የአንድ አገር ስፖርት ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው በታዳጊና ወጣት ስፖርተኞች ላይ መስራት ግዴታ ነው። በተለያዩ ስፖርቶች ውጤታማ የሆኑ አገራት ስምና ዝናቸውን ይዘው መዝለቅ የቻሉትም በታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው በመስራታቸው ነው። ኢትዮጵያ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስምና ዝናን ባተረፈችበት አትሌቲክስ ስፖርት ውጤቷ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ በታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባት በተደጋጋሚ ይነሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ቢሆን በተለያዩ ስፖርቶች የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶች በተለያዩ ክልሎች ተከፍተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ከነዚህ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ የታዳጊ ወጣቶች አካዳሚ በአዲስ አበባና በአሰላ ተከፍቶ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እየተመለከትን እንገኛለን።
የታዳጊ ወጣቶች ፕሮጀክቶችን ስናነሳ ምን ጊዜም የሚነሳው ጉዳይ የዕድሜ ተገቢነት ነው። ይህ ችግር በአገራችን ስፖርት በተደጋጋሚ የሚነሳ ቢሆንም በአንዳንድ የስፖርት ዓይነቶች ላይ ውስን ለውጦችን መመልከት ተችሏል። ለምሳሌ ያህል በእግር ኳስ የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ አሳሳቢ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎችን እየተመለከትን ነው። ለዚህም ዘመናዊው የህክምና መሳሪያ ኤም.አር.አይ ውስንነቶች ቢኖሩበትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታዳጊና ወጣት ቡድኖች ላይ ለውጦችን እያሳየ መምጣቱ አይካድም። ይህም የወጣት ብሔራዊ ቡድኖች ላይ ከዚሁ ከዕድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተስፋ ሰጪ ወጣቶችን መመልከት ጀምረናል።
የደም ስራችን በሆነውና ተተኪ ታዳጊ ወጣቶችን ማፍራት ይቆይ በማንለው የአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ግን አሁንም የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ ስር የሰደደ ሆኖ ቀጥሏል። በታዳጊና ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድሮች ላይም ይህ ችግር ከመሻሻል ይልቅ እየባሰበት ሄዷል። ባለፈው ሳምንት በአሰላ አረንጓዴው ስቴድየም ለስድስተኛ ጊዜ በተካሄደው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮናም የዕድሜ ተገቢነት ችግር ተሻሽሎ ሳይሆን ብሶበት ነው የተገኘው። ከአሥራ ስድስት እስከ ሃያ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አትሌቶች የሚሳተፉበት ይህ ውድድር በትክክለኛው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ አትሌቶች እንደናፈቁት ተጠናቋል።
በውድድሩ እንደ ሲዳማ ቡና ያሉ አዳዲስ የአትሌቲክስ ክለቦች በተለያዩ ርቀቶች ጠንካራ ተፎካካሪዎችን ይዘው ብቅ ማለታቸው መልካም ዜና ሆኖ እነዚህ ክለቦችን ጨምሮ በታዳጊና ወጣቶች ላይ ይሰራሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ለውድድር ያቀረቧቸው አትሌቶች ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው። ሌላው ይቅርና ታዳጊ ወጣቶች ላይ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ እንኳን ለውድድር ያቀረባቸው አትሌቶች በተገቢው የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደማይገኙ መታዘብ ይቻላል።
የአንድን ስፖርተኛ ዕድሜ ያለ ህክምና ምርመራ ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር ባይቻልም ቻምፒዮናው ከሃያ ዓመት በታች ሳይሆን ከሰላሳ ዓመት በታች ይመስል እንደነበር በስፍራው የነበረ ሊመሰክር ይችላል። አንዳንድ አትሌቶች ዕድሜዬን የት ታውቃለህ? በማለት ሊከራከሩ ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ አይን አይቶ ልብ እንደሚፈርደው ሁሉ በትክክለኛው ዕድሜ ወደ ውድድር እንዳልመጡ የሚናገሩ አትሌቶችም ነበሩ።
የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ አንስተውት ያልተፈታ፤ የሚመለከተውም አካል ችላ ብሎት የተደጋገመ የዘወትር የአትሌቲክሱ ጩኸት ነው።በዚህ ችግር ምክንያት የበርካታ ታዳጊና ወጣቶች ህልም እንዲጨልም ማድረጉ ጉዳዩን ምን ጊዜም እንዲነሳ ያደርገዋል።
የአገራችን ስፖርተኞች ሁሉም ባይሆኑም በብዛት የዕድሜ ጉዳይ እንዲነሳባቸው አይፈልጉም። በተለያዩ አጋጣሚዎች የምናስተውለው የስፖርተኞቻችን የዕድሜ ጉዳይ ስር የሰደደ ችግር እንደሆነ ነው። በዕድሜ ጉዳይ ላይ ስፖርተኞች ከጋዜጠኞች ጋር በተደጋጋሚ ሲጣሉ የምናይበት አጋጣሚ የሩቅ ጊዜ ትዝታ ሳይሆን አሁን ላይም የምናስተውለው እውነታ ነው። አሁን አሁን ስፖርተኞች ከጋዜጠኞች የዕድሜ ጉዳይ ጥያቄ የሚያመልጡበት ቁልፍ ፓስፖርት ሆኗል። « ትክክለኛውን ወይንስ የፓስፖርቱን» በሚል በዕድሜ ጉዳይ ላይ መዘባበትም የዘመኑ ፋሽን ሆኗል። ዳሩ ግን ዓይን አይቶ ልብ ለሚፈርደው ነገር በፓስፖርት ማጭበርበር ቢቻልም ተክለ ሰውነት እውነቱን ያጋልጣል።
ይህን ስር የሰደደ የዕድሜ ጉዳይ ለመፍታት የተለያዩ መፍትሄዎች በፌዴሬሽኖች በኩል ተግባራዊ ሊደረጉ ቢሞከርም ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። ለዚህ ሁሉ ችግር ዋነኛ መንስዔ ሆኖ የምናገኘው ሽልማት ነው።
ሽልማት ስንል የተለያዩ ክልሎችና ክለቦች አሰልጣኞች በአገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ላይ ወክለው ከመጡበት አካል ባስመዘገቡት ውጤት መሰረት የሚበረከትላቸውን ሽልማት ነው። እነዚህ አሰልጣኞች በአገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ላይ ውጤታማ ሆነው ሲገኙ የወከሉት ክልል ወይንም ክለብ የተለያዩ ሽልማቶች፤ ማዕረግና ዕድገት ያገኛሉ። ለዚህም የትኛውም አሰልጣኝ በውድድሮች ላይ ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። ለእዚህ ውጤት ለመብቃት ደግሞ በተለይም በታዳጊዎችና ወጣቶች ቻምፒዮናዎች ላይ በተገቢው ዕድሜ ስፖርተኞችን ማሰለፍ ለእነሱ አዋጭ አይደለም። ምክንያቱም ተፎካካሪ በተገቢው ዕድሜ ስፖርተኞችን አያወዳድርምና ለምን እንበለጥ የሚል የጥርጣሬ ስሜት በአሰልጣኞች መካከል አለ።
ለዚህ ማስረጃነት አንዳንድ ክልሎች ወይንም ክለቦች በዕድሜ ተገቢውን ስፖርተኛ አሰልፈው ተገቢ ያልሆነ ስፖርተኛ ባሰለፉት የሚወሰድባቸው የበላይነት በቂ ነው። ዛሬ በተገቢው ዕድሜ ስፖርተኞችን አሰልፎ ተገቢ ባልሆኑት ስፖርተኞች የበላይነት የተወሰደበት አሰልጣኝ ነገ ላይ ምኑን ተማምኖ በተገቢው መንገድ ወደ ውድድር ይመጣል? ታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ጥቂት አሰልጣኞች አሉ። እነዚህ አሰልጣኞች የት ደረሱ? እነዚህ አሰልጣኞች ውጤትን እንጂ የዕድሜን ተገቢነት ትኩረት ሰጥተው በማይሰሩት አሰልጣኞች ተውጠው እናገኛቸዋለን። ማንም ሰው ከዛሬ ነገ የተሻለ ለውጥና ዕድገት ይፈልጋል። ስለ እዚህም በተጭበረበረ መንገድ ወደ ውጤት በርካቶች እየገሰገሱ በትክክለኛው መንገድ የሚሰሩት አሰልጣኞች እስከ መቼ ተደብቀው ይኖራሉ?።
ከአሰልጣኞቹም በላይ የነገ ተስፋዎች ይሆናሉ ተብለው ትልቅ ተስፋ የሚጣልባቸው ታዳጊዎች ለሽልማት በሚሮጡ አሰልጣኞች ምክንያት እየተዋጡ ይገኛሉ። በርካታ ታዳጊዎች ሽልማት ባመጣው ጣጣ ተስፋቸው በጊዜ እየጨለመ ነው። ታዳጊዎች ታዳጊ ነን በሚሉ ታላላቆቻቸው በስፖርቱ ያላቸው ተሰጥኦ እየተደበቀ አገሪቱም ማግኘት የሚገባትን ተተኪዎች እያጣች ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህን ችግር ለመፍታት ከአቅሙ በላይ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ፌዴሬሽኑ ማህደሮችን አገላብጦ በመመርመር ዕድሜን በማጣራት ከውድድር የቀነሳቸው ተወዳዳሪዎች ከዚህ ቀደም ነበሩ። ይህ አካሄድ ሁሉንም መለየት የሚያስችል አልነበረም። ምክንያቱ ደግሞ አትሌቶች ስም ቀይረው አዲስ ፓስፖርት በማውጣት በዕድሜያቸው ላይ ማስተካከያ አድርገው መምጣታቸው ነው። የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ቢሮ በቅርቡ ፓስፖርት ለማሰራት የሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ በመሆኑ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሚገኝ በቅርቡ መግለፁ ይታወሳል። ለዚህም አንድ ሰው ከአንድ በላይ ፓስፖርት እያሰራ መሆኑ በምክንያትነት ተገልጿል። ለዚህ ደግሞ አትሌቶች ሁሉንም ባያካትትም ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም በታዳጊና ወጣት አገራዊ ውድድሮች ላይ ከአምስትና ስድስት ዓመት በፊት የምናውቃቸው አትሌቶች ጭምር አሁንም ድረስ እንደሚወዳደሩ ራሳቸውም አይክዱትም። ይህ ማለት እነዚህ አትሌቶች በየዓመቱ ስማቸውና ዕድሜያቸው ላይ የተወሰነ ማስተካከያ እያደረጉ በርካታ ፓስፖርት በእጃቸው ይገኛል ማለት ነው። ይህም ሳያንስ አሁን አሁን ስምም ፓስፖርትም ሳይቀይሩ በማናለብኝነት ወደ ውድድር የሚመጡም አልጠፉም። እነዚህ አትሌቶችና አሰልጣኞች እንዲሁም ቡድን መሪዎች እዚህ ግባ ለማይባል ጥቅም ያልቀየሩት ነገር ቢኖር ፆታና ዜግነት ብቻ ነው።
ችግሩ ፌዴሬሽኑ ብቻ ሊፈታው የሚችለው አይደለም። ችግሩን ለመፍታት ክለቦች፤ ክልሎች፤ አሰልጣኞችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ኃላፊነትና ቀናነት የተሞላበት መንገድ ሊከተሉ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ፌዴሬሽኑ የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ከባድ እንደሚሆንበት ደጋግሞ ይናገራል። ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ ፓስፖርትን ጨምሮ ሌሎች ሰነዶችን መርምሮ የቀረቡትን ተወዳዳሪዎች ከማወዳደር በዘለለ ማስረጃዎቹን ውድቅ አድርጎ ተገቢ አይደለም ያለውን ስፖርተኛ የማገድ መብት የለውም። ይህ ችግር በስፋት የሚታየው ጠንካራ ፉክክር በሚያደርጉ ክለቦችና ክልሎች እንጂ በአዳጊ ክልሎች ላይ አይደለም። በርካታ ታዳጊዎችን በስፋት ለአገር የማበርከት አቅም ባላቸው መሆኑ ደግሞ በችግሩ እሳት ላይ ቤንዝል እንደ ማርከፍከፍ ይሆናል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በአንድ ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት «የአመለካከት ችግር አለ፤ ፌዴሬሽኑ ህግና ደንብን ማውጣት እንጂ ክለቦችና ክልሎችን ተክቶ ሊሰራ አይችልም፤ ህጉን ያላከበረና በህጉ መሰረት ያልሰራ ክለብ፤ ቡድን ወይንም ግለሰብ ላይ እርምጃ መውሰድ ነው» ብለው ነበር። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ አሁን የተቸገረው ክልሎችና ክለቦች እንዲሁም አካዳሚዎች የተባለውን መመሪያና ደንብ አንብበውና ተረድተው ባለመምጣታቸው ነው። «ፌዴሬሽኑ ቢያንስ ከስድስት ወር በፊት የውድድር ደንብ ይልካል፤ አንዱ ደንብ የዕድሜ ጉዳይ ነው፤ ወጣት ላይ ሊሰለፍ የሚችል አትሌት ዕድሜው ከሃያ በታች የሆነ ከስራ ስድስት ዓመት በታች ያልሆነ በሚል ተቀምጧል። ይሄን ተከታትሎ መስራትና ማስፈፀም የክልልና ክለቦች ኃላፊነት ነው፤ ፌዴሬሽኑ ህግና ስርዓት ዘርግቶ የማወዳደር ኃላፊነት ብቻ ነው ያለበት፤ አሰልጣኞችን ማብቃት ደንብ ማዘጋጀት ሌላ ሥራው ነው፤ ክልሎች ራሳቸውን የቻሉ መንግሥት ስለሆኑ ጣልቃ መግባት አይቻልም፤ ፌዴሬሽኑን የቸገረውም ይሄው ነው» የሚሉት አቶ ዱቤ፣ ችግሩን ለመፍታት ከነዚህ አካላት ጋር መወያየት አንድ መፍትሄ እንደሆነ ያስቀምጣሉ።
የዕድሜ ጉዳይ ይህን ያህል አትሌቲክሱን ከተፈታተነ እግር ኳስ ላይ በአንፃራዊነት ለውጥ ያመጣው ወይንም ተስፋ የሰጠው የኤም.አር.አይ የህክምና ምርመራ አትሌቲክሱ ላይ ለምን ተግባራዊ አይሆንም? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዱቤ የኤም.አር.አይ ምርመራ ለመጀመር በቅድሚያ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር (አይ.ኤ.ኤ. ኤፍ ) መጀመር እንደሚኖርበት ያብራራሉ። ኢትዮጵያ ብቻ ይህን ምርመራ ተግባራዊ ብታደርግ ትርጉም እንደማይኖረው የሚናገሩት አቶ ዱቤ፣ የዓለምን አትሌቲክስ የሚመራው አካል ሌሎች አገራት ምርመራውን እንዲጀምሩ ኢትዮጵያ የማትጀምርበት ምክንያት አይኖርም።
የታዳጊ ወጣቶችን ውድድር አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ አንድ ጊዜ አካሂዶ መሰረዙን ያስታወሱት አቶ ዱቤ፤ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት የነበረው የዕድሜ ጉዳይ መሆኑን ያነሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ታዳጊዎች ወደ ላይ መምጣት እንዳልቻሉ በጥናት ማረጋገጡ ነው። « አትሌቶች ልማት ላይ መሰራት አለበት፤ ተመሳሳይ አትሌት እያመጣን አገር አንለውጥም፤ አትሌቱ አቅም ባለው ወቅት ነው የሚሮጠው፤ በጊዜው ካልሮጠ ከሁለትና ሦስት ዓመት በኋላ ዋጋ አይኖረውም፤ ከስር እየተካን ካልሄድን ትርጉም የለውም፤ ከስር የሚመጣው ደግሞ ከታዳጊ ጀምሮ ወደ ወጣትና አዋቂ እያለ መምጣት ይኖርበታል፤ አትሌቱ ከታች ነው ያለው እታች ወርዶ የሚሰራ ሰው ደግሞ የለም፤ ሁሉም ጊዜያዊ ውጤት ይዞ መሄድ እንጂ የነገን አያስብም፤ ያ ደግሞ የትም አያደርሰንም፤ ስለዚህ የአትሌት ልማት ላይ ካልተሰራ ወደ ፊት ትልቅ ችግር ያመጣል ብዬ እሰጋለሁ» በማለትም አቶ ዱቤ የችግሩን ስር መስደድ ይናገራሉ። ስለዚህም እንደ መንግሥት ከላይ ጀምሮ በመነጋገር ፤ የክልል መንግሥታትም ጣልቃ በመግባት ሊታሰብበት እንደሚገባ ያስቀምጣሉ።
አትሌቶቻችን ሰንደቅ ዓላማችንን በዓለም ከፍ ከማድረግ በላይ በኢንቨስትመንት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውና ከዚህም በላይ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጡ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ ዱቤ ፣እንደነ አሜሪካና እንግሊዝ አትሌቲክሱን እያጠናከርን ከሄድን የአገሪቱ ዓመታዊ በጀት ግማሹን ድርሻ ሊሸፍኑ ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ በተገቢው ዕድሜ መስራት ወሳኝ ይሆናል። ዋናው የስፖርቱ አካል ወጣቱ ነው፤ ወጣቱን መያዝ የግድ ነው፤ ስለዚህ እንደ መንግሥትም እዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
የዕድሜ ማጭበርበር ዞሮ ዞሮ መንስዔውም መፍትሄውም ክለቦች፤ ክልሎች፤ አሰልጣኞችና ራሳቸው ስፖርተኞቹ እንደሆኑ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ካገኘነው አስተያየት መረዳት ይቻላል። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ በእነዚህ ባለ ድርሻ አካላት ላይ ኃላፊነት ጥሎ መቀመጥ አይገባውም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩ እየተባባሰ እንጂ እየተሻሻለ ካልመጣ ፌዴሬሽኑ ያልታመነበትን ውድድር በማከናወን ገንዘብና ጊዜን ከማባከን ይልቅ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጊዜ ወስደው ችግሮቻቸውን እስኪፈቱ ድረስ ውድድሮችን መዝጋት አማራጭ እንደሆነ የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
ቦጋለ አበበ