
>8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ታስመዘግባለች ተብሎ ይጠበቃል
> የህዳሴ ግድብን በመጪው መስከረም ታስመርቃለች
> በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዝ ምርት ለገበያ ማቅረብ ትጀምራለች
አዲስ አበባ፡- በዓመቱ የታቀደው 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚሳካ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን በአገልግሎትና ሌሎችም ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች አመላካች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያ በመጪው መስከረም የህዳሴ ግድብን እንደምታስመርቅና በቅርቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የጋዝ ምርት ለገበያ ማቅረብ እንደምትጀምርም ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ትናንት በሰጡት ማብራሪያ፤ በበጀት ዓመቱ በሁሉም መስክ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን በአገልግሎትና ሌሎችም ዘርፎች የተገኙ ውጤቶችም በበጀት ዓመቱ የታቀደው 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚሳካ አመላካች ናቸው ብለዋል፡፡
እንደጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም የወጪ ንግድ ገቢያችን ዋልታም ነው፡፡
በዚህ ዓመት 6 ነጥብ አንድ በመቶ ዕድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል፡፡ ግብርናው የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥም ወሳኝ ነው፡፡፡ አምርታ መብላት ያልቻለች ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ ትቸገራለች በሚል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብ ይዘን ሠርተናል።
በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት 27 ሚሊዮን በሴፍቲኔት የተያዙ ዜጎች ነበሩ፤ እነዚህን ከሴፍቲኔት ለማሸጋገር ሲሠራ ቆይቷል፤ 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከሴፍቲኔት ተረጂነት ነፃ ወጥተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ይህ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያ ስለሆነ ኩራት ሊሰማን ይገባል። ቀሪው ከ4 ሚሊዮን ያላነሰ ተረጂም ነፃ በማውጣት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ሀገር ማድረግ አለብን ብለዋል።
ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 8 ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ አሳክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ይህም ከታቀደው 3 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ፣ ከአምናው ከእጥፍ በላይ ነው። ከሬሚታንስ 7 ቢሊዮን ዶላር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ቢሊዮን ዶላር፣ ከአገልግሎት 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። አምና የውጭ ምንዛሪ ማግኛ መንገዶችን ከብድርና ርዳታ ውጭ ያሉትን ተጠቅመን ያገኘነው 24 ቢሊዮን ዶላር ነበር፤ ዘንድሮ 32 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተናል። ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል የአገልግሎት ዘርፍ 8 ነጥብ አንድ በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተው፤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ዘንድሮ 12 በመቶ ገደማ ዕድገት ለማምጣት ታቅዶ እየተሠራ ነው። ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ንቅናቄ በጣም ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አምና 59 በመቶ ነበር የደረሰው፤ ዘንድሮ 65 በመቶ ደርሷል። ይህም የፋብሪካዎችን የማምረት አጠቃቀም በማሳደግ ነው። በዚህ ዓመት የኢንዱስትሪው የኃይል አቅርቦት በ40 በመቶ ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል።
መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ዓመቱን ሙሉ ብድር ሳይወሰድ ማጠናቀቁ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን አመልክተው፤ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ፣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ማሻሻያ፣ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ከፍተኛ ድጎማ መደረጉ፣ ምርትንና ገበያን በቀጥታ ማገናኘት መቻሉ ትልቅ ውጤት እንዲመጣ አስችሏል ነው ያሉት።
የዋጋ ግሽበቱ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳያሳድር 350 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን አመልክተው፤ ዋጋ ግሽበትን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም የሚቻለው የእያንዳንዱን ሰው ገቢ ማሳደግ ሲቻል በመሆኑ አጠቃላይ ሀገራዊ እድገትን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው። መፍትሔውም ፈተናዎችን በጋራ ተቋቁሞ መሥራት እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የመንገድ ሽፋን 175 ሺህ ኪሎ ሜትር ደርሷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አንድ ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር የሚጠይቁ 300 ፕሮጀክቶች ፀድቀዋል። ውል በመፈራረም በተለያየ የሥራ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ 169 ፕሮጀክቶች ከ11 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ በአሁኑ ወቅት እየተገነባ ነው ብለዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማት ሽፋንን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርሙም በዚህ ዓመት አዎንታዊና ጤናማ ዕድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ የዲጂታል ግብይት 12 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከጥሬ ገንዘብ ግብይቱ ከፍተኛ ብልጫ አለው፡፡ 24 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በቨርቹዋል ብድር ተደራሽ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
የሀገሪቱን ዕዳ ጫና ለመቀነስ በተያዘው ዓመት 92 ቢሊዮን ብር ዕዳ መክፈል መቻሉን ጠቁመው፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድም የንግድ ብድር አልተወሰደም። በተሠሩ ሥራዎች 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ዕዳ በማሸጋሸግ የኢትዮጵያን የዕዳ ቀንበር ማንሳት ችለናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የጋዝ ምርት በቅርቡ ለገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር ጠቁመው፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል፡፡ ከ40 ወራት በኋላም ተጠናቅቆ ሥራ ይጀምራል።
በዚህም ሠርቶ አዳሪ እንጂ አውርቶ አዳሪ አለመሆናችንን እያሳየን እንቀጥላለን ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ህዳሴ አልቋል፤ ህዳሴ እንዳይመረቅ የሚያደርግ ነገር የለም፤ ክረምቱ ሲወጣ እናስመርቃለን ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስከረም ላይ ግድቡ ሲመረቅ የግብፅና ሱዳን እንዲሁም የተፋሰሱ ሀገራት መንግሥታት የደስታችን ተካፋይ እንዲሆኑ ሲሉ በይፋ ጋብዘዋል፡፡
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 27 ቀን 2017 ዓ.ም