ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አቶ አቡበከር ያሲን ይባላሉ። በዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ዘርፍ በማስተርስ መርሐ ግብር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። በአሁኑ ወቅት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር እንዲሁም የማህበራዊ ሳይንስ ፋካልቲ መምህር ናቸው።
ከዚህ በዘለለ ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በንቃት ከሚከታተሉ ወጣት ምሁራን መካከል ናቸው። የቀጣናውን ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ጥቅም አኳያ በመመዘንና በመተንተን በርካታ ሃሳቦችን እያራመዱ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችና የምጣኔ ሃብት ዕድገትን የሚገዳደሩና ብሎም እንደ መልካም አጋጣሚ የሚታዩ ሁኔታዎችን በጥልቀት ይዳስሳሉ። በእነዚህ ጉዳዮችም ላይ የተለያዩ ምሁራዊ መጣጥፎችን አሳትመዋል።
ከኢትዮጵያ ውጭም በአንዳንድ አገራት ልምድ የመለዋወጥና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትርክት ህፀፆችና መልካም አጋጣሚዎችን አነጻፅረው ለማየት በሚያስችል መልኩ ፅሁፎችን አበርክተዋል። በእነዚህና መሰል ጉዳዮች ላይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ያደረጉትን ቆይታ እነሆ።
አዲስ ዘመን፡– ፖለቲካ እንደሚከታተልና እንደ ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርነትዎ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገነዘቡታል?
አቶ አቡበከር፡- አሁናዊ ፖለቲካውን ከመዳሰሳችን በፊት ያለፈውን በተወሰነ መንገድ መጥቀስ ጠቃሚ ነው። ያለፉት 27 ዓመታት እንደ አገር የመጣንበት መንገድ ያሳዝናል።
ታልሞ የነበረው በህዝቦች ጥቅም ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ መንግስት ተመስርቶ ሠላምና ዴሞክራሲ እንዲመጣ እንዲሁም ሀገረ መንግስት በጥሩ ሁኔታ ተቃኝቶ የተሻለች ኢትዮጵያን የማየት ጉጉት ነበር።
መጀመሪያ ታስቦ የነበረው የፌደራል ሥርዓቱ ተቋቁሞ ሁሉም ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር እና የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት የሚል ትልም ነበር። ግን ይህ ሊሆን አልቻለም። እንግዲህ ከዚያ ወዲህ በድልድዩ ሥር ብዙ ውሃ አልፏል።
ይህም የሆነው እንደ ኢትዮጵያ መልካም ዕድል ማስመለጥ ስተለማመድን ነው።
1966 ዓ.ም እና 1983 ዓ.ም ጥሩ ዕድል አምልጦናል። እንደ አገር ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉብን። ይህን መልካም ዕድል እንደ አገር ማስኬድ አልተቻለንም።
እንደ በለፀጉ አገራት አድገን ብሎም ህዝባችን ካለበት የድህነት አረንቋ ወጥቶ የሚገባንን ቦታ አግኝተን እንደ አገርም በልጽገን ሰብዓዊ ደህንነቱ ተረጋግጦና የዴሞክራሲ መብቱ ተከብሮ እንዲሁም የፍትህና የዴሞክራሲ ተቋማት ተጠናክረው ሙሉ ሆነው እንዲገኙ ተመኝተን ነበር።
ግን ሥልጣን ላይ የነበረው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መራሽ የኢህአዴግ መንግስት ይህን ማስኬድ አልቻለም። ይህም የሆነው ካለፈው ስህተት መማር አለመቻል እና ተደጋጋሚ ስህተት መድገማችን ነው።
ስልጣን የህዝብ መሆኑን ዘንግተን ስልጣን ለግል ጥቅም ማዋል፣ ህዝብን ማዕከል ያደረገ ፖለቲካን ከመከተል ይልቅ የፓርቲ ፖለቲካን መከተልና እኛ እናውቅልሃን በሚል አስተሳሰብ ህዝብን በሚገባ ካለማዳመጥ የመጡ ናቸው።
ይህም በድህነት ማቅ ውስጥ እንድንቆይ፣ የህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት እንዲደርስ በማድረጉ ህዝብና መንግስት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ሆኗል።
አዲስ ዘመን፡– ዕድሎች እንዲያመልጡ ያደረ ገው ዋንኛ ምክንያት ምንድን ነው ?
አቶ አቡበከር፡- እኛ እንደ ሀገር የፖለቲካ ‹‹ሀ፣ ሁ›› የተረዳንበት አግባብ በጣም የተሳሳተ ነው። ፖለቲካ ህዝብን የምናገለልግበት መሣሪያ ነው። የህዝብ ጥቅም የሚከበርበት እንዴት፣ መቼ እና በምን መንገድ እንድምናስተዳድር የሚነግረን የሙያ ዘርፍ ነው። ይህን ሙያ ደግሞ ተግባራዊ የሚያደርጉት ፖለቲከኞች ናቸው።
ፖለቲከኝነት አገልጋይ መሪ መሆንን የሚጠይቅ ነው። ግን ፖለቲካ እንደ አቋራጭ መንገድ የግል መበልፀጊያና ሀብት ማከማቻ የስልጣን ጥም መወጣጫ የማድረግ አስተሳሰብ ነው ብዙ ጊዜ የተጠናወተን። ይህ ሁሉ ምስቅልቅል እየታየ ያለው ፖለቲካ እና ፖለቲከኞች ባለመለያየታቸው ነው። ስለዚህ ፖለቲካ ከፖለቲከኞች ነፃ ወጥቶ ፖለቲካ እንደ ሙያ ዘርፍ ብሎም እንደ ህዝብ ማስተዳደሪያ መሣሪያ መሆኑን ማወቅና መረዳት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ‹‹ፖለቲካ ከፖለቲከኞች ነፃ ይውጣ›› የሚለውን ሐሳብ ቢያብራሩልኝ?
አቶ አቡበከር፡- ፖለቲካ በራሱ ከፖለቲከኞች ነፃ መውጣት አለበት። ፖለቲከኞች ምን ዓይነት መሆን አለባቸው የሚለው መታወቅ አለበት። ፖለቲካ ላልተገባ ዓላማ፣ ለግል ጥቅም ማበልጸጊያ እና መበልፀጊያ መሣሪያ አድርገው በሚጠቀሙት እጅ ነው የወደቀችው። ስለዚህ ሙያው ነፃ መውጣት አለበት።
ይህ ካልሆነ እንደ አገር የህዝብን ችግር መረዳትና ለችግሩ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም። ህዝብ ማገልገል ትልቅ ክብር መሆኑን ብሎም ሙያው ትልቅ መሆኑ መታወቅ አለበት። ለህዝብ የሚበጅ ፖለቲካ መቅረፅና አገርን መምራት ከተቻለ ሌሎች አገራት እንደበለፀጉት ከፍ ማለት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማንም ሰው ዘው ብሎ የሚገባበት፣ የፈለገውን የሚጫወትበትና ህዝብን የሚጎዳበት ነው። ስለዚህ ፖለቲካው ከፖለቲከኞች ባርነት ነጻ መውጣት አለበት።
አዲስ ዘመን፡– በአገሪቱ የተጀመረውን አሁናዊ የፖለቲካ ለውጥ ከአፋር ክልል አኳያ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ አቡበከር፡- ወደ አፋር ክልል ከመሄዳችን በፊት መሃል አገር ዶክተር አብይ ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ አገሪቱ ከነበረችበት ጨለማ ወደተሻለ ብርሃን መሻገርና የተሻለ ተስፋ ጭላንጭል የታየበት ነው።
ውጭ አገር ተሰደው የነበሩ ፖለቲከኞች የተመለሱበት፣ ትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ አገር ቤት የገቡበት፣ ሚዲያ በፈለገው መንገድ የዘገበበት፣ ፖለቲካው ካለመረጋጋት ድባብ ወደ መስከኑ የገባበት፣ ከኤርትራ ጋር ከ20 ዓመት በላይ ከቆየው ጦርነት አልባ ግጭት የተላቀቅንበት፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አገራት ተርታ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ አንገታችንን ቀና አድርገን የተሻለ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የጀመርንበት ትልቅ አጋጣሚ ነበር።
ይህ ለውጥ ወደ አፋር ክልል የወረደበት ሁኔታን በግሌ ስመለከተው “Ethiopia in the wake of political reform” በሚል መፅሐፍ ውስጥ “Between hope and spade reflections on the current political development in afar” በሚል በሰፊው ተንትኛለሁ።
በመሃል አገር የተለኮሰው የተስፋው ችቦ እዚህ ትልቅ ተስፋ ጭሯል። ይህም አሁን ያለው የፖለቲካ ለውጥ በአፋር ክልል ላይ ያመጣውን የተስፋ ጸዳል በተመለከተ የሚዳስስ ነው።
በተለይ ታዳጊ ክልሎች የተወሰነ ፖለቲካ ኃይል እጅ በፈለጉት መንገድ የሚዘውሩት፣ በክልሉ ፖለቲካ ጣልቃ እየተገባ የሚፈነጩበት እና በተለይ አፋር ክልል ኋላ ቀር በሚል ስያሜ ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጠረበት፣ ክልሉ በሚገባ ያልለማበትና የተፈጥሮ ሃብቱ የመበዝበዝ ሁኔታ ነበር።
ስለዚህ አገሪቷ ላይ ያንዣበበው ደመና እና የተሰማው የለውጥ ነጎድጓድ እዚህ ያካፋል በሚል ትልቅ ተስፋ አጭሮ ነበር።
በወቅቱ የነበረው የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ስልጣን ላይ ነበር። እነርሱ ዕድል ተሰጥቷቸው ነበር። የለውጥ ጊዜ ደርሷል እና ራሳችሁን ለውጡ ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ መልዕክት ደርሷቸው ነበር።
ያን ችላ ብለው ነበር። ሆኖም ግን ጊዜው የደረሰ ለውጥ ማንም ስለማያቆመው ሳይወዱ በግድ ወደ ለውጡ ፊታቸውን አዙረዋል። በዚያን ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደረገው ጥሪ ራሳቸውን ፈትሸው እንደ ድርጅት የመጣው ለውጥ እንዴት እንቀበል ብለው መሄድ ነበረባቸው።
ይህን ማድረግ ሲያቅታቸው ወይንም መልካም ፈቃዳቸውን መግለፅ ሲያቅታቸው ለውጡ አስገድዷቸው ወይ ደግሞ በፖለቲካው የለውጡ ሃዋሪያ የሆኑ የፖለቲካ ‹‹ኤጀንቶች›› አራት ኪሎ ሄደው እራሳቸውን እዚያ ገምግመው በመጣው የለውጥ ባቡር እንዲሳፈሩ ተነግሯቸዋል።
በዚያም መሰረት እዚህ መጥተው ራሳቸውን ፈትሸው ህዝቡ እያሰማ የመጣውን የለውጥ ጥማት ጥያቄ እንዲመልሱ ታልሞ ጥረት ነበር። በጊዜው የአፋር ወጣቶች ‹‹ዱካሂና›› ሠላማዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነበር።
ለመጀመሪያ ጊዜ በ27 ዓመት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተናገሩበት ወቅት ነው። በወቅቱ እኔም ሆንኩ በርካቶች ደስተኞች ነበርን። ከዚያ በፊት አፋር ድምፁን የሚያሰማበት ዕድል ተነፍጎ ነበር።
ከዚያ ወዲህ የለውጡ አየር እየነፈሰ ሃያል እየሆነ ሲመጣ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ቁጭ ብለው ራሳቸውን እንዲፈትሹና ከለውጡ ጋር እንዴት መሄድ እንዳለባቸው ስብሰባ ተቀምጠው ነበር።
በወቅቱ 172 የሚሆኑ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ነባር አባላት በክብር ተሸኝተዋል። አፋር ክልል ውስጥ ትጥቅ ትግል ላይ የነበሩት ወደ ሰላማዊ መንገድ የመጡበትና የተስተናገዱበት፣ የአፋር ምሁራንና ወጣቶች ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉበት፣ የመሰላቸውን እንዲፅፉና እንዲናገሩ፣ እንዲደራጁ ዕድል ያገኙበት ነበር። የክልሉ ልዩ ኃይል ራሳቸውን ፈትሸውና ሪፎርም አድርገው ተጠያቂ የሚሆነውን ተጠያቂ አድርገው ይበል የሚያሰኝ ለውጥ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ያለው ሁኔታስ?
አቶ አቡበከር፡- አሁን ያወራነው ከነበርንበት ሁኔታ ተስፋ መሰነቅ መቻል፣ በነፃነት መናገርና መደራጀት፣ በተቃራኒ የተሰለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላማዊ መንገድ መንቀሳቀሳቸው ተስፋ የሚያጭር ነበር።
ግን ትልቅ ስህተት ተፈጠረ ብዬ የማምነው በወቅቱ የነበረው የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ራሱን በሚገባ ፈትሾ አልገመገመም።
የነበረበትን ችግር በሚገባ ነቅሶ ለውጡ ከሁሉ ነገር በፀዳ መንገድ መሆን ሲገባው አሁንም ተመልሶ ጭቃ የሚያደርገው ነገር ላይ ነው የወደቀው። አሁንም ቡደንተኝነት፣ አካባቢዊነት፣ ጎሰኝነት፣ በኔት ወርክ መደራጀት ፓርቲው የነበረውን የመሻሻል አጋጣሚና ዕድል እንዲመክን ሆኗል።
በክብር ተሰናበቱ የተባሉ 172 የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) አባላት የራሳቸው ቅርብ ዘመዶችና የአካባቢያቸው ሰዎች ቦታቸውን እንዲተኩዋቸው ተደርጓል።
ይህም በህዝቡ አገላለፅ ‹‹አንበጣው ሄዷል፤ ግን እንቁላል ጥሎ ነው የሄደው›› የሚል ነው የፈጠረው። እርግጥ አንበጣው ሄዷል። ራሱን በብዙ እንዲያበዛ ግን እንቁላል ጥሏል፤ መልሶ ይፈለፈላል።
የተፈጠረውን የፖለቲካው ሁኔታ መሸከም የሚችል ኃይል አልተፈጠረም። ትልቅ ዕድል ነበር የተፈጠረው።
ስለዚህ የመጣው ለውጥና ለውጡን አሜን ብለው የተሸከሙት አልተመጣጠኑም ማለት ነው። ከዚህ ወዲህ የተፈጠረው ፓርቲ ፖለቲካና ስልጣን የያዘ አካል እና በአዲስ አስተሳሰብ በዚህ ልክ ሆኖ ፍኖተ ካርታ ቀርፆ፣ እንደ አፋር ህዝብ እስካሁን የተመጣበት ጉዞ ምንድን ነው፣ ምን ጎደለ፣ ምን የተሻለ ነገር አለ ብሎ ማስኬድ አልተቻለም።
ይህን ህዝብ ወደ ብልፅግና ጎዳና ለማምጣት ያለበትን ነባራዊ ሁኔታና ተግዳሮት ለይቶ በዚያ አቅጣጫ መፍትሄ አስቀምጦ መሄድ አልተቻለም።
ስለዚህ የነበረው አስተሳሰብ ነው የቀጠለው። በበር የወጡ ሰዎች በመስኮት ነው የተመለሱት። በለውጥ ሥም እዚህም እዚያም የተቀመጡ ሰዎች አሉ። በዚህ የተነሳ የሚፈለገውን ለውጥ ማስመዝገብ አልተቻለም።
ያኔ ህዝቡን በተለያየ መንገድ ሲበድልና ሲበዘበዝ ነበር። በመሆኑም ሲታሰብ የነበረው በፖለቲካ ሙስና እና በሌላ እኩይ ተግባር የተሳተፉ የሚጠየቁበት፣ የህግ የበላይነትና ፍትህ የሚሰፍንበት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት የሚገነቡበት፣ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ምሁራን የሚሳተፉበት ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ቢታሰብም ይህ አልሆነም።
ይህም ያልሆነው ከምር ለህዝብ መስዕዋት ያለመሆንና ለውጡ የሚፈልገውን ያህል መራመድ ባለመቻላቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደ አገር ያለውን ለውጥስ እንዴት ይረዱታል?
አቶ አቡበከር፡– እንደ አገር የመጣው ትልቅ ዕድል ነው። ይህን ዕድል ስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ተዋናዮች የፖለቲካ ስልጣን ከመያዝ ባሻገር ሀገረ መንግስቱን እና ብሄረ መንግስቱን መገንባት መሆኑ ታውቆ የአገሪቱን ዕጣ ፋንታ መወሰን ላይ ትኩረት አልተደረገም።
ስልጣን ላይ የነበረው ቡድን መቐለ ሄዶ ከመሸገ በኋላ የለውጡ ጀልባ ተሳፋሪዎች ተረጋግተው እንዳይሳፈሩ እዚህም እዚያም ቀዳዳ በመፍጠር ጀልባው እንዲሰጥም የራሳቸውን ጥረት አድርገዋል።
የፖለቲካ ኃይሎችም ስልጣን ከመያዝ ባሻገር ትልቁን ምስል ማየት ባለመቻላቸው ዛሬ እርስ በእርስ የመገዳደል፣ የመፈናቀልና የመቆራቆስ ችግሮች እንዲፈጠሩ ሆኗል።
በእርግጥ ዕድል ሳይሰጥ ቀርቶ አይደለም። ግን ሰከን ብሎ በማሰብ ያለነው የት ነው፣ ወዴት እንሂድ? የተሻለች ኢትዮጵያን በጋራ እንዴት እንፍጠር በሚለው ላይ መሥራት ባለመቻሉ ነው።
ሆኖም የመጣው የለውጥ ኃይል አገሪቱን የማስተዳደር፣ በየቦታው ብቅ የሚሉ ግጭቶችን የመፍታትና አንዳንድ ጉዳዮች ማስተንፈስ ላይ ነው ያተኮሩት። መሆን የነበረበት የተረጋጋ ሁኔታ ኑሮ በመመካከር የጋራ አገር ስለሆነች ምን ይበጃል፣ ከታሪክ ስህተት ምን እንማር፣ ወደፊት ለመቀጠል የጋርዮሽ ታሪክ ላይ በማተኮር እንዴት እንሻገር የሚለው ላይ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ከክልልና አገር አኳያ ችግሮችና ተስፋዎች እነዚህ ከሆኑ በምሥራቅ አፍሪካ እንደመገኘታችን የኢትዮጵያ ተስፋና ተገዳዳሪ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
አቶ አቡበከር፡- ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና የአፍሪካ ቀንድ ለግጭት የተጋለጠ፣ የአካባቢ መራቆት ያለበት፣ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች የበዙበት ነው። ይህ አካባቢ የውስጥና የውጭ ፈተናዎች የበረከቱበት ነው። ቀጣናውን ለመቆጣጠርና ያለውን ሃብት ለመቀራመት የሚፈልጉ በርካታ ኃይሎች ሽኩቻ የፈጠሩበትና የሰፈሩበት ነው።
በዚህም እጅግ በጣም ለግጭት የተጋለጠ ቀጣና ነው። በዚህ ቀጣና እንደ አገር ኢትዮጵያ ትልቅ ድርሻ አላት። እኛ ተረጋግተን በራሳችን ጉዳይ ላይ አተኩረን የመጣውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን የተሻለች አገር ለመመስረት በምናደርገው ጥረት እነርሱ ካላቸው አካባቢያዊ ፍላጎት አኳያ አሉታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡– እነዚህ አገራት እንቅስቃሴና ፍላጎታችው ከኢትዮጵያ ጥቅም አኳያ እንዴት ይመዘናል?
አቶ አቡበከር፡– በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል። አንደኛው ይህ አካባቢ ለዓለም አቀፍ ሠላምና ደህንነት ትልቅ ሚና አለው። በተለይ ቀይ ባህር አካባቢ የዓለም ትልቁ የንግድ መስመር ነው። በቢሊዮኖች ዶላር በቀን ይዘዋወርበታል።
አንዳንድ አገራት የራሳቸውን ዓለም አቀፍ ንግድ ከግምት ውስጥ በማስገባትና በቀጣናው የሚፈጠሩ አለመረጋጋቶችን እንደ መነሻ ምክንያት በማድረግ ወደ ቀጣናው እየተጠጉ ነው።
ወደ ጅቡቲ ብንሄድ 10 የሚጠጉ አገራት ወታደራዊ መሠረት ጥለዋል። ዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶች የራሳቸውን የወታደር ቤዝ መስርተዋል። አሜሪካ፣ ቻይና፣ ጃፓን እና ሌሎች ኃያላን አገራት የአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ብሎም አካባቢው ለዓለም አቀፍ ፖለቲካ ወይንም በጂኦ ፖለቲኪስ ሁኔታ ብሎም ጂኦ ስትራቴጂ ጠቃሜታ አኳያ አካባቢውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፍላጎት ይስተዋላል።
ከፍ ስንል ደግሞ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በተለይም የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ ለመበልፀግ በምታደርገው ጥረት ግብፅ በውስጣዊ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት በማስታጠቅና በመደገፍ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት እንዳትጠቀም የራሷን አፍራሽ ሚና እየተጫወተች ነው።
በዚህም የዓለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ብድር ቢከለክሉም ኢትዮጵያ ደግሞ በዓባይ ጉዳይ ቆራጥ አቋም ይዛለች። ይህ ያሰጋቸው አካላት በኢትዮጵያ ላይ እያሴሩ ነው። እርስ በእርስ መገዳደል፣ አለመረጋጋት፣ መፈናቀል፣ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርና በመሳሰሉት እኩይ ተግባራት ላይ አጥፊ ኃይሎችን መደገፍና አለፍ ሲልም በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የመፍጠር ሁኔታዎች አሉ።
ሆኖም መንግስት ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለማገባደድ እጅግ ቆራጥ ውሳኔ መውሰዱ ተገቢ ነው። ከጩኸት የዘለለ ሚና እንደማይኖርም መገንዘብና ጥንቃቄም ማድረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– በእርስዎ አገላለፅ እነዚህ ኃያላን አገራት በአንድ ፊት ቀጣናውን ይፈልጉታል። በሌላ ደግሞ ሽኩቻ በመፍጠር ትርምስ መፍጠራቸው ነገሮችን ተፃራሪ አያደርጋቸውም?
አቶ አቡበከር፡- በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ስናይ አገራት ሁሌም ጥቅማቸውን ነው የሚያከብሩት። ለዚህም ሽኩቻ አለ፤ ግን ደግሞ ተደጋግፎ መስራት ይቻላል። በቀይ ባህር አካባቢ የመን የወደቀች አገር ናት። የመን ላይ የገልፍ አገራት ፍላጎት አሳይተዋል።
ኢራን እዚህ ፍላጎት አላት። በዚህ አገር ጦርነት የሚካሄደው በምድር ብቻ ሳይሆን በመርከብና በጀልባ ነው። ሶማሊያን ጨምሮ በዚህ አካባቢ ያለው የባህር ላይ ውንብድና ተጨምሮ በሰላማዊ መንገድ መፍታት እየተቻለ መሰል ግጭት የሚታየው ለዚህ ነው።
በጦርነቱ አትራፊዎች አሉ። ለምሳሌ የመን ውስጥ ተከፋፍለው በሚያደርጉት ጦርነት የጦር መሳሪያ በከፍተኛ ደረጃ የሚሸጡ አሉ።
ሳውድ አረቢያ እና የገልፍ አገራት ከኃያላን አገራት መሳሪያ በገፍ ይገዛሉ። ይህ የአደባባይ ሚስጥር ነው። በመሆኑም ኃያላን አገራት የሚያሳዩት የፖለቲካ እና የምጣኔ ሃብት ሽኩቻ አለመረጋጋት እንዳይኖር አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡– የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በተለይ በጀቡቲ ወደብ አካባቢ የኃያላን አገራት ትርምስና ፍላጎት ከፍ ያለ ነው። የጅቡቲ ወደብ ደግሞ ለኢትዮጵያ የወጭና ገቢ ምርቶችን ዋነኛ መስመር መሆኑ ስጋት ላይ አይጥላትም?
አቶ አቡበከር፡- በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሲታይ ሁለት ነገሮች አሉ፤ እነርሱም ግጭት እና መተባበር ናቸው። ግጭት እዚህም እዚያም ይፈጠራል። አገራት በዓለም አቀፍ ህግ ተገናኝተው ጥቅማቸውን የሚያስከብሩበት ሁኔታ አለ።
ኢትዮጵያም እንደ አገር በዓለም አቀፍ ህግ የሚፈቅድላት መብት አላት። ቀይ ባህርን የመጠቀም ብሎም ሳይንሳዊ ጥናት የመፍጠር፣ የንግድ መስመርና የወደብ ግልጋሎት ማግኘት መብት አላት።
ዋናው ነገር የውስጥ አቅምን ማጠናከርና መቆራቆሱ እልባት ሊሰጠው ይገባል። ኢትዮጵያውያን አቅማችን አጠናክረን በዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሚናችን መጉላት አለበት። ወጣቶችን መሸከም የሚችል ኢኮኖሚና ተፅዕኖ የሚፈጥር ዓለም አቀፍ ፖሊሲ መከተል ይገባል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በመሳሰሉት ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ማደግ አለበት።
በቀጣናውም ያለን ሚና እየጎላ መሄድ አለበት። በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ ስጋት አስወግዳ ጥቅሟን ማሳደግ ትችላለች። በተረፈ ግጭት ሊቀር የሚችለው መቃብር ውስጥ ብቻ ነው። በመሆኑ የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ እንቅስቃሴዎች መደረግ አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ቀጣይ ፈተናዎች እና መልካም አጋጣሚዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
አቶ አቡበከር፡- ከተፈጥሮ ሃብቷ የሚመነጩ ፈተናዎች አሉ። ዓባይን ለመጠቀም የሚደረገውን ጥረት ጨምሮ ፈተና ነው። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ወንዞችን መጠቀም ብንፈልግ እንኳን ጎረቤት አገራት አይፈቅዱም።
በቀጣናው ያለው የኮንትሮባንድ ንግድና ከበስተጀርባ ያሉ ኃይሎች፣ አክራሪነት፣ ከጎረቤት አገራት አኳያ የበላይ የመሆንና የመሬት ይገባኛል ፍላጎት፣ በቀጣናው የራሳቸው ፍላጎት ያላቸው ኃያላን ሀገራት መስፋፋት ለኢትዮጵያ ቀጣይ ፈተናዎች ናቸው።
አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ የመበታተንና የባይተዋርነት ስሜት ይስተዋላል። በመሆኑም ሁሉን አሳታፊ የሆነ ፖለቲካ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀትና ሰጥቶ በመቀበል መርህ ብሎም ከታሪክ ተምሮ ስህተት የማረም ፍላጎት ካለ በርካታ ዕድሎች አሉ።
ይህ ከሆነ የተሻለ አገር መንግስት የመመስረት ዕድልም ይኖራል።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታና ሙያዊ ማብራሪያ አመሰግናለሁ።
አቶ አቡበከር፡– ለአገራችን ህልውና እና ቀጣይ ዕድገት ሁላችንም ኃላፊነታችን ልንወጣ ይገባል የሚል መልዕክት አለኝ። እኔም ስለአብሮነታችን አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 07/2013