠቃት … መንገድ ላይ ከሚያጋጥሙ ዋና ዋና ፈተናዎች መካከል ውስኖቹ እንደሆኑ ታውቋል።
ከእነዚህ ሁሉ አኳያ ስንመለከተው ነው እንግዲህ ከላይ “ጥረህ ግረህ በወዝህ ብላ” የሚለው የፈጣሪ ቃል ያለ አውዱ ተተርጉሞ የምናገኘው፤ እርግጥ ከሱ አንፃር ከሆነ ማለት ነው።
“ከ2014 ጀምሮ እስከ አሁን ከ1000 በላይ ስደተኞች በሜዲትራንያን ባህር ውስጥ ህይወታቸው የጠፋ ሲሆን፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ በጠቅላላ 18ሺህ 900 ስደተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል።
” የሚለውን የጠቀስነውን ተቋም ጥናት ስናስብ ኢኮኖሚያዊ አይደለም ምንም አይነት ምክንያት ቢኖር ይህ አይነቱ አገር ለቆ መሰደድ ተቀባይነት የለውምና ሁሉም ባገሩ፣ ላገሩና ለራሱ እንላለን።
በተለይ ወደ አውሮፓ ከተሰደዱት አብዛኞቹ ወንዶች፣ ህፃናትና ሴቶች የከፋና ከባድ ችግርን እያሳለፉ …” መሆናቸውን በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ከሰጡት ከአህጉራዊ የስደተኞች ድርጅት በሜዲትራንያን ባህር የውህደት ክፍል ሃላፊ ከሆኑት ሚስተር ላውረንስ ሃፍትን ማብራሪያ ስንመለከት “እንዲህም ይኖራል” ብቻ ብለን እንድናቆም ሳይሆን “እንዲህ መኖር የለበትም” እንድንልና ትኩረታችንን ወደ አገር ቤት በማድረግ እንደገና “ሁሉም ባገር ነው” እንድንል ያስገድደናል።
ደሞም ልክ ነን። “የተሻለ ህይወት ፍለጋ” ተብሎ “ከጥር 1- ጥቅምት 3/ 2019 ብቻ በሶስቱም የመካከለኛ ባህር የጉዞ መስመሮች 1000 ስደተኞች ህይወታቸውን” ያጣሉ። ችግሩ ይህን ያህል ከሆነ የተሻለ ህይወት እያልን ለተሻለ ሞት እንኳን እየበቃን አይደለምና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ያለባቸው የቤት ስራ ቀላል አይደለም።
እንደው ለማሳሰብና ለጉዳዩ ትኩረትን ለመስጠት ያህል “አህጉራዊ የስደተኞች ድርጅት ጥቅምት 4 ባሰራጨው ዘገባ ከጥር 1 እስከ ጥቅምት 3/2019 በሶስቱም አውራ የሜዲትራንያን ባህር መስመሮች በትንሹ የ1 ሺህ 41 ስደተኞች ህይወት መጥፋቱን አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ በ2018 በመተላለፍያው መስመሮች ህይውታቸውን ያጡ ስደተኞች ቁጥር 1 ሺህ 890 መሆኑን” የሚለውን የላውረንስ ሃፍትን ማብራሪያ ጨምረን ከላይ ያሰፈርነውን እንበል እንጂ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ችግሩ በየጊዜው እየከፋ እንጂ እየተሻለው አይታይም ተሰዳጁም፣ አሳዳጁም፤ የሁለቱም አስተናባሪ (ዎች)ም ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል እንላለን።
ሌላው “እንዲህም ይኖራል እንዴ?” ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርገን አቢይ ማህበራዊ ችግር የጎዳና ተዳዳሪነት ህይወትና ኑሮ ነው።
የጀርመን ሬዲዮ (DW) በጃንዋሪ 15/2019 ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ “በኢትዮጵያ አስራ አንድ ከተሞች ብቻ 88 ሺህ 960 የጎዳና ተዳዳሪዎች” አሉ።
በ”ጉዳያችን ሚድያ፣ ኮምኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት” በሚዘጋጀው ድረ-ገፅ አማካኝነት ለንባብ እንደበቃው መረጃ (ማርች 8/2016) ከሆነ “በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው።
100 ሺህ ሕፃናት በአዲስ አበባ፣ በሌሎች ከተሞች ደግሞ 600 ሺህ ሕፃናት የጎዳና ተዳዳሪዎች ናቸው። ከእዚህ ውስጥ 150 ሺው መንግስት እራሱ ያመነው ቁጥር ነው።”
“ሪፖርተር” ጋዜጣ ጃንዋሪ 30/2019 በ”ማህበራዊ” አምዱ “የጎዳና ተዳዳሪዎች መፃኢ ዕድል” በሚል ርእስ ባሰፈረው ጽሑፍ ስር እንዳሰፈረው በአዲስ አበባና ዋና ዋና መንገዶች ከወዲህ ወዲያ ሲሯሯጡ የሚታዩት የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ አብዛኞቹን ለዚህ ሕይወት ያበቃቸው የቤተሰብ መለያየት መሆኑ ተገልጿል። ከሁሉም አካባቢ በተለይ ከደቡብ የአገሪቱ ክፍል እንደሚመጡም ተነግሯል። ብዙዎችም ትምህርትን ከጀመሩ በኋላ፤ አሊያም መሃል ደርሰው ያቋረጡ ናቸው።
በደቡብ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ቢሮ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በቅርቡ እንዳስታወቀው ህጻናት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ለጎዳና ህይወት ሊዳረጉ ይችላሉ።
እ.ኤ.አ በ1993 እና በ2004 ዓ.ም በህዝብና ቤት ቆጠራ የተካሄዱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትን በአራት ይከፍሏቸዋል። እነዚህም ለጎዳና ህይወት መጋለጥ ስጋት ውስጥ ያሉ፣ በጎዳና ላይ የሚሰሩ ህጻናት፣ ከፊል ጎዳና ተዳዳሪ ህጻናትና የተተዉ ህጻናት በሚል ይከፈላሉ።
በአገራችን እንዲሁም በክልላችን በጎዳና ላይ የሚኖሩና የሚሰሩ የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አሁን ያሉ ተጨባጭ መረጃዎች ያመለክታሉ። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ህጻናት ወደዚህ አስቸጋሪ ህይወት የሚገቡበት ምክንያት የተደላደለና ምቹ የሆነ ህይወትን ጠልተው ወይም የጎዳና ህይወት ናፍቀው ሳይሆን በዋነኝነት በቤተሰብ ችግር የሚወጡት ህጻናት ቁጥራቸው የትየለሌ ነው።
እንደ ዳይሬክቶሬቱ ከሆነ የስጋቱ ምንጭ እንዲህ ነው ብሎ ፍረጃ መስጠት የሚያስቸግር ቢሆንም መሰረታዊ ምክንያቶቹ ቤተሰባዊ ችግር ናቸው። በዚህ ውስጥም የሚከሰቱ ድህነት፣ በልጆች መብዛት ምክንያት ልጅን መግቦና አልብሶ አስተምሮ ማኖር ያለመቻል፤ ወላጅ አባትን ወይም እናትን በሞት ማጣት፤ እንዲሁም የተሻለ ኑሮ ፍለጋና በመልካም ስነ ምግባር ተቀርጾ ያለማደግ እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
ይህ የሚያሳየን ልጆችም ሆኑ ትልልቅ ሰዎች ወደ ጎዳና የሚወጡት የተሻለ ህይወትን ፍለጋ ሳይሆን በችግርና ችጋር ተገፍተው መሆኑን ነውና ጉዳዩ በግለሰብ ወይም በአንድ ድርጅት የሚፈታ ሳይሆን ከፍተኛ ንቅናቄን የሚፈልግ መሆኑን ነው።
“ጉዳያችን ሚድያ፣ ኮምኒኬሽን እና ምክር አገልግሎት” የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን የጠቀሰውን የተባበሩት መንግሥታት የዜና ወኪል (RIN)ን ጠቅሶ እንደዘገበው በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር 150 ሺህ (በማርች 8/2016) ሲሆን የእርዳታ ድርጅቶች ግን በአዲስ አበባ ብቻ ቁጥሩን 100 ሺህ፤ በሌሎች ከተሞች የሚገኙትን ደግሞ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ማለትም 600 ሺህ ያደርሱታል።
ከላይ ከተጠቀሱት ሪፖርቶች ወዲህ በርካታ መፈናቀሎች፤ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች የድህነት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ይታወቃል። በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ከላይ በኢሪንም ሆነ ሌሎች የቀረቡት ቁጥሮች የበለጠ እንደሚሆኑ ይታመናል።
ከእዚህ ጋር በተያያዘ በ2018 ለሕዝብ ይፋ በሆነ አንድ ጥናት ላይ የኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር እስከ 2030 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) እስከ 40 በመቶ እንደሚሄድ ያብራራል።
ይህ እንግዲህ የአገልግሎት ዘርፉ እንጂ በርካታ ሰው የሚቀጥር ኢንዱስትሪ የሌላት አገር አሁንም መጪውን ጊዜ የከፋ ያደርገዋል። በመሆኑም ይህ ከመሆኑ በፊት የተሻለ የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫና አተገባበር፣ የባለ ድርሻ አካላት ጠንካራ ተሳትፎና የመላው ህዝብ ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ከወዲሁ ያመለክታል።
በመሆኑም እነዚህ ወገኖች ከዚህ አይነቱ ህይወት ሊወጡ ይገባል የሚል አቋም ተይዞ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ይነገራል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ የከፈተው የአዲስ አበባ ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ የባንክ ቁጥር 1000272444726 ወይም በ6400 ላይ A ብሎ በመላክ የከተማው ሕዝብ፣ የእምነት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና ሌሎችም የተቻላቸውን ሁሉ በማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነ የሚመለከታቸው በወቅቱ መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ያን ጊዜ የመገናኛ ብዙሃንን በመጥራት መግለጫ እንደተሰጠው ሁሉ አሁንም ምን ላይ እንደደረሰ እነዚህኑ አካላት በመጥራት የደረሰበትን በተመለከተ መግለጫ መስጠት ይገባል እንላለን።
የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት የተጀመረውን ፕሮጀክት አስመልክተው ጥር 21 ቀን/2011 ዓ/ም በጽሕፈት ቤታቸው የሰጡት መግለጫም ምን ላይ እንደደረሰም ቢነገር በዘርፉ በመሳተፍ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖችን ያበረታታል፤ ያደፋፍራልም።
እርግጥ ነው እነ”መቄዶንያ”ን፣ “መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት”ን የመሳሰሉ በግለሰብ አእምሮ ተፀንሰው፣ በግለሰብ ተወልደው፣ በግለሰብ ተመስርተው፣ በግለሰቡና ማህበረሰቡ ጥረት የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሰው እነዚህን ወገኖች በመታደግ፣ ከመታደግም ባለፈ የተሻለ ህይወት እንዲኖሩ የማድረግ ስራ ላይ የተጠመዱ ተቋማት አሉ።
ይሁን እንጂ ከእነዚህ ባለፈ አሁን ካሉት በእጥፍ ቢኖሩ እንኳን ከችግሩ ግዝፈት አንፃር ይፈቱታል ተብሎ ለማሰብ ይከብዳልና ጥረቱ የጋራ መሆን ይጠበቅበታል።
ያም ሆነ ይህ፤ እያልን ያለነው ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩና ለከፉ አደጋዎች ሲጋለጡ ይታያል፤ ይህ ደግሞ “የተሻለ ህይወትን ፍለጋ” አገር ጥለው ከሚሰደዱት እና በማያውቁት አገር ለህልፈት ከሚዳረጉት በተጨማሪ እዚሁ አገራቸው ውስጥ ሆነው ወደ ጎዳና በመውጣት ለችግር ሲጋለጡ እየተመለከትንና ችግሩም ከእለት ወደ እለት እየከፋ ሲሄድ እየተመለከትን ነው። ከእነዚህ የጎዳና ተዳዳሪ ዜጎች መካከልም በተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ አማካኝነት ወደ ተሻለ ህይወት የገቡ ብዙዎች ናቸው (ከዚህ ቀደም በዚሁ ጋዜጣ፣ በዚሁ አምድ ላይ የወጡ ጽሑፎችን ይመለከታል)።
ሌሎችም በሚመለከታቸው አካላት ድጋፍና እገዛ ካሉበት ችግር እንደሚላቀቁ ተስፋ እናደርጋለን። ስደትም በዚሁ ቆሞ ሁሉም ባገርና በወገን፤ ሁሉም ላገርና ለወገን እንደሚሆንም እንደዛው።
አዲስ ዘመን ጥር 8/2013