ኢትዮጵያና ሱዳን የረጅም ዘመን የጉርብትና ታሪክ ያሏቸው፤ከሚዋሰኑት ሰፊ ድንበር ባለፈ በርካታ ባህላዊ እሴቶችን የሚጋሩ፣ እርስ በእርስ የተሳሰሩና የተጋመዱ ወንድም ህዝቦች ናቸው። ይህንንም ደግመው ደጋግመው ካለፈ ታሪካቸው በተግባር አረጋግጠዋል፡፡
በየዘመኑ ባጋጠሙ ክፉና ደግ ጊዜዎች ተባብረው በመቆምና በችግራቸው ወቅት አንዳቸው ለአንዳቸው ፈጥነው በመድረስ እውነተኛ አጋርነታቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል።
ዘመናትን ያስቆጠረው ይህ መልካም ግንኙነታቸው በመካከላቸው ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በድርድርና በውይይት እንዲፈቱ በማስቻል ረገድ ከየትኛውም ሀገር ይልቅ የተሻለ ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ይታመናል።
ማናቸውም ዓይነት ችግራቸው ከመጡባቸው መልካም የጉርብትና መንገዶች እና ከዚሁ ከሚመነጨው ወንድማማችነታቸው በምንም መልኩ ይበልጣል ተብሎም አይታሰብም።
ሀገራቱ ከቅኝ ገዥዎች ጋር ተያይዞ የተፈጠረ እና ለ100 ዓመታትት ሲንከባበል የመጣ የድንበር ማካለል ችግር እንዳለባቸው ይታወቃል። ችግሩ በሀገራቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረ ባለመሆኑ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ይህንኑ ታሳቢ ያደረጉ መሆን ይኖባርቸዋል፡፡
ከሁሉም በላይ ከድንበር አከላለል ጋር ተያይዞ ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ዘመናት ያስቆጠረ ጉርብትናና የህዝቦቹን ወንድማማችነት ሊጎዳ አይገባም።
ችግሩን ለመፍታት የሚደረግ የትኛውም አይነት የመፍትሔ መንገድ ችግሩን ለዘለቄታው የሚፈታው ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ይኖርበታል፡፡
የሀገራቱን ሕዝቦች ከሚፈልጉት ልማትና ከልማት ከሚመጣ የብልጽግና ተስፋቸው ሊጎትታቸው የማይገባ፣ ከዚህ ይልቅ የጋራ ተጠቃሚነት እና ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅሞቻቸውን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባዋል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግሥት እስከአሁን ችግሩን በውይይትና በድርድር ለመፍታት እየሄደበት ያለው መንገድም ይህንን እውነታ ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ የሚያስመሰግነው ነው።
ይህም አካሄድ ችግሩ ከሁለቱ ህዝቦች የቆየ ወዳጅነትና ወዳጅነቱ ከፈጠረው ወንድማማችነት አይበልጥም ከሚል የወዳጅነት መንፈስ የመነጨ ነው። ከዚህም በላይ ችግሩን በድርድርና በውይይት መፍታቱ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ነው ብሎ የሚያምን በመሆኑ ተገቢም ትክክለኛም መንገድ ነው።
በተለይም በአሁን ወቅት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ከመቼውም ጊዜ በላይ በለውጥ መንፈስ የተቃኙበትና በዚህ የለውጥ አስተሳሰብ ሀገራቸውን ወደተሻለ የታሪክ ምዕራፍ ለማሻገር የተነቃቁበት ከመሆኑ አንጻር ችግሮቻቸውን በውይይትና በድርድር የመፍታታቸው ዕውነታ ለጀመሩት ለውጥ ስኬት የተሻለ አቅም እና የመተባበር መንፈስ መፍጠር እንደሚችል ይታመናል።
የሱዳን ህዝብ የለውጥ ፈላጊነት በቀደሙት ዓመታት በሱዳን አደባባዮች በተደጋጋሚ ሲታይ የቆየና አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ማምጣት ያስቻለ ነው። ይህ ለመለወጥ የመነሳሳት መንፈስ ህያው ሊሆን የሚችለው በዚሁ መንፈስ ችግሮችን መፍታት ሲቻል ብቻ እንደሆነ ይታመናል።
እያንዳንዱ የችግር አፈታት ሄደት ይህንን የሱዳን ህዝብ መሻት መሰረት ማድረግም ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ከሱዳን ጋር ያለውና የሚኖረው ግንኙነት ዘላቂ ብሄራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገ፣ ከዚህም በላይ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች አብሮ የማደግ መሻትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡
ከዚህም በመነሳት ከሱዳን ህዝብና መንግሥት ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ለሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
ይህ ተጨባጭ እውነታ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ በግልጽ የታየና በቡዙ የመስኩ ባለሙያዎች ጭምር የተረጋገጠ ነው። የግድቡ ግንባታ አንድም ሀገሪቱ የሚያጋጥማትን የደለል ጎርፍ መከላከል የሚያስችል በዚህ ምክንያት ይፈጠር የነበረውን መፈናቀልና ውድመት የሚያስቀር፤ ከዚህም በላይ ለሀገራዊ እድገቷ ወሳኝ የሆነውን ኃይል አቅርቦት በርካሽ ዋጋ ማግኘት የሚያስችላት ነው።
ከድንበር ማካለሉ ጋር በተያያዘም የያዘችው አቋም ችግሩን በውይይትና በድርድር የመፍታት አቅጣጫ፣ አንድም ችግሩን በውይይትና በድርድር የመፍታቱ አማራጭ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚያስችል ነው ብሎ ከማመን የመነጨ ሲሆን፤ ከዚህም በላይ ችግሩን በግጭት አማራጭ ለመፍታት መሞከር ለሀገራቱ አላስፈላጊ ኪሳራ ውስጥ ከመክተት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለ ው ስለምታምን ነው።
በሱዳን በኩል ለችግሩ እንደመፍትሔ ተደርጎ እየተወሰደ ያለው የኃይል አማራጭ ግን በየትኛውም መልኩ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፣ ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለቱን ሀገራት መልካም ጉርብትና ከማጠላሸት ባለፈ ትርጉም የለውም።
ይህን እውነታ የሱዳን መንግሥት በአግባቡ ሊረዳው ይገባል። እንደ መንግሥትም ካለበት የህግና የሞራል ኃላፊነት አንጻር እየሄደበት ያለውን መንገድ ከሱዳን ህዝብ ፍላጎትና ዘላቂ ጥቅም አንጻር ደጋግሞ ሊያጤነው ይገባል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ ችግሩን በድርድርና በውይይት ለመፍታት እየሄዱበት ያለው ኃላፊነት የተሞላበት መንገድ ትክክለኛውን ትርጉምና የእሳቤ መሰረት በአግባቡ ለመረዳት ለሱዳን መንግሥት የረፈደ አይደለም።
ዓለም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያውያን ለጦርነት እንግዳ አይደሉም። ለነፃነትና ለሉአላዊ ክብራቸው ካለቸው ቀናኢነት አንጻር የብዙ ተጋድሎ ታሪክ ባለቤት ናቸው። የነፃነት መሰረታቸውም ይኸው ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 6/2013