አሊ ሴሮ
አምባገነኖች ያሳዝኑኛል። ሲለቋቸው አንደተራራ ይኮፈሳሉ፤ ሲይዟቸው ደግሞ ጭብጥ አይሞሉም።
ቀድመው የተዋረዱ በመሆናቸው ውርደት ብርቃቸው አይደለም። ከቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ተጎትተው ሲወጡ፤ በወጣትነታቸው የዘለሉትን ገደል ዛሬም እዘላለሁ ብለው ወድቀው ሲሰበሩ፤ ከሞቀና ከተንደላቀቀ ኑሮ በወራት ውስጥ ወርደው የአደፈ ልብስና የጨቀየ ሰውነት ይዘው ሲታዩ ሌሎችን ቢያሸማቅቅም እነሱ ግን ደንታ የላቸውም።
ቀድሞ የተዋረደ ስብዕና ያላቸው በመሆኑ እነሱ ማፈር ሲገባቸው እኛ አፈርንላቸው፤ አዘንላቸውም። ሳያት ታሳዝነኛለች ያለው ዘፋኝ ማን ነበር?
አምባገነኖችና ፈሪዎች ብዙ ያወራሉ። ወሬያቸውን ድርጊታቸው ግን ለየቅል ነው። ጀግኖች እንደሆኑ፤ ጦርነት ማለት ለእነሱ ባህላዊ ጨዋታ መሆኑን ሲናገሩ አፋቸውን ወለም ዘለም አይላቸውም። ከሁለት ወር በፊት አንድ የጁንታው አፈቀላጤ አሜሪካ ተቀምጦ ጦርነት ማለት ለእኛ ባህላዊ ጨዋታችን ነው ሲል ጦርነት ማለት የሰውን ህይወት የሚቀጥፍ ንብረት የሚያወድም መሆኑን ረስቶት እርሱ የሚያላዝንላቸው ሰዎች የማይሸነፉ እና የማይያዙ መስሎት ነበር።
ለካ ይህ አፈቀላጤ ቀባጣሪ እንኳን ጦርነትን የገና ጨዋታን በአግባቡ ተጫውቶ እንደማያውቅ ደረስኩበት።
ጦርነት አሜሪካ ቁጭ ብሎ በርገር እየገመጡ ኮምፒዩተር ላይ ጌም እንደመጫወት ቀላል መስሎት ነበር።
ጦርነት ማለት ሀገር አውዳሚ፤ የሰዎችን ነፍስ የሚቀማ፤ እንደወዳጆቻቸው ከሞቀ ኑሮ አስወጥቶ የዝንጀሮ ገደል የሚያዘልል፤ ከሰውነት ጎዳና የሚያስወጣና ጣዕረ ሞት የሚያስመስል ክፉ ነገር ነው። አለፍ ሲል ቀሚስ ለብሶ እግሬ አውጪኝ የሚያስብል ክፉ ደዌ ነው።
ይሄንን አፈቀላጤና መሰሎቹን ግን ታዘብናቸው። አሜሪካ ተቀምጠው፤ ‹‹ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው›› እያሉ ምቾታቸው ሳይጓደል፤ ሊሞዚን እየነዱ እና በቅንጡ ቤት እየኖሩ የድሃውን ልጅ በጦርነት ማገዱት።
የእነርሱ ነፍስ ከሌላው የድሃ ነፍስ የበለጠ እንደሆነ ስለሚያምኑና ሌላው እየሞተላቸው የተንደላቀቀ ህይወታቸውን ማጣጣም ስለሚፈልጉ እሳት ጭረው ገሸሽ ማለት ያውቁበታል። ምን በወጣቸው ይሞታሉ የድሃ ልጅ ይሙት እንጂ።
ደግሞ እኮ! እንኳን አስተሳሰባቸው አነጋገራቸው አይለያይም። አቤት ይሄኔ ምን እያሰቡ ይሆን? እንደው ምናልባት ይህን ፅሁፍ ካገኙት የምላቸው አለኝ።
‹‹ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው›› ላለው እና ፤‹‹ጦርነትን መስራትም ማፍረስም እንችላለን›› ብሎ ሲደሰኩር የነበረውና ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ቅድሚያ ለራስ ብሎ ወደ አሜሪካ ላሽ ያለው። ይህኛው የአወራውን አውርቶና ወጣቱን አነሳስቶ እሱ አሜሪካ ቦስተን አለሙን እየቀጨ መሆኑን ሰምቻለሁ።
ግን የአምባገነኖች ቃልና ተግባር የሚገናኘው መቼ ይሆን? እኛ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው፤ ጦርነትን መስራት፤ ማፈረስና መበተን እንችላለን ስትሉን እኮ አምነናችሁ ድል አድርጋችሁ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ይገባሉ ብለን አስበን ነበር።
ምነው አስራ አምስት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተሸመደመዳችሁ? ቢያንስ እንዳላችሁት ባታሸንፉም በወጉ መሸነፍ እኮ የአባት ነው። ሸህ ሁሴን ጅብሪል እንዳሉት በአስራ አምስት ቀን በናችሁ ጠፋችሁ እኮ ።
በሞቴ ፤ያ ‹‹በመብረቃዊ ምት›› መከላከያን አጥቅተን ድል እንቀዳጃለን ብሎ ሲፎክር የነበረውን አፈቀላጤ እረሳሁት እኮ። ቢረሳ ቢረሳ መብረቃዊ ምቱ ይረሳል እንዴ? ደግሞ የሚገርመው ተናግሮ ሳይጨርስ እራሱ በለኮሰው መብረቃዊ ምት አፈር መልበሱ ነው።
ግን አፈሩን ገለባ ያድርግለት፤ ነፍስ ይማር ይባል ይሆን እንዴ? በገዛ እጃችሁ ወግና ባህላችንን ስላጠፋችሁብን ለአሁኑ ይዝለለኝ።
መብረቃዊ ምታችሁን ካነሳሁ ላይቀር አዲስ አበባ ቶሎ እንገባለን ስትሉን ደጋግማችሁ እንደምትነግሩን ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችሁ ስለሆነ ጀብድ ሰርታችሁ፤ ገላችሁና ማርካችሁ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ስትሉ ሀገሪቱን መልሳችሁ የምትገዟት መስሎን ነበር።
ለካ የእናንተ ቅኔ አያልቅምና አዲስ አበባ መሰስ ብላችሁ ለመምጣት ያሰባችሁት ከቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ተጎትታችሁ፤ ከዝንጀሮ ገደል በሸክም ታዝላችሁ፤ ከሰው ተራ ወጥታችሁና ተጎሳቁላችሁ የፊጥኝ ተይዛችሁ እንደምትመጡ መች ገባንና።
እነዚህ ሰዎች ከምድር ላይ ከመጥፋታቸው በፊት ሊጠኑ ይገባል ያለው አዋቂ ሰው ማን ነበር? እውነቱን ነው። ባህሪያችሁ ከኢትዮጵያውያን የማይገጥም፤ ወግና ልማድ የማታውቁ፤ ሰብዓዊነት ያልፈጠረባችሁ ንቅሎች ናችሁ።
በሰላም ተንደላቃችሁ የዘረፋችሁትን ገንዘብ እየበላችሁ፤ ሲያሻችሁም ሰልጣን ተቆናጣችሁ፤ አልያም በረጅሙ እጃችሁ ነግዳችሁ ኑሩ ተብላችሁ ስትለመኑ አሻፈረኝ ብላችሁ ቀሪ ህይወታችሁን ወህኒ ለማሳለፍ ተመኛችሁ። እናም ይሄ እንቆቅልሽ ያልተጠና ምን ይጠናል።
እኔም ዕድሉን ከሰጣችሁኝ ያቋረጥኩትን ትምህርቴን በመቀጠል የመመረቂያ ጽሁፌን በእናንተ ላይ ለመስራት አስቤያለሁ። በርታ በሉኝ።
ስለእናንተ ሳስብ የኢራቁ መሪ ሳዳም ሁሴንና የሊቢያው ሙአመር ገዳፊ ድቅን አሉብኝ። አንዱን አምባገነን ከሌላው የሚያመሳስለው አንዱ ከአንዱ ውድቀት መማር አለመቻሉ ነው ያለው ምሁር ሃሳቡ አሁን ገና ገባኝ።
እናንተ በስልጣን ላይ እያላችሁ ሳዳም ሁሴን ከአዛዥ ናዛዥነታችው፤ ከቅንጡ ህይወታቸውና ከብረት ከጠነከረ አመራራቸው ተሽቀንጥረው አንድ ስርቻ ውስጥ ተወሽቀው ሲገኙ ነግ በኔ ብላችሁ አልተማራችሁም።
ጋዳፊም ቢሆኑ ከሊቢያ አልፈው የአፍሪካ መሪ ነኝ ብለው ሲመጻደቁ የአርባ ዓመታት ስልጣን ዘመናችው አልበቃ ብሏቸው የሊቢያ ዘላለም መሪ ነኝ ብለው ሲመጻደቁ ቆይተው በናንተው ስልጣን ዘመን ወቅት በህዝብ አመጽ ተሽቀንጥረው ቱቦ ውስጥ ተወሽቀው ተገኙ።
እናንተም ከቢጤዎቻችሁ መማር ባለመቻላችሁ ለ30 ዓመታት ቀጥቅጣችሁ ከገዛችኋት ሀገር በህዝብ አመጽ ተሽቀንጥራችሁ ተጣላችሁ። እንደልባችሁ ስትመነዝሯትና ስታስመነዝሯት ከነበረችው ጥገት ላም በሃይል ተመንጭቃችሁ ጥጋችሁን ያዛችሁ።
በመጨረሻም እንደሳዳምና ጋዳፊ ጺማችሁ ጎፍሮ፤ አድፋችሁና ተጎሳቁላችሁ ጉድባ ውስጥ ተወሽቃችሁ ተገኛችሁ። ሁኔታችሁን ላይ አይ ሰው ከንቱ ያስብላል።
የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት የተከበሩ ሙስጠፌ እንዳሉት የማትወዷትን ሀገር የመራችሁ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ናችሁ። ለማትወዱትና ለማይወዳችሁ ህዝባችሁ ስትሉ ዴሞክራሲን ለማስፈን ብዙ ባተላችሁ። ዓለም ባይቀበለውም የ11 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ እንቅልፍ አጣችሁ።
ምን ቸገራችሁ? ሌላው ባያድግም እናንተ ከ1ሺ በመቶ በላይ አድጋችኋል። የ11 በመቶውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያደናቅፉና እየተሳለጠ የነበረውን ዴሞክራሲ የሚጎትቱ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰዳችሁ በሰብአዊ መብት ቢያስተቻችሁም እናንተ አትሳሳቱምና እኛም አሜን ብለን ተቀብለናል።
ጥፍር ብትነቀሉም፤ በጨለማ ቤት ብታጉሩም፤ ከአውሬ ጋር ብታስሩም፤ ቶርች ብታደርጉም፤ የሰው አካል ብታጎድሉም፤ በታንክ ብትደፈጥጡም፤ በሲኖትራክ ብትጨፈልቁም፤ በጅምላ ብትቀብሩም ለልማትና ዴሞክራሲ መሳለጥ ነውና ደግ አደረጋችሁ።
አንድ የህግ ሰው ግን ‹‹የጁንታው ቡድን አባላት የወንጀል ቡፌ ነው ያነሱት›› የሚል ስም ማጥፋት የሚመስል ሃሳብ ሲሰነዝር የሰማሁ መሰለኝ።
አሁን እናንተ በዚህ የምትጠረጠሩ ናችሁ? እሬሳን ልብስ አስወልቆ በጸሃይ ከማቃጠልና አልፎም የጅብና የአሞራ እራት ከማድረግ ውጪ ሌላ ምን ሰራችሁ? ማይካድራ ላይ ሰዎችን በማንነታቸው ከመጨፍጨፍና በጅምላ ከመቅበር ውጪ ምን ሃጢያት ፈጸማችሁ? ሰዎች በዘርና በሃይማኖት እንዲጫረሱ ከማድረግ ውጪ ምን አደረጋችሁ? ጡት ከመቁረጥ፤ ከማኮላሸት እና ሀሺሽ ከመነገድ ውጪ ምን የህግ ጥሰት ፈጸማችሁ?
የሀገርን ጥቅም አሳልፋችሁ ከመስጠት ውጪ ምን አደረጋችሁ? ቢሊዮን ብሮችን በማሸሽ ሀገርና ህዝብ በዕዳ እንዲዘፈቁ ከማድረግ ውጪ መቼ ትውልድና ሀገርን በደላችሁ? ደጋፊዎቻችሁ እንደሚሉት ዝም ብሎ የየዋህ ሰዎችን ስም በየአደባባዩ ማጥፋት ተገቢ አይደለም። ሰይጣን በዕድሜ እንጂ በተንኮል አይበልጣቸውም የሚሉ የፌስ ቡክ ቀበኞችን ደግሞ አትስሟቸው።
ምነው ዝም አላችሁ? ድምጹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትራችን መለስ ዜናዊ፤ ይቅርታ ሚኒስትራችሁ ያልተሰማ ታጋይ እንደሞተ ይቆጠራል በለው ነበርኮ።
አሁን እንደዚህ ዝምታ ውጧችሁ፤ ደንዝዛችሁ፤ ወኔ ከድቷችሁና በካቴና ታስራችሁ ቢያይዋችሁ ለፊልም ቀረጻ እየተወናችሁ እንጂ የምራችሁን እንዳልሆነ መገመታቸው አይቀርም። እንኳን ይህንን ጉዳችሁን አላዩ።
ምነው ቆፍጠን በሉ እንጂ ማስገደል እንጂ መሞት አያውቁም ለሚሏችሁ ሟርተኞች እራሳችሁን አጋልጣችሁ አትስጡ እንጂ።
ደግሞም እኮ ጀግንነት እየተመረጠ የታደላችሁ መሆኑን 27 ዓመት ስትነግሩን ቆይታችሁ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ ውሃ የገባች አይጥ መምሰላችሁን አልወደድኩትም።
በነገራችን ላይ በእናንተ የሚጨክን አንጀት የለኝምና ቃሊቲ ከወረዳችሁ ከአራዳ ልጆች ጋር መገናኘታችሁ አይቀርምና እስኪ ጥቂት በአራዳ ቋንቋ እናውጋ። ወደ ቃሊቲ መመረሻችሁን ስታረጋግጡ በስልጣን ላይ እያላችሁ ‹‹እስር ቤቱን በጣም አታጥብቡት የሚገባበት አይታወቅምና ››ያለው ሟርተኛ ትዝ አላላችሁም።
ምን አይነት አዝግ ሰው ነው እባካችሁ? አሁን እንዲህ ተብሎ ሙሾ ይወረዳል። እኔ ግን የገረመኝ ያን ሁሉ ወጣት አስጨርሳችሁ ቀሪ ህይወታችሁን በቃሊቲ ልታሳልፉ ስትወስኑ ሼም አይቆነጥጣችሁም። አሁን ለመኖር የምትጓጉት ምን ቀረን ባልችሁ ነው? ነገሩ አልፈርድባችሁም ሃብታም ሁልጊዜ ወጣት ድሃ ደግሞ ሽማገሌ ነው።
ለስንት ያሰብናችሁ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወዛችሁ ጠፍቶ፤ ቆሌያችሁ ተገፎና ጣዕረ ሞት መስላችሁ ከች ስትሉ የልብ ህመም፤ ደም ግፊትና ስኳር ያለበት ሰው በድንጋጤ ይደይማል ብላችሁ አታስቡም እንዴ? ተው አሁን እንኳን ለሰው ማሰብ ጀምሩ። እኛ እናንተ ባታስቡልንም ጠላታችሁ ክው ይበል ክው ብለን ቀርተናል።
ለ30 ዓመታት የቆረጣችሁት ጮማ፤ የተራጫችሁበት ውስኪ ለአንድ ወር እንኳን አይሆንም እንዴ? እኛ ተርበን እንዳላበላን፤ ተበድረን እንዳልሰጠን፤ ውሃ ጠምቶን ውስኪ እንዳላጠጣን ለምን ክፉ ታስብሉናላችሁ? ወይስ እንደዶላራችሁ ስትበሉና ስትጠጡ የነበረውን የምታስቀምጡት በውጭ ባንክ ነው?
መቼም ካነሳነው አይቀር ለ30 ዓመታት ስታሸሹ የነበረውን ቢሊዮን ዶላሮች ምን ልታደርጉት አሰባችሁ? እስር ቤት ተቀምጠን እንጦርበታለን የሚል የልጆች ጨዋታ እንደማታመጡ እርግጠኛ ነኝ።
ምክንያቱም ገንዘባችሁ ግለሰቦችን ሳይሆን ሀገርን ለዘላለሙ የመጦር አቅም እንደላው አጥኚ ነን የሚሉ ምሁራን ሲናገሩ ሰምቻለሁ።
ብቻ እኛንም አትርሱን። እኛ እኮ የተጎሳቆልነው፤ የተራብነው፤ የተጠማነው፤ የተሰደድነው፤ በበረሃ የአውሬ እራት ሆነን የቀረነው የእናንተ ምቾት እንዳይጓደል ነው። እናንተ በሊሞዚን እንድትንሸራሸሩ፤ በቅንጦት ቤት እንድትኖሩ፤ ቁርሳችሁን ዱባይ፤ ምሳችሁን ለንደን እንድትበሉ እኛ ለ30 ዓመታት የረሃብ አድማ አድርገን ኖረናል።
አሁን እኛ የሚቆጨን ተጎሳቁላችሁ ማየታችን ነው። አንገታችሁ ተሰብሮ፤ ጺማችሁ ጎፍሮ፤ አንድ እግር ካልሲ አድርጋችሁ፤ ሸበጥ ተጫምታችሁ ስናያችሁ ሆዳችን ተንቦጫቦጨ። መሪር ሀዘን ተሰማን።
ከማዘን ውጪ ግን ምን ማድረግ እንችላለን። በስልጣን ዘመናችሁ ምቾታችሁን አካፍላችሁን ቢሆን ኖር ዛሬ በጉስቁልና እንዴት እንደሚኖር እናሳያችሁ ነበር። ተዳፈርኩ እንዴ?
ከተዳፈርኩ ላይቀር አንድ ነገር ላውራና ጉዳዩን ልጨርስ። ነበር ለካ እንደዚህ ቀርብ ነው አሉ እቴጌ ጣይቱ። ከሁለት ወር በፊት ፈላጭ ቆራጭ ነበራችሁ፤ ዛሬ እፍኝ የማትሞሉ አሳዛኝ ፍጥረቶች ሆናችኋል።
ትላንት ታሪካዊቷን፤ ድንቋንና ሰፊዋን ኢትዮጵያን ትመሩ ነበር፤ ዛሬ ከአንድ ጠባብ ክፍል የዘለለ ቦታ የላችሁም። ትላንት ካለእኛ ጀግና የለም ብላችሁ ስታቅራሩ ዛሬ ቀሚስ ለብሳችሁ ስትሸሹ ከማይቀረው ሞት ጋር ተጋፍጣችኋል።
ገደል ገብታችሁ ተሰባብራችሁ ሞታችኋል። የቀራችሁትም በሸክም ከዝንጀሮ ገደል ተጎትታችሁ ወጥታችኋል፤ ከቀበሮ ጉድጓድ ታድናችሁ ተይዛችኋል። ኢታማዦር ብርሃኑ ጁላ እንዳሉት የእናንተ አወዳደቅ በዘራችን አይድረስ ከማለት ውጪ ምን ይባላል?
አዲስ ዘመን ጥር 6/2013