አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ አመለካከትን በሰላማዊ ውይይት የመለዋወጥ ልምድን ለማሳደግ የሚያግዝ የተለያዩ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ትናንት ተካሂደ፡፡
በመድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የቀረበውን ጨምሮ አራት የጥናት ወረቀቶች ተስተናግደዋል፡፡ የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች የተገኙበት ሲሆን፤ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ መርተውታል፡፡ ውይይቱ የትኛው ተፎካካሪ ፓርቲ ይሻላል ወደሚል ክርክር ውስጥ ለመግባት ሳይሆን ሜዳው የተስተካከለ እንዲሆን የሁሉም አስተዋፅኦ ምን መሆን አለበት? በሚል የተዘጋጀ መሆኑም ከመነሻው ተገልጿል፡፡ መድረኩ በለውጡ ሂደት ለሰላምና መረጋጋት የሁሉም ርብርብ አስፈላጊ በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሰባስበው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ማዘመን እንዲችሉ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
በመድረኩ በኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ምን ይመስላል? በምን መልኩስ ይመለሳል? በሚል ዶክተር አረጋዊ በርኸ ያቀረቡት የጥናት ወረቀት አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና በኢትዮጵያ ምን መምሰል አለበት? እንዲሁም ዶክተር መረራ ጉዲና ፌዴራሊዝም ላይ ያተኮረና በመጨረሻም ዶክተር ዐብይ አህመድ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የፖለቲካ ባህል ዙሪያ የጥናት ወረቀት አቅርበዋል፡፡
ዶክተር ዐብይ፤ በ1953 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፖለቲካ የዴሞክራሲ ሃሳብ እንደ ጥንስስ መጀመሩንም አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፖለቲካ ባህሉ ከራስ አልፎ ሌሎችን ወደማሳመንና ገንቢ ክርክር ወደማድረግ ከፍ አለማለቱን አንስተዋል። ትርጉም ያለው ዴሞክራሲን ለመገንባትም ትክክለኛው አካሄድ በተለያዩ የፖለቲካ መስመሮችና እሳቤዎች ውስጥ በተቀናጀ መልኩ መስራት ነው፡፡ በመሆኑም ስለትናንት በመውቀስ ዛሬን ከማበላሸት በእጅ ላይ ያለውን ዛሬን በመተባበር መልካም ነገር በመሥራት ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት አገር በመሆኗ አትበተንም ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ያስተሳሰሩ ገመዶች ለሺህ ዓመታት ሳይበጠሱ የዘለቁ ናቸው፡፡ የነበረውን አንድነት ለማስቀጠልም የኋላ ታሪክን አውቆ ነቅሶ ማውጣትና መሄድ ይገባል፡፡ በቀጣይም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ስለዴሞክራሲ ያለው አተያይ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ፤ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህልን በኢትዮጵያ ለመገንባት የፖለቲካ ምህዳሩ አካታች መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚስፈልግና በዚህም ሂደት ሁሉም ተዋናዮች የመንግሥትን አቅም ለማጠናከር መንቀሳቀስ ብሎም መተማመንን ለማጠናከር መስራት እንደሚጠበቅባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ተሳታፊዎች በበኩላቸው ውይይቱ ገንቢ በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ፍዮሪ ተወልደ