
አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታገኝ ጎረቤቶቿ በጎ ምላሽ መስጠት አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ትናንት ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ውጭ ሕልውና የላትም፤ ከኢትዮጵያ ውጭ ጎረቤት ሀገራትም ሕልውና የላቸውም። ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ማሳካት የምትፈልገው በጋራ ተጠቃሚነት መርሕ እና በሰላማዊ መንገድ እንጂ በኃይል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የበለጠ ምሉዕ እንዲሆን ጎረቤት ሀገራት የባሕር በር እንድታገኝ በጎ ምላሽ መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድም ግጭት ከጎረቤት ሀገራት ጋር አላደረግንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ፍላጎታችን በትብብር አብሮ ማደግ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የማንሰራራት ጉዞዋ እንዳይስተጓጎል ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላም መኖር እንደምትፈልግ ጠቅሰው፤ ለሰላሟ የሚያሰጋ ነገር ካለ ግን ራሷን መከላከል የሚያስችል በቂ አቅም እንዳላት አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር፤ ትልቅ ባሕር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በትናንሽ ጠጠር የምትታወክ አለመሆኗን አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚ፣ የሕዝብ ቁጥርና የዘመነ ሠራዊት ያላት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚያውካትን እየተከላከለች መልማት የምትችል ሀገር ስለመሆኗ ተናግረዋል፡፡
ከኤርትራ ጋር የጦርነት ስጋት እንዳለ የሚያነሱ አካላት መኖራቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ በኩል ምንም ዓይነት የውጊያ ፍላጎት እንደሌለ ማወቅ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የፀጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
የስንፍና ፖለቲካ እንደተንሰራፋ ጠቅሰው፤ ይህም ጠብና ተቃርኖን ይወልዳል ብለዋል። እንደሀገር አርሶ አደር፣ አርብቶ አደር፣ ላብ አደር እንዳለ ሁሉ፤ አሁን ደግሞ አውርቶ አደር ተፈጥሯል ነው ያሉት።
አውርቶ አደሮች ገቢ የሚያገኙት እያጋጩ እንደሆነ አስረድተው፤ ሥራ ሳይሠሩና አገልግሎት ሳይሰጡ መብላት የሚፈልጉ ሰነፎች ናቸው ብለዋል።
ሁለተኛው መንስኤ የኃይል ፖለቲካ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ክላሽ ካነገትኩ ፍላጎቴ ይሳካል ብለው የሚያምኑ፤ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኃይልና በወሬ እናፈርሳለን ብለው የሚያምኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት አትማሩ፣ ማዳበሪያ አትውሰዱ ብለው ሰዎችን የሚገድሉ ስለመኖራቸውና ይህም እኩይ ዓላማ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ድህነት ሌላው የችግሮች መንስኤ እንደሆነ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ድህነትን መቀነስና ሥራ መፍጠር ከተቻለ ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ ኋላቀርነት እና ዘረኝነትም አባባሽ ችግሮች እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡
የፕሪቶሪያ ስምምነት ለትግራይ ሕዝብ እፎይታን እንደፈጠረ እና የትግራይ ሕዝብን ልጆቹን በየቀኑ ከማጣት እንደታደገው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ቴሌኮም፣ ባንኮች፣ አየር መንገድና ሌሎችም አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ሥራ መጀመ ራቸውን ጠቅሰው፤ የተፈናቀሉ ሰዎችን በሚመለከት ራያ መቶ በመቶ ፀለምት በከፊል መመለ ሳቸውን አመልክተዋል፡፡
በወልቃይትም ያልተመለሱ ተፋናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መንግሥት የጸና አቋም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀል በፍጥነት መፈጸም ያለበት ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል።
የፌዴራል መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በሰላም የመፍታት ፅኑ አቋሙን በተደጋጋሚ እንዳሳየ ገልጸው፤ ሆኖም መንግሥት በተለያዩ ችግሮች ተወሯል፤ የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን እያሉ ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ፤ በመንግሥት በኩል አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት እንደሌለው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጭልፊቶች እንዳሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያውያን እሳት ጫሪዎችን ማወቅና ማረም እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሑራንና ኤምባሲዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳይገባ አሁኑኑ የሰላም ሚናችሁን ተወጡ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በኢያሱ መለሰ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም