መርድ ክፍሉ
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሚያወጣቸው መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው ዓለማችን በየቀኑ ለመኖር የማትመች እያደረጓት ያሉ ፈተናዎቿ በቁጥር እየጨመሩ ነው።
እነዚህም ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ደግሞ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚያደርጓቸው ድጋፎች በተጨማሪ የእያንዳንዱን የምድር ነዋሪ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት የሚሹ ሆነዋል።
ኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመስጠት ባህል የነበራትና በፍጹም ወንድማማችነት ዜጎች የሚኖሩባት ችግራቸውን በጋራ በመተባበር የሚያሳልፉባት ሀገር ነች። ይህ በመስጠት የሚገለጸው በጎ ፈቃደኝነት የሀገሩ ባህል ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት ልማድና ወግም ነበር።
ሲወልድ የግምዶ፣ ሲያዝን የዝን ብሎ ከመስጠት ጀምሮ ሲዘምት የስንቅ፣ ሲመለስ የደስታ፣ ሲሻር የሹመት አይደንግጥና ሲሾም የምስራች ብሎ እስከመስጠትም የረቀቀ ነው። ከነዚህ ሁኔታዎች አንፃር በመመልከት በአሁን ወቅት በተለያዩ ቦታዎች የበጎ አድራጎት ማህበራት እየተቋቋሙ ይገኛሉ።
የሚቋቋሙ በጎ አድራጎት ማህበራት የሚኖሩበት ከተማ አስተዳደር አስፈላጊ ድጋፍ ሊያደርግላቸው ያስፈልጋል። ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ማህበራት በድጋፍ እጦት ምክንያት ያሰቡትን ያክል እየሰሩ አይደለም። ከነዚህም ውስጥ ምሳሌ የበጎ አድራጎት ማህበር አንዱ ነው።
ምሳሌ የበጎ አድራጎት ማህበር ከሚገኝበት ጠበላ ከተማ አስተዳደር ምንም አይነት ድጋፍ እያገኘ አይደለም። ከተማ አስተዳደሩ የማህበሩን ስራዎች በማሳነስና ለራሱ በመጠቀም ከፍተኛ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ የማህበሩ አባላት ይናገራሉ።
የምሳሌ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ሰብሳቢ ወጣት እንደግ እንድሪያስ በወላይታ ዞን ጠበላ ከተማ ነዋሪ ነው። ማህበሩን ለመመስረት ምክንያት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ሲሆን በአካባቢው የሚገኙትን ወጣቶች በመሰብሰብ ሊመሰረት ችሏል።
ማህበር ውስጥ የመንግስት ሰራተኞችን በማስተባበር በከተማ ውስጥ የድጋፍ ስራ መከናወን አለበት በሚል እንደተመሰረተ ይናገራል።
በማህበሩ የተከናወኑ ተግባራት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአገሪቱ ከተከሰተ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች ማዕድ ማጋራት፣ መረዳዳት እንዲሁም ማህበራት ተቋቁመው ሰፋ ያሉ ድጋፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የተቋቋሙት ማህበራት ስራዎቻቸውን ቀጥለው አቅም ለሌላቸው ሰዎችም አሁንም ድረስ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። ከነዚህም ውስጥ ምሳሌ በጎ አድራጎት ማህበር ይጠቀሳል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በገበያ ቦታዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል።
የእጅ ማስታጠብ፣ መልዕክቶችን የያዘ በራሪ ወረቀቶች በመበተን እንዲሁም በየመዝናኛ ስፍራዎች ትምህርት ይሰጥ እንደነበር ወጣት እንደግ ያስታውሳል። ከጤና ባለሙያዎች የሚመጡ መልእክቶችን ለህብረተሰቡ በቀጥታ የማስተላለፍ ስራ ሲከናወን እንደነበርም ይጠቁማል። በዚህም ማህበሩ የስራ እንቅስቀሴዎችን መጀመሩን ይናገራል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከቤት መውጣት ለማይችሉ ሰዎች በየወሩ አስቤዛ፣ የተፈጨ በቆሎ፣ ሳሙናና አልባሳት ከህብረተሰቡ በማሰባሰብ፣ ከአባላት መዋጮ በየወሩ ሀምሳ ብር በመሰብሰብ እንዲሁም ውጪ ከሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ በመሰብሰብ ድጋፍ ሲደረግ እንደነበር ይናገራል።
በዚህም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት አቅም የሌላቸው ሰዎች ተደግፈዋል።
ለበዓላት ወቅት ደግሞ በሬ በመግዛት ህብረተሰቡን በማሰባሰብ አብሮ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም አቅም ለሌላቸው ሰዎች የቅርጫ ስጋ የማከፋፈል ስራ ተሰርቷል። በተመሳሳይም የደም ልገሳ የማድረግ ስራም በቋሚነት እንደሚከናወን ወጣት እንደግ ይጠቅሳል። በቋሚነት በየወሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ያሉ ሲሆን እነሱንም በተቻለ አቅም አስፈላጊ ነገሮች እንደሚሟሉላቸው ያመለክታል።
ሌላው የማህበሩ ጸሀፊና አባል ወጣት ምህረቱ ማርቆስ እንደሚናገረው፤ ምሳሌ የበጎ አድራጎት ማህበር 2012 ዓ.ም ላይ በተወሰኑ ሰዎች ተመሰረተ።
ማህበሩ ስራውን ሲጀምር ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም አረጋውያን፤ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው ሰዎች፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ አላማ አድርጎ እየሰራ ያለ ነው።
በመደበኛ መንገድ የሚደረጉት ድጋፍና እርዳታዎች እንደተጠበቁ ሆነው ለበዓላት ወቅት የሚደረጉ ድጋፍና እርዳታዎች እንዳሉ ወጣት ምህረቱ ይናገራል።
ከተለያዩ ሰብዓዊ እርዳታ ከሚያደርጉ ሰዎች ገንዘብ በማሰባሰብ እንዲሁም በውጭ አገር ከሚገኙ ለጋሽ ግለሰቦች እንዲሁም የማህበሩ አባላት ከሚያደርጉት መዋጮ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ያመለክታል። በተጨማሪም በየሳምንቱ እሁድ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች ቤታቸው በመሄድ ጥየቃ እንደሚደረግም ይናገራል።
በቋሚነት በየወሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው አባወራዎች ያሉ ሲሆን የመማሪያ ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ ተማሪዎች ከአካባቢው ህብረተሰብ በዘመቻ መልክ ደብተርና እስክሪቢቶ የማሰባሰብ ስራ ተከናውኗል። በዚህም ለመቶ ሀምሳ ተማሪዎች ድጋፍ ተደርጓል። ዩኒፎርም ለሌላቸውም የማሰፋት ስራም ተሰርቷል። ለበዓል ደግሞ ከብት በማረድ ቅርጫ የማከፋፈልም ስራ መሰራቱን ይጠቅሳል።
የህብረተሰቡ አቀባበልየአካባቢው ህብረተሰብ ለማህበሩ ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ለበዓል ወቅት ማህበሩ የገንዘብ ችግር በገጠመው ወቅት የሎተሪ እጣ ማዘጋጀቱን ወጣት እንደግ ይናገራል።
አንዱን ሎተሪ ለመሸጥ መቶ ብር ዋጋ ወጥቶለት በመጀመሪያ እጣ ላፕቶፕ፣ ሁለተኛ ስልክ እንዲሁም ሶስተኛ እጣ ገንዘብ በማድረግ አራት መቶ እጣዎች ተዘጋጅተው ወደ ህብረተሰቡ መገባቱን ይጠቅሳል። ህብረተሰቡ ከአንድ በላይ እጣዎችን የገዛ ሲሆን የመንግስት ሰራተኛው በዱቤ በመውሰድ ሁሉን እጣዎች መሸጣቸውን ይጠቁማል።
ህብረተሰቡ በተቻለው አቅም ለማህበሩ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። በገና በዓልም በደመቀ ሁኔታ ነበር የተከበረው። 40 አረጋውያን ቅርጫ እንዲከፋፈል ተደርጓል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ በቻሉት አቅም ከገንዘብ ጀምሮ ድጋፎችን የሚያደርጉ መሆናቸውን የማህበሩ አባላት ይናገራሉ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ህብረተሰቡ ከማህበሩ የሚወርድለትን መልዕክት በመቀበል ጥንቃቄ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በደም ልገሳና በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝም ያመለክታሉ።
ማህበሩ ያጋጠሙት ችግሮች በማህበር ውስጥ ተካተው የሚገኙት አባላት በሁሉም የሙያ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ናቸው። በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስራዎች መከናወን ችለዋል። ነገር ግን ፖለቲካዊ በሆነ ምክንያት ማህበሩን ለማዳከም ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው።
የከተማ አስተዳደሩ ማህበሩ የሰራውን ስራ እራሱ እንደሰራ አድርጎ የማቅረብ ሁኔታዎች አሉ። ማህበሩ ከማንኛውም ፖለቲካ አመለካከት የፀዳ ሲሆን የከተማው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ማህበሩ የሰራቸውን ስራዎች ሰብስቦ ሪፖርት የሚያቀርብ ሲሆን በዚህም አለመስማማት ውስጥ መገባቱን ወጣት እንደግ ይናገራል።
ማህበሩ በራሱ እቅድ የሚመራ እንደመሆኑ የማንንም ጣልቃ ገብነት ሳይፈልግ መስራት የሚችል መሆኑን ይናገራል። ወጣቱን ፖለቲካ ታራምዳላችሁ በሚል ጫና እየተፈጠረ ይገኛል።
‹‹የሰራነውን ሪፖርት አንሰጥም፣ እኛ የምንሰራው ለህብረተሰቡ እንጂ ለናንተ አይደለም፣ እናንተ የኛን ስራ ለዞንና ለተለያዩ አካላት ሪፖርት ማቅረብ አትችሉም›› በሚል ከፍተኛ የሆነ ክርክር መደረጉን ያመለክታል።
ማህበሩ ስራዎችን የሚያከናውንበት ቢሮ የሌለው ሲሆን የከተማ አስተዳደሩን በተደጋጋሚ በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራል። የከተማ አስተዳደሩ ማህበሩ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን የሚያራምድ በመሆኑ ጊዜ ተወስዶ መታየት አለበት በሚል ጥያቄያቸው ምላሽ አለማግኘቱን ይጠቁማል። ለቢሮ የሚሆን ቦታ መታጣቱንም ይጠቅሳል።
እንደ ወጣት ምህረቱ ማርቆስ አባባል፤ ማህበሩ አዲስ እንደመሆኑ አንፃርና ስለ በጎ አድራጎት ማህበር ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ሳይኖር ነው ወደ ስራው የገባው። ለዚህም የተጠናከረ ድጋፍ የሚያስፈልግ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ትብብር ያስፈልጋል።
በአሁን ወቅት መልካም ከሚያስቡ ሰዎች ድጋፍ እየተገኘ ነው።
የከተማ አስተዳደሩ ማህበሩን ለመደገፍ ምንም አይነት ተነሳሽነት የሌለ በመሆኑ የቢሮና ሌሎች ነገሮችን ለማሟላት እንቅፋት መፍጠሩን ያመለክታል። ስራዎች እንዲሰሩና ማህበሩ በእግሩ እንዲቆም ከንቲባው ምንም አይነት ድጋፍ እያደረገ አይደለም።
አስተዳደሩ በተደጋጋሚ ድጋፍ እንዲያደርግ ማህበሩ ጥያቄዎችን ቢያቀርብም ምንም አይነት ምላሽ አለመገኘቱን ይናገራል።
በተለያዩ ጊዜያት የማህበሩን እንቅስቃሴ ለማበላሸት ከአስተዳደሩ የተለያዩ ጫናዎች እንደሚደረጉ በመጥቀስ፤ በበዓላት ወቅት ለተረጂዎች በተደረገው ድጋፍ ማህበሩ ያለ አስተዳደሩ ድጋፍ ስራዎችን ቢያከናውንም የከተማው አስተዳደር በእለቱ ተገኝተው ፎቶ አንስቶ እራሳቸው የሰሩ በማስመሰል መጠቀማቸውን ወጣት ምህረቱ ያስረዳል።
በዚህ ድርጊታቸው ማህበሩ በማዘኑ አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ በመነገሩ የመቀየምና ድጋፍ ላለማድረግ ሲጥሩ ይታያል።
በተለያዩ አመራሮች የማህሩን ገፅታ የሚያበላሹ ነገሮችን እያከናወኑ ሲሆን ማህበሩ በከተማ ውስጥ እንደ ጠላት እንዲታይ እያደረጉ መሆናቸውን ይገልፃል። ተቀራርቦ ለመስራትና አስተዳደሩ ከማህበሩ የሚፈልገውን፣ ማህበሩ ደግሞ ከአስተዳደሩ የሚፈልገውን ነገር ለመደጋገፍ ውይይት እንዲካሄድ ጥያቄ ቢቀርብም አስተዳደሩ ፍላጎት ስለሌለው ሊሳካ አለመቻሉን ያመለክታል።
የገና በዓል በተከበረበት ወቅት የተለያዩ የድጋፍ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ድጋፍ ያገኙና ያላገኙትን ጭምር የቅርጫ ስጋ መከፋፈሉን ይገልፃል። በቀጣይም ብዙ ስራዎችን ለማከናወን ቢታቀድም ድጋፍ ባለመኖሩ ፈተና ውስጥ መግባታቸውንም ይጠቁማል።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድበቀጣይ ማህበሩ በቋሚነት ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን በየወሩ ለመርዳት ሀሳብ አለው። በየሶስት ወሩ፣ በዓላት ሲደርሱ የደም ልገሳ የማድረግ ስራ፣ አልባሳት የማሰባሰብ እንዲሁም ትምህርት ሲከፈት ደብተርና እስኪርቢቶ ከህብረተሰቡ በመሰብሰብ እንዲሁም አቅም የሌላቸውን ተማሪዎች ቤት ለቤት በመጎብኘት አስፈላጊ ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን በቀጣይም ለማስቀጠል እቅድ እንዳለ ወጣት እንደግ ይገልፃል።
ሱቃቸው በእሳት ቃጠሎ የወደመባቸውን ለመርዳት ገንዘብ መሰባሰቡን በመጥቀስ፤ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ሰዎችን የማንሳት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ያስረዳል።
አንድ በጎዳና ላይ የሚገኝ ወጣት በማሳከምና ወደ ቤተሰቦቹ እንዲመለስ የማድረግ ስራ ማህበሩ ማከናወኑን ይጠቁማል። በአልባሳትና በሌሎች ነገሮች ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ያሉ ሲሆን በተጨማሪም የስራ እድሎችን ለመፍጠር እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ያስረዳል።
ወጣት ምህረቱ ማርቆስ እንደሚናገረው ከሆነ፣ ማህበሩ በቀጣይ ብዙ ስራዎችን አስቧል። በአካባቢው በማህበር ተደራጅተው ወጥ በሆነ መንገድ እርዳታ በማድረግ ረገድ የመጀመርያው ምሳሌ በጎ አድራጎት መሆኑን ይገልፃል።
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እስካሁን መዝለቁንም ያስረዳል። ይደረጉ የነበሩ ድጋፎች የሚቀጥሉ ሲሆን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ የግንዛቤ ስራ መስራት እንደሚቀጥል ይናገራል።
የማህበሩን የመርዳት አቅም ወይም የሚደገፉ ሰዎችን ቁጥር በማብዛት እንዲሁም የማህበሩን አባላት ቁጥር በማሳደግ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ሰፋ ባለ መልኩ ለማስተካከል ታስቧል።
ማህበሩ በአሁን ወቅት አነስተኛ ሰዎችን እየረዳ ሲሆን በቀጣይ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች ቁጥር ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ያብራራል።
ትምህርት ለመማር ፍላጎት ያላቸውና በችግር ምክንያት ቤታቸው የተቀመጡ ሰዎችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን እንዲሁም በህመም ምክንያት መስራት የማይችሉትን ቤታቸው ድረስ በመሄድ ልየታ እንደሚከናወን ያመለክታል።
ለድጋፍ የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር ብዙ ቢሆንም ማህበሩ በቻለው አቅም ድጋፍ ያደርጋል። የአቅም ውስንነቶች ካሉ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ያለውን አቅም ክፍት በማድረግ እንዲሁም በየጊዜው ውይይት በማድረግ የስራ እቅጣጫዎች እንደሚወጡ ያመለክታል።
ወቅታዊ ጉዳዮችም ሲኖሩ ማህበሩ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ ያስረዳል።
አዲስ ዘመን ጥር 07/2013