ምህረት ሞገስ
በሃይማኖት ተገርቶ ባደገ ማህበረሰብ ውስጥ፤ ማህበረሰብ ብቻ አይደለም፤ በሃይማኖት ውስጥ በኖረ ህዝብ ዘንድ ቤተ ዕምነትን ማቃጠል የብዙዎችን ስነልቦና የሚጎዳ እና ትልቅ የሞራል ድቀት የሚያስከትል መሆኑን ጠያቂ አያሻም።
ቤተ እምነት በየትኛውም ጊዜ በማንኛውም ሁኔታ መቃጠል የለበትም ሲባል፤ ጉዳዩ እጅግ ከባድ ወንጀል ከመሆኑ ጋርም የተያያዘ ነው።
ወንጀሉ ከተፃፈ ህግ ባሻገር በሰዎች ህሊና ውስጥ ካለው የሰብዓዊነት የጋራ ባህሪንም የሚፃረር በመሆኑም ጭምር ነው።
ቤተ እምነት የሰዎች ስጋ ብቻ ሳይሆን የነፍስ ምግብ የሚገኝበት ስፍራ ነው።የድርጊቱ መፈፀም የሚቆጠረው የሰብዓዊ መብትን ከመግፈፍ አንፃር ጭምርም ነው። ይህ በመሆኑ ምንም እንኳ በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ተቋማት ሲቃጠሉ፤ በጦርነት ውስጥ ሳይቀር ቤተ እምነት አይቃጠልም።የጥቃት ሰለባ የሚሆንበት አጋጣሚም ውስን ነው።
ይህ ቢሆንም ቅሉ በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያየ መልኩ ቤተ እምነቶች ተቃጥለዋል።
በሶማሌ ክልል ከሁለት ዓመት በፊት የታየው የቤተክርስቲያን ቃጠሎ፣ በኦሮሚያ ጅማ እና በሌሎች አካባቢዎች አልፎ አልፎ ታይቷል።
በተጨማሪ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን መስጊዶች ላይ የተፈፀመው ጥፋት እና መስኪዶችን የማቃጠል ሂደት የሚዘነጋ አይደለም።ተደራጅቶ ቤተ ዕምነትን የማጥቃት ጉዳይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በአላባ ከተማ በፕሮቴስታንቶች ቤተ እምነት ላይ ቃጠሎ ነበር፤ በሶማሌ ክልል በቤተክርስቲያናት ላይ የደረሰው ውድመትም ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።
ይህ ተግባር እጅግ የሚወገዝ ከመሆኑም ባሻገር ወንጀሉ እንዳይፈፀም አጥፊዎችን ለህግ የማቅረብ ዕርምጃው የተጠናከረ ሊሆን ይገባል።
ይህንን ችግር በህብረተሰብ ተሳትፎ እና በፀጥታ አካላት ርብርብ ለመከላከል ጥረት ቢደረግም፤ አሁን ደግሞ እንዲሁ በህውሓት ጁንታ ቡድን የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ህግ ለማስከበር ዕርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ ጁንታው በተለያየ መልኩ ቤተ እምነቶች እንደመሸሸጊያ በመቁጠር እንዲጠቁ አድርጓል።እርሱም ሆን ብሎ ቤተ እምነትን ለማጥፋት በሚል ጥቃት ሰንዝሯል።
በጦርነት ወቅት መሳሪያ ታጥቀው ውጊያ ያልገጠሙ ንፁሐንን ማጥቃት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጠን የሰብዓዊ መብት ህግን የሚጥስ ሲሆን፤ የእምነት ቤቶችን ማቃጠልም በተመሳሳይ መልኩ ትልቅ የሰብዓዊ መብት የህግ ጥሰት መሆኑ በዓለም ህግ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል።
እ.ኤ.አ በ1977 ዓ.ም የጸደቁት የጀኔቫ ኮንቬንሽን ፕሮቶኮሎች በንጹሐን ሰዎችና የጦርነቱ አካል ባልሆኑ ነገሮች ላይ ጉዳት ማድረስ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋትን መጻረር መሆኑን አስቀምጧል።
የጦርነቱ አካል ያልሆኑ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ በጦርነቱ ውስጥ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌላቸው ናቸው።እነዚህም ባህላዊ ስፍራዎችና ዕቃዎች፣ የእምነት ተቋማት፣ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ውሃ፣ መብራት፣ ግድብ፣ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የመሳሰሉት ናቸው።
በመሆኑም እነዚህ ተቋማት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ በጦርነት ወቅት ለእነዚህ ነገሮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግና የጦርነት ዒላማ እንዳይሆኑ አጥብቆ ያስገነዝባል።
የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ በአንቀጽ 270 ሥር በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ወንጀል መሆኑን ደንግጓል።በሕጉ መሰረት በጦርነት፣ በጦርነት ግጭት ወይም በጠላት ወረራ ጊዜ የዓለም አቀፍ ሕግ ድንጋጌዎችን በመጣስ በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ በማደራጀት፣ በማዘዝ ወይም ድርጊቱን በመፈጸም ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ታሪካዊ ሐውልቶችን፣ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ወይም የማምለኪያ ቦታዎችን ማውደም፣ መውሰድ፣ ከጥቅም ውጪ ማድረግ፣ ለራስ ማድረግ ወይም እነዚህን ነገሮች ለወታደራዊ ዓላማ ማዋል በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሚፈጸም የጦርነት ወንጀል በመሆኑ በከባድ ቅጣት ያስቀጣል።
እነዚህ የጦርነት አካል ያልሆኑ ነገሮች የሚባሉት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግጋት እና የአገራችንን የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች መነጽርነት በመታገዝ ህወሓት በአል-ነጃሺ መስጂድ እና በአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት ላይ የፈጸመውን ድርጊት ስንመለከት በእርግጥም እነዚህን የአምልኮ ቦታዎች ለወታደራዊ ዓላማ ሲጠቀምባቸው ነበር።
በመሆኑም እነዚህ ወንጀሎች እንዲፈጸሙ ያደራጁ፣ ያዘዙ፣ ወይም ድርጊቱን የፈጸሙ በማናቸውም መንገድ ተሳትፎ ያደረጉ ሁሉ መንግሥት ለፍትህ ሊያቀርባቸው ይገባል።
እነኚህ አካላት በሃይማኖት ተቋማት ላይ የፈፀሙት ወንጀል ሲጠቀስ በጦርነቱ ወቅት ብቻ የነበረው በእነርሱ ስለመፈፀሙ ይጠቀስ እንጂ፤ ከጦርነቱ በፊት በተለያየ መልኩ ሲገለጽ እንደነበረው የእምነት ተቋማት ለጥቃት የተጋለጡት በእነኚሁ በህውሓት ጁንታ አባላት ታዞ እና ተቀናብሮ እንደነበር ይነገራል።
የጁንታው ቡድን ለእምነትና ለሀገራዊ ባህሎችና ወጎች ግድ የሌለው አካል በመሆኑ ከጥንስሱ ጀምሮ የእምነት ተቋማትን ለጦርነት ዓላማ ሲጠቀምባቸው መቆየቱን የሚያመላክቱ የተለያዩ ማስረጃዎች አሉ።
ስልጣን በያዘባቸው ባለፉት 27 ዓመታትም የሃይማኖት እሴቶች እና መርሆች እናዳይከበሩና ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ እንዳይሆኑ በርካታ ሴራዎችን ሲሸርብ ኖሯል።
ቤተእምነቶች ውስጥ የራሱን የፖለቲካ አጋፋሪ በመሾምና በተለያዩ አካባቢዎችም በተላላኪዎቹ አማካኘነት ቤተእመነቶችን በማቃጠልና በማውደም በርካታ ጥፋቶችን ሲሠራ ኖሯል።
የተለያዩ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ ቢጠይቅም፤ በአገሪቱ በስፋት እነኚህን የመሳሰሉ ተቋማት በተለያዩ ክልሎች አደጋ ላይ እንዲወድቁ እና እንዲቃጠሉ የተፈፀመው ወንጀል ተጣርቶ አጥፊዎች ለፍርድ ይቀርባሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
አሁን የተጀመረው የህግ ማስከበር ሂደትም አንዱ ትኩረቱ ባለፉት 27 ዓመታት እንዲሁም በቅርቡ በተለያዩ አካባቢዎች በሃይማኖት ተቋማት ላይ የደረሱንት ጥቃቶች በማጣራት አጥፊዎች የህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 07/2013